Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያልዘሩትን ማጨድ አይቻልም

0 328

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ያልዘሩትን ማጨድ አይቻልም

ዓለማየሁ ማሞ (ሴ/ህ/ጉ/ሚ/ር)

ሀገራችን ለዘመናት የነበረችበት የድህነት ታሪክ ተለውጦ ስሟ ከስኬት ጋር መነሳት ከጀመረ ዋሎ አድሯል፡፡ በዓለም ሀገራት ዘንድም ተደማጭነቷ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ስለሆነም ይህ ትውልድ የሀገሩን ታሪኩን በሚገባ አውቆ እንዲያሳውቅ  የታሪክ ቅብብሎሽ መስመር መያዝ አለበት፡፡  ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝን የሚዲያ ላይ ገጠመኞች ለማንሳት ወደድኩ፡፡

ጋዜጠኛው ለተለያዩ ተማሪዎች ስለሀገራቸው ያላቸውን ግንዛቤ ለመረዳት ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራል፡፡ የካቲት 12 ና ህገመንግስትን በተመለከተ ለእያንዳንዳቸው ጥያቄ ያቀርባል፡፡ የተማሪዎቹም መልስም አላውቀውም ሲሆን  ትክክለኛ መልስ የሰጠ አልነበር፡፡ በዚህም ጋዜጠኛው በጣም ተበሳጨ፡፡ እንደ እኔ ተማሪዎቹ የሰጡት ምላሽ የሚያበሳጭ ሊሆን አይገባም፡፡ አካፋን አካፋ እንደማለት እንጂ፡፡  ባይሆን የማያውቁትን ከመዘላበድና አዋቂ መስሎ ለመታየት ከመጣጣር ይልቅ አበው “እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ይሻላል!” እንዲሉ  በግልጽ መናገር የሚበጀ ይመስለኛል፡፡ አለማወቅን ተረድቶ ታሪክን ለማወቅ መጣር ሊያበረታታ እንጂ ሊያስነቅፍ አይገባም – የተማሪዎቹ ምላሽ ብዙ ልንሰራ እንደሚገባ ጠቋሚ ምላሽ የሰጠ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስድስት ኪሎ በሚገኘው የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያን ሃውልት ግርጌ ላይ “አትርሱት አንርሳው!” በሚል ርዕስ እንዲህ ሲል አስፍሯል፡፡

“አትርሱት አንርሳው!”

ራስን ካንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ

በችንካር ቸንክሮ ሰው እየገደለ

ሰውን ከነቤቱ አብሮ እያቃጠለ

ማነው እንደፋሺስት በሰው ግፍ የዋለ

ስጋችንን ቆርጠው ሊቀብሩት ከጀሉ

በዚህ ያልነበሩ ሃሰት እንዳይሉ

እኒህ አስከሬኖች ይመሰክራሉ

ይህን ታላቅ ስቃይ መከራና ግፍ

                   ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ …እያለ ይቀጥላል፡፡

ይህ ግጥም ከ80 ዓመት በፊት በፋሺሽት ኢጣሊያ ወረራ በማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ  አማካይነት ከየካቲት 12 ቀን አንስቶ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ በሰማዕትነት ላለፉ  30 ሺህ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ መቆሙንና የእለቱን ታላቅነት ለማመልከት እንዲህ ተጽፎ ይነበባል፡፡

ስለ ህገ መንግስቱ ለመናገር ደግሞ  እውቀት ያስፈልጋል፡፡ ስለተጠየቀ የሚመለስ ካልተጠየቀ የሚቀር ሳይሆን ህገመንግስቱ ከህልውናችን ጋር የተሳሰረ በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ የአንድን ሀገር ሕገ መንግሥት መሠረታዊ ዓላማዎች፣ መርሆዎችና ዕሴቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ ድንጋጌዎችንና አሠራሮችን ከአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱ መንፈስ አንፃር መገንዘብ የሁሉም ዜጎች ግዴታ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱን  በአግባቡ መገንዘብ፣ ሀገራዊ መግባባት መፍጠርና ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ደግሞ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ሕይወታቸውን በሕግና ሥርዓት ለመምራት፣ በዚህም ዓላማ አድርገው ያስቀመጡትን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡

ሕገ መንግስት በአንድ ሀገር ውስጥ የመንግሥት የአስተዳደር አካላት እንዴት እንደሚፈጠሩ፣ እንደሚደራጁና የእነዚህ የአስተዳደር አካላት የሥልጣን ወሰንና አተገባበር ምን እንደሚመስል የሚደነግግ፣ መሰረታዊና አጠቃላይ መርሆዎችንና ሥነ ሥርዓቶችን የያዘና የአንድ ሀገር መንግሥት ዋና መተዳደሪያ ሕግ ነው፡፡

ሕገ መንግሥት በአንድ ሀገር ስለሚኖረው የፖለቲካ ሥርዓት፣ የሥልጣን ባለቤትነት፣ የመንግሥት አካላት አወቃቀር፣ የሥልጣን ክፍፍልና የመንግሥት አሰራርን እንዲሁም የዜጐችን መብቶች፣ ነፃነቶች፣ በመንግሥትና በዜጐች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚደነግግ ዋና የፖለቲካና የሕግ ሰነድ ነው፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ልማትና እድገትን ስንመለከት በሃገራችን ሶስት መሰረታዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎች የተቀመጡ ሲሆን  ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በነዚህ አቅጣጫዎች መዘውርነት የሚመሩ ናቸው፡፡ እነዚህ  ሶስት  መሰረታዊ አቅጣጫዎች  የሚመነጩት ከህገ መንግስታችን ነው፡፡

እነዚህ ሶስት መሰረታዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ ዋሰትና ያለው ዴሞክራሲ ማስፈንና እንዲሁም  ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማትና እድገት ማረጋገጥ የሚሉ ናቸው፡፡

የልማት ማጠንጠኛዎቻችን መሰረቶች የሆኑት እነዚህ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች  በህገመንግስታችን መግቢያ ላይ የሰፈሩና ሁሉም ሰው ሊገነዘባቸው የሚገቡ ቁልፍ ሃሳቦች ናቸው፡፡

የመጀመሪያው መንግስት በዚህች ሃገር ውስጥ ልማትን ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ ይህንን ልማት ለማረጋገጥና ከሌሎች ሃገሮች ተርታ ለመሰለፍ ደግሞ ፈጣን ልማትና እድገቱ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ሊሆን ግድ ይላል፡፡

ሁለተኛው  አቅጣጫ ደግሞ  ሰላም ፣ መልካም አስተዳደርንና ዴሞክራሲን የማስፈን ጉዳይ ከልማታችን ተነጥሎ የማይታይ መሆኑ  ነው፡፡

ሶስተኛው የምናረጋግጠው  ፈጣንና  ዘላቂ ና የምንገነባው መልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት በየደረጃው ያለውን ምልዓተ ህዝቡን ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያድርግና  የሃብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና እድገት /equitable development/ ጽንሰ ሃሳብን ያረጋገጠ  ነው ፡፡

በዚህ መሰረት በሃገራችን  የየትኛውንም ዘርፍ  ፖሊሲና ስትራቴጂ አምጥታችሁ ብትመዝኑ ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የተነደፉ በመሆናቸው ቀደም ሲል ያነሳናቸውን ሶስት ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ከውስጣቸው መምዘዝ ይቻላል፡፡

ስለዚህ የወጣቶችን ልማትና  እድገት፣ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የህጻናት መብትና ደህንነት ፣የትምህርትን ተሳትፎ ፣ጥራትና ተደራሽነት ፣ የጤና አገልግሎት መስፋፋት   እንዲሁም የመጀመሪያውም ሆነ ሁለተኛው የእድገትና  ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጽንሰ ሃሳብ  የተቀዱት ከህገ መንግስቱ ሶስቱ መሰረታዊ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች መሆኑን ልንረዳ ይገባል፡፡

በህገመንግስታችን መግቢያ ላይ እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነጻ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን መነሳታችንን የሚገልጽ ዓላማ በጉልህ የሰፈረው ፡፡

በዚህች ሃገራችን  ፈጣንና ዘላቂ ልማት ልናረጋግጥ ከሆነ ወይም ደግሞ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን  ልንገነባ ከሆነ የዜጎችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ ድርድር ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ይህንን ተግባራዊ  ለማድረግ ደግሞ በህገመንግስቱ ላይ ያለን እውቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡

በዚህ መሰረትም ሚዲያው ከተቋቋበመት መረጃ የመስጠት ፣የማሳወቅና የማዝናናት ተልዕኮ አንጻር  ሰፊውን ጊዜ የወሰደው የመዝናኛ አገልግሎት ነው፡፡ ሚዲያ በሀገራችን ወሳኝ በሆኑ ሌሎች  ሃገራዊ አጀንዳዎችን ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ከማድረግ ባሻገር ያልዘሩትን ማጨድ እንደማይቻል በመገንዘብ በየደረጃው በሚገኘው የትምህርት እርከን ህገ መንግስቱን ፣ታሪካዊና ብሔራዊ ቅርሶቻችንንና እንዲሁም ጠቃሚ ልምዶቻችንን ሊያስተዋውቁ የሚችሉ መረጃዎች በመቀመር በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በማካተት ትውልድን የመቅረጽ ሰናይ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy