Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መልካም አስተዳደር – ዛሬም ቀዳሚ ትኩረት

0 487

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መልካም አስተዳደር – ዛሬም ቀዳሚ ትኩረት

አባ መላኩ

 

በኢትዮጵያ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየገለበተ የመምጣቱ ሁኔታ እርግጥ ሆኗል።  አንዳች እንከን የለበትም ማለት ግን አይደለም። ይህንን በተገቢው መንገድ የመገንዘብ ችግር አሁን ላይ መንፀባረቁ አልቀረም፡፡ በእርግጥ መልካም አስተዳደር የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግሥት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ማንኛውም ጉዳይ ህዝብ ካልተሳተፈበት ተፈፃሚ ሊሆን አይችልምና።

 

በመሆኑም በመንግሥት በኩል መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በሂደት የሚከናወኑት ቁርጠኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው መላው ህዝብም ዛሬም እንደ ትናንቱ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርበታል።

 

በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዓይነቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው። መንግሥት ምንም እንኳን ግዴታው ቢሆንም ህገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ብሎም ራሱም ለዴሞክራሲ ሥር መስደድ ካለው ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የዜጎች አቤቱታ የሚደመጥበት እንዲሁም ተገቢው ምላሽ የሚሰጥበት የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን አቋቁሟል።

 

ክንዋኔዎች በአንክሮና በሰከነ አዕምሮ ከታዩ መንግሥት ለዴሞክራሲው ግንባታ እውን መሆንና ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ሊመሰገን ይገባዋል። በስሜት ብቻ እየተገፋፉ መንግሥት በዘርፉ እያደረገ ያለውን ጥረት በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ታውሮ ላለመቀበልና ለማጣጣል መሞከር በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። እንዲህ ዓይነት ስንኩል አመለካከት ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ ይህ ጭፍን እሳቤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱ አሜኬላ እሾህ መሆኑ አይቀርም።

መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ሥርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ እርግጥ ነው። ታዲያ የአገራችን ፖለቲካዊ ሥርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያለው ብቻ ሳይሆን፤ መልካምና የተመቻቸ ምህዳር ጭምርም የነገሰበት ነው። ለምን ቢባል ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሥልጣን የህዝብና የህዝብ ብቻ መሆኑን በግልፅ በማስቀመጡ ነው። ሥልጣን የተገልጋዩ ህዝብ መሆኑ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር እመርታ የራሱ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አይካድምና።

 

እንደሚታወቀው መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ ሐሳብ ጉዳይ አይደለም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው የመልካም አስተዳደር ተግባር ከዜጎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፤ በአተገባበሩ ላይ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት። ህዝቡ በህገ መንግሥቱ የተጎናፀፈውን ሥልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ዕድል ይፈጥራል።

 

ታዲያ የአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይህ ሁኔታ እንዲተገበር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ችግሮችን እየተከተታተሉ በማረም ለመልካም አስተዳደር ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ከተቋቋሙት ገለልተኛ አካላት ውስጥ ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው።

 

ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እነዚህ አካላት እንዲቋቋሙ በአዋጅ ከማፅደቅ ጀምሮ ተግባራቸውንም የመልካም አስተዳደር እመርታን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈፅሙ እስከ ማድረግ ድረስ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

 

እነዚህ ገለልተኛ አካላት ህዝቡ በህገ መንግሥቱ ላይ የተደነገጉትን መሠረታዊ መብቶች ተግባራዊ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። እስካሁንም ድረስ በርካታ ህዝባዊ ጉዳዮችን በመመልከት የተጣለባቸውን ኃላፊነት አቅም በፈቀደ ሁኔታ እየተወጡ ነው። የመልካም አስተዳደር ሥራ ሂደት ነው። ምሉዕ ሊሆን በርካታ ዓመታትን ይጠይቃል።  ሀገራችንም ካለባት የማስፈፀም አቅም ውስንነት አኳያ ተያይዞ የሚታይ ነው።

እንዲህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ያለው የመልካም አስተተዳደር ትግበራ አፈፃፀም የአቅም ውስንነትን ተሻግሮ መሻሻል እያሳየ ነው። ይህ ማለት ግን ፈፅሞ የመልካም አስተዳደር ችግር የለም ማለት አይደለም። በአስቸኳይ መፈታት ያለባቸው ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሄ እየተሰጣቸው ነው። ሌሎችም እየታዩ በሂደት ምላሽ ያገኛሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማንኛውም የመልካም አስተዳደር ችግር በሂደት መስተካከሉ አይቀሬ ነው።  

 

በዛሬይቷ ኢትዮጵያ እውን በሆነው ባልተማከለው ፌዴራላዊ ሥርዓት መሠረት፤ ህዝቡ የፖለቲካ መሪዎቹንና ተወካዮቹን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ይሾማል፤ ይሽራል። ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማካይነት በቀጥታ የሥልጣን ባለቤት የሆነበት ይህ አሠራር በሥርዓቱ ውሰጥ ወሣኝ ሚና ቢኖረውም፤ በህዝቡ በቀጥታ የማይመረጡና ሊመረጡ የማይችሉ አካላት መኖራቸው አይቀርም። በዚህ የአሠራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱት ሥራ አስፈፃሚው፣ ሲቪል ሰርቪሱና የዳኝነት አካላት ናቸው።

እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅም እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ ይሆናሉ። ሆኖም ግን የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን መዘንጋት አያስፈልግም። እነዚህ አካላት ህዝቡና የህዝቡ ተወካዮች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ማወቅ ተገቢ ይሆናል። እነዚህ አካላት ይህን በማድረጋቸው የህዝቡ ሉዓላዊነት መሣሪያዎች፣ አገልጋዮችና የመልካም አስተዳደር ፈፃሚዎች ከሆኑ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱ የተጠቃሚው መብትና ጥቅም እንዳይሸራረፍ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በርካታ ተግባባራትን አከናውኗል። ይህ ተግባርም መንግሥት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መተኪያ የሌለው ድርጊት መሆኑን እንደሚያምንና በቁርጠኝነት ለመተግበርም በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀሱን የሚያመላክት ነው። ከዳኝነት ሥርዓቱ ጋር በተያያዘም ህዝቡ በተወካዮቹ አማካይነት ያፀደቀውን ህገ መንግሥትና ይወክሉኛል ባላቸው አካላት በኩል የሚወጡ ህጎችን በትክክል መተርጎሙ በዚህ መሠረትም አቅም በፈቀደ መጠን ለባለ ጉዳዩ ፈጣንና ትክክለኛ ፍትህ ያለ አንዳች አድልኦ መስጠቱ ሥር እየሰደደ ነው።

 

ታዲያ እዚህ ላይ ከአገራችን ለጋ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት አኳያ ሲቪል ሰርቪሱም ይሁን የዳኝነት ሥርዓቱ ፍፁማዊ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት አዳጋች ነው። ዴሞክራሲው ገና ጅምር በመሆኑ ብሎም ካለፉት ሥርዓቶች የወረስናቸው የተለያዩ አመለካከቶች እንቅፋት መፍጠራቸው አይቀሬ ነው። ይሁንና መንግሥት ይህን ሁኔታ ለመቅረፍ ችግሮቹን በአፋጣኝ ለመፍታት በርካታ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።  

 

የሰለጠነ የሰው ኃይልን በመፍጠርና ሥርዓቱ የሚፈልገውን የሥራ አስፈፃሚና የህግ ተርጓሚ አካላትን እውን ለማድረግ የማስፈፀም አቅምን በመገንባት ረገድ የወሰዳቸው ወሣኝ ርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው። የሰው ኃይልን በተግባር ሂደት የማብቃት፣ አሠራርና አደረጃጀትን ለማሻሻል የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስና የፍትህ አስተዳደር ማሻሻያ ተቀርፆም ወደ ተግባር በመግባት ከፍተኛ ውጤት ተገኝቶበታል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ሊያሰራ የሚችልና ወደፊት የሚጎለብት የማስፈፀም አቅምን በሲቪል ሰርቪሱና በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ ለመገንባት ተችሏል።

 

በጥቅሉ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተከናውነው ውጤት ተገኝቶባቸዋል። ይህን እውን ለማድረግም መንግሥት በየደረጃው ተጨባጭ ርምጃዎችን ወስዷል። በርካታና የተወሳሰቡ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ካለፉት ሥርዓቶች ቢረከብም በየደረጃው ተገቢ ናቸው ተብሎ በታመነባቸው ላይ ርምጃዎች ተወስዷል፤ በመውሰድ ላይም ይገኛል። መልካም አስተዳደር – ዛሬም ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶታልና!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy