Artcles

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ 91 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ አደረገች

By Admin

August 31, 2017

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የድርቅ መቋቋሚያ ተጨማሪ የ91 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሰብዓዊ ድጋፍ አደረገች።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) ሃላፊ ማርክ ግሪን በሁለት ቀናት ቆይታቸው በኢትዮጵያ በድርጅቱ የሚደገፉ ማህበረሰብ አቀፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝቷል።

ማርክ ግሪን በጉብኝታቸው ማሳረጊያ ላይም ዛሬ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው መክረዋል።

በውይይታቸው ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ድጋፍ መስጠቷን እንደምትቀጥል ኣስታውቀዋል።

ግሪን የምግብ ዋሰትናን ለማረጋገጥ በቀረፀችው መርሃ ግብር ትኩረት ከሚያደርግባቸው 12 አገራት መከካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አንስተዋል።

ማርክ ግሪን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላም የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ኢትዮጵያ ድርቅን ለመቋቋም ለምታከናውነው ተግባር 91 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያደርግ ይፋ አድርገዋል።

ከድርቁ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ አስከፊ ጉዳት እንዳይደርስ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በውይይቱ ወቅት የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስቴር ኋይለማርያም ደሳለኝ፥ የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ ዜጎቿን ለመታደግ እያደረገች ያለውን ጥረት በመደገፍ ላይ መሆኑንም አድንቋል።

ውይይቱን የተከታተሉት አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ድርቅ ቢከሰትባትም ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር በራሷ አቅም መቋቋም ችላለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በውይይቱ ድርቁን ከመቋቋም በተጨማሪ በሁለቱ ሀገራት መካከል ንግድና ኢንቨትመንት በሚጠናከርበት ሁኔታ ከአሜሪካ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ መግለጻቸውንም ተናግረዋል።

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ውስጥ ለምግብ እና ለህክምና ክብካቤ የሚውል ገንዘብ የዛሬውን ጨምሮ ከ450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ድጋፍን አሜሪካ ለኢትዮጵያ አድርጋለች።

በዚህም በቅርብ ዓመታት ውስጥ ለአነስተኛ የንግድ ሥራ ፈጣሪዎች ዘላቂ ብድር በመስጠት፣ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን በማስተማር እና የአመጋገብ ትምህርትን በማቅረብ ባደረገችው ድጋፍ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ ዋነኛዋ ለጋሽ ሀገር ሆናለች።

አሜሪካ በእርሻ እና በኢኮኖሚ ረገድ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ግሪን አረጋግጠዋል።

በደስታ ተካ