Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዲስ ተስፋ የታጀበ ወጣት

0 330

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ ተስፋ የታጀበ ወጣት

                                                ደስታ ኃይሉ

መንግስት በአዲሱ ዓመት የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የገባውን ቃል በመፈጸም ላይ ይገኛል። በተለይም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከማስፋፋት ባሻገር ከፍተኛ በጀት በመመደብ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን በመገንባት ወጣቱ  የትምህርት ዕድሉ እንዲሰፋ በማድረግ፣ በአገሩ ውስጥ ሰርቶ እንዲለወጥ ተዘዋዋሪ ፈንድ በማቅረብ፣  በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ባሉት የልማት ስራዎች ላይ ተጠቃሚ እንዲሆን…ወዘተ ተጠቃሚነቶችን ለወጣቱ አቅርቧል። ይህም ወጣቱ በአዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ ውስጥ ታጅቦ መጪውን ዓመት በተስፋ እንዲቃኝ አድርጎታል።

 

እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ሥርዓቶች ለትምህርት ተቋማት መስፋፋትና ለፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት የተሰጠ ትኩረት አልነበረም፡፡ ከታች እስከ ላይ ድረስ የነበሩት የትምህርት ተቋማት ውስን ከመሆናቸውም በላይ የተቋቋሙት በከተሞች ብቻ ነበር፤ በአገሪቱ አንድም የግል ዩኒቨርስቲ ሆነ ኮሌጅ አልነበረም፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት ትምህርት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቷል፡፡ በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል፡፡ እድሜው ለትምህርት  የደረሰ ህጻን ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋንም ሰፍቷል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የሚታደሙበት ማዕድ ሆኗል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ተስፋፍተዋል፡፡ ይህም ዛሬ ከሶስቱ ኢትዮጵያ አንዱ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኝ አድርጓል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርትን አስፈላጊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር  በትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ህፃናት የምግብ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ ምገባው ህፃናት በምግብ አቅርቦት ማነስ ምክንያት ከትምህርታቸው እንዳይሰናከሉ የገዘ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት ቤቶች ስርጭት ኢ- ፍትሃዊነትን ለማስወገድ በአገሪቱ እያደገ የመጣው የትምህርት ቤቶች ቁጥር ሥርጭት ፍትሃዊነቱን እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡  ከዚህ አንፃር ቀደም የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡

በትምህርት ሥርጭት ላይ የነበረው ኢ-ፍትሃዊነት በክልሎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ኢ-ፍትሃዊ ስርጭት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተመጣጣነ ሁኔታ ማደግ እንዳይችሉ እንዲሁም የልማት ተጠቃሚነታቸውም ላይ ልዩነት መፍጠሩ የሚታወቅ ነው፡፡

በአገራችን ባለፉት 26 ዓመታት ከተሰሩት ተግባራት አንዱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የትምህርት ስርጭት እንዲኖር መደረጉ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው የትምህርት አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

በአገሪቱ የነበሩት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታድሰዋል፣ የማስፋፊያ ግንባታም ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በልዩ ትኩረት እንዲስፋፉ በመደረጉ የተቋማቱ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ባለፉት 26 ዓመታት በተግባር ታይቷል፡፡ ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንጂ ክፍት ስራ ፈላጊ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድም ውጤታማ ተግባር እየፈፀሙ ነው፤ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡፡

በእነዚህ ዓመታት ወጣቶች ስራ ፈጣሪና ባለሙያ ሆነው የሚሰለጥኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በአገሪቱ ሥራ ፈጣሪና በራሱ የሚተማመን ወጣት ማፍራት የሚችሉ ከአምስት መቶ በላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተቋቁመው የሥልጠና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ተስፋፍተዋል። ተቋማቱ በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ያፈራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን ያደርጋሉ፡፡

የእነዚህ ተግባሮች ደግሞ ግንባር ቀደም ተዋናዩች ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህን በመንግስት ለወጣቱ የተበረከተ ምቹ ሁኔታ ወጣቶች በተገቢው ሁኔታ ከተጠቀሙበት ራሳቸውንና አገራቸውን መለወጥ የሚችሉበት ታላቅ መሳሪያ ይሆናል፡፡

 

የወጣቱን የትምህርት እድል ለማስፋት የግል የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ተደርጓል። ይህ አገሪቱ ለልማት የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የግል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ የተማረና ብቃት ያለው ባለሙያ በሌለበት አገር ዘላቂ ልማት የሚታሰብ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያሳየችው ውጤትም አገሪቱ እያስመዘገበች ላለው የምጣኔ ሃብት እድገት መሠረት ነው፡፡ በዚህም አገራችን የሚሊየሙን የልማት ግብ ከማሳካት ባሻገር፤ ለጥራት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው፡፡ በሐሰት የትምህርት ማስረጃ ላይ በየክልሉ እየተደረጉ ያሉት የማጋለጥ ጥረቶች የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ አንዱ መንገድ ነው፡፡

ከትምህርቱ ባሻገር ለወጣቱ የተመቻቸለት ሌላው ጉዳይ ተዘዋዋሪ ፈንዱ ነው። ወጣቱ ዛሬ በፌዴራል ደረጃ በተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ ሆኗል። እንዲሁም ክልሎች ከመደቡት በጀት መጠቀም ችሏል።

ይህ ተጠቃሚነቱም በሚቀጥሉት ዓመታት እጅግ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መንግስት ቃል ገብቷል። ስለሆነም ተዘዋዋሪ ፈንዱንም ይሁን የክልሎችን በጀት በአግባቡ በመጠቀም ራሱንና ቤተሰቡን ብሎም ሀገሩን የመለወጥ ስራ ፊቱ ላይ ተደቅኖበታል።

ወጣቶች ከፊታቸው አዲስ ዓመት አለ። የበዓል ድባቦችም ይኖራሉ። በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ ሊሰንቁ ይገባል። እርግጥ ከድህነት ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ተጠቃሚ እየሆነ ያለው ወጣት፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ሁለንተናዊ የጥቅም ተጋሪነቱ የኋሊት ተጎትቶ እንዲሸረሸርበት አይፈልግም፡፡

ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት የትናንት እሱነቱን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት እንጂ፤ ሁከትን በማዳመጥ አይደለም፡፡ እናም እነርሱ ባህር ማዶ ሆነው ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውንና ህይወቱን ለመቀየር እየተጋ ያለውን ወጣት በእሳት ለመማገድ የሚሹ የሁከት ኃይሎችን መዳመጥ የለበትም። የአገሬ ወጣት በአዲስ አገራዊ ተስፋ የታጀበ በመሆኑ ፊቱን ወደ ስራው ብቻ ማዞር ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy