Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምክንያታዊነት—ለህገ መንግስታዊ የበላይነት

0 291

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምክንያታዊነት—ለህገ መንግስታዊ የበላይነት

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

በምክንያታዊነት የሚመራ ህዝብ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባሮች የበሰለና የሰከነ ምልከታውን የሚያሳይ ነው። አንድ ህዝብ ምክያታዊ ሳይሆን አራዶች እንደሚሉት “በአቦ ሰጠኝ” አሊያም በአሉባልታ የሚመራ ከሆነ፤ የማገናዘብ አቅሙን በሌሎች ግለሰቦች አሊያም ቡድኖች በቀላሉ ሊቀማ ይችላል። ይህ ደግሞ ዞሮ…ዞሮ በአንድም ይሁን በሌላ መልክ የህግ የበላይነት፤ በተለይም የህገ መንግስት የበላይነት ሊናድ ይችላል። ይህም በፊናው ህግና ስርዓት በስርዓት አልበኞች እንዲደፈጠጡ ምክንያት ይሆናል።

ርግጥ ምክንያታዊነት ሲጎለብት ለህገመንግስት የበላይነት የሚኖረው ጠቀሜታ አይታበይም። ከዚህ በተጨማሪ ሀገራችን እውን በማድረግ ላይ ላለችው ህገመንግስታዊ ስርዓት ቀጣይነት ያለው ጠቀሜታ የላቀ ነው። ህገ መንግስቱ የበላይ ሆኖ እስከተከበረ ድረስ በሀገራችን ውስጥ እየጎለበተ የሄደው ስርዓት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያስችላል። ይህም ስርዓቱ የሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮችን እያረመና እየፈታ እንዲሄድ ያስችለዋል።  

እንደሚታወቀው ባለፉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ምክንያታዊ የሆነ አስተሳሰብ  በመጎልበት ላይ ይገኛል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የህገ መንግስት የበላይነትና ህገመንግስታዊነት በህዝቡ ውስጥ እየሰረፁና እየጎለበቱ ናቸው። ርግጥ ሁሉም ዜጋ በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ ሊይዝ አይችልም።

ያም ሆኖ ግን አብዛኛው ዜጋ ህገመንግስታዊ ስርዓቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር መሆኑን ግንዛቤ መጨበጥ ችሏል—ባለፉት አስር ዓመታት። ታዲያ ለዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅ ሊሆን የሚችለው በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ህዝቡ ህገ መንግስትን ከማክበር ባሻገር፤ ህገ መንግስቱ በሌሎች እንዲከበር ያደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ህገ መንግስቱን ማክበርና ማስከበር የሁሉም ዜጋ የውዴታ ግዴታ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በ106 አንቀፆች የተዋቀሩ መብቶችንና ግዴታዎችን የያዘ ሰነድ ነው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ስለ የህግ የበላይነት የሚያወሳው የህገ መንግስቱ ክፍል ነው፤ በአንቀዕ ዘጠኝ ላይ። በዚህ አንቀፅ ስር ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑ፤ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደሆነ፤ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ህገ መንግስቱን የማክበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ይደነግጋል። እንዲሁም በዚህ ህገ መንግስት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ስልጣንን መያዝ የተከለከለ መሆኑን ያስረዳል።

በአንቀፁ ስር የተደነገጉት ጉዳዩች የህግ የበላይነትን የሚገልፁ ናቸው። ይህ የህግ የበላይነት ሁኔታ በሁሉም ሀገር ውስጥ የግድ መኖር ይኖርበታል። ምክንያቱም የህግ የበላይነት በሌለበት ሀገር ውስጥ ማንኛውም ሰው በሰላም ወጥቶ ሊገባ አይችልም። መብት ሰጪዎችና ነሺዎች ጉልበተኞች ይሆኑና ስርዓት አልበኝነት ይነግሳል። ጉልበተኞቹም ሌሎች ዜጎችን እንዳሻቸው በማድረግ የባሪያና ሎሌ ስርዓት ይፈጥራሉ።

ስርዓት አልበኝነት ሲገነግንም ህግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ዜጋ አይኖርም። ሁሉም በየፊናው እየሮጠ የራሱን የበላይነት ለማስጠበቅ ለማረጋገጥ ይጥራል። ይህ ሁኔታም አንድን ሀገር የነበረበትን ሰላማዊ ምህዳር በማወክ በሁከት እንዲታመስ ያደርገዋል። በሰላም ውስጥ ኖሮ ሀገርን ማበልፀግና ወደ ተሻለ ህይወት መረማመድ ያበቃለታል። እናም ይህን ሁኔታ ለመከላከልና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር የግድ ይላል።

ይህም የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር መሆኑን የሚያመላክት ነው። ምክንያቱም ህገ መንግሰቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ አስፈፃሚውም አካል ሆነ ማንኛውም ዜጋ መፍቀድ ያለበት አይመስለኝም። የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ ነውና።

የህገ መንግስታዊ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። እናም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ገቢራዊ ለማድረግ የህግ የበላይነት በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል።

የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።

እርግጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው። ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚኖርባት ይመስለኛል።

በህገ መንግስቱ መሰረት አንዱን ዜጋ ከሌላው በማበላለጥ የሚከናወን የህግ አሰራር ፈፅሞ ቦታ የለውም— መቼም ቢሆን። እናም የህግ የበላይነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስከበር ማለት የህገ መንግስቱን መንፈስ በሁሉም መስኮች ማስፈፀም ማለት መሆኑን የትኛውም ዜጋ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ይመስለኛል።

የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በነበርንበት ወቅት እንኳን የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይነካ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ይህ ጥንቃቄ የተደረገው ህገ መንግስታዊው ፌዴራላዊ ስርዓት ለሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚያደርግ ነው። የቱንም ወገን ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሲባል የሚከናወን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የለም። ሊኖርም አይችልም።

ሀገራችን ሰብዓዊ መብቶችን የምታከብረው የምትከተለው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ስለሚያዛት ብቻ ነው። ስርዓቱ ደግሞ ህዝቦች በበርካታ መስዕዋትነት ያመጡት ነው። ራሳቸው ይሁንታ እነዚህ ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የፈቀዱት ነው። ሰብዓዊ መብቶችን በማይነካና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የህግ የበላይነትን የማስከር ስራ እንዲከናወን ይፈቅዳል። ይህ ሁኔታም ማናቸውም ችገሮች በህግ አግባብ ብቻ እንዲፈቱ የሚያደርግ ነው። ምንም እንኳን በየትኛውም ሀገር ውስጥ ችግሮች መኖራቸው ነባራዊ ሃቅ ቢሆንም፤ ችግሮቹን በተገቢው ሁኔታ መፍታት ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።

ችግሮች አግባብ ባለው መንገድ ከተፈቱ ደግሞ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ እየፈካና እየጎመራ እንዲሄድ ያስችላል። ታዲያ ይህን ለማድረግ ሀሉም በምክንያታዊ አስተሳሰብ መደርጀት አለበት። ምክንያታዊነት የህገ መንግስታዊ ልዕልናን ከማረጋገጥ ባሻገር ህዝቦች በስምምነት እውን እንዲሆን የፈቀዱት ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲቀጥል የሚያደርግ ስለሆነ፤ ባለፉት አስር ዓመታት እየሰረፁ የመጡትን ይህን ሚዛናዊ አስተሳሰብ ይበልጥ ማጎልበት ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy