Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሙሰኞችን የመመንጠር ዘመቻው በአዲሱ አመት

0 411

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሙሰኞችን የመመንጠር ዘመቻው በአዲሱ አመት

 

                                                            ይነበብ ይግለጡ

 

ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የመንግስትንና የሕዝብን ሀብትና ንብረት በመዝረፍ ድንገተኛ ክብረትን የሚያስገኝ ነው፡፡ ሙስና መገለጫው ብዙ ቢሆንም በዋነኛነት በመንግስታዊ ኃላፊነት በተለያየ ደረጃ ያሉትን ግለሰቦች በማጥመድና ተባባሪ በማድረግ የራሱን መረብ (ኔት ወርክ) በመፍጠር፣ የጥቅም ተጋሪዎችን በማሰለፍ በሕዝብና በመንግስት ሀብትና ንብረት ላይ የሚሰራ የዘረፋ ወንጀል ነው፡፡

 

በመሆኑም፣ የተሀድሶውን ለውጥ በመከተል በተሰመሩት መስመሮች መሰረት በብሔራዊ ደረጃ በሙስናና በሙሰኞች ላይ ሰፊ ዘመቻ ተጀምሮአል፡፡ ይህ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተጀመረው መጠነ ሰፊ ትግል በተጀመረው አዲስ አመት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብዙዎቻችን እምነት ነው፡፡ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የሀገርን ልማትን እድገት የትውልድንም የነገ ተሰፋ የሚገል፤ ሀገራዊ አደጋና ለመልካም አስተዳደር መጓደልና ለፍትሕ እጦት ችግሮች አይነተኛ መንስኤም ስለሆነ መዋጋትና ማጋለጥን ግድ ይላል፡፡

 

በሙስና ውስጥ በማስረጃ የተገኙ በተለያዩ ከፍተኛ መንግስታዊ የኃላፊነት ቦታዎች የነበሩ ግለሰቦችን በሕግ ቁጥጥር ስር አውሎ የመመርመሩ ስራ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ፀረ-ሀገር ጉዳይ ውስጥ የተገኘ ማንኛውም የመንግስት ኃላፊ ከመጠየቅ ሊያመልጥ የማይችል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ ለሕዝብ ገልጸዋል፡፡ እርምጃም በሕዝቡ በኩል ከፍተኛ ድጋፍን አስገኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይህ እርምጃ እስከምን ድረስ ይዘልቃል? የሚለው ከፍተኛ የሕዝብ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ውሎ ያደረ ሲሆን፤ ሕዝቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙሐን ቀርቦ በሚሰጠው አስተያየት የተጀመረው እርምጃ በመንግስት በኩል ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየጠየቀ ይገኛል፡፡ በጸረ ሙስና ትግሉ ውስጥ ከፍተኛውንና ወሳኝ ሚናና ድርሻን የሚጫወተው ሕዝቡ ነው፡፡

 

በየመስሪያ ቤቱ፣ በየተቋሙ፣ በየድርጅቱ ስለተፈጸሙ የሙስና ወነጀሎች በማስረጃ ለመንግስት ጥቆማ እያደረገ ያለውም ሕዝቡ ነው፡፡ ሀገርንና ትውልድን ከመታደግ፤ ሙሰኞችንና ኪራይ ሰብሳቢዎችን ከማጋለጥ ረገድ ታልቁን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኘውም እራሱ ህዝቡ ነው፤ ከሕዝብ ሊሰወር የሚችል አንድም ነገር የለምና፡፡

 

እያንዳንዷን የሙሰኞች እንቅስቃሴ ሕዝቡ የሚያውቅ በመሆኑ የተደበቀና የተሰወረ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ትላንት የነበረውንና ዛሬ ስርነቀል በሆነ ደረጃ የተለወጠውን ኑሮአቸውን ያውቃል፡፡ ትላንት ምንም በቂ መተዳደሪያ ያልነበረው ሰው ከመቅጽፈት በድንገት ተነስቶ ለሚሊዮነርነት ሲበቃ የበርካታ ሀብቶች፣ የቀላልና ከባድ መኪናዎች፣ የብዙ ቤቶች ባለቤት ሁኖ ሲገኝ ሕዝቡ ሲያስተውል፤ ሲታዘብ፤  እንዲህ አይነቱ ድንገቴ ክብረት ከሰማይ የወረደ ወይንስ ከየት የተገኘ/የመጣ ነው እያለ በመገረም ሲነጋገርበት፤ ሲወያይበት፤ ሲደነቅበት፤ ሲደመምበት ኖሯል፡፡

 

ሙሰኞች የሚፈልጉትን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማያንኳኩት በር የለም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ከጀርባ በሚያሰማራቸው ደላሎችና አቀባባዮች አማካኝነት ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሕዝብና የመንግስትን መሬትና ቤት ጭምር ሕገወጥ የሆነ ካርታ እንዲሰራ በማድረግ የዜጎችን በሕግ የተከበረ ሰብአዊ መብትና ነጻነት በመድፈርና በመንፈግ፤ በሕግ ስም በማስፈራራት ሲያሻቸውም በሕገ-ወጥ ተባባሪዎቻቸው አማካኝት ከሕግና ከስርአት ውጪ በማሳሰር ጭምር ተቆጥረው የማያልቁ ዘግናኝ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ በመንግስት፣ ሲያሻቸውም ስም እየጠቀሱ በከፍተኛ ባለስልጣናት ስም ሲነገድ፣ ቢዝነስ ሲሰራና እከሌ ከእኛ ጋር ነው ሲባል ተኑሮአል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምስክሩ ሕዝብ ነውና ገና ብዙ ምስክርነቶችና ተጨባጭ ማስረጃዎችን ህዝቡ ሲሰጥና ሲያጋልጥ እናያለን፡፡

 

እከሌም ሆኑ እነእከሌ በሕዝብ ተመራጭነትና አገልጋይነት የመንግስት ስልጣንና የሕዝብ ኃላፊነት ቦታዎችን ይዘው የተቀመጡት ለሀገርና ለሕዝብ ለመስራት እንጂ ቦታው በአስገኘላቸው ልዩ ኃላፊነት በመጠቀም ለመነገድ፤ ወይም የመንግስትንና የሕዝብን ሐብት በጠራራ ጸሀይ ለመዝረፍና ለመንጠቅ አይደለም፡፡ በሌላም መልኩ ከተወሰደ ሙሰኛውና ኪራይ ሰብሳቢው የባለስልጣናትን ስም ከእነሱ እውቅና ውጭ ለማስፈራራት የሚጠቀምበት፤ ተጠቃሾቹ ደግሞ ስለጉዳዩ ምንም የማያውቁበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው፤ ደላላውና ሙሰኛው በባለስልጣናት ስም መነገድ ለስራዬ ስኬት ያስገኝልኛል ብሎ ካመነ ይሄን ከማድረግ ወደኋላ እንደማይልም ሊታወቅ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ግን በእርግጠኝት አንድ ነገር ማለት ይቻላል፤ በብዙ ባለስልጣናት ስም ደላላው፣ ሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ስማቸውን እየጠራ ሲነግድባቸው ለመኖሩ መጠራጠር አይገባም፡፡ አንዳንዱም የቆሎ ጓደኛው ያህል ቅርበትና ቤተሰብነት እንዳለው እሱ ያላቸውን ሁሉ እንደሚፈጽሙለት፤ ቤት ከቤት እንደሚገናኝ ወዘተ እያስመሰለ ለባለጉዳዮች በመናገር በስማቸው ሲዘርፍና ሲነግድበት ኖሮአል፡፡ ይህም ባለስልጣናት እንደማንኛውም ወንጀለኛ ከሕግ ስር እንጂ ከሕግ በላይ ሊሆኑ እንደማይችሉ እንኳን ካለመገንዘብ የመጣ መሆኑ እነሱ ባይናገሩትም ግልፅ ነው።

 

በተቀመጠበት የኃላፊነት ወንበር ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ መልካም ስራ መስራት የሚጠቅመው ለራስም ለወገንም ነው፡፡ ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች በመንግስት ስም እየነገዱ፤ ሕገወጥ ስራ እየሰሩ፤ መንግስትንና ሕዝብን ሲያጋጩ ኖረዋል፡፡ እነዚህ ዘመናዊ ሌቦች ማስፈራሪያቸው መንግስት ነው፡፡ ከባለሀብት ጋር ከጀርባ በመደራደር የሚቀበሉትን ኮምሽን በሚሊዮን ካሰሉ በኋላ መንግስት ቦታውን ለልማት ይፈልገዋል፤ መንግስት ተነሱ ብሎአል፤ መንግስት ለልዩ ስራ ይፈልገዋል፡ እምቢ ካላችሁ ትታሰራላችሁ፤ እርምጃ ይወሰድባችኋል በሚል ሕዝብን እያስፈራሩ ያሻቸውን ሲሰሩና ወንጀል ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ አንድ ቀን በሕግ መጠየቅ እንደሚመጣ፤ ስልጣን ዘላለማዊ እንዳልሆነ ለማስተዋል እንኳን ሕሊና የላቸውም፡፡ ያሰቡት ቀርቶ ያላሰቡት ሆነና ይሄው መጠየቅ መጣ፡፡ ድሮም ውሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው አይነት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየን ስልጣንና ዘመን እንደ ጥላ የሚያልፉ መሆናቸውን እያወቁ አላውቅም የማለት ድንቁርና የሚያመጣው ጣጣ መሆኑን ነው፡፡

 

ሕዝቡ ድሮ ጉቦ ድብቅ ነበር ዛሬ ግን መንግስት ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ሰጥቶ ሕዝብን እንዲያገለግሉ ያስቀመጣቸው ሰዎች በአደባባይ አንድም ሀፍረት ብሎ ነገር ሳይኖርባቸው ይሄን ያህል ሺህ ብር ካላመጣህ/ካላመጣሽ ስራውን አንሰራም እስከማለት መድረሳቸውን በአደባባይ ይናገራል፡፡

 

ዛሬም ይህ ሁሉ መንግስታዊ መግለጫ እየተሰጠና እርምጃ እየተወሰደ በአይናቸው በብረቱ እያዩ እኛ ምን አገባን እነሱ የታሰሩት ከበቂ በላይ ዘርፈው ነው፡፡ ቢታሰሩ ቢፈረድባቸው ምን ይሆናሉ፡፡ ቤተሰባቸው አይቸገሩም፡፡ ታስረው ግዜያቸውን ጨርሰው ቢወጡም ችግር አያጋጥማቸውም፡፡ እኛም ያለውን አጋጣሚ በመጠቀም ገንዘብ ማግኘት አለብን የሚሉ ወገኖች መኖራቸውን አውቆ መንግስት ከፍተኛና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚለው የሕዝብ አስተያየት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ይህም ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ በተለይ መንግስት በሙስና ላይ የጀመረውን ሀገራዊ ዘመቻ ያሳኩልኛል ብሎ ሙሉ እምነት የጣለባቸውንም ክፍሎች መልሶ መፈተሽ ያለበት መሆኑን ያሳያልና ቸል ሊባል የሚገባው ጉዳይ አይደለም።

 

ሌባን ተከታተል፣ ያዝ ተብሎ የተላከ የሕግ አስከባሪ ከሌባው ጋር ከተባበረ፤ በሕግ የሚፈለገውን በሀገር፣ በመንግስትና በሕዝብ ሀብትና ገንዘብ ላይ እጅግ ከፍተኛ ዘረፋ የፈጸመን ተጠርጣሪ እንዲጠፋና እንዲሰወር፣ እንዲያመልጥ፣ መረጃውንም አስቀድሞ እንዲያገኝ ካደረገ ይሄ ለመንግስት ትልቅ ፈተና ነውና ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ አቅጣጫ ነው፡፡

 

ሕዝቡ መንግስት ይሰራሉ ብሎ በአመራር ላይ ባስቀመጣቸው ሰዎች የተነሳ ከፍተኛ በደል ሲፈጸምበት መንግስትን ቢያማርር ምንም የሚገርም ነገር የለም፡፡ የሕዝብ አመጽና ሁከት እንዲቀሰቀስ ያደረጉት ሕዝቡን በማስመረርና በማስከፋት ስራ ተጠምደው የኖሩት የመንግስት ኃላፊዎች የነበሩ ሰዎች እንጂ ሌላ ከውጭ የመጣ አካል አለመሆኑም ሊታወቅ ይገባል፡፡

 

ሕዘብ ከመንግሰት ብዙ ሲጠብቅ አሁንም የመንግስት ሰዎች ይሄን አይነቱን ስራ ሆን ብለው የሚሰሩ ከሆነ፤  ይህ መንግስት ለማምጣት ለሚፈልገውና ለጀመረው የተሀድሶ ለውጥ ትልቅ ጋሬጣና እንቅፋት ነውና፤ ከማንም በላይ ውስጡን መፈተሸ ያለበት መንግስት ነው፡፡ ሕዝቡ ዛሬም መንግስት ሆይ ጉያህን አጥራ ውስጥህን ደግመህ ደጋግመህ ፈትሽ እያለ ነው፡፡ ሕዝብና መንግስትንም ለማቃቃር ሆን ተብሎ  እየተሰራ ያለ ሌላ ዙር ደባና ሴራ ለመኖሩም አመላካች ነው፡፡ በመሆኑም ፀረ-ሙስና ዘመቻው በአዲሱ አመትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፤ ሳፋ ባለ እይታ የታገዘ ልዩ የአሰራር ብልሀትም ያሻዋል እላለሁ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy