Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው ከሰሩ የማይወጡት ዳገት የለም!

0 332

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው ከሰሩ የማይወጡት ዳገት የለም!

                                                  ዘአማን በላይ

መንግስትና ህዝብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። አንዱ ያለ ሌላው ሊኖር አይችልም። ሊነጣጠሉ የሚችሉ አይደሉም። መንግስት ያሻውን ያህል ዕቅድ ቢያወጣ፣ የህዝቡ ድጋፍና ተሳትፎ እስካልታከለበት ድረስ እውን ሊሆን አይችልም። ህዝብም መፃዒ ህይወቱን በብሩህ ጎዳና፣ በአስተማማኝ ሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመምራት እነዚህን ተግባራት የሚያስፈፅምለት አካል ያስፈልገዋል። ይህ አካል ደግሞ መንግስት ነው።

እነዚህ በአንድ የተረጋጋ ማህበረሰብ ውስጥ መኖር የሚገባቸው ሁለት አካላት ተቀራርበውና ተናበው ከሰሩ በሀገራችው ውስጥ ተዓምር ሊያስብል የሚችል ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። ከዚህ አኳያ የኢፌዴሪ መንግስትንና ታታሪው የሀገራችንን ህዝብ ጥሩ ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ ይመስለኛል። ባለፉት 26 ዓመታት በሀገራችን ውስጥ የተገኙት ድሎች፤ በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት የተመዘገቡት ስኬቶች የእነዚህ ሁለት አካላት መናበብና ተቀናጅቶ መስራት መሆኑ ሁሉም የሚያውቀው እውነታ ነው። ታዲያ ለዚህ እውነታ በዓይነተኛ ምሳሌ ሊቀርብ የሚችለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው።

እንደሚታወቀው የግድቡ ግንባታ እውን ከሆነ በኋላ እስከዛሬ ባሉት ከስድስት ዓመታት በላይ በተቆጠሩ ጊዜያት ውስጥ መንግስትና ህዝብ ተቀራርበውና ተናበው በጋራ እየሰሩ ነው። ይህን በማድረጋቸውም ከዚህ ቀደም አስሮ የያዛቸውን የ“አይቻልም” መንፈስ መስበር ችለዋል። የህዳሴያችን መደላድል ፈጣሪ ከሆኑት የልማት ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ ፕሮጀክት፤ የዚህ ትውልድ አሻራ በመሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ የልማት ተቋም እንዲሆን መንገስትና ህዝብ በጋራ ርብርብ እያደረጉ ነው።

በዚህ ረገድ የመንግስትንና የህዝቡን ርብርብ ለመጥቀስ ያህል፤ የሀገራችን ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚል መንግስት ያዘጋጀውን ቦንድ በመግዛት የበኩሉን ተወጥቷል፤ በመወጣትም ላይ ይገኛል። መንግስትም ግድቡን በመገንባት ረገድ የመሪነት ሚናን በመጫወት ህዝቡ በእነዚህ ከስድስት በላይ ዓመታት በሁሉም መስኮች እንዲረባረብ አድርጓል።

የኢትዮጵያውያን የትላንት ታሪክ ሀገር በወራሪዎች ስትደፈር በአንድ ላይ በመዝመት ጠላት ላይ ድል መንሳት ነበር። ይህ እሳቤም ወደ ድህነትን ድል መንሳት ወቅታዊና ትክክለኛ አስተሳሰብ ተቀይሮ ሁሉም ዜጋ በህዳሴው ግድብ ዓይነት ዓይነተኛ ሚናውን እንዲወጣ እየተደረገ ነው።  

የኢፌዴሪ መንግስት የትኛውም የሀገራችን ቀደምት መንግስታት ደፍረው የማያውቁትን በአባይ ወንዝን የመጠቀም መብታችንን ካወጀ ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ እጅና ጓንት ሆኖ በተገኘው የልማት አጋጣሚ ያለ ዕረፍት እየሰራ ነው። ወትሮም ቢሆን ይህ ድህነት ያንገሸገሸው ህዝብ እንስራና ሀገር በጋራ እንገንባ የሚል መንግስት አጥቶ እንጂ፤ በተፈጥሮው ስንፍና አይደለም።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከምንም በላይ ህዝቦች በተፈጥሮ ሃብታቸው ማልማት እንዲችሉና ድህነትን ታሪክ በማድረግ ዘመቻ ላይ በጋራ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያነሳሳ ነው። ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የሰንደቅ ዓላማችን ፕሮጀክት እየሆነ ያለው፤ አንድም ግድቡ ሲጠናቀቅ ሊሰጠው የሚችለው ጠቀሜታ እኛን ብቻ ሳይሆን ከዓባይ ጋር የተቆራኙ ሀገሮችን የሚጠቅም፣ ሁለትም ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶቻችን አቅማቸውን በመገንባት እንደገና ለተጨማሪ ታሪክ እንድንዘጋጅ አዲስ ምዕራፍ በመክፈቱ ነው። ሌላ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም። በዚህ ረገድ መንግስትና ህዝብ ተናብበውና የሀገራቸው ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑን ተገንዝበው እየተገበሩት ያለ ፕሮጀክት መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።

ይህም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተሳሰብ የለወጠ ነው ማለት ይቻላል። የአሁኑ ልጆች ዛሬ ላይ ሆነው የዚህን ታሪካዊ ግድብ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ግድቡ አልቆ ነገ ለሚወልዷቸው ልጆች ክስተቱን በታሪክነት የመናገር ጉጉታቸውን ጫፍ ላይ ያደረሰ ግድብ ሆኗል ማለት ይቻላል።

ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በመነሳሳት ወደፊትም በየጊዜው ቃላቸውን እያደሱ ለፕሮጀክቱ ይሁንታቸውን እንደሚሰጡ ከስድስት ዓመታት በላይ ያከናወኑት ተግባራቸው ምስክር ሆኖ በታሪክ ፊት ሊቀርብ የሚችል ይመስለኛል።

ይህ እውነታም ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት የሚያካሂደው ጥረት እየተጠናከረ ከመሄድ ያገደው አንዳችም ኃይል አልተገኘም። የህዝብና መንግስትን ልማታዊ ቁርጠኝነት ብሎም ተናብቦ የመስራት ውጤት ነው። እናም እንደ ትናንቶቹ አበውና እመው ይህ ትውልድም ዘወትር የሚዘከርበትን የውሃ ላይ ሃውልት እያቆመ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራዊ የፀረ ድህነት ትግሉን በማቀጣጠል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራን ይፋ የማድረጉ ምክንያትም ይኸው ይመስለኛል። ርግጥ የግድቡ ግንባታ ለዘመናት የዘለቀውን የድህነትና የኋላቀርነት ታሪካችንን የመቀየርና ያለመቀየር ጉዳይ አንዱ ምክንያት በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም።

የግድቡን ግንባታ የማሳካቱ ጉዳይ የአሁኑን ትውልድ ህይወት የመለወጥና ያለ መለወጥ ጥያቄና ውሳኔ ብቻ አይሆንም—የቀጣዩን ትውልድ ህልውና የማረጋገጥና ያለማረጋገጥ ብሎም ሀገራዊ ህልውናን የማስቀጠል ፋይዳ ያለውም ጭምር ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ሆኗል። ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ የትየሌለ ነው።

ርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብሔራዊ መግባባት መንፈስ ግድቡን ካለአንዳች ልዩነት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለመገንባት ሲነሱ ተርፏቸው አይደለም። በሚያከናውኑት ልማት ነገ ሰው እንደሚሆኑ ከመንግስት ጋር የጋራ መግባባት ላይ ስለደረሱ ነው።

ታዲያ እነዚህ እውነታዎች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር፤ መንግስትና ህዝብ በምሳሌነት ባነሳሁት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ይሁን በሌሎች የልማት ስራዎች የሚያከናውኑት ተግባር በበለጠ መናበብ፣ በበለጠ ቅንጅትና በበለጠ የጋራ ራዕይ አብረው እየሰሩ መሆናቸውን ነው። ይህም በእያንዳንዳችን ውስጥ የሚገለፅ ነው። እናም ይህ የመንግስትና የህዝብ ቅርርብ በመጪዎቹም ዓመታት ይበልጥ መጠናከር ይኖርበታል።

በመሆኑም መንግስት የመሪነት ሚናውን ሲወጣ እኛም እንደ ህዝብ ተግባራችንን ይበልጥ መወጣት ይኖርብናል። የትናንት ርብርባችን የዛሬ እርሾ መሆን አለበት። ትናንት ከነበርንበት ከፍታ ዛሬ በበለጠ ከፍ ማለት አለብን። ባለፉት ዓመታት ከመንግስት ጋር ያለን ትስሰር፣ መናበብና የጋራ የቤት ስራ በአንድነት መከወንን ነገም ቢሆን እውን ማድረግ ይኖርብናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy