Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

      ሙስናን የመዋጋት ቀዳሚ አጀንዳ!!  

0 372

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

      ሙስናን የመዋጋት ቀዳሚ አጀንዳ!!  

                                           ይነበብ ይግለጡ

በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተጀመረው ብሔራዊ ዘመቻ በአዲሱም አመት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡በተለያየ መንግስታዊ ኃላፊነት ላይ ሆነው የተሰጣቸውን ሕዝባዊና መንግስታዊ አደራ በመተላለፍ በብልሹ አሰራር ውስጥ ተዘፍቀው የተገኙትን በየደረጃው በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ በይደር የሚቆይ አይደለም፡፡ትግሉ በሰፊው ይቀጥላል፡፡

ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት የመንግስትን የሕዝብን ንብረትና ሀብት በከፍተኛ ደረጃ በመዝረፍና በማራቆት ላይ ተሰማርቶ ከአንድ ድህ ሀገር ካዝና በመመዝበር ሕገወጥ ሀብት የማከማቸት ወንጀል የሚፈጽም በመሆኑ መንግስትና ሕዝብ በቁርጠኝነት እየታገሉት ይገኛሉ፡፡

መንግስት ይህንን ሰር የሰደደ ሀገራዊ ችግር ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ሙስናን የሚያጣሩና የሚከታተሉ በፌደራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ የተለያዩ ቢሮዎችን ከፍቶአል፡፡ሕዝቡ በቀጥታ ጥቆማ የሚያደርግባቸው መድረኮችም ተመቻችተዋል፡፡

በዚህም መሰረት የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፤የጸረ ሙስና ኮሚሽን፤በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በቀጥታ የሚመራው የልዩ ምርመራ ቢሮ፤የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እነዚህ ሁሉ ከፍተኛ ሕዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነትን ተሸክመው በመንግስትና በሕዝብ ሀብት ላይ የተፈጸመውን የዘረፋ ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ እየመረመሩ እያጣሩ በበቂ ማስረጃ የሚገኘውን በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውል በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከሕዝብና ከመንግስት የሚሰወር ተሰውሮም የሚቀር ወንጀልም ሆነ ዘረፋ አይኖርም፡፡ የተጀመረው ጥልቅ ሀገራዊ ተሀድሶ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ ረገድ በሕዝቡ በኩል ምሬት ያስከተሉ ችግሮችን ለመፍታት በወሰደው የተሀድሶ እርምጃ  መሰረት ነው የጸረ ሙስና ትግሉ ውጤት እያስገኘ ያለው፡፡ይህም የተሀድሶው ውጤት ነው፡፡

በዚህም መሰረት በፌደራል፤ በክልል፤በዞን፤በወረዳና በሌሎችም የአስተዳደር እርከኖች ላይ የነበሩና በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው የተገኙ አመራሮች በተጨባጭ ማስረጃ  በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ይህ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡አይሆንምም፡፡

በመላው ሀገሪቱ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ከሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ በተጨባጭ በቀርበባቸው ማስረጃ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጎአል፡፡ወደፊትም ይሀው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ማስረጃ እስከተገኘበት ግዜ ድረስ ከተጠያቂነት የሚያመልጥ ወይም የሚተው ሰው እንደማይኖር መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቶአል፡፡

ለግለሰቦች ሲባል ሀገርን የሕዝብን ሰላምና መረጋጋት አሳልፎ መስጠት አይቻልም፡፡ ማንም ይሁን ማን በሕግና በስርአቱ መሰረት ተጠያቂ መሆን ካለበት ይሆናል፡፡ይህ አካሄድ አንድም የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራር እየጎለበተ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡ ለዲሞክራሲው ማደግም የበኩሉን ትልቅ ድርሻ ይወጣል፡፡በሙሰኛውና በኪራይ ሰብሳቢው አማካኝነት በሕዝብና በመንግስት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ሰፊ ክስተት ያጠበዋል፡፡

በጸረ ሙስና ትግሉ ውስጥ ዋናው የትግሉ መሪና ባለቤት ሕዝብ ስለሆነ የበለጠ እምነት እንዲያሳድር ያደርገዋል፡፡ሕዝቡ ትግሉን ከመንግስት ጎን ቆሞ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ይኸው ሂደት በዘንድሮው አመት ተጠናክሮ የሚገፋበት ሲሆን ወንጀለኞችን በማጋለጥ ረገድ ሕዝቡ የላቀ ሚና በመጫወት ለጸረ-ሙስናው ትግል ፋና ወጊ በመሆን በስፋት እየተንቀሳቀሰም ይገኛል፡፡

ግለሰቦችን ለሰሩት የሙስና ወንጀል ተጠያቂ የማድረግ ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ተግባር ነው፡፡አይቆምም፡፡ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማድረቅ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከመታገል አንጻር ቁርጠኛ አቋም የያዘው ዛሬ ሳይሆን ቀደም ባሉት ጊዜያትም በርካታ ከፍተኛ የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች መረጃ በተገኘባቸው ጊዜያት ለፈጸሙት ጥፋት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ከዳር የሚደርሰው ሙሰኛ ግለሰቦችን በማሳደድ ብቻ አይደለም፡፡ይልቁንም ሰፊ የአመለካከትና የግንዛቤ ማሳደግ ስራ በሕብረተሰቡ ውስጥ ሲሰራ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚጸየፍ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ለመገንባት ሲቻል ብቻ መሆኑን መንግስት ያምናል፡፡ይህ ረዥም ግዜና ሂደትን ትውልድን የማነጽና የመቅረጽ ሰፊ የቤት ስራንም ይጠይቃል፡፡ወደፊት በሰፊው የሚሰራበትም ይሆናል፡፡

የተሰጣቸውን መንግስታዊ ሕዝባዊ ታላቅ አደራና ኃላፊነት በመርገጥ በሙስና ውስጥ ሲርመጠመጡ የተገኙትን በተጨባጭ ለሕግና ፍትሕ የማቅረቡ ስራ ተከታታይት ባለው መልኩ በቋሚነት የሚኬድበት አጀንዳ ነው፡፡አይቆምም፡፡አይገታም፡፡ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ውስብስብ ባሕርይ ያለው ስለሆነ የማምከኑ ስራ ግዜን የሚጠይቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሕዝቡን አገልግሉ ሲባሉ ሕዝቡን ሲያንገላቱና በሕዝቡ ሲጠቀሙ የነበሩትን ጉዳዩን በፍጥነት ከመፈጸም ይልቅ በቀጠሮ የሚያጉላሉ የሚያስመርሩ ጉቦ ጠያቂዎች እነማን እንደነበሩ ሕዝቡ ያውቃል፡፡ያጋልጣልም፡፡የሕዝብ አደረጃጀቶችን በስፋት በመፍጠር ለጸረ ሙስና ትግሉ ወሳኝ አጋዥኃይል ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ መንግስት ሊፈጥር ይገባዋል፡፡

ዛሬም በብሔራዊ ደረጃ ስለ ጸረ ሙስና ትግሉ በሰፊው እየተነገረ እየተወራ ባለበትም ሰአት ሙሰኛውና ኪራይሰብሳቢው ኃይል አልተኛም፡፡ባለፈው ሳምንት በጉለሌ ክፍለ ከተማ መሬት ይዞታ አራት ሰራተኞች ከፍተኛ ጉቦ ሊቀበሉ ሲሉ እጅ ከፈንጅ  በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ለዚህ አቢይ ማሳያ ነው፡፡ዛሬም ስርቆቱ ዘረፋው ጉቦው አልቆመም፡፡ዛሬም በኃላፊነት ቦታው የተቀያየሩት ሰዎች ዘዴ ፈልገው ከመስረቅ ከመዝረፍ አለመታቀባቸውን ያሳያል፡፡

ሙስና የሚወለደውና የሚያድገው ምዝበራ የሚያካሂደው መንግስታዊውን የቢሮክራሲ ጫንቃ በመጠለል ነው፡፡ምክንያቱም, ያለመንግስት ኃላፊዎች ትብብርና እገዛ ልዩ የጥቅም ቁርኝት መተጋገዝና መረዳዳት ሙስና ብቻውን ሕይወት ሊዘራ አይችልም፡፡ይህን ስራ የሚሰሩት ተባባሪዎች ከ—እስከ ሳይባል በሁሉም የመንግሰት መስሪያቤቶችና ተቋማት ውስጥ እንዳሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ውስብስብና ግዜ የሚጠይቅ ትግል የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡  

አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ይላሉ አበው፡፡በሕገወጥነት የመንግስትንና የሕዝብን ሐብት  ዘርፎ ለመክበር ተግቶ ሲሰራ የነበረው ሙሰኛው ኃይል ዛሬ በተፈጠረው ሕዝባዊ ንቅናቄ  ተሸብሮአል፡፡መላ ቅጡ የጠፋውም ይመስላል፡፡ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ምጣድ ጥዶ ማና ማልቀስ እንዲሉ ሆነ፡፡ንጽሕናና ሕዝባዊ ታማኝነት መቅደም የነበረበት በፊት ነበር፡፡ሌባ ሌባ ነው ምን ቢያሽሞነሙኑት ስሙ አይቀየርም፡፡

በሕዝቡ ሰፊ ተሳትፎና ጥቆማ መሰረት የሚጋለጡ ብዙ ውስብስብ የሙስና ታሪኮችና ወንጀሎችን ገና እናያለን፡፡በሀገሪትዋ በየትኛውም አካባቢ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት አንድ መደበኛ ስራ ሁኖ ተንሰራፍቶ ጎልብቶ ጡንጫ አግኝቶ ኖሮአል፡፡ግዙፍ ዘረፋዎች ተካሂደዋል፡፡የተጠኑ ምዝበራዎች የተቀናጁ ዘረፋዎች ከደላሎች ጋር በመመሳጠር የሕዝብና የመንግስትን ሀብትና ንብረት እንደ ጠላት ገንዘብ መዝረፍ ዘርፎም መክበር በእጅጉ ገኖ ተንሰራፍቶ ቆይቶአል፡፡መጠኑ ሊለያይ ይችላል፡፡የተካሄደው ዘረፋ በምንም መልኩ ለማመንም ለመገመትም ከሚቻለው በላይ ነው፡፡አንድ ግለሰብ 980 ሚሊዮን ብር  ብር የመንግስትና የሕዝብ ሀብት በተለያየ መልኩ ዘረፈ ማለት የክብደቱን ጣሪያ ያሳያል፡፡ ,ጭካኔ የተሞላበት ዘረፋም ነው፡፡በሀገር ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የወንጀል ድርጊት ነው፡፡

የተጀመረው የጸረ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በሕዝባዊ ንቅናቄ የተደገፈ ዘመቻ በመሆኑ ሕዝብና መንግስት በጋራ ከዳር ያደርሱታል፡፡ኪራይ ሰብሳቢነትን በዘላቂነት ለማስወገድ ዋነኛ መንገድ ሊሆን የሚችለው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን የማይሸከም ሕብረተሰብ ሲፈጠር በመሆኑ ሕዝቡ በጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የመሪነት ሚናውን በግንባር ቀደምትት ይጫወታል፡፡ሙስናና ብልሹ አሰራርን ከመቆጣጠር አኳያ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ ቢሆንም ችግሩን ከመሰረቱ የሚያስወግደው በሕዝብ ደረጃ የአመለካከት ለውጥ ሲመጣና ሙስናን የሚጸየፍ ሕብረተሰብ ደረጃ በደረጃ መገንባት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ይህን ለማድረግ ግዜ ቢጠይቅም ቀጣይ ሰፈ ስራዎች መስራት ይጠበቅብናል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy