Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለተጨማሪ  ስኬቶች የምንተጋበት ዓመት ይሁን!

0 409

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለተጨማሪ  ስኬቶች የምንተጋበት ዓመት ይሁን!

አባ መላኩ

በአዲሱ ዓመት ተጨማሪ ስኬቶችን በማስመዝገብ  አገራችን ከድህነት ለመውጣት የጀመረችውን እልህ አስጨራሽ ትግል አንድ ምዕራፍ የምናራምድበት ዓመት መሆን መቻል አለበት። አገራችን ባለፉት 14 ዓመታት በየዘርፉ ዓለምን ያስደመመ  ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች።  የአገራችን ችግሮች  መሰረተ ሰፊና በርካታ  በመሆናቸው ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት  በተከታታይ ዓመታት ማስመዝገብ  ብንችልም ችግሮቻችንን አቃለልናቸው እንጂ አልተላቀቅናቸውም። ድህነትን ማሸነፍ በሚያስችለን ትክክለኛ መስመር ላይ ነን። ከረጅም ጊዜ እንቅልፋችን ነቅተናል፤ ሌቱ መንጋት ጀምሯል፤የለውጥና የዕድገት ብረሃን በአገራችን ፈንጥቋል። ሚሊዮኖች ከከፋ ድህነት ተላቀዋል። በየዓመቱ አዳዲስ ድሎችን እያስመዘገብን የለውጥ ጉዟችንን ተያይዘነዋል። በዚህ ዓመትም አዳዲስ ድሎች የምናስመዘግብበትና ዓመት ይሆናል።   

 

የኢኮኖሚ ችግሮቻችን  ዕልባት ማግኘት የጀመሩት አገራችን ለዘመናት የነበሩባት የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ ማግኘት በመቻላቸው ነው። ለከረሙት ችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄ የሰጠው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ነው። ሕገ-መንግሥታችን   የአዲሲቷ ኢትዮጵያ  የህልውና መሰረት ነው። የአገራችን የለውጥ ዓብነቶች  መሰረት ያደረጉት ይህን ሰነድ ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት  የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል  በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖር ከማድረጉም በላይ መንግስት  ህዝብ ከሰጠው ስልጣን  በላይ እንዳይባልግ ልጓም ሆኗል።   በአዲሰቷ ኢትዮጵያ ማንም ለፈጸመው በደል ይዋል ይደር እንጂ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም። አሁን የተጀመረው የጸረሙስና ትግል ለዚህ ጥሩ ማሳያ  ነው።  

 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ-መንግሥት ተራማጅ (Progressive) ተብሎ ከሚጠቀሱ  የዓለም ሕገ-መንግስቶች መካከል የሚመደብ ነው።  ይህ ሰነድ ዓለም አቀፍ መልካም ተሞክሮዎችን  ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያጣጣመ መሆኑ፣ የቡድንና የግለሰቦችን መብት  አጣምሮ ማስከበር መቻሉ፤ በተለያዩ የመንግስት አካላት መካከል ሚዛናዊ  የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ማደንገጉ፣ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በግልጽ ማስፈሩ፣ ራሱን በራሱ ለማደስ የሚያስችል አቀጾች ያካተተ መሆኑ እና በሕዝቦች ሙሉ ፈቃድ የጸደቀ መሆኑ ተጠቃሾች  ናቸው።

 

የኢትዮጵያ መንግሥት አወቃቀር ፓርሊሜንታዊ ሲሆን ሁለት ምክር ቤቶች  (Bicameral) የሚባል ነው። በእነዚህ ምክር ቤቶች የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸው ተድርጓል። በየአምስት ዓመቱ በሚካሄድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እነዚህ ምክር ቤቶች  ስራቸውን  ያከናውናሉ።  አገራችን ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት ያላት አገር ከሆነች 23 ዓመታትን አስቆጥራለች። በእነዚህ የሕገ-መንግሥት ዓመታት በአገራችን አምስት አጠቃላይ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዷል። ህብረተሰቡም ይሆነኛል ይበጀኛል የሚለውን ተወካዩን መርጧል።

አገራችን በምስራቅ አፍሪካ የሰለም ደሴት ለመባል የበቃችው በአገር ውስጥ በገነባችው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳቢያ ነው። አዲሲቷ ኢትዮጵያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የጎረቤት አገራት ዜጎች መጠጊያ ለመሆን በቅታለች። ዛሬ ላይ ለሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ  ስደተኞች ኢትዮጵያን  እንደሁለተኛ አገር የምትቆጥርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዲፕሎማሲው ረገድም  ኢትዮጵያችን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ተደማጭና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን በቅታለች። የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ለመሆን ችላለች። ኢትዮጵያዊው ተወካይ የዓለም የጤና ድርጅት አመራር ሆነው እንዲመረጡም የጤና ፖሊሲ ውጤታማነት ወሳኝ ሚና ነበረው።

 

ኢትዮጵያ የሰላም አምድ ለመባል በቅታለች። ባለፉት 26 ዓመታት አገራችን በርካታ ስኬታማ የሆኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን  ተወጥታለች። ኢፌዴሪ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን ዳርፉር፣ በአቢዬ፣ በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ  ህዝባዊ ወገንተኘነታቸውን በተግባር አሳይተዋል። ይህ የአገራችን መልካም ተግባር በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ  የሚቀጥል  ይሆናል።  ለተባበሩት ድርጅት ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በርካታ ሰራዊት በማዋጣት   ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በአራተኝነት  በአፍሪካ ደግሞ  በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።   

 

ሕገ-መንግሥቱ የዜጎችን ፖለቲካዊ መብቶችን ከማስከበሩም ባሻገር ዜጎች በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ አመቻችቷል ።  በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ለሁለም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እኩል  የመልማት ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎች በመመቻቸታቸው በአገራችን በሁሉም አካባቢ ተመጣጣኝ ልማት በመካሄድ ላይ ነው።  በተሃድሶ ወቅት አንድ የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊ እንዳሉት እያንዳንዱ ክልል ለልማቱም ይሁን ለውድቀቱ የመጀመሪያ ተጠያቂ ማድረግ ያለበት የራሱን ልጆች ወይም ተወካዮች መሆን መቻል አለበት ሲሉ የተናገሩት ክልሎቻችን ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እድል እንዳገኙ ሁሉ እጥረቶችንም ወደሌላ ከማሳበብ ይልቅ ወደውስጥ ማየት ይኖርባቸዋል ማለታቸው ነው። አዎ ያልተማከለ አስተዳደር አንዱ መገለጫ ስልጣንም ሆነ ተጠያቂነት  ለታችኛው የአስተዳደር ደረጃ የሚሰጥ በመሆኑ ነው።

 

ግብርና የአገራችን ኢኮኖሚ  የጀርባ አጥንት ነው። በመሆኑም በዚህ  ዘርፍ  እየተመዘገበ ያለው  ፈጣን ዕድገት  የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እጅጉን ቀይሮታል።  አገራችን ባለፈው የመኸር የምርት ዘመን ብቻ በዋና ዋና የሰብል አይነቶች  ከ323 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማሰባሰብ ችላለች። በዘንድሮው የአዝመራ ወቅት  ይህን አሃዝ   ወደ 345 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ጥረት በመደረግ ላይ ነው። በአገር ደረጃ የመግብ ሰብል ፍላጎታችንን ማረጋገጥ ተችሏል።  ይህን ተሞክሮ በቤተሰብ ደረጃ  ለማሳካት ጥረት  በመደረግ ላይ ነው።  ስኬታማ እንደምንሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻልል።  የግብርናውን ስኬት በኢንዱስትሪው ዘርፍም  በመድገም  የአገራችንን ህዳሴ ማረጋገገጥ ይቻላል። የእስካሁኑ አገራችን ተሞክሮም ይህን የሚያረጋገግጥ ነው።

 

በግብርናውን ከኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰርና የአገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ትራንስፎርም ለማድረግ  የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው።  በአገር አቀፍ ደረጃ  ወደ 11  የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም 17 የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎችን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች  በመገንባት ላይ ናቸው። እስካሁን ባለው ሶስቱ ግንባታቸው  ተጠናቆ  ስራ ጀምረዋል።  በዚህም ለበርክታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ከመቻሉም በላይ ግብርናውንና  ኢንዱስትሪውን ለማስተሳሰር ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ ፋብሪካዎች በየአካባቢው ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለአገርም ሆነ ለአርሶ አደሩ ጥቅም ያስገኛሉ።   

 

በመሰረተ ልማት ረገድም ኢትዮጵያ እጅግ ውጤታማ የሆነ ዕድገት አስመዝግባለች።  ባለፉት አስር  ዓመታት ብቻ ኢትዮጵያ በመቶ አመት ያልሰራቻቸው መሰረተ ልማቶች አስፋፍታለች። የአገር አቋራጭ የአስፋልት መንገዶች ግንባታ፣ የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ ግዙፍ የሃይል ማመንጫዎች (አገራችን በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ከአስር ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የሚያስችላት ግድቦችን) ግንባታ፣ የስኳርና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎች፣ የቤቶች ልማት እስካሁን በአዲስ አበባ ብቻ ከ170 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በመንግስት ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል። የቤቶች ግንባታ የታሰበውን ያህል ውጤት ባይመዘገብም፤ በአዲስ አበባ ብቻ 170 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ያስረከበ  እጅግ ፈታኝ ነው።  በዚህ ረገድ አንድም አፍሪካዊ አገር የኢትዮጵያን ግማሽ እንኳን ያሳካ መኖሩን እጠራጠራለሁ። በአዲሱ ዓመት ይህን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ መትጋት ተገቢ ነው።

 

በማህበራዊ ልማት ረገድም ከፍተኛ ለውጥ ታይቷል። በአገራችን የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን ከ97 በመቶ በላይ ደርሷል። የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች (አዲስ የሚገነቡትን 15 ዩኒቨርሲቲዎች ሳይጨምር)  ከ35  በላይ ተገንብተው ወደ 600 መቶ ሺህ የሚጠጉ  ከፍተኛ  ትምህርት ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ናቸው።  የጤና አገልግልት  በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷል። በአገራችን ገዳይ ተብለው የተለዩ ተላላፊ በሽታዎችን እጅጉን ቀንሰዋል። መከላከል ላይ የተመሰረተው የአገራችን የጤና ፖሊሲ ውጤታማ ሆኗል።

 

የአገራችን ዴሞክራሲ ስርዓት ያልጎለበተ ከመሆኑ አንጻር ለመልካም አስተዳደር ችግር የተጋለጠ ነው።መንግስት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የእጃቸውን እያገኙ ናቸው። የዴሞክራሲ ስርዓትን ማጎልበትና መልካም አስተዳደርን ማስፈን የአገራችን የቀጣይ የህልውና ጉዳይ ነው። በመሆኑም በዚህ በተሃድሶ ሂደት ከላይኛው የመንግስት ሃላፊዎች እስከታችኛው ዕርከን ድረስ በርካታ አስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ እንዲሁም እንደየጥፋት ደረጃቸው ተጠያቂ እየተደረጉም ነው። ማንም ለሰራው ጥፋት  ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ተዘርግገቷል። ለጥፋተኛ ቅጣት ተገቢ ቢሆንም የሰዶ ማሳደድ አካሄድ ብቻውን የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም። በመሆኑም የህዝብ አገልጋይ የሆነው የመንግስት ሰራተኛ  አገልግሎቱን በቀልጣፋነት፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ መስጠት  እንዲችል  የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ተገቢ ነው።  

 

አንዳንዶች መልካም አስተዳደር መስፈን የመንግስትና መንግስት ጉዳይ ብቻ አድረገው ይመለከቱታል። ይህ ስህተት ነው። መልካም አስተዳደር መስፈን የበርካታ ባለድረሻ አካላት ጥረት  ውጤት ነው።  መንግስት የቱንም ያህል መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ብቻውን ቢጥር ሊያሳካው የሚችል ጉዳይ አይደለም። መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ የመንግስት ድርሻ ወሳኝ  ቢሆንም ያለህብረተሰቡ ተሳትፎ ስኬታማ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም   ህብረተሰቡ  ከዚህ በፊት ያደርግ የነበረውን  ተሳትፎ  በአዲሱ ዓመት የበለጠ ማጠናከር  ይኖርብታል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy