በቀል ማንንም አሸናፊ አድርጎ አያውቅም!
ወንድይራድ ኃብተየስ
የፌዴራል ሥርዓታችን የአገራችን እስትንፋስ ነው። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲም ሆነ ፈጣን ልማት የዚህ የፌዴራል ሥርዓት ውጤት ነው። ጽንፈኛው ኃይል ድብቅ የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካት ሲል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ሰሞኑን በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በወንድማማች ህዝቦች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ከዚያም ነገሮችን በማራገብ ግጭቱ የተለየ መልክ እንዲይዝ በማድረጉ ለበርካታ ንጹሃን ዜጎቻችን ህይወት መጥፋት፣ አካል መጉደል፣ ለንብረት መውደምና ለመፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ለዘመናት አብረው የኖሩ በበርካታ ነገሮቻቸው ተወራራሽ የሆኑ ለመለየት በሚከብድ ሁኔታ አንድ የሆኑ ህዝቦች ናቸው። በድንበር አካባቢ የሚኖሩት የሁለቱ ብሄሮች ህዝቦች ከመቀራረባቸው የተነሳ አንዱ ሌላውን መለየት እስከሚከብድ ድረስ የተሳሰሩ ናቸው።
ጽንፈኛው ሃይል ተቆርቆሪ በመምሰል ህዝቦች ለባሰ ግጭት እንዲነሳሱ የበቀል ስሜቶችን ሲቀሰቅሱ የሚችሉ ነገሮችን ሲያናፍስ ነበር። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች በርካታ የዋሆችን አሳስተው ለጥፋት አላማቸው ማሳኪያ አድርገዋቸዋል። ይሁንና ሠላም ወዳዱ የሁለቱ ብሄሮች ህዝቦች ሰከን ብለው በማሰባቸው የባሰ እልቂት እንዳይከሰት ማድረግ ችለዋል።
ጽንፈኛው ሃይል እነዚህን ህዝቦች በማታኮስ፣ እነዚህን ህዝቦች በማጋደል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚያደርገው ሲሯሯጥ ምን ያህል የወረደ አስተሳሰብ እንዳለው የሚያሳይ ነው። በሁለቱም ብሄሮች በኩል ያሉ ጽንፈኛ ሃይሎች ለህዝብ ጥቅም አሳቢና ተቆርቋሪ መስለው በመቅረብ ህዝቦችን ለበቀል እንዲነሳሱ ሲቀሰቅሱ ታይተዋል። በመደጋገፍ፣ በመተባበርና በመተሳሰብ እንጂ ልዩነትን በማስፋትና እርስ በርስ በመገፋፋትና በመጠላለፍ ለህዝቦች ጥቅምና ለአገር እድገት የሚመጣ አንዳችም መልካም ነገር የለም። የመጣንበት 27 ዓመታትም የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ማንኛውም አካል እጁ በዚህ ግጭት ውስጥ ያለ አካል ከህግ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ አስረግጠው የተናገሩት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለድርድር እንደማይቀርብ አንዱ ማሳያ ነው። አዎ ማንኛውም አካል ለዚህ ግጭት ምክንያት የሆነ አካል ከህግ ፊት ቀርቦ ማየት እንፈልጋለን።
ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው አንዳንዶች የህዝብን ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ ህገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ታይተዋል። የጥበትና ትምክህት ሃይሉ ለህዝብና አገር ተቆርቋሪ በመምሰል ህዝቡን ተጠቃህ፣ ወገኖችህ አለቁ ወዘተ…በማለት በግጭቶች ላይ ቢንዚን ሲያርከፈክፍ ታይተዋል። ህብረተሰቡ እነዚህን የጥፋት ሃይሎች ለህግ አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል።
ጽንፈኛው ሃይል እያከናወናቸው ያለው መርዘኛ የፖለቲካ አካሄዱ ከህዝብ የሚያራርቀው እንጂ የሚያቀራርበው አይደለም። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች የሚያሰራጯቸው መርዘኛ መረጃዎች ለህዝብ የሚያስብ፣ ለአገር አንድነት የሚጨነቅ አለመሆኑን በግልጽ እየታየ ነው።
የእነዚህ ሃይሎች ህዝብን በተሳሳተ ዓላማቸው ዙሪያ ለማሰባሰብ እና የግል የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ በፈጠሩት ሁከት የንጹሃ ህይወት ተቀጥፏል፣ አካል ጎድሏል፣ ንብረት ንብረት ውድሟል። እነዚህ ሃይሎች አገራችን እንድትረጋጋ አይፈልጉም። በመሆኑም በእንዲህ ያለ የወረደ ድርጊቶችን የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ አካላትን ከመንግስት ጎን ቆመን ልናወግዛቸው ወደ ህግ እንዲቀርቡና ለፈጸሙት እብደት እንዲጠየቁ ማድረግ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ተግባር ሊሆን ይገባል።
የትምክህትና የጥበት ሃይሎችን አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። ሁለቱም ሁከት ቀስቃሾች መሆናቸውና ንጹሃንን በማጋጨትና ደም በማፍሰስ፣ ንብረት በማውደም በሁከት መካከል ወደ ሥልጣን መሰላል መሰቀል የሚፈልጉ መሆናቸው ነው። እነዚህ አካላት ስለመቻቻል፣ ስለእኩልነት፣ ስለአብሮ መኖር ወዘተ…አይሰብኩም። እነዚህ አካላት ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት፣ ስለዕድገትና ልማት እንዲሁም ስለህዝቦች አብሮነት ሲናገሩ አይደመጡም። እነዚህ አካላት ህዝቦችን ለማጋጨት አበክረው ይሰራሉ። ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሰሞኑን በምስራቁ የአገራችን ክፍል የተከሰተውን ግጭት ማየት ብቻ በቂ ነው።
ለአገራችን ሠላም መሠረቱ የአገራችን ህገ-መንግሥት ነው። ህገ-መንግሥታችን ለቆዩ ችግሮቻችን እልባትን አስገኝቷል። የፌዴራሊዝም ስርዓታችን ያስተማረን ትልቅ ነገር መቻቻልና መከባበርን ነው። ይሁንና ይህን እሴታችንን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች በየአካባቢው እያስተዋልን ነው።
ህዝቦችን በማጋጨት የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ለማንም አይበጅ። ወክለዋለሁ ለሚባለው ብሄርም ቢሆን በመደጋገፍና በመተሳሰብ አብሮ በመኖር እንጂ በመነቋቆር የሚገኝ አንዳችም ትርፍ የለም። በዚህ የጥፋት ድርጊት የተሰማራም ሆነ የጥፋት ሃይል ያሰማራ ማንኛውም አካል መጠየቅ ይኖርበታል። አገራችን ላለፉት 14 ተከታታይ ዓመታት ዓለምን ያስደመመ ባለሁለት ዲጂት ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው በመደጋገፍና በመተሳሰብ መሥራት በመቻላችን እንጂ በሁከትና ቀውስ አይደለም።
በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ፌዴራሊዝም ሥርዓታችን የፈጠራቸው ችግሮች እንዳልሆኑ በእርግጠኝነት ግን መናገር ይቻላል፡፡ በህግ መንግሥቱ የተቀመጡ የፌዴራሊዝም መርሆዎችና እሴቶችን በአግባቡ በመፈፀም ላይ ውስንነቶች ቢታዩም እንዲህ ያለ ህዝብን ለመጉዳት ታስቦ የሚደረግ እንቅስቃሴዎችን ግን የፌዴራል ሥርዓቱ ክፍተት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የፌዴራል ስርዓታችን የቡድኖችን መብት ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችንም ማንኛውንም መብት ማረጋገጥ የቻለ አገራችን ዘላቂ ሠላም እንድታገኝ ያስቻለ ሥርዓት ነው።
ብዝሃነት ዋጋ የሚከፈልለት እንደመሆኑ መጠን በአሁኑ ወቅት ብዝሃነትን የሚሸረሽሩ አንዳንድ ለይቶ የማጥቃት ጅማሮዎች እየታዩ ነው። እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ አካሄዶችን ገና በእንጭጩ መቅረፍ የመንግሥት ሥራ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ተግባር መሆን መቻል አለበት። ይህ ተግባር የህገ መንግሥቱን መርህ ይቃረናል።
ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበትም ሆነ ከድህነት ለመውጣት ለምናደርገው ርብርብ የሚበጅ አይደለም። መንግሥት በየትኛውም አካባቢ በየትኛውም ወቅት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማስጠበቅ ግዴታ አለበት። ይህን ማስጠበቅ የማይችል መንግሥት መንግሥት ሊባል አይችልም። የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያሯሩጡ አካላትን ለህግ አሳልፈን በመስጠት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የማድረግ ሥራ የሁላችንም ተግባር መሆን ይኖርበታል።