Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መቻቻል፣ መከባበርንና መተማመንን ያጎለበተ ስርዓት

0 422

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መቻቻል፣ መከባበርንና መተማመንን ያጎለበተ ስርዓት

                                                               ደስታ ኃይሉ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን መቻቻል፣ መከባበርና መተማመንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያጎለበተ ነው፡፡ ይህ ቢሆንም የጥበትና የትምክህት አስተሳሰብን የሚያራምዱ የህዝብ ጠላቶች አሉባልታ የአገሪቱን ህዝቦች የእኩልነት የሚያደናቅፍ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን አንድነትን የሚያናጋ፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለአደጋ የሚዳርግ አካሄድን እየተከተሉ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች የፈለጉትን ቢሉም ፌዴራላዊ ስርዓቱ የአገራችን ህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መሰረት በመሆኑ፤ ዜጎች ፅንፈኞችን በመታገል የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመስረት ውድ የህዝብ ልጆች ህይወታቸውን የሰጡትንና አካላቸውን ያጎደሉትን ብሎም ንብረታቸውን ያጡትን ያህል እንኳን ባይሆንም፤ ከሥርዓቱ ምስረታ በኋላ በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል፡፡

ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊው ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ ከተከፈለው መስዕዋትነት አንፃር ሲታይ አሁን የተፈጠሩት ችግሮች የማይፈቱ አይደሉም፡፡ ሥርዓቱ ተግዳሮቶቹን ለመፍታት ልምድ ያለው ብቻ ሳይሆን አቅምም ያለው ነው፡፡

ያለፈውን ታሪካችንን መለስ ብለን ስንመለከት ያለፉት ሥርዓቶች ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ገዥዎችን ተጠቃሚ ያደረጉት ብቻ ሳይሆኑ፤ ሀገራችንን በሁለንተናዊ መልኩ ጎድተዋታል፡፡ ምጣኔ ሀብቷን አድቅቀዋል፤ ዜጎቿን የበይ ተመልካች በማድረግ ለችጋርና ለስደት ዳርገዋል፡፡

ይህ የታሪካችን አንድ አካል መሆኑ ጨርሶ የሚካድ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ በተለይ የጥቂት መኮንኖች ስብስብ የነበረው ወታደራዊው አምባገነናዊ የደርግ ሥርዓት የህዝቡን የትግል ውጤት በመቀማትና አጋጣሚውን በመጠቀም ድሉን ወደ የራሱ አስመስሎ በሀገሪቱ ላይ ተጨማሪ ጣጣ ፈጥሮ ማለፉ የትናንት ትውስታችን መሆኑ አይረሴ ነው፡፡ ሆኖም ሕዝቦቿ ከደርግ ውድቀት በኋላ የተረጋጋች እና ዜጎቿም ተፈቃቅደውና አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መስርተው እርስ በርስ እየተከባበሩ በፈጠሩት ፌዴራላዊ ሥርዓት የፈጣንና ተከታታይ ልማት ተቋዳሽ የሚሆኑበት ሀገር ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡

ታዲያ ይህን እየጎለበተ የመጣውንና የዴሞክራሲ ባህል እየተገነባባት ያለች ሀገርን ለመመስረት እልህ አስጨራሽ ትግልንና የህይወት መስዋዕትነትን ጭምር ጠይቋል፡፡ ይህ በታሪክ ሁሌም የሚወሳ ሃቅ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ወታደራዊው አምባገነን የደርግ ሥርዓት በተደመሰሰበት ማግስት ለሌላ ትግል የሚጋብዙ ፈታኝ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶች በሀገሪቱ ተፈጥረው ነበር፡፡ በወቅቱ ተራማጅ አስተሳሰብን የያዙ ፌዴራሊዝም ለዘመናት ደም አፍሳሽ የሆነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ያመኑ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በአንድ ጎራ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ሁለት ፅንፎች ጫፍ ላይ የወጡ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ወገኖች ነበሩ፡፡

ከእነዚህወገኖች ውስጥ አንደኛው፣ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ባላገናዘበ መልኩ የችግሮቹ መፍትሄ መገነጣጠል ነው ብሎ የሚያምን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሀገሪቱ መፍትሔ የሆነውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደ መበታተን አደጋ በመቁጠር ባረጀ እና ባፈጀ የአንድነት ስም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎም መፈቃቀድን በራሳቸው የፖለቲካ እሽክርክሪት በማጦዝ ሀገሪቱን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት አልመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡

ሆኖም በወቅቱ እነዚህን ተግዳሮቶች በሰከነ ብስለት በመፍታት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊት ሀገርን ለመመስረት ከፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ከባድ ትግል ማካሄድ ግድ ብሎ ነበር። ውጤቱም በተራማጅ ኃይሎች አሸናፊነት እልባት ሊሰጠው ችሏል፡፡

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በሚከሰቱ ጊዜያዊ ግጭቶችን ተከትሎ ፌዴራላዊ ስርዓቱ የፈጠራቸው አይደሉም፡፡ እውነቱን ለመነጋገር ግጭቶች በየትኛውም ሁኔታ ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ግጭት መፈጠር የለበትም ሊባል አይችልም፡፡

 

በየትኛውም ህዝብ መስተጋብራዊ ግንኙነት ውስጥ ግጭት መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ዋናው ጉዳይ እንዴት አድርገን ልናረጋጋቸው እንችላለን የሚለው ነው፡፡ ግጭቶች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡ መጥፎ የሚያደርጋቸው አስተሳሰባችን ነው፡፡ ለውጥን መሰረት ባደረገ አስተሳሰብ ከተቃኘ፣ ግጭት የለውጥ መነሻም ሊሆን ይችላል፡፡ እናም ፌዴራሊዝም የግጭት መነሻ ሊሆን አይችልም፤ ሆኖም አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት መቻቻልን ያመጣና በሂደትም በመጎልበት ላይ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ አወቃቀር ብዝሃነትን እንደ ውበት አድርጎ የሚነሳ በመሆኑ ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን በማጠናከር የመቻቻል መንፈስ እንዲዳብር ተደርጎ በህዝቦች ስለተዋቀረ ነው፡፡

 

የስርዓቱ ጥንካሬ ባለፉት ህገ መንግስታዊ ዓመታት ራሱን በራሱ እያረመና የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ተግዳሮቶችን እያስተካለ እንዲደርስ አስችሎታል። እንደሚታወቀው ሁሉ ከደርግ ውድቀት በኋላ የተረጋጋች እና ዜጎቿም ተፈቃቅደውና አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መስርተው እርስ በርስ እየተከባበሩ በፈጠሩት ፌዴራላዊ ሥርዓት የፈጣንና ተከታታይ ልማት ተቋዳሽ የሚሆኑበት አገር ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይህ እየጎለበተ የመጣውና የዴሞክራሲ ባህል እየተገነባባት ያለች ሀገርን ለመመስረት እልህ አስጨራሽ ትግልንና የህይወት መስዋዕትነትን ጠይቋል፡፡

 

ዛሬ ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አያሌ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ሕዝቦቿም የውጤቶቹ ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ ጨለምተኞቹ ሠላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም፡፡

በተለያዩ ወቅቶች ‘ሀገሪቱ ህገ መንግሥት ሊኖራት አይገባም እንዲሁም ብሔርን መሠረት ያደረገ ፈዴራላዊ ሥርዓት የምትገነባ ሀገር በምንም መልኩ ተጠቃሚ ልትሆን አትችልም’ የሚሉ ተቃራኒ አመለካከቶች ዋነኛ ፈተናዎች ሆኑ፡፡

ታዲያ እነዚህ መሰናክሎች ዴሞክራሲያዊ ምላሽ እየተሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቅደውና ተማምነው የአገራችንን ህገ መንግሥትን እንዲፀድቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ህገ መንግሥትም የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በመሆን የኢትዮጵያ ህዝቦችን የዘመናት ጥያቄዎችን መልሷል፡፡

አገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ መግጠም ተያዘ፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከድህነት በላይ ጠላት እንደሌላቸውም አረጋገጡ፡፡ ይህን በጽናት ለመዋጋትም እጅ ለእጅ ተያይዘው ዛሬ ድረስ ዘልቀዋል፡፡ መቻቻል፣ መከባበራቸውና መተማመናቸው ከፍ ብሏል፡፡ እነዚህ የስርዓቱ መገለጫ የሆኑት ቁልፍ ጉዳዩች ሁሌም የህዝቡ መለያ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy