Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስኬቶች ለማሳነስና ድክመቶችን  ለማጎን እንሽቀዳደም!

0 385

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስኬቶች ለማሳነስና ድክመቶችን  ለማጎን እንሽቀዳደም!

አባ መላኩ

 

የፌዴራል ስርዓታችን  አገራችን  ላስመዘገበችው  ዘርፈ ብዙ ስኬቶች  መሰረት ሆኗል።  ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀ የነበረውን ችግሯን መፍታት የቻለችው በዚህ  የፌዴራል ስርዓት ነው። አንዳንዶች እዚህና እዚያ የሚነሱ ትናንሽ ግጭቶችን እንደማሳያ በማቅረብ  ፌዴራል ስርዓቱ  ድክመት አድርገው ለማቅረብ  ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።  ጽንፈኛው አካል  የፌዴራል ስርዓቱ ካስገኛቸው በርካታ  ትላልቅ ጠቀሜታዎች ይልቅ  በየአካባቢው የሚከሰቱ ትናንሽ ግጭቶችን በማነፍነፍ  የፌዴራል ስርዓቱ  ውጤት አድርገው ለማቅረብ  በመሯሯጥ ላይ ናቸው። እንደእኔ  ይህ ለማንም የሚበጅ አይደለም። ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች፣ የበርካታ ሃይማኖቶች፣ በርካታ አስተሳሰቦች፣ በርካታ ባህሎች ወዘተ  ያሉባት አገር ናት። እነዚህን በርካታ ልዩነቶች ሊያስትናግድ የሚችል የአስተዳድር ስርዓት መከተል የግድ ይላታል፤ ይህ ስርዓት ደግሞ ከነእጥረቱም ቢሆን  የፌዴራል ስርዓት ነው።   

    

በኢትዮጵያ የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦችን  ማንነት፣ እኩልነትና ነጻነት አሁን ካለው የፌዴራል ስርዓት በተሻለ ሊያረጋግጥ የሚችል ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።  በደርግ ስርዓት ውድቀት ማግስት የአብዛኛውን  ህዝቦች ፍላጎት ሊያሟላና የአገሪቱን  አንድነት  ሊያስቀጥል የሚችለው ይህ የአስተዳደር ስርዓት ብቻ ነበር።  በዚያን ወቅት ከ17 በላይ በርካታና የተለያዩ  የታጠቁ ሃይሎች በነበሩበት ሁኔታ  ሁሉንም ፍላጎቶች ማጣጣም የሚችል የአስተዳደር  ስርዓት  ከመተግበር ውጪ  አማራጭ አልነበረም። ያ ስርዓት ደግሞ የአሁኑ የፌዴራል  የአስተዳደር ስርዓት ነው።  ይህ የፌዴራል ስርዓት ምንም ችግር የለበትም ፍጹም ነው ባይባልም ከአህዳዊ የአስተዳደር ስርዓት ግን እጅጉን የተሻለና  በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ተጨባጭ  ለውጦችን  ማምጣት የቻለ፤ አገራችንን ወደ ከፍታ ያሸጋገረ ነው።   

 

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በዚህ  የፌዴራል ስርዓት በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ፣ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደሩ  ወዘተ  በማድረግ  ሁኔታዎችን አመቻችቷል።  የፌዴራል ስርዓታችን  የአገራችንን  ሰላም  ዘላቂና አስተማማኝ ከማድረጉም  ባሻገር  የአገሪቱን አንድነት  በጠንካራ አለት ላይ እንዲመሰረት አድርጓል።  አገራችንን ከብተና የታደገና ወደ ብልጽግና እንድታመራ ያደረገው ይህ   የፌዴራል ስርዓት መሆኑ መታወቅ አለበት።  በተለያየ ምክንያት  ግጭቶች ሲከሰቱ  የፌዴራል ስርዓቱን  ውጤት ተደርጎ  መወሰድ  የለበትም።  የአካባቢ ግጭቶች   በቀድሞዎቹ  አህዳዊ  ስርዓቶችም  የነበሩ፤ ምናልባትም  ነገም የሚኖሩ ናቸው። ምክንያቱም የእነዚህ ግጭቶች መንስዔ እጅግ በርካታ በመሆናቸው ነው።  

 

አገራችን የተከተለችው ያልተማከለ አስተዳደር  የህዝቦች  ዴሞክራሲያዊና ሰባዊ መብቶች ከማረጋገጥ ባሻገር አገሪቱን በፈጣን  የኢኮኖሚ ለውጥ ምህዋር ውስጥ አስገብቷታል። ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ መድረክ የነበራት ገጽታም ሆነ  ተሰሚነት እጅጉን  ተለውጧል። አገራችን ትላንት ትታወቅበት የነበረው ድርቅ፣ ረሃብና ጦርነት ዛሬ የለም። ዛሬ ላይ አገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ሰፍኗል። አገራችን በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው። ከባድ ድርቅ ለተከታታይ ዓመታት ቢከሰትም በራስ አቅም መቋቋም ተችሏል።  አሁን ላይ  በረሃብ የሚሞት አንድም ዜጋ  የለም። ስራ የማማረጥ አባዜ እና  የክፍያ ማነስ ካልሆነ በስተቀር  ማንም መስራት የሚችልና  የሚፈልግ  ዜጋ ጦሙን የማያድርባት አገር መፍጠር እየተቻለ ነው።  በአትኩሮት ለተመለከተው ትልቅ ጥንካሬ ነው።  ይህ የፌዴራል ስርዓታችን ስኬት አይደለምን?

 

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ  በአፍሪካ ሆነ  በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ በማደጉ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን በተባበሩት መንግስታት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረከኮች ያላት ቦታ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን መንግስት ባከናወነው  ተግባር ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ  አገራችን በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅት አመራር ለመሆን የበቃችው በስኬታማ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ሳቢያ ነው።  ይህ የፌዴራል ስርዓቱ ስኬት አይደለምን?  እነዚህን ትላልቅ  የፌዴራል ስርዓታችን  ስኬቶች ወደ ጎን ተብለው  ለምን  ትናንሽ ነገሮችን ብቻ ለማጎን  እንሽቀዳደማለን?

 

ከጥቂት ዓመታት በፊት  የድርቅና ረሃብ ተምሳሌት ተደርጋ ትጠቀስ የነበረች አገር ዛሬ ላይ ባለ ብዙ ቢሊዬን ዶላር ወጪን የሚጠይቁ  ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሳይቀር በራስ አቅም የመገንባት  አቅም መፍጠር የቻለች በለተስፋ አገር ለመሆን በቅታለች።  አሁን ላይ  በመላ አገሪቱ  በርካታ መሰረተ ልማቶች  በመስፋፋት ላይ ናቸው።  መዲናችን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነች።  የዓለም ዓቀፍ  ተቋማትና ዲፕሎማቶች መኖሪያ  የሆነችው አዲስ አበባችን  ፈርሳ በመገንባት ላይ ያለች ከተማ  ሆናለች። በየትኛውም  የአዲስ አበባ ክፍል የሚዘዋወር  ሰው  አዳዲስ ህንጻዎችንና  መንገዶችን  መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።  እጅግ የሚገርመው ጽንፈኛው ሃይል  ፈርሳ በአዲስ መልክ እየተገነባች ያለችው   አዲስ አበባችን ለውጥ እንኳን አይታየውም። አዲስ አበባችን እንደስሟ  አዲስ  በመሆን ላይ ነች። ይህ ስኬት  የተመዘገበው  በፌዴራል ስርዓታችን ሳቢያ አይደለምን?

አገራችን ከራሷ አልፋ  ለቀጠናው አገራት ሊተርፍ  የሚችል ትላልቅ  ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነች።  በታዳጊ  አገር  አቅም ለመገንባት አይታሰብም የሚባለውን ታላቁ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ  በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና  ህዝቦች  ጥረት  ከግማሽ በላይ ደርሷል። ይህ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር   የአካባቢው አገራትን   የኢኮኖሚ ትስስሩንም  የበለጠ ያሳድገዋል። ይህ የፌዴራል ስርዓቱ እውን ከሆነ ብኋላ የመጣ ስኬት አይደለምን?

ኢትዮጵያ አህጉሩን እየመራች ያለችው በኤኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው አገሮች  የነበረውን ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ መፍትሄ በማፈላለግ ጭምር ነው።  ሽብርተኝነትንም  በመዋጋት ረገድ  ኢትዮጵያ ለዓለም ዓቀፉ  ማህበረሰብ  ግንባር ቀደም ተዋናይ ነች።   የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው ጽንፈኛ አልሸባብ  በሶማሊያና በአካባቢው አገሮች እያደረሰ ያለውን ጥፋት ለመከላከል ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ  በመወጣት ላይ ነች።  የመከላከያ  ሃይላችን  የህዝቦችን  ደህንነት  ለመጠበቅ ይቅርና ለአፍሪካ ህዝቦች  ድህንነት መረጋገጥ  ድንበር  ተሻግሮ  በመስራት ስኬታማነቱን አረጋግጧል። በዚህ  ሰራዊት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ አፍሪካዊያን ጭምር የሚኮሩበት ሃይል ነው።     

አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን  ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባባሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር ሙገሳን ተችሯታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተሰደዱ ከስምንት መቶ ሃመሳ  ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ስናስታውስ እንኳን ለሌሎች አገሮች ዜጎች መጠለያ ልትሆን ይቅርና የራሷ ህዝቦችም በጦርነትና በረሃብ ሳቢያ የትውልድ ቀያቸውን  ጥለው የሚሰደዱባት አገር ነበረች።  

ይሁንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት  በተመዘገቡ  ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች   ለአገር ውስጥ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገራት ህዝቦች ጭምር  አምባ መጠጊያ ለመሆን በቅታለች።  ከፍተኛ ቁጥር ያለው  ስደተኛ   የሚፈጥረው  ጫና ከባድ ቢሆንም አገራችን አቅም በፈቀደ ሁሉ ለስደተኞች  ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው እያደረገች ትገኛለች። እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች የመነጩት አገራችን ከምትከተለው የፌዴራል ስርዓት መሆኑን መገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy