Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ነብሩን በመረብ

0 429

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ነብሩን በመረብ

ክፍል ሁለት

ኢብሳ ነመራ

በዚሁ ርዕስ በቀረበ ክፍል አንድ ጽሁፍ ሰሞኑን ጃዋር መሃመድና አጋሮቹ በኦሮሚያ ያወጁትን አድማ መነሻ በማድረግ ጉዳዩን በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ የውጭ ሚዲያዎች የያዙበትን አኳኋንና የጃዋር የአድማ አዋጅ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የማሽመድመድ ዓላማ ምንነትና አንድምታ ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ሁለት ጽሁፍ ጃዋርና መሰሎቹ ያቀረቧቸውን ጥያቄዎችና የአድማውን ባህሪ እንመለከታለን።

አድማው ይዞ የተነሳቸውን ጥያቄዎች በመመልከት እንጀምር። ጃዋር ሶስት ጥያቄዎችን ነው ያቀረበው። የመጀመሪያው የታሰሩ ፖለቲከኞች ይፈቱ የሚል የተለመደ ጥያቄ ነው። ሁለተኛው ግብርን የሚመለከት ነው። ጃዋር ያለአግባብ ከአቅም በላይ የተጫነው ግብር ይነሳ ባይ ነው። ሶሰተኛው በኦሮሚያና በኢትዮጰያ ሶማሌ ክልሎች አወሳኝ አካባቢዎች ያለ የድንበር ጉዳይ ነው። ጃዋር ከኦሮሚያ መሬት ላይ ተቆርሶ ለኢትዮጵያ ሶማሌ ተሰጥቷል ባይ ነው። እነዚህን የጃዋር ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንመልከታቸው።

የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለው ጥያቄ አዲስ አይደለም። ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት የኢፌዴሪን የመንግስት ስርአት ገጽታ ለማበላሸት ያለማቋረጥ ሲቀርብ የቆየ ጥያቄ ነው። በተለይ ህጋዊነትና ህገወጥነትን እያጣቀሱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አንድ የትግል ስልት የያዙት ይመስላል። በመሰረቱ አንድ ግለሰብ የፖለቲካ እስረኛ የሚባለው፣ በያዘው አመለካካት ወይም በሰላማዊ መንገድ በሚያራምደው አመለካካት ምክንያት ሲታሰር ነው።

በኢትዮጵያ ያለው እውነታ የዜጎች የፈቀዱትን አመለካካት የመያዝና የማራመድ፣ በአመለካከት የመደራጀት፣ ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር መብት በኢፌዴሪ ህገመንግስት ላይ የሰፈረ ብቻ አለመሆኑን ያሳየናል። እነዚህ መብቶችና ነጻነቶች የሃገሪቱ የዴሞክራሲ እድገት በሚፈቅደው ልክ በተጨባጭ ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

በሃገሪቱ በተለያየ መነሻ ምክንያት፣ በተለያየ አመለካከት የተደራጁ ከ60 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ፓርቲዎች የሚያራምዱት አቋም ህገመንግስቱ ላይ የሰፈሩ መሰረታዊ ድንጋጌዎችን የሚቃወሙ ናቸው። የብሄር ብሄረሰቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ያረጋገጠውን የህገመንግስቱን አንቀጽ 39 እንዲሁም መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የህዝብና የመንግስት ሃብት ነው የሚለውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ በፕሮግራማቸው የሚቃወሙ፣ የምርጫ አጀንዳ አድርገው ያቀረቡ፣ በዚህ አቋማቸው የምርጫ ክርክር ያካሄዱ በርካታ ፓርቲዎች አሉ። በያዙት ልዩ አመለካከት ብቻ አንዳችም ጫና አልተደረገባቸውም። በዚህ ምክንያት የታሰረ፣ የተከለከለ፣ የተጋዘ ወዘተ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የለም።

አሁን ክስ የተመሰረተባቸውና ጉዳያቸው በሂደት ላይ ያለ እንዲሁም የተፈረደባቸው  ፖለቲከኞች ለእስር የበቁት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በህዝብ ውክልና ስልጣን ላይ የቆየውን ፓርቲ ፕሮግራም ወይም ህገመንግስቱን የሚጻረር አቋም ስለያዙና ስላራመዱ አይደለም። በዚህ ምክንያት ተከሰውና ቅጣት ተፈርዶባቸው ቢሆን ነበር የፖለቲካ ወይም የህሊና እስረኛ ሊባሉ የሚችሉት። ፖለቲከኞቹ የታሰሩት በህገመንግስቱ፣ በሃገሪቱ የወንጀል ህግና ሌሎች በልዩ ሁኔታ አዋጅ የወጣላቸውን የወንጀል ድርጊቶች በመፈጸም ተጠርጥረውና መፈጸማቸው ተረጋግጦ ነው። እውነቱ ይህ ነው። ይህ ደግሞ የህግ የበላይነትን የማረጋጋጥ ጉዳይ ነው።

ዴሞክራሲና የህግ የበላይነት አይነጣጠሉም። ያለየህግ የበላይነት ዴሞክራሲን መገንባትና ማስፈን አይቻልም። ህግን የተላለፉ ዜጎችን ወይም ቡድኖችን ህግ በሚያዘው መሰረት ተጠያቂ ማድረግ ደግሞ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው። ህግ የተላለፉት ፖለቲከኞች የተከሰሱትና የተፈረደባቸው የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዴሞክራሲን ለመገነባትና ሰላምን ለማሰፈን ዓላማ ነው፤ በቃ።

በህግ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን ጉዳይ የትኛውም የመንግስት የስራ ሃላፊ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፕሬዝዳንቱ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቢሆን የመቀልበስ ስልጣን የላቸውም። የተከሳሾችን ጉዳይ በይፋ ችሎት የመመለከት፣ ከተጠያቂነት ነጻ የማድረግ ወይም የመቅጣት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው። ከመንግስት ተጽእኖ ነጻ የሆኑ ፍርድ ቤቶች መኖር የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ መሰረታዊው መርህ ነው።

ይህን መሰረታዊ የህግ የበላይነት መርህ የሚተላለፉ ባለስልጣት ያሉት መንግስት ሃገረ መምራት አይችልም፤ ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ማስከበር አይችልም፤ ሰላም ማስፈን አይችልም፤ የልማት ፖሊሲዎችን ማስፈጸም አይችልም፤ ዴሞክራሲን መገንባት አይችልም። ውሳኔዎች በህግና በህግ ብቻ ከመመራት ይልቅ የዘፈቀደ ይሆናሉ። ስለዚህ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ የወንጀል ተጠርጣሪዎችና ፍርደኞች እንዲፈቱ በሚል ጃዋር ያቀረበው ጥያቄ የህግ የበላይነት መርህን የሚጻረር ነው። አስፈጻሚው አካል የሌለውን ስልጣን እንዲጠቀም የመጠየቅ፤ በሌላ አነጋጋር መንግስት እንዲባልግ የመጠየቅ አካሄድ ነው።

መንግስት ይህን አድርጎ ቢገኝ ለአንድም ቀን ስልጣን ላይ የመቆየት የህግም ሆነ የሞራል መሰረት ያጣል። እውነተኛ ተቃዋሚዎችም መንግስት ይህን አድርጎ ቢገኝ በዝምታ አይመለከቱትም። የህግ የበላይነትን የተላለፈ መንግስት መቃብሩን የሚቆፍር መንግስት ነው። በመሆኑም የጃዋር የህግ እስረኞችን ፍቱ፣ ክሶችን ውድቅ አድርጉ የሚል ትእዛዝ በስርአቱ መቃብር ላይ ካልሆነ የሚሆን አይደለም። እርግጥ ፍርደኞች ይቅርታ የሚያገኙበት ህጋዊ ስርአት አለ። ታራሚዎች ህጉ በሚያዘው መሰረት ይህን የይቅርታ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይችላሉ።

ጃዋር ያለአግባብ የተጫነ ግብር ይነሳ በሚል ያቀረበው ጥያቄ በነጋዴው ዘንድ የተፈጠረን የግንዛቤ ክፍተት በመጠቀም ግርግር ለማስነሳት ያለመ ነው። በመሰረቱ በነጋዴው ላይ የተጫነ ከአቅም በላይ የሆነ ግብር የለም። እርግጥ ነጋዴው ማህበረሰብ በ2009 ዓ/ም የተካሄደ የእለተ ገቢ ግምትን መነሻ በማደረግ የተሰላው አመታዊ አጠቃላይ ገቢ ወይም ሽያጭ አስደንግጦታል። የድንጋጤው መንስኤ ግን የገቢ ግምቱን እንደግብር ከመውሰድ ወይም መከፈል የሚገባውን የግብር መጠን በትክክል ካለማወቅ የመነጨ ነው። የገቢዎች መስሪያ ቤት አሰራር ለዚህ የግንዛቤ ክፍተት መፈጠር ምክንያት ሆኗል። መስሪያ ቤቱ ለነጋዴው የሰጠው ደብዳቤ የገቢውን መጠን ብቻ የሚገልጽ ነበር። አጠቃላይ ገቢውን፣ ከወጪ ቀሪ ግብር የሚከፍልበትን የገቢ መጠንና የግብሩን መጠን ዘርዝሮ አያሳውቅም። ይህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ በነጋዴው ላይ የተፈጠረው ድንጋጤና ድንጋጤው ያስከተለው ተቃውሞ አዘል ቅሬታ አይኖርም ነበር። እያደረ ይህ የግንዛቤ ክፍተት ሲሞላ የታየው ሁኔታ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።

በብዙዎቹ ክልሎች አዲስ አበባን ጨምሮ እስከ 40 በመቶ የሚደርሱ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የገቢ ግምቱ ላይ ቅሬታ አቅርበዋል። ከእነዚህ መሃከል በተደረገ ዳግም የገቢ ማጣረት ስራ የአብዛኞቹ ተስተካክሏል። እርግጥ ከ5 በመቶ በታች የሚሆኑ ነጋዴዎች አሁንም ቅሬታቸው እንዳልተፈታ እየገለጹ ይገኛሉ። ይህም ቢሆን ግን ቅሬታ የሚቀርብበት ህጋዊ የይግባኝ ስርአት ስላለ ይህን የመጠቀም መብት አላቸው። በአጠቃላይ ከደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ጋር በተያየዘ የነበረው ቅሬታ ተፈትቷል ማለት ይቻላል። እናም ነጋዴውን ለአድማ የሚያነሳሳ የቀረ ችግር የለም።

ሶስተኛው የጃዋር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተላልፎ የተሰጠ መሬት አለ የሚለው ነው። ጃዋር በምስራቅ ሃረርጌ በርካታ የኦሮሚያ ቀበሌዎች ለኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተሰጥተዋል ባይ ነው። በመሰረቱ መንግስት ለሁለቱም ክልሎች ሊሰጥ፣ ሊከለክልም የሚችለው መሬት አልነበረም፤ ለወደፊትም ሊኖር አይችልም። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ነዋሪዎች ዘንድ፣ ጥብቅ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ትስስር በመኖሩ የባህልና የቋንቋ መወራራስ ተፈጥሯል። ሁለቱ ህዝቦች በጋብቻ ተሳስረው ተዋልደዋል። ከዚህ በተጨማሪ የቀደሙት ስርአቶች የአስተዳደር አወቃቀር ከህዝብ ማንነት ይልቅ በገዢዎች ፍላጎት መወሰኑ፣ በጊዜ ሂደት የሁለቱን ህዝቦች የመኖሪያ ወሰን ተረስቶ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ የሁለቱ ክልሎች የወሰን ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ ውሳኔ መስጠት እንዳይቻል አድርጓል።

በመሆኑም ከአስር ዓመት በፊት የትኛው ቀበሌ ወደየትኛው ክልል እንደሆነ ህዝቡ ራሱ እንዲወስን ህዝበ ውሳኔ ተካሂዷል። ይሁን እንጂ በህዝበ ውሳኔ የተላለፈው ወሰን መሬት ላይ ሳይካለል ቆይቷል። ይህ ሁኔታ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ጃዋርን ለመሳሰሉ የሁከት አጋፋሪዎች መልካም አጋጣሚ ፈጥሮ፣ ለጉዳዩ ያልሆነ ገጽታ በመሰጠት በሁለቱም ወገን ህዝቡን አነሳስተው ግጭት ቀስቅሰዋል። ይህን ችግር ለመፍታት በ2009 ዓ/ም ወሰን የማካለል ስራ ተከናውኗል። የወሰን ማካለሉ የህዝቡን ውሳኔ የተከተለ ነው። በዚህ ውስጥ መንግስት ህዝብ የወሰነውን መሬት ላይ ከመከለል ያለፈ የሰጠውም፣ የነሳውም መሬት የለም።

ጃዋር ግን መሬት ከኦሮሚያ ተቆርሶ ለኢትዮጵያ ሶማሌ ተሰጠ እያለን ነው። እውነታው ግን የህዝብን ውሳኔ መሬት ላይ ከማሳረፍ ውጭ ምንም የተፈጸመ ነገር እንደሌለ ነው የሚነግረን። ጃዋር ይህን ጉዳይ ያነሳው የእርስ በርስ ግጭት መቀስቀስ የሚያስችል ስሱ (sensitive) ጉዳይ ነው በሚል ስሌት ነው። ይሁን እንጂ መንግስት የህዝቡን ውሳኔ ከመፈጸም ያለፈ የሰጠውም የነሳውም ነገር ስለሌለ ጥያቄው መሰረተ ቢስ ነው። የጃዋር አካሄድ የህዝብን ውሳኔ ዋጋ የሚያሳጣ ነው። በሌላ አገላለጽ የህዝብ ንቀት የተንጸባረቀበት፣ የጃዋርን ማንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው።

ጃዋር ስላነሳቸው ጥያቄዎች ይህን ያህል ከተመለከትን ወደአድማው ባህሪና አፈጻጸም እንመለስ። በቅድሚያ ሰሞኑን ጃዋር የጠራውን አድማ ማካሄድ በተለይ የአድማው ተሳታፊ የሆነው ነጋዴ ፍላጎት አልነበረም። አድማው ከውስጥ የመነጨ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጃዋርና የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች በማህበራዊ ሚዲያ ያወጁትና አድማውን በማይተገብሩ ላይ እርምጃ እንወስዳለን በሚል ማስፈራሪያ እንዲፈጸም ያደረጉት ነው።

ጃዋር አዋጁን ሲያስተላልፍ፣ ክልከላውን የተላለፈ እርምጃ ይወሰድበታል የሚል ማስፈራሪያም አስተላልፏል። ምን ያህል የተደራጀ ሃይል እንዳሰማራ መናገር ባይቻልም ቄሮ በተሰኘ ቡድን እርምጃ እንደሚወስድ በይፋ ተናግሯል። ከተማውን መግለጽ አልፈልግም፤ እኔ በማውቀውና የተወሰኑ ሰዎችን ባነጋገርኩበት ከተማ አብዛኛው ነጋዴ ሱቁን የዘጋው፣ ጃዋር አሰማርቶታል በተባለ የወሮበላ ቡድን ሊደርስበት የሚችለውን ጥቃት በመፍራት ነው። ከአዲስ አበባ ወደኦሮሚያ ከተሞች የሚሄዱ የታክሲ አሸከርካሪዎችን ማነጋጋር ለዚህ በቂ አስረጂ ነው። እኔ የነጋገርኳቸው ባለተክሲዎች ወይም አሽከርካሪዎች መኪና የገዛነው ልንሰራ ነው፣ ቤተሰብ የምናስተዳድረው በዚህ ስራ በምናገኘው ገቢ ነው፤ ጥሩ ገቢ ወደምናገኝባቸው የአዲስ አበባ አጎራባች ከተማ መሄድ የተውነው ጃዋር በሚባል ጎረምሳ የታወጀውን አድማ ደግፈን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ብንሄድ በህይወታችንና በንብረታችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ፈርተን ነው የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል። ሱቃቸውን የዘጉትም ነጋዴዎች፣ የጃዋር ወሮበሎች ቤታችንን  ከሚያቃጥሉ፣ ቤተሰባችን ላይ አደጋ ከሚጥሉ . . . ዝጉ እስካለበት ቀን ብንዘጋ ይሻላል ብለን ነው የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡት። በዙዎቹ ነጋዴዎች መንግስት ጃዋር የሰማራቸው ወይም አሰማርቻቸዋለሁ ያላቸውን ወሮበሎች ለመከላከል ዋስትና መሰጠት የማይችል ሆኖ ስላገኙት አዝነዋል። ሁሉም መንግስት እነደሌለለበት ሃገር . . . ሲሉ ነው የሚደመጠው።

በጃዋር ትእዛዝ መሰረት ባልተዘጉ ሱቆችና የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት በቀጠሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል። በጅማ ከተማ የወትሮ የንግድ ስራቸውን ሲያከናውኑ በነበሩ ሱቆች ላይ የተወረወረው የእጅ ቦምብ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። በጅማ ከተማ የቦምብ ጥቃት መሰነዘሩን ተከትሎ መረጃ ዶት ኮም የተሰኘው የኤርትራ መንግስት ማህበራዊ ሚዲያ በኦሮሚያ ክልል የተጠራው ከቤት የመቆየት አድማ እንደቀጠለ ሲሆን፣ አድማውን የናቁ የእጃቸውን አግኝተዋል የሚል መልእክት አስተላልፋል። ጃዋር በዚሁ ማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፈው መልዕክት እስካሁን በ76 መኪኖች ላይ ትምህርት በሚሆን መልኩ እርምጃ ተወስዷል ብሏል።

እነዚህ እውነታዎች አድማው በህዝብ/ በነጋዴው ተነሳሽነትና ፍላጎት የተፈጸመ ሳይሆን፣ ጃዋር ያሰማራቸውን አሸባሪ ወንበዴዎች በመፍራት የተፈጸመ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። የሚያሳዝነው ለተከታታይ ቀናት ጉዳዮን ሲያጯጩሁ የነበሩት ቪኦኤና የጀረመን ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኞች ሁኔታው የዚህ አይነት ገጽታም እንደነበረው ማሳየት  አልመረጡም።

በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ከላይ በተገለጸው ሁኔታ ነጋዴዎች በፍርሃት ሱቃቸውን መዝጋታቸው እውነት ቢሆንም፣ ይህ የሆነው በብዙ መቶ ከሚቆጠሩ የኦሮሚያ ከተሞች በተጋነነ ግምት በሃያ ያህል ከተሞች ብቻ  ነው። የተቀሩት በርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ትልቋን አዳማ ጨምሮ ሰላማዊ የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎት ሲከናወንባቸው ነበር የሰነበተው። ነጋዴዎች ሱቃቸውን እንዲዘጉ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳይሰጡ የተደረገው በሽብርተኘነት ድርጊት ዛቻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አድማው የተወሰኑ አካባቢዎች የተካሄደ መሆኑ መታወቅ ይገባዋል። እናም ጃዋርና የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች እንዳሰቡት የተሳካ አይደለም። እነጃዋር ከሶስት ቀናት ያልተሳካ በሽብር ጥቃት ዛቻ የተመራ የአድማ ሙከራ በኋል፣ ቄሮ በኦሮሚያ ክልል የጠራውን የአምስት ቀን አድማ በሶስተኛው ቀን አቋርጫለሁ ብሏል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ይህን ያደረጉት የእንጃዋር ትእዛዝ ህዝቡና ነጋዴው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ስለሆነ፣ ይህ ሊያስከትል የሚችለውን ርምጃ በማወቅ ይመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ፤ ጃዋርና የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች የጠሩት አድማ አድማውን በጠሩት ሰዎች አንደበት በግልጽ እንደተነገረው፣ ህዝቡንና ነጋዴውን በማስፈራራት ሊፈጸም የተሞከረ የሽብርተኝነት ድርጊት ነው። መኪናዎች በድንጋይ ሲሰበሩ፣ ሱቆች ላይ ቦምብ ሲወረወር፣ የድብደባና የግድያ ዛቻ ሲዘነዘር የሰሙ ነጋዴዎች በፍርሃት የተጠየቁትን መፈጸማቸው እንደጥፋት ሊወሰድ አይችልም። በመንግስት በኩል ጃዋር ያሰማራቸው አሸባሪ ወሮበሎች የማስፈራራት አቅም እንዳይኖራቸው የማደረግ ስራ ላይ ግን ክፍተት ታይቷል።

ጃዋርና የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች ለወደፊትም የዚህ አይነት የአድማ እንዲሁም የሁከት ድርጊት ሊያውጁ መቻላቸው የሚያጠያይቅ አይደለም። ይህ አካሄድ በቀጣይነት በተለይ በአማራ ክልልም ሊያጋጥም ይችላል። በመሆኑም ወሮበላ አሸባሪዎች ህዝቡን የማስፈራራት አቅም እንዳይኖራቸው ማድረግ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። ይህ ካልሆነ የእነጃዋር የአድማና ሁከት ጥሪ ስርአት የማፈረስ ጉልበት ሊኖረው እንደማይችል እርግጠኛ ቢሆንም፣ የዜጎችን ሰላማዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ማወክ የሚችሉበትን እድል መፍጠር የለበትም። ህዘቡም አሸባሪን መፍራት፣ የበለጠ አደጋን ከመጥራት ያለፈ ደህንነትን እንደማያረጋግጥ ተገንዝቦ ከመንግስት ጎን በመቆም አሸባሪዎችን ሊያጋልጥ ይገባል። ህዝብ መንግስት ላይ ቀሬታ ቢኒረው ቅሬታውን የሚያሰማበት መድረክ እንዲመቻች ማድረግ ነው ያለበት።  አሁን ስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ባይፈልግና እንደው ቀልቡ አልወድም ቢል እንኳን መቀየር የሚችለው በአድማ አይደለም። በምርጫ ካርድ እንጂ። አድማና ሁከት አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የመንግስት ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ሃገሪቱንና ህዝቡን ይዞ ነው ገደል የሚገባው። እናም ህዝብ መረብ ሆኖ ጃዋር የላከውን አውዳሚ ነብር ማጥመድ አለበት።     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy