Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ሁለቱን ህዝቦች አይወክልም- የሁለቱ ክልል ርእስ መስተዳድሮች

0 479

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ሁለቱን ህዝቦች አይወክልም- የሁለቱ ክልል ርእስ መስተዳድሮች

ሰሞኑን በኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ሁለቱን ህዝቦች እንደማይወከል የሁለቱ ክልል ርእስ መስተዳድሮች ገለጹ።

የኦሮሚያ ክልል ርእስ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አቻቸው አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር በጉዳዩ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ርእሳነ መስተዳድሮቹ በጋራ መግለጫቸው፥ በግጭቱ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ፥ ጉዳቱም ሀዘኑም የሁለቱም ክልሎች የጋራ ጉዳት እና ሀዘን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ ኡመርም፥ ከሁለቱም ወገን በግጭቱ ምክንያት ለሞት የተዳረጉትም ሆነ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ዜጎች ወንድሞቻችን ናቸው፤ ሀዘኑም የጋራችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የሁለቱም ክልል ርእሳነ መስተዳድሮች የበርካታ ዜጎች ህይወት የተቀጠፈበት ግጭት የኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝቦችን እንደማይወክልም ተናግረዋል።

አቶ ለማ፥ ድርጊቱን በማንኛውም መስፈረት የኦሮሞ እና ሶማሌ ህዝብን እንደማይወክል በማንሳት አውግዘውታል።

አቶ አብዲም፥ ድርጊቱን የፈፀሙት ግለሰቦች የኦሮሞንም የሶማሌንም ህዝብ አይወክሉም በማለት ድርጊቱን እኩይ ምግባር ብለውታል።

ሁለቱ ሀዝቦች የአንድ ኢትዮጵያ አካል ብቻ ሳይሆን ዘመናትን የተሻገረ የጋራ እሴት እና ትስስር ባለቤት መሆናቸውን ያነሱት ርእሳነ መስተዳድሮቹ፤ ግጭቱ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ወደ ማረጋጋቱ የመመለስ እና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የፌዴራል እና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔም፥ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች፤ የኦሮሞ ህዝብ ሶማሌዎችን ሶማሌዎችም የኦሮሞ ተወላጆችን ከጥቃት ለመከለል መሞከራቸውን አንስተዋል።

ግጭቱ ሁለቱን ህዝቦች አይወክልም ሲሉም አቶ ከበደ ጫኔ ተናግረዋል።

ቀጣይ ተግባራትን በተመለከተ፥ ሁለቱ ርእሳነ መስተዳድሮች በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ፣ አካባቢዎችን ማረጋጋት እና በግጭቱ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው መመለስ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

ሁለቱ ክልሎች ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር በእኩይ ድርጊቱ ተሳታፊ የነበሩ ወንጀለኞችን ለህግ እንደሚያቀርቡም አረጋግጠዋል።

የፌዴራል እና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ፥ በድርጊቱ የተሳተፈ ማንም አካል በህግ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል።

የግጭት አካባቢዎች በፌድራል መንግስት እንዲጠበቁ፣ የክልል ጸጥታ ሃይሎች ከወሰን አካባቢዎች ርቀው ህዝባቸውን እንዲያረጋጉ፣ ዋና ዋና መተላለፊያ መንገዶች በመከላከያ ሃይሎች እና በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ የተላለፈው ውሳኔ መተግበር እንዳለበትም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የሁለቱ ክልል መንግስታትም ከፈረዴራል መንግስት ጋር በመተባበር ውሳኔውን ለመተግበር እና ለማስተግበር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የሁለቱ ክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ለህዝቡ ባስተላለፉት መልእክት ብዙ ዘመናትን አብረው የኖሩት ሁለቱ ህዝቦች አብሮነታቸው እና ሰላማቸውን በጋራ እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።

በዳዊት መስፍን

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy