Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለአገራችን መሪ ቃሉን ተግባራዊ ብናደርግላት ምን ይቀነስብናል?

0 459

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እኛ ኢትዮጵያውያን በወልም ይሁን በተናጠል የምንታወቅበት ከደማችን ጋር የተቆራኘ የማንነታችን መለያና መገለጫ አገራችንን ወዳድ መሆናችን ነው፡፡ የአገር ፍቅርን የተመለከቱ ጉዳዮች ሲነሱ ስሜታችን ገንፍሎ ፍቅራችን የሚገለጽበት ጉዳይም  ምክንያቱ አገርን በጥልቅ መውደዳችን ነው፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው በየትውልዱ የህይወት ቅብብሎሽና የታሪክ ዘመናት ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው  ክብር ሲሉ የመጨረሻውን የጀግንነት ተግባር በመፈፀም ሕይወታቸውን ሰውተው አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዓለም ጥሪ ባቀረበልን የሰላም ማስከበርና ዓለም አቀፍ ውድድር ሰንደቅ ዓላማችንን ይዘን በኩራት የምንሰለፈው ለአገራችን ባለን ፍቅርና ክብር ነው፡፡
በአገራችን ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈልን የመተሳሰብ ፣ የመረዳዳት፣ በደስታና በኀዘን የምናሳልፋቸው ወቅቶች  የግል እሴቶቻችን ናቸው፡፡ በእነዚህና ለአገራችን ክብርና ሉአላዊነት ጠንክረን በመቆም የዘመናት የአርበኞች የተጋድሎ ታሪክ  እንዲሁም በልዩነታችን ውስጥ ያለው ውብ አንድነታችን ለጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት ያደረገን በፍቅርና በክብር መኖራችን ነው፡፡
አገራችን የተለያዩ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች መናኸሪያ በመሆኗ ይህንን  ልዩነታችንን እንደ ጥንካሬ በመውሰድና ዴሞክራሲን በማጎልበት የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር እንዲሁም ብዝሃነትን ማስተናገድ የተቻለው፣ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ልማት የተረጋገጠው፤  ባሳየነው የእርስ በርስ ፍቅርና ለአገራችን ባለን ክብር እንጂ እንዲሁ በዘፈቀደ የተገኘ አይደለም።
የዚህ ሁሉ መሰረት ፌዴራላዊ ህገ-መንግሥቱ ሲሆን ፤ የሁሉንም ዜጎች መሠረታዊ መብት ያጎናፀፈና ያከበረ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡  አዎ! በህገ-መንግሥቱ ሳቢያ ሁሉም የግልና የቡድን ዴሞክራሲያዊ መብቶች አንዱ የሌላውን በሚደግፍ አኳኋን በተቀናጀ መልኩ ተመልሰዋል።
የአገራችን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዴሞክራሲያዊው መንግሥት በተጎናፀፉት ድል ብዝሃነታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ አድርገው በፍቅር ሌት ተቀን ለልማትና ብልጽግና በመሥራታቸው አገሪቱ አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡
ባለፉት ዓመታትም  በዓለም ቀዳሚ የሆነ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቧና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
ኢትዮጵያ ህዝቦቿ እኩልና ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ነድፋ በራሷ አቅም እየሠራች የምትገኝ ብትሆንም የልማትና የፀረ ድህነት ትግሉ ስኬታማ እንዳይሆን የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የተከሰተው ድርቅ፣ የሥነ ምግባርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለአገሪቱ ዕድገና ልማት  ፈታኝ ሆነዋል። እነዚህን መሰሎቹን ችግሮች አስወግዶ  ወደ ዕድገት ለሚደረገው ጉዞ አገር ወዳዱ ህዝብ በሙሉ ኃይሉ መረባረብ ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች የጥንካሬያቸው  መሰረት በአገር ፍቅር ስር ተጠልለው ድህነትን ለማሸነፍና የውጤቱ ባለቤት በመሆን ከዓለም በፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡት ከቻይናና ከህንድ ቀጥሎ ተጠቃሽ መሆን የምትችልበትን ስልት በመቀየስ በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወደ መካከለኛ ገቢ የመገስገስ ራዕያቸውን ተያይዘውታል። የብዝሃነት ትስስር የዘመናት የሐፍረት መለያ የሆነውንና አንገቱን ያስደፋውን ድህነት አምርሮ በመጥላት ድል ማድረግ የሚችለው ለአገሩና ለወገናቸው  ባላቸው ፍቅር በመሆኑ ዛሬንም ሆነ ነገን በፍቅር ተሳስሮ የሚያጋጥመውን ፈተና ሁሉ ድል ያደርጋል፡፡
ዛሬ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ  የአገር ፍቅር ቀንን ስናከብር «እጃችን እስኪሻክር እንሠራለን ምክንያቱም ኢትዮጵያን እንወዳታለን!» በሚል መሪ ቃል ሲሆን፤ በርግጥም በሰላምና በፍቅር ለምንኖርባት ፣ ወልደን ለምንስምባት፣ ሠርተን ለምንከብርባት አገራችን መሪ ቃሉን ተግባራዊ ብናደርግላት ምን ይቀነስብናል?

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy