ድርቅን ጉልበት እንንሳው!
ኢብሳ ነመራ
በኢትዮጵያ የአስቸክይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ጠባቂዎች ቁጥር ጨምሯል። እስከ ታህሳስ 2010 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች 8 ነጥብ 5 እንደሚሆኑ የብሄራዊ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ሰሞኑን አስታውቋል። ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 10 ነጥብ 2 ሚሊየን እንደነበረ ይታወሳል። ይህ የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር የመኸር ምርት በተሰበሰበበት ጥር 2009 ዓ/ም ላይ በ4 ነጥብ 6 ቀንሶ 5 ነጥብ 6 ሆኖ ነበር። መጋቢት ወር ላይ የተረጂዎቹ ቁጥር መልሶ ጭማሪ አሳይቶ 7 ነጥብ 8 ደረሰ። አሁን ይህ አሃዝ በ7 መቶ ሺህ ጨምሮ 8 ነጥብ 5 ደርሷል።
የብሄራዊ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን፣ በ2009 ዓ/ም በበልግ አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች የምግብ ዋስትና የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ገልጿል። ከግንቦት 15 እስከ ሰኔ 15፣ 2009 ዓ/ም በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት፤ የዝናብ ሁኔታ፣ የእርሻ ስራ እንቅስቃሴ፣ በማሳ ላይ ያለ ሰብል ሁኔታ፣ የምርት ግምት፣ የግጦሽና የውሃ አቅርቦት፣ የእንሰሳት አቋምና የምርት ሁኔታ፣ የሰውና የእንሰሳት ጤና እንዲሁም በወቅቱ እየቀረበ የሚገኝ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች የስርጭት ሁኔታን በማጥናት የማህበረሰቡ የምግብ ዋስትና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መገምገሙን አስታውቋል። 7 ነጥብ 8 ሚሊየን የነበረው የተረጂዎች ቁጥር ለቀጣዮቹ አምስት ወራት ወደ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ከፍ ማለቱ የተረጋገጠው በዚህ የዳሰሳ ጥናት ነው።
የ2009 ዓ/ም የበልግ ዝናብ መዛባት፣ የመኖና ግጦሽ ማነስ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የምርት መቀነስና የውሃ እጥረት የተረጂዎቹ ቁጥር እንዲጨምር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል። በዚህ ጥናት የፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ሴክተር ቢሮዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ያላቸው ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ የረድኤት ድርጅቶች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ ከድርቅና ድርቅ ከሚያስከትለው የምግብ እጥረት ጋር የኖረች ሃገር ነች። ከሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በፊት ድርቅ እንደብርታቱ መጠን የሚሊየኖችን፣ መቶ ሺሆችን ህይወት የሚቀጥፍ ችጋር ያስከትል ነበር። ሚሊየኖችን ተወልደው ካደጉበት፣ ተድረው ከወለዱበት፣ ድረው ወግ ማዕረግ ካዩበት፣ አርጅተው የሃገር ሽማግሌነትን ማዕረግ ካዩበት የመኖሪያ ቄዬአቸው ያፈናቅላቸው ነበር። ከሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ችጋሩና መፈናቀሉ ቀርቷል። ድርቅ ግን አልቀረም።
ድርቅና ችጋርን፣ ድርቅና ከመኖሪያ ቂዬ መፈናቀልን ያለያየው ቀዳሚው ምክንያት መንግስት ድርቅን ተጽእኖ ከማስከተሉ በፊት ይፋ አድርጎ እርዳታ ማቅረብ መቻሉ ነው። በ1986ና በ1992፣ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት መንግስት እርዳታ የማቅረብ አቅም አልነበረውም። በመሆኑም የውጭ እርዳታ ማግኘት የሚያስችል ርብርብ በማድረግ ድርቁ ያስከተለው የምግብ እጥረት ጉዳት ማድረስ ከመጀመሩ በፊት እርዳታ ማቅረብ ችሏል።
መንግሥት ድርቅ የሚያስከትለውን ችጋርና መፈናቀሉን ያስቀረው በዚህ አኳኋን ነበር። በ2003 ዓ/ም በተለይ ምስራቅ ኢትዮጵያን የመታው አስከፊ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ለአምስት ዓመታት ያህል ባስመዘገበው ተከታታይ እድገት የውጭ እርዳታ እስኪገኝ ከመጠባበቂያ የእህል ክምችት እርዳታ ማቀረብ የሚያስችል አቅም ተፈጥሮ ነበር። በመሆኑም የድርቁን ተዕእኖ ለለጋሾች አሳውቆ፣ የውጭ እርዳታ እስኪደርስ ከመጠባበቂያ የእህል ክምችት ድጋፍ አቅርቧል።
በ2007 ዓ/ም በግማሽ ክፍለ ዘመን በአስከፊነቱ ወደር ያልተገኘለት የተባለው ድርቅ ሲከሰት መንግስት የድርቁን ተጽእኖ የመከላከል አቅሙ ጐልብቶ ነበር። ድርቁ ሲከሰት መንግስት በመጠባበቂያ የእህል ክምችቱ 455 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጠባባቂያ እህል ነበረው። የድርቁን ተጽእኖ ለለጋሾች ይፋ አድርጎ የእርዳታ ጥሪ አስተላልፎ እርዳታ እስኪደርስ ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ አቅም እርዳታ መስጠት ጀምሮ ነበር።
ታህሳስ 2008 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ሲደርስ መንግስት 16 ቢሊየን ብር በጀት መድቦ ዋነኛ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ አቅራቢ ሆኗል። በኢትዮጵያ የድርቅ ታሪክ መንግስት በእርዳታ አሰጣጥ የአንበሳውን ድርሻ ሲይዝ የ2007/2008 ድርቅ የመጀመሪያው ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ደረስ ከነበሩት 7 ነጥብ 8 የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂ ዜጎች ውስጥ መንግስት ለ4 ነጥብ 7 ወይም 60 በመቶ ያህሉ እርዳታ ሲያቀርብ ቆይቷል። ከአጠቃላይ ተረጂዎች ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ወይም ለ21 በመቶ እርዳታ ሲያቀርብ የቆየው የዓለም የምግብ ፕሮግራም የእርዳታ እህል ክምችቱን ስላሟጠጠ እርዳታ ሊያቋርጥ መሆኑን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ይህ ከሆነ በመንግስት የሚረዱ ዜጎች ከአጠቃላይ ተረጂዎች ወደ82 ሚሊየን ከፍ ይላል። መንግስት ይህን የማድረግ አቅም እንዳለው አስታውቋል።
የብሄራዊ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ሰሞኑን እንዳስታወቀው፣ የተረጂዎቹ ቁጥር በ7 መቶ ሺህ ጨምሮ 8 ነጥብ 5 ደርሷል። ተጨማሪዎቹ ተረጂዎች መንግስት ላይ መውደቃቸው የማይቀር ነው። ይህም መንግስት በራሱ አቅም የሚረዳቸው ዜጎች መጠን ከአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊዎች ከ83 በመቶ በላይ እንዲሆን ያደርጋል።
እርግጥ ባለፈው ዓመት 16 ቢሊየን ብር መድቦ እርዳታ ሲያቀርብ ለነበረው የኢፌዴሪ መንግስት፣ ዘንድሮም እርዳታ ማቅረብ አያቀተው ይሆናል። ባለፈው ዓመት እንደገለጸው የምግብ እጥረቱ እጅግ የከፋ ቢሆን እንኳን፣ በብዙ ቢሊየን ብር የሚያካሂዳቸውን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ገታ ያደርግ እንደሆን እንጂ የዜጎቹ ህይወት ለአደጋ አይጋለጥም።
ይህ ሁኔታ ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያድርበት አድርጓል። ይሁን እንጂ የመንግስት ጥንካሬ እርዳታ በማቅረብ የተገደበ መሆን የለበትም። ቀድሞውኑም ድርቅ የምግብ እጥረት የማያስከትልበትን ሁኔታ የመፍጠር ተግባር ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ረገድ ቀዳሚው ተግባር፣ በአካባቢ እንክብካቤ በተለይ በተፋሰስ ልማት የውሃ ግኝት መጠንን ማሻሻልና የአፈር እርጥበትን መጠበቅ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየአካባቢው በአርሶና አርብቶ አደሮች አባወራ ደረጃ የአነስተኛ የውሃ ክምችት እንዲያዝ በማድረግ የሚቻለውን ያህል በዚህ ውሃ በመጠቀም የመስኖ ልማት ማከናወን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በቂ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃ ባለባቸው አካበቢዎችም የመስኖ ልማት ከክረምትና ከበልግ እርሻ ጎን ለጎን ማካሄድ የዘውትር ስራ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ያበቃላቸው ባይሆኑም፣ ተስፋ ሰጪዎች መሆናቸው ግን እውነት ነው። የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ በአማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች በክረምቱ ወቅት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የውሃ ማሰባሰብ ስራዎች መሸፈኑን አስታውቋል። የውሃ ማሰባሰብ፣ በክረምት የሚጥለውን ዝናብ ኩሬዎችን ቆፍሮ ማጠራቀም፣ የዝናቡ ውሃ በጎርፍ መልክ እንዳይሄድ የሚያስችሉ ቦዮችንና ጉድጓዶችን በማዘጋጀት ውሃው ወደ ማሳ እንዲገባና ወደመሬት እንዲሰርግ የሚያስችል ተግባር ነው።
ይህ ስራ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለውን ድርቅ ተጽእኖ በዘላቂት ለመቋቋም ከሚያስችሉ አማራጭ መፍትሄዎች አንዱ ነው። በ2007 አስከፊ ድርቅ ከተከሰተ በኋላ ይህ ውሃ የማሰባሰብ ስራ በስፋት ተሰርቶ ውጤት ማስገኘቱን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም መከናወን ያለበት ተግባር የመስኖ እርሻ ነው። የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ያደረገው መረጃ፣ ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ያስመዘገበችው ውጤት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በዘርፉ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል። በ2009 ዓ/ም 7 ሚሊየን ገደማ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ በተካሄደ የመስኖ ልማት 370 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በዚህ ክንውን የእቅዱ 95 በመቶ ማሳካቱን ነው መረጃው የሚያሳየው። በ2010 ዓ/ም የተሳታፊ አርሶ አደሮችን ቁጥር ወደ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን በማሳደግ፣ በመስኖ የሚለማውን መሬት ደግሞ ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር ከፍ በማደረግ 469 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
በአጠቃላይ የድርቅን ተጽእኖ፣ ድርቁ የሚያስከትለውን የምግብ እጥረት ተፅዕኖ በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በመከላከል ረገድ የታየው የመንግስት ተግባር በህዝብ ላይ የመተማመን ስሜት የፈጠረ ቢሆንም፣ ይህ የመንግስት ተግባር የድርቅን ተጽእኖ የመከላከል አቅም በመገንባት ሊተካ ይገባል። ከላይ የተጠቀሱት መረጃዎች እንደሚያመለከቱት፣ በዚህ ረገድ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ይታያሉ። ድርቅ በየጊዜው ከሚያስከትለው የምግብ እጥረት ተፅእኖ አኳያ ሲመዘን ግን አሁንም ብዙ ይቀራል። እርዳታ በማቅረብ የተፈጠረው የድርቅን ተጽእኖ የመቋቋም አቅም፣ ድርቅን ጉልበት በማሳጣት መተካት አለበት።