ድንቅ መድረክ!
ይነበብ ይግለጡ
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከንግዱ ማሕበረሰብ ጋር ሶስተኛውን ሀገራዊ የመንግስትና የግሉን ዘርፍ የምክክር መድረክ መርተዋል፡፡ ሸራተን አዲስ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ በሀገር አቀፍ ደረጃ የንግዱን ማህበረሰብ የሚወክሉ መሪዎች ታዋቂ ነጋዴዎች ኢንቨስተሮች የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡ ድንቅ መድረክ ነበር፡፤
ተሰብሳቢው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በጥያቄና መልስ ሀሳባቸውን አንሸራሽረዋል፡፡ ይህ መድረክ ሰፊ ሀሳቦች ተስተናግደውበታል፡፡ የንግድ ማሕበረሰብ አሉኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች አንስቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ በወቅታዊው ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ ጎልቶ የወጣውና የመነጋገሪያ ርእስ የነበረው የሙሰኛውና የኪራይ ሰብሳቢው ጉዳይ በውይይቱ ወቅት ልዩ ትኩረት የሳበ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት መልስ ግልጽና ሊደነቅ የሚገባው ነው፡፡ ሲጀመር ሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢው ተቆራኝቶ ተንሰራፍቶ መረብና ድሩን ዘርግቶ የሚሰራው በሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ውስጥ ሁነኛ ቦታ ይዘው ያሉት ግለሰቦች ከባለስልጣናት ጋር በሚፈጥሩት መሞዳሞድና በእከክልኝ ልከክልህ ነው፡፡
ሰፊው የሕብረተሰብ ክፍል ከዚህ የራቀና በእለት ኑሮው ላይ ብቻ የሚያተኩር ነው፡፡ የሙስና መቀፍቀፊያ ማእከሉ በተለያየ የመንግስትና የሕዝብ ኃላፊነት ላይ የተቀመጡትን ኃላፊዎች እንደ በሬና ላም ጨው እያላሰ የጉቦ ገንዘብ እየሰጠ በእጅ አዙር እጅ መንሻ እያቀረበ አንዴ ከቀመሱ ሊርቁ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ በመክተት ይዞአቸው የጠፋው በንግዱ ስራ በከፍተኛ ደረጃ ተሰማርቶ የሚገኘው ኃይል ነው፡፡ ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ አፍረጥርጠው የተናገሩት፡፡መቶ በመቶ ትክክልም ነው፡፡
እኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌላውም አለም ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የሚንሰራፋው የከፍተኛው ነጋዴ ማሕበረሰብ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በሚፈጥረው መመሳጠርና ቁርኝት ነው፡፡ ይህ አልጠግብ ባይና ስግብግብ የሆነ የግለሰቦች መንፈስ በቃኝን የማያውቅ በመሆኑ ዘርፎና አግበስብሶም የማይረካ ስለሆነ የመንግስትን ሀብትና ንብረት በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ባለስልጣናትን ሽፋን በማድረግ ይዘርፋል፡፡
ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው ባልሰራበት ባልደከመበት ባለፋበት የዘረፋ ሀብት አንቱ የመባል ሕልሙ መንጠራራቱ የት የለሌ ነው፡፡ ለፍቶ ያገኘው ቢሆን ኖሮ ያስከብራል፡፡ እውነቱ ደግሞ ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ የተለያዩ ከላይ እስከታች የነበሩ የመንግስት ኃላፊዎችን ከለላ በማድረግ ተጨማሪ ዘረፋ ሲያካሂድ ኖሮአል፡፡ በዘረፋ በተገኘ ሀብት ከጣሪያ በላይ ከብሮአል፡፡ የብዙ ሀብቶች የብዙ ንብረቶች ባለቤት ለመሆን በቅቶአል፡፡ ከዚህም በላይ የገነፈለው ጥጋብና እብሪት ድሀውን እስከማፈናቀል ድረስ ተረማምዶአል፡፡ የዜጎችን የንብረት መብትና ሰብአዊ መብት ጥሶአል፡፡ዛሬ ላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ግዜው አብቅቶአል፡፡ የማይነካ የማይጠየቅ የለም፡፡
ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው አዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ከየኃላፊዎች ጋር በመቀናጀት የመንግስትን ወንበርና ማሕተም ምርኩዝና ሽፋን በማድረግ ብዙ ወንጀሎች ፈጽሞአል፡፡ ማስረጃዎቹ በህዝብ እጅ ይገኛሉ፡፡በጥቆማ እየቀረቡም ነው፡፡ መንግስት መንቀሳቀስና እርምጃ እንዳይወስድ ሸብበውት አደንዝዘውት ኖረዋል ማለት ይቻላል፡፡ የሕዝቡ የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄና ተሀድሶው ነው ሁነኛ ለውጥ እያስመዘገበ ያለው፡፡ የአሁኑ እርምጃ መንግስት የጀመረው ተሀድሶ ውጤት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳሉት ሁሉ እከሌ የተባለው ባለሀብት ከጀርባው እነእከሌ የተባሉ ታላላቅ ባለስልጣናት አሉት እየተባለ በሀገርና በሕዝብ ላይ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ሲቆምሩ በሕዝብና በመንግስት ሀብት ላይ የገዘፈ ዘረፋና ንጥቂያ ሲያደርጉ ነው የኖሩት፡፡ ሕዝቡ እስኪሰማና እስኪለይ ድረስ የነእከሌ ቡድን የእነእከሌ ጎራ እየተባለ ሙሰኛው በስም ሲነግድ ኖሮአል፡፡እንዲህ አይነቱ ነውረኛ ተግባር ለትልቅ ሀገርና ሕዝብ ጭርሱንም አይመጥንም፡፡ ቡድን ማደራጀቱ ጎራ መለየቱስ ለምን አስፈለገ የሚለውም ጥያቄ ብዙ ርቀት ወስዶ ያነጋግራል፡፡
ይህ ሁኔታ በአይና አውጣነት መንገድ እየገዘፈ ሲሄድ የሕዝቡም ምሬትና ጩሀት ኢሕአዴግን የግድ ከተኛበት እንቅልፍ እንዲባትት ነው ያደረገው፡፡ ማን ማንን ይነካል እየተባለ ይህ ችግር የሀገሪቱን ሰላምና ሕልውና እስከሚፈታተንበት ደረጃ ድረስ እንዲዘልቅ መፍቀድ የማይቻል ስለሆነ ነው ጥልቅ ተሀድሶው ለችግሮቹ መፍትሄዎች ናቸው ያላቸውን በየደረጃው በማስቀመጥ ወደስራ የገባው፡፡
መንግስት በሙሰኞች ላይ የጀመረው እርምጃ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ አስገኝቶአል፡፡ በሕዝባዊ ንቅናቄም የተደገፈ በመሆኑ ሕዝቡ ባለው ጅምር ሁኔታ ከፍተኛ ድጋፉን በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡ ትግሉ በሕዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ ጎልብቶ ሳያሰልስ ወደፊት እንደሚገፋ ጥርጥር የለውም፡፡
በምንም መስፈርት ሌብነት ሌብነት ነው፡፡ ትንሹም ሌባ ባለከረባትና ባለቪኤይቱም ሌባ ያው ሌባ ነው፡፡ ከሀገርና ከሕዝብ ጓዳና ካዝና የሚሰርቁ ሌቦች፡፡ ሰርተውና ላባቸውን አፍሰው ሳይሆን ዘርፈው የከበሩ ሌቦች፡፡ በማጭበርበር በማታለል የመንግስትና የሕዝብ ሀብት በመዝረፍ የከበሩ ሌቦች፡፡ ሕሊና ቢኖራቸው ኖሮ ለሀገርና ለሕዝብ በንጽህና ይሰራል እንጂ አይሰረቅም ነበር፡፡ የሰረቁት የድሀውን ሕዝብ ሀብት ነው፡፡አሳፋሪውም ምግባራቸው ይሄ ነው፡፡
ሕዝቡ በየአካባቢው ጠንቅቆ የሚያውቃቸውን በኢንቨስትመንት ስም መሬት በመቀራመት ከየዋሁና ምንም ከማያውቀው ድሀው ገበሬ አርሶ ልጆቹን ከሚያሳድግበት መሬቱን አታለውት በመግዛት በትንሽ ብር እያፈናቀሉ የሪል ስቴት ባለቤት ነን ባዮችን፤ በአስመጪና ላኪ ዘርፍ ተሰማርተው ከኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር መንግስት ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በማስቀረት በማጭበርበር የከበሩትን ሁሉ ሕዝብ ከመንግስት ጎን ቆሞ ያጋልጣል። ሰፊ ጥቆማዎችን እየሰጠም ይገኛል፡፡
በፌደራል የመንግስት ተቋማት፤በኮንስትራክሽን፤ በመንገድና በቤት ግንባታ፤በግዢና ጨረታ፤በአዲስ አበባ ክፍለከተሞች የመሬት ይዞታና ማኔጅመነት የተሰሩትን ሚሊዮን ወንጀሎች ሕዝብ ለመንግስት መጠቆሙን ቀጥሎአል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከሕዝብ የሚሰወር ምንም ነገር የለም፡፡ ሌቦቹም ሰርቀው የትም ማምለጥ አይችሉም፡፡
ጥቆማዎቹ ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ፤ለጸረ ሙስና ኮሚሽን፤ለልዩ ምርመራ ቢሮና ለፖሊስ ኮሚሽን እየደረሱ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተናገሩትም በላይ ከሕዝብ የተሰወረና የተደበቀ ምንም ነገር ስለሌለ ሕዝቡ ሰፊና በበቂ ማስረጃዎች የተደገፉ ጥቆማዎችን በስፋት እየሰጠ ይገኛል፡፡
የተዘረፈው ሙሰኛው የተጫወተበት የቀለደበት የመንግስትና የሕዝብ ሀብት በመሆኑ ነው ሕዝቡ በልበ ሙሉነት እያጋለጠ ለመንግስት ጥቆማ በመስጠት ላይ የሚገኘው፡፡ ኢሕአዴግ ከእንግዲህ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎችን የሚሸከምበት አንቀልባ መበጠሱን ለሕዝቡ በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡እንደቀድሞው ሙሰኞች በስሙ ሊነግዱ ከሕዝቡም ጋር ሊያቃቅሩት የሚችሉበት መረብ መበጣጠስ ጅምሮአል፡፡ችግሩ ተለይቶ የታወቀ በመሆኑ በተሀድሶው ጥልቀትና ሂደት ሙሰኞችንና ኪራይ ሰብሳቢዎችን በስፋት የማጋለጡ ስራ ይቀጥላል፡፡የዘረፉትን ሀብትና ንብረት የትም ይዘውት መሄድ አይችሉም፡፡በቅርቡ እንደታገዱት ድርጅቶችና ካምፓኒዎች ሁሉ በሙስና ውስጥ የተገኘው ሁሉ በሕግ ንብረትና ሀብቱ ይታገዳል፡፡በውጭ ሀገራት ያካበቱት ገንዘብም ካለ መንግስት የማስመለስ መብት አለው፡፡
ይሄ ሁሉ ከመንግስትና ከሕዝብ የተዘረፈ ገንዘብና ሀብት ስንትና ስንት ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች፤የጤና ጣቢያዎች፤ሆስፒታሎች፤ድልድዮች፤መንገዶች፤ ግድቦች ሊሰራ ይችል እንደነበር ሲታሰብ በእጅጉ ያማል፡፡ዘረፋቸው ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ገለዋታል ማለት ይቻላል፡፡ትውልዱንም በቆሸሸ የሙስና ባሕል በክለውታል፡፡ሰርቶ ተምሮ ለማደግና ለመስራት ሳይሆን በአቋራጭ ሳይሰራ ለመክበር የሚሮጥ እንዲሆን መንገድ መርተዋል፡፡ ወንጀላቸው ብዙ ነው፡፡
ሕዝቡን ለምሬትና ለብሶት ያበቃው ሙሰኛውና የኪራይ ሰብሳቢው ኃይል የከፋ ዘረፋ ሌብነትና ማጭበርበር ነው፡፡ዛሬ እርምጃ መውሰድ በመጀመሩ አንገት መድፋት ደብቁኝ ማለት የተጀመረበት ሁኔታም እየተስተዋለ ነው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በሙሰኞች ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ያስታወቀ እለት ባለሀብቱ ኢንቨስተሩ ታዋቂው ነጋዴ ንክኪ ያለው ሳይቀር መንገዶች ሁሉ ወደቦሌ ያመራሉ በሚል የፍርሀት ሩጫ በአውሮፕላን ለመውጣት የቦሌን ሰልፍ አጣቦት ነበር፡፡ሀገርና ሕዝብ ዘርፎ መውጣት እንደምን ይቻላል ??
መንግስትንና ሕዝብን ዘርፎ የትም መውጣት መሄድ እንደማይችሉ ሲረዱት አደብ ይዘው ወደቤታቸው ተመልሰዋል፡፡በመኪና መንገድ ድንበር አቋርጠው ለመውጣት እንዳይችሉም ድንበሮች ሁሉ በጥብቅ ቁጥጥር ስር ናቸው፡፡ይህ እንዳይሆን ነበር ተጠንቅቀው ሕግና ስርአትን አክብረው በላባቸው ሰርተው ዘረፋ ውስጥ ሳይገቡ የሕሊና መድማትና መቁሰል ሳይጨመር መሰብሰብ የነበረባቸው፡፡ቀድሞ ባልዘፈንሽ ከዘፈንሽም ባላፈርሽ ይላል የሀገራችን ሰው፡፡እንዴት እንዴት አድርገው በሕገወጥ ዘረፋና ማጭበርበር እንደከበሩ ሕሊናቸው ስለሚያውቀው በተንኳኳ ቁጥር መበርገጋቸው ትንፋሻቸው ማጠሩ የሚጠበቅ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄም አቅርበዋል፡፡እስቲ ከንግዱ ማሕበረሰብ በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ጥቆማ ያቀረበ አለ ብለው ለጠየቁት ጥያቄ መልስ አልተገኘም፡፡ዋናው በሽታ የት ሆነና ነው መልስ ሰጭ የሚኖረው ??
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡ ሰፊ ጥቆማ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ትክክልም ነው፡፡ እናንተ ናችሁ የምታውቁአቸው ምንም ያልነበረው ሰው ባለብዙ ፎቆች ባለቤት ሲሆን የምታውቁት እናንተ ናችሁ፡፡አብራችሁ የምትበሉ የምትጠጡ እናንተ ናችሁ፤በሰርግ በድግስ የምትቆዩ እናንተ ናችሁ፡፡ስለዚህ እኛን አከናንባችሁ አሁን ላይ መንግስት ዘግይቶ እንዲህ አደረገ ብላችሁ ልትሄዱ አትችሉም፡፡ጠቁሙ፤ኃላፊነታችሁን ተወጡ ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም የሀገሪቱን መረጋጋት በምንም ሒሳብ ለድርድር አናቀርብም፡፡እስከአሁንም ከወጣቶቻችን ጋር የተጋጨነው ይበቃል፡፡ስሩን ሳንነቅል አንተውም፡፡እንደበፊቱ መንግስት እንደሆነ ይሆናል እከሌ ከተነካ እንትን ይሆናል የሚባል ጨዋታ አብቅቶአል፡፡እንኳን እነእንትና የሚባሉት ቀርቶ በአሁን ሰአት የመንግስት ባለስልጣናት መያዣ መጨበጫ አጥተው ነው ያሉት፡፡ሁለት ስለት ያለው ቢላዋ አንዱን ቆርጦ አንዱን የሚያስቀርበት ሁኔታ የለም፡፡እዚህ ውስጥ እከሌ የሚባል ባለስልጣን ስለማውቅ እንደፈለኩ እሆናለሁ የሚል ሰው ካለ አሁኑኑ እጁን ይሰብስብ፡፡የሚቀጥለው እርምጃ ወደ ንግዱ ማሕበረሰብ መግባት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀልብ በሳበውና መሳጭ በሆነው በዚህ መድረክ ንግግራቸው ከዚህ በፊት ወስጥ ውስጡን የሚወሩ ነገሮች አሉ፡፡እከሌ ባለስልጣን ስለሚያውቅ አይነካም ይባላል፡፡እስቲ እንደማይነካ እናያለን፡፡እውነት የምላችሁ የማይነካ ሰው የለም፡፡ምክንያቱም ሀገር ይበልጣል፡፡ከግለሰቦች ሀገር ይበልጣል፡፡በዲሞክራሲያዊ ስርአት ውስጥ ትልቁ ምሰሶ የሕግ የበላይነትን ማክበር ነው፡፡ሌባም ቢሆን ራሱን የመከላከል መብት አለው ብለዋል፡፡
አምስት የኪራይ ሰብሳቢዎች ቦታ እንዳሉ ለይተን አውቀናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተጀመረውን ትግል ለማንቋሸሽ ብዙ እየተባለ ይገኛል፡፡አሁን ላይ የመንግስትን ጥረት ካልገታነው እሳቱ የት እንደሚደርስ አይታወቅም በሚል የሚረብሹ አሉ፡፡የፈለጉትን ቢሉ ትግላችንን አጠናክረን እሳቱ መድረስ እስከሚችልበት ድረስ መሄዳችን አይቀርም፡፡የምንታገለው ኃይል አደገኛ ነው፡፡የራሱ ኔት ወርክ ያለው ሲሆን ሕዝባዊ ንቅናቄ በጸረ ሙስና ትግሉ ላይ ካላንቀሳቀስን የመጨረሻውን ግብ ሊመታ አይችልም ሲሉ ለተሰብሳቢው የነጋዴ ማሕበረሰብ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ድንቅ መድረክ ድንቅ ንግግር፡፡
ማጠቃለያ
በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ መንግስት የጀመረውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በመወሰድ ላይ ያለው እርምጃ ተሀድሶው በግልጽ ያሰፈረው ሲሆን በተግባርም እየዋለ ይገኛል፡፡በቂ ማስረጃ እስከተገኘ ድረስ የማይጠየቅ ማንም ኃላፊ አይኖርም፡፡ከግለሰቦች በላይ ሀገር ትበልጣለች፡፡በሀገር ሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ድርድር አይኖርም፡፡በሕዝባዊ ንቅናቄ የተደገፈው የጸረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ሕዝብ አጋርነቱን በስፋት በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡