ethiopian news

Artcles

ጥልቅ ተሃድሶውና የመንግስት ቁርጠኝነት

By Admin

August 02, 2017

ጥልቅ ተሃድሶውና የመንግስት ቁርጠኝነት

ዳዊት ምትኩ

መንግስት በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ባለሃብቶችና ደላላዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወቃል። እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው 42 ደርሷል። ይህ የመንግስት ተግባር የጥልቅ ተሃድሶው አካል ነው። መንግስት ቀደም ሲል በመታደስ ሂደቱ ወቅት ኪራይ ሰብሳቢዎችን በቁጥጥር ስር እንደሚያውል በገባው ቃል መሰረት የተፈፀመ እርምጃ ነው። የመንግስት ቁርጠኝነት መገለጫም ጭምር ነው።

ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ይበልጥ እንዲሰፋና የኪራይ ሰብሳቢነትን ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነትን ለማስቀረት ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም መረጃ በመስጠት የተለመደ ድጋፉን ማድረግ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው በሀገራችን ረጅም የፖለቲካ ሂደት ወስጥ የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ፍትሐዊ የዘመናት ጥያቄዎችን አንግቦና ከአምባገነኖች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ እንዲሁም የህይወትና የአካል መስዕዋትነትን ከፍሎ በአሸናፊነት የድል ፅዋን ያነሳው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ታሪክ በተሃድሶ ውስጥ ያለፈ ነው።

የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ድርጅቱን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊያመሩ የሚችሉ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህትና የጠባብነት የዝቅጠት አደጋዎችን በተካሄደው ተሃድሶ ችግሩን መቅረፍ ችሏል። የህዝቡን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያሳልጡ የሚችሉ ዙሪያ መለስ ስትራቴጂዎችም በመንደፍም ዛሬ ለምንገኝበት አስተማማኝ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና ስር የሚሰድ ዴሞክራሲ ዕውን እንዲሆን ተደርጓል።

በእኔ እምነት ይህ የድርጅቱ ተሃድሶ ሀገራችንን አሁን ላለችበት የዕድገት ጎዳና ያበቃት ነው። በወቅቱ በአንድ በኩል ስልጣንን የኢኮኖሚያዊ ሃብትና የብልፅግና መሳሪያ በማድረግ ፀረ-ዴክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በሚሹ ወገኖች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የሃብት ምንጭ እንዳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲያብብና እንዲዳብር ብሎም የጥገኝነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዳያገኝ በሚተጉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ግምገማና የመድረክ ትግል መካሄዱን እናስታውሳለን።

ታዲያ በድርጅቱ ውስጥ ተፈጥረው በነበሩት በእነዚህ ሁለት ፅንፍ አመለካከቶች ዙሪያ በተካሄዱ ግምገማዊ የሃሳብ ፍጭት፤ ስልጣን የጥቂቶች የሃብት ማካበቻ እንዳይሆን እንዲሁም ዴሞክራሲና ዴክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ብሎም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት እንዳያገኝ የታገለው ወገን ነጥሮ በመውጣት ተሃድሶው ግቡን መትቷል፤ ውጤትም አምጥቷል።

እንደ እውነቱ ከሆነ በወቅቱ እንዲህ ዓይነቱ የተሃድሶ ርምጃ በድርጅቱ ውስጥ ባይካሄድ ኖሮ፤ ሀገራችን የምትመራባቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ስልቶች ባልተነደፉ ነበር። በድርጅቱ ውስጥ አቆጥቁጦ የነበረው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብም በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር አብሮ ባልከደሰመ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም በአንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕድገት የተገኘው ሁለንተናዊ እመርታ አይታሰብም ነበር። ሁለተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕድገት ዕቅድም ሊታለም አይችልም።

ከሁሉም በላይ ለህዳሴያችን ጉዞ የመረባረብ ሃሳቡም አይኖረንም ነበር። እናም በወቅቱ የተካሄደው ተሃድሶ ውጤታማ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ላለንበት ሀገራዊ ቁመና ፈር የቀደደ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ራሱን በራሱ እያረመ ለሚሄደው ኢህአዴግ ጠንካራ ትምህርት የሰጠው ይመስለኛል።

እርግጥ ኢህአዴግ ተሃድሶን ለታይታ የሚያደርግ ድርጅት አይደለም። የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የተካሄደው የተሃድሶ መስመር የዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅ ነው። በወቅቱ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የተካሄደው ግምገማ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ዋነኛ እንቅፋት የነበሩትን አስተሳሰቦች ማስወገድና አዲስ እሳቤን  ማረጋገጥ ተችሏል።

ይህ ሁኔታም ድርጅቱ በውስጡም ይሁን እንደ ገዥ ፓርቲነቱ በሀገር ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ በአስተማማኝ ሁኔታ በማስወገድ ፊቱን ወደ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያዞር ያደረገው ነው።

በተሃድሶው ውጤትም መላው የሀገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት በበጎ ገፅታ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ ያደረጋት ይመስለኛል። የምትከተለው በሳል የዲፕሎማሲ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች የሰላም ጠባቂ፣ መጠጊያና መጠለያ ሆናለች።

ኢህአዴግ ዳግም በመታደስ ሂደት ውስጥ ራሱንና የመንግስት አሰራሮችን ሲፈትሽ መነሻውም ሆነ መድረሻው ስር ነቀል ለውጥን ማዕከል ያደረገ መሆኑን በግልፅ ገልጿል። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የትኛውንም ወገን የሚለይ አይደለም።

መንግስት ከህዝቡ ጋር የተጀመራቸው የትግበራ ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል። የዚህ ውጤትም በቅርቡ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።

ይህ ተግባር ሁከትንና ብጥብጥን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ ለሚሹ ኃይሎች የራስ ምታት ሆኗል። በዚህም የበሬ ወለደ አሉባልታ እያሰሙ ነው። እናም ጥልቅ ተሃድሶ በሁከት ሃይሎቹ አማካኝነት “አይሳካም” በማለት የሚነዛው አሉባልታን ባዶ ያስቀረ ነው። ያም ሆኖ የሁከት ኃይሎቹ በህዝቡ ውስጥ ውዥንብርና አሉባልታ በመንዛት ውይይቶቹን ለማደናቀፍ ለመጣር ቢሞክሩም ህዝቡ ራሱ የሰላሙ ባለቤት በመሆኑ ለቅጥፈታቸው ቦታ አልሰጣቸውም።

ይህ የመንግስት ቁርጠኛ አቋም መንግስት ዛሬም እንደ ትናንቱ ቃሉን የማያጥፍና ሁሌም የሚያካሂደው ተሃድሶ በውጤት የሚታጀብ መሆኑን ያሳየ ነው። መንግስት ትናንትም ይሁን ዛሬ ያከናወናቸውና የሚያከናውናቸው ተሃድሶዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ያመጡ ናቸው።

መንግስት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የተሃድሶ ሂደት የመንግስት መዋቅሮችን የህዝቡን እርካታ በሚፈጥሩ መንገድ እያከናወነ ነው። ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በነበሩ የተሃድሶ መንገዶች የተከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክርና ይበልጥ የሚያሰርፅ ነው።

ይህ የመንግስት የተሃድሶ ቁርጠኛ አቋም በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ መጎልበት አለበት። ኪራይ ሰብሳቢዎችንና መዝባሪ ሙሰኞችን ህዝቡ በሚገባ ያውቃቸዋል። ከህዝብ ዓይን የሚሰወር ምንም ዓይነት ተግባር ባለመኖሩ መንግስት እያካሄደ ላለው ቁርጠኛ አቋም ህዝብ የማይተካ ሚና አለው። መንግስት ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ እስካገኘ ድረስ እገሌን ከእገሌ በሚል የሚለይበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም። እናም የአገራችንን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ከኪራይ ሰብሳቢነት ምህዳር ለማዳከምና በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ለመቀየር ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።