Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ሐገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?” (ክፍል አንድ)

0 1,002

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ሐገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?” (ክፍል አንድ)

አሜን ተፈሪ

አንድ የድሮ ዘፈን አለ፡፡

“ሐገር መውደድ ማለት፣ ምንድን ነው ትርጉሙ

ማንቀላፋት ነው ወይ፣ ዓይንን ማስለምለሙ፡፡”

የጌታ መሣይ አበበ ዘፈን መሰለኝ፡፡ ዘፈን በዜማ እንጂ በፊደል አይሆንም፡፡ ሆኖም ለእኔ ጉዳይ ፊደሉ ይበቃል፡፡ የእኔ ጉዳይ ከዜማው ሳይሆን ከመልዕክቱ ነው፡፡ በእውነት ሐገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?

በነገራችን ላይ፣ ይህን ጉዳይ እንዳስብ ምክንያት የሆነኝ ባለፈው ሣምንት ወይም ባለፈው ዓመት የተከበረው የሐገር ፍቅር ቀን ነው፡፡ ስለዚህ ቀኑን ያከበርኩት፤ ‹‹በእውነት ሐገር መውደድ ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?›› የሚል ነገር እያሰላሰልኩ ነው፡፡

በነገሩ ብዙ አሰብኩበት፡፡ አስቤ … አስቤ ቁርጥ ካለ አንድ ሐሳብ መድረሱ ተሳነኝ፡፡ እናም ሐሳቤ ተበታትኖ ሲያስቸገረኝ፤ ‹‹የሐገር መውደድ ነገር አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም የለውም›› ለማለት ሞከርኩ፡፡ እንደኔ አስተያየት፣ የሐገር መውደድ ስሜት መገለጫ ወይም መከሰቻ ማህደር ካላገኘ አደናጋሪ እና ረቂቅ ሐሳብ ሆኖ ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግር ወይም የማይጨበጥ ጉም ሆኖ የሚቀር ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የሐገር ፍቅር ጉዳይ መከሰቻ ወይም መገለጫ እሴት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህም መከሰቻ እና መገለጫ ማህደር፤ እንደ ሐገሪቱ ተጨባጭ ወይም ወቅታዊ ይዞታ የሚለዋወጥ ገጽታ ያለው ሊይዝ የሚችል ነገር መሆኑ ሳይዘነጋ፤ ከሰው ልጆች ሁሉ መሠረታዊ ጥቅም ጋር የተጣጣመ ወይም ለዚህ እሴት ተጻራሪ ባልሆነ አመለካከት የሚገዛ ጉዳይ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ሆኖም ለሐገር መውደድ ስሜት ከድንጋይ የተቀረጸ አንድ ወጥ ትርጉም እንስጠው ከተባለ፤  ሐገር መውደድ ማለት ‹‹ሁሌም ለሐገር ወይም ለህዝብ ታማኝ ሆኖ መገኘት ነው›› የሚል ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ለሐገር ታማኝ መሆን በአንድ ድንበር ወይም የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ታማኝ በመሆን የሚገለጥ እሴት ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለተካተቱት እና በተለያየ አመለካከት (ግለሰባዊ እና ቡድናዊ) ሊገለጡ ወይም ለሚወከሉ ለሚችሉ ሰዎች ሁሉ ታማኝ መሆን ማለት ነው፡፡ እንዲህ ማድረግ የሚቻለውም ለሰው ልጆች ሁሉ ታማኝ የሚያደርግ እሴት በመያዝ ነው፡፡ ስለዚህ ሐገርን መውደድ ማለት ለሰው ልጆች ሁሉ ጠበቃ በሚያደርጉ እሴቶች እየተመሩ፤ በአንድ የፖለቲካ ማህበረስብ ለታቀፉ ሰዎች ታማኝ መሆን ማለት ነው፡፡

የሐገር መውደድ ስሜት፤ የግድ የሰው ልጆችን ከመውደድ መነሳት ይኖርበታል፡፡ በአንተ እንዲሆን የማትፈልገውን ነገር በሌሎች እንዲሆን ካለመፈለግ እሴት መነሳት አለበት፡፡ እሴቶቹ ሁሉንም ሰዎች ወይም ህዝቦች የሚመለከቱ ቢሆኑም፤ በአሁኑ ዓለማዊ ሁኔታ የሐገር ፍቅር ጉዳይ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በተመሠረተበት ክልል የሚወሰን ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብም በተለያዩ ዘመናት የሚኖሩት ዋነኛ ትኩረቶች የሚለያዩ በመሆናቸው፤ የሀገር ፍቅር መገለጫው እንደ ጊዜው የተለያየ መሆኑ አይቀርም፡፡ ሆኖም ከዚህ ተለዋዋጭ ከሆነ ጉዳይ አንድ ዘላለማዊ ወይም ቋሚ ነገር ማውጣት ይቻላል፡፡ የሐገር መውደድ ጉዳይ ማሰብ እና ማስተዋል የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሐገርን መውደድ በመሠረታዊነት በእሴቶች እና በመርሆዎች ዙሪያ የሚመሰረት አመለካከት ነው፡፡ ይህ የማይለዋወጥ ቋሚ የሀገር ፍቅር ስሜት ባህርይ ነው፡፡ ሐገርን የመውደድ ስሜት በየዋህነት እና ባለማወቅ ከተመራ አደገኛ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ባለማወቅ አንቀልባ ላይ የታዘለ የሐገር መውደድ ስሜት አጥፊ ነው፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት unpatriotic ነው፡፡

ለምሣሌ፤ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሐገር ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ እሴት ይዞ ሐገር ወዳድ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ እንዲሁም ሐገርን የመውደድ ስሜት ከግለሰብ ወይም ከቡድን ጋር መያያዝ የለበትም፡፡ በርግጥ ሐገርን የመውደድ ስሜት ከግለሰብ ወይም ከቡድን ጋር ተያይዞ የሚከሰትበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ታዲያ በዚህ መሰል አጋጣሚዎች ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ አንድ መሪ፣ ግለሰብ ወይም ቡድን ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የሚወክል ሆኖ ሲገኝ፤ በሰው ልጆች ሁሉ ተቀባይነት ያለውን እሴት ያነገበ መሪ ወይም ቡድን ሆኖ ሊወደድ ይገባዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሊቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ያ ግለሰብ ወይም ቡድን ከእሴቶቹ ተቃራኒ የሆነ ሥራ ውስጥ ሲገባ ውዴታው ይነሳል፡፡

ስለዚህ፤ ለሐገር ዘወትር ታማኝ መሆን ይገባል፡፡ ለግለሰብ ወይም ለቡድን ታማኝ የምንሆነው ወይም የምንወደው በቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ግለሰቡ ወይም ቡድኑ ክብር የሚገባቸው ሆነው እስከተገኙ ድረስ ሊከበሩ ወይም ሊወደዱ ይገባል፡፡ ከእነዚያ እሴቶች ተጻራሪ ሆነው ሲገኙ ውዴታው ይነሳል፡፡ ስለዚህ ለግለሰብ ወይም ለቡድን የሚኖረን ታማኝነት በሁኔታ የሚወሰን ሲሆን፤ ለሐገር የሚኖረን ታማኝነት ግን ቋሚ እና ዘላለማዊ ነው፡፡ ማርክ ትወይን፣ “Loyalty to country ALWAYS. Loyalty to government, when it deserves it” ይላል፡፡ በሌላ አገላለጽ “Patriotism is supporting your country all the time and your government when it deserves it” ያለው ለዚህ ነው፡፡

እንዲሁም ኤድዋርድ አቤይ (Edward Abbey) “A patriot must always be ready to defend his country against his government” የሚል ሐሳብ አለው፡፡ ይህ የማርክ ትወይን ሐሳብ ሌላ ዐ.ነገር ነው፡፡ ሐገር መውደድ ማለት “ሐገርህ በተሳሳተች ጊዜ በድፍረት መሳሳቷን መናገር ነው” ከሚል አቋም ጋር የሚገናዘብ ነው፡፡ ስለዚህ “The greatest patriotism is to tell your country when it is behaving dishonorably, foolishly, viciously” የሚሉት ትክክል ነው፡፡

ሰው በመሆን ያገኘናቸውን እና አጥብቀን የምንሻቸውን ውድ ህብረተሰባዊ እሴቶች የሚወክል ግለሰብ እና ቡድን ሊወደድ ይገባል፡፡ የሚወደደው ግን በስሙ ወይም በመልኩ አይደለም፡፡ የሚወደደው በተላበሳቸው እሴቶቹ ነው፡፡ ያ ግለሰብ ወይም ቡድን አጥብቀን የምንሻቸውን እሴቶች የሚጠብቅ እና የሚያረጋግጥ ሰው ወይም ቡድን በመሆኑ ይወደዳል፡፡ የእኒያ ውድ እሴቶች መገለጫ ወይም መከሰቻ የሆነ መሪ ወይም ቡድን ሊወደድ እና ሊከበር ይገባል፡፡ ሆኖም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የወደድነው ግለሰቡን ወይም ቡድኑን አይደለም፡፡ ይልቅስ በእርሱ የሚገለጸውን እሴት ነው፡፡

ሐገር ሁሌም መወደድ ይገባታል፡፡ ሆኖም መንግስት እና የመንግስት ወኪል የሆኑ መሪዎችን የምንወዳቸው የሚወደዱ (እጅግ የሚከበሩ እሴቶቻችንን የሚጠብቁ) ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ እነርሱ ሊወደዱ የሚገባቸው፤ እጅግ ተወዳጅ የሆኑ እሴቶታችን መገለጫ እና ጠበቃ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ነው፡፡ ስለዚህ ለመሪዎች የሚሰጥ ከበሬታ እና ታማኝነት ሊወሰድ የሚችል ችሮታ ነው፡፡ ለሐገር የሚኖረን ታማኝነት ግን ዘወትር ጸንቶ የሚኖር ነው፡፡

ለሐገር የሚኖር ታማኝነት ለተራራው ለወንዙ አይደለም፡፡ ተራራው እና ወንዙ ትርጉም የሚኖራቸው ለሰዎች ሲያገለግሉ ነው፡፡ ህዝብን ሲያገለግሉ ነው፡፡ ስለዚህ ሐገርን መውደድ ሰውን ወይም ህዝብን መውደድ ነው፡፡ አርስጣጣሊስ “Man is the measure of all things” ይላል፡፡ አዎን፤ ሰው የነገሮች ሁሉ መመዘኛ ነው፡፡ ተራራው እና ወንዙ ለሰው ወይም ለህዝብ ነው፡፡ የሁሉም ነገሮች ወይም ሥራዎች ፋይዳ መመዘኛው ለሰው የሚሰጠው ጥቅም ነው፡፡

እንደሚታወቀው፤ ሰው አብዝቶ የሚወዳቸው እና የሚኖርላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ሥራ ትልቅ ትርጉም እንዲኖረው የሚያደርገው፤ ሰው አብዝቶ  የሚወዳቸውን እና የሚኖርላቸውን እሴቶች የሚያከብር ሥራ በመሆኑ ነው፡፡ ሰው የሚወዳቸውን ነገሮች እያጠፉ ለሰው መኖር አይቻልም፡፡ ለህዝብ ጥቅም እያሉ ህዝብን የመጨፍጨፍ ተግባር ውስጥ መዘፈቅ፤ በምንም ዓይነት ሰፊ ባንዲራ ሊሸፈን የማይችል ወራዳ ተግባር ነው፡፡ መሪዎች የሚወደዱት ወይም ሊወደዱ የሚገባቸው፤ ሰዎች አብዝተው የሚሿቸውን ነገሮች የሚያስፈጽሙ መሪዎች ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የሐገር ፍቅር ስሜት በእሴት ላይ ሊመሠረት የሚገባው ለዚህ ነው፡፡ እሴቶችን እየረገጥን ስንሄድ የሐገር መውደድ ስሜት ከንቱ ይሆናል፡፡ በሐገር ፍቅር ስም የሚፈጽሙ ነውሮችን የተመለከቱ አንዳንዶች “Patriotism is the virtue of the vicious”  ያላሉ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡

የሆነው ሆኖ፤ ሐገር በየዘመኑ የሚኖራት ትኩረት የተለያየ ነው፡፡ በመሆኑም የሐገር ፍቅር ስሜት መገለጫው በዚሁ አኳያ የተለያየ ይሆናል፡፡ የሚለያየው ይዘቱ አይደለም፡፡ ቅርጹ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በምሳሌ እንፈሸው፡፡ የጃፓን የ19ኛው ክፍለ ዘመን ገጠመኝ የሐገር ፍቅር ስሜት ምን እንደሚመስል ያሳየናል፡፡ የጃፓኖች ታሪክ በዚህ ረገድ ጥሩ አብነት ሊሆን ይችላል፡፡ ሐገራችን የዘመነ መሣፍንት አስተዳደር ውስጥ በነበረች ጊዜ፤ ጃፓንም ከእኛው ጋር ተመሳሳይ በሆነ አቋም እና ስርዓት ውስጥ ትገኝ ነበር፡፡

እንደኛ ሺህ ዘመናት ባይቆዩም፤ ጃፓኖችም ለሁለት መቶ ሐምሳ ዓመታት ለሚሆን ጊዜ ከዓለም ተነጥለው ይኖሩ ነበር፡፡ ዓለም በጃፓን ውስጥ ምን ይሰራ እንደነበር አያውቅም፡፡ እርሷም በዓለም ምን እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ሳትችል ብዙ ዘመን ኖረች፡፡ የረሳትን ዓለም ረስታ ተኝታ ዘለቀች፡፡

ሆኖም፤ ከ250 ዓመታት በኋላ ሁኔታዎች ተቀየሩ፡፡ መጀመሪያ አሜሪካ፣ ቀጥሎ ፈረንሳይ፣ ከዚያም እንግሊዞች በጦር ኃይል በሯን ሰብረው ገቡ፡፡ በዚያን ጊዜ ኃያላን የሆኑትን የአውሮፓ ሐገራት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል የሌላት ደካማ ሐገር መሆኗን ተረዱት፡፡ የጃፓኑ ንጉሥ ሙትሱሂቶ ገሩ የኃያላን ሐገራትን ጉልበት ተቋቁማ ለመኖር እንደማትችል አወቀ፡፡ ጃፓን እንደ ፈለገችው ኃያላኑን መንግስታት ተከላክላ ወደ ድንበሯን ተሻግረው እንዳይገቡ ለማድረግ የማትችል ደካማ ሐገር መሆኗን አወቀው፡፡ ጃፓን የአውሮፓን ሥልጣኔ ተምራ ራሷን በጥበብ አጠናክራ ለመሄድ ካልቻለች፤ የቀድሞ አባቶቹ የፈሩት በሌሎች ኃያላን መዳፍ የመደፍጠጥ ዕጣ እንደሚገጥማት ተረዳ፡፡ ስለዚህ ሙትሱሂቶ ሐገሩ የአውሮፓን ሥልጣኔ እንድትቀበልና ትምህርት ቤቶች በሰፊው እንዲከፈቱ አዘዘ፡፡ በዚህ ወቅት የሐገር ፍቅር የሚገለጸው የምዕራቡን ጥበብ ተግቶ በማጥናት እና በመማር ነበር፡፡

ስለዚህ ጃፓኖች “የሜይዢ ዘመን” የሚሉት ዘመን ተጀመረ፡፡ “ሜይዢ” ማለት ብርሃን ማለት ነው፡፡ ጃፓኖች ከዓለም ተነጥለው ሲኖሩ በዕውቀት እና በሥልጣኔ ወደ ኋላ ቀርተው እንደተጎዱ ስለተረዱ እጅግ ተቆጩ፡፡ ፊውዳላዊ በሆነ እና እንደኛው የዘመነ መሳፍንት አገዛዝ በመሰለ የአስተዳደር ዘይቤ ሥር የቆየችው ጃፓን፤ ማዕከላዊ ኃይል በሌለው የተበታተነ እና የተዳከመ መንግስት እጅ ቆይታለች፡፡ ህዝቡ ወደ ውጪ እንዳይወጣ እና የውጭ ሰዎችም ወደ ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጎ በኖሩበት ዘመን፤ ዓለም ጥሏቸው እንደሄደ አስተዋሉ፡፡ ይህን በጃፓን ህዝብ ዘንድ የነበረውን የቁጭት ስሜት የሚያንጸባርቅ አንድ አስተያየት በ1921 ዓ.ም (እኤአ) በታተመ አንድ የቶክዮ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር፡፡

…እኛ በቤታችን ቁጭ ብለን ቅኔ በመጻፍ እና የሻይ ግብዣ በማድረግ ጉልበታችንን ሁሉ ማባከን ግዴታ ሆኖብን ኖርን፡፡ በዚህ ምክንያት ዛሬ ያገኘነው ትርፍ የሕዝባችን ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ መቸገር እና በዘር ምክንያት የተናቅን ሕዝብ ሆነን መታየት ብቻ ነው፡፡ ባለፈው የመሣፍንት አገዛዝ ዘመን ለተሰራው ስህተት ዛሬ እኛ ዕዳ ከፋዮች ሆነናል። የሚለው አስተያየት፤ የጃፓንን ህዝብ የቁጭት ስሜት

ብቻ ሳይሆን አስተዋይ መንፈሱንም የሚገልጥ ቃል ነው፡፡  

ሐገርን መውደድ፤ ሐገር በወቅቱ ወይም በዘመነ-ትውልዱ ምን እንደምትፈልግ ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ሐገርን የመውደድ ስሜት መነሻ ሊደረግ የሚገባው፤ በዘመኑ ሐገር ከምን ችግር ውስጥ እንደሆነች በመረዳት ያ የተጋረጠባት ችግር አፍኖ እንዳያስቀራት አስተውሎ ለመራመድ የሚያስችላትን እሴት አንጥሮ በማውጣት፤ ይህንንም እሴት አክብሮ በመያዝ አደጋዎችን እያስተዋሉ ለመጓዝ መጣጣር ነው፡፡ ለመሆኑ በእኛስ ዘንድ የሐገር መውደድ ስሜት ምን መልክና ይዘት አለው? ምን ምን መገለጫዎችስ አሉት? በሚቀጥለው ክፍል ይዤ እመለሳሉ። እስከዚያው ሰላም!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy