Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተደማጭነታችንን ያረጋገጠው ሌላኛው የሰላም አጀንዳ

0 304

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተደማጭነታችንን ያረጋገጠው ሌላኛው የሰላም አጀንዳ

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

ከመሰንበቻው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 72ኛ መደበኛ ስብሰባ ኒውዮርክ ላይ ተካሂዶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ሀገራችን በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሰላኝ አማካኝነት አንድ አከንዳን አቅርባ ነበር። ይህ አጀንዳ የሰላም ማስከበር የማሻሻያ ነው።

የፀጥታውን ምክር ቤት በሊቀመንበርነት እየመራች የምትገኘው ኢትዮጵያ ያቀረበችውና ባለ አራት ፅንሰ ሃሳቦች የሰላም ማስከበር የማሻሻያ አጀንዳ ያለ ምንም ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ ከመፅደቁም ባሻገር አጀንዳው በቁጥር 2378/2017 የውሳኔ ሃሳብ ሆኖ እንዲመዘገብ ተደርጓል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ ተደማጭነቷ ምን ያህል እየጨመረ እንደመጣ የሚያሳይ ነው። የሀገራችንን ዓለማቀፋዊ ተሰሚነት በግልፅ የሚያረጋግጥና ምንግዜም ለሰላም ያላት ፅኑ አቋም እንደማይወላውል ያረጋገጠም ጭምር ነው ማለት ይቻላል።

ይህ የማሻሻያ ሃሳብ በዋነኛነት አነባለ ሀገሮች አንድ ግጭት በውስጣቸው ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል እንዳለባቸው የሚደነግግ ነው። ይህም የሰላም ማስከበር ተግባሩ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ በመከላከል የአንድን ሀገር ሰላም ሊያስጠብቅ የሚችል ነው።

ሀገራችን ያቀረበችው ይህ ባለ አራት ነጥብ የማሻሻያ ሃሳብ የመንግስታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በቅድሚያ ቅድመ-መከላከልን ማካተት እንዳለበት ያስረዳል። ለጥቆም በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ግጭቶች ዓይነታቸው በፊት ከነበሩት እየተለዩ በመምጣታቸው ምክንያት ሳይንሳዊ ዘዴን በመጠቀም በቅንጅት መፍታት ላይ የሚያተኩር ነው። በተለይም የግጭቶቹ ተዋንያን እንደ ኢጋድ ካሉ ቀጣናዊ ድርጅቶች ጋር ተመድ በጋራ መስራት እንዳለበት የሚገልፅ ነው።

ሶስተኛው፤ በሀገራት ውስጥ በሚካሄዱ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በአያሌው ተጎጂ የሆኑትን ሴቶች የሚመለከት ነው። እናም ቅድሚያ ለሴቶች መስጠት እንደሚገባ የሚያስረዳ ነው። ይህም በግጭቶች ወቅት ዋነኛ ሰለባ የሆኑትን ሴቶችንና ህፃናትን ለመታደግ የሚያስችል ነው።

ርግጥ ኢትዮጵያ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ ለአፍሪካም ይሁን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በተለይም በሩን ለዓለም አቀፉ የሰላም ማስከበር ተግባራት ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ የነበረው አምባገነኑ የደርግ ስርዓት ግብዓተ-መሬት ወዲህ በህዝቦች ትግል እውን የሆነው የኢፌዴሪ መንግስት ለከባቢውም ይሁን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰላም ማስከበር ተግባሮች ዙሪያ በርካታ ጉዳዩችን ፈፅሟል።

ጥቂቶቹን እዚህ ላይ መዘርዘር የሀገራችንንና የህዝባችንን ሰላም ወዳድነት ለመገንዘብ ያስችላል። ኢትዮጵያ ደርግ እንደወደቀ በነበሩት የሽግግር መንግስት ዓመታት በሩዋንዳ የመጀመሪያውን የሰላም ማስከበር ተግባር ተወጥታለች። ብሩንዲ በወቅቱ ሁቱና ቱትሲ በሚባሉ ጎሳዎቿ አማካኝነት በተካሄደውና ከ800 ሺህ በላይ ዜጎቿን ህይወት የቀጠፈው የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም በሰላም አስከባሪነት የተሰማራችው ኢትዮጵያ በሚያስደንቅ ህዝባዊ ወገንተኝነት የዚያችን ሀገር ሰላም በሂደት ወደ ነበረበት መመለስ ችላለች። በዚህም ወንድም ከሆነው የሩዋንዳ ህዝብና መንግስት አክብሮት እንዲሁም የሀገሪቱን ከፍተኛ ሚዳሊያ ልትሸለም በቅታለች።

በዚያ ተልዕኮ አዲሲቷ ትምህርት የወሰደችበት ነው። ተልዕኮው ለሀገራችን አዲስ እንደመሆኑ መጠን እንደ መጀመሪያ ልምድ የሚታይ ቢሆንም፤ ህዝባዊነትን የሰነቀው የሽግግር መንግስቱ ሰራዊት በህዝባዊ ወገንተኝነት ተግባሩን በብቃት መወጣት ችሏል። ከዚያም በኋላ በሩዋንዳ በተካሄደው የእርስ በርስ ግጭት ሀገራችን አስቸጋሪ ቦታዎችን በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመረከብ ውጤታማ ተሳትፎ አድርጋለች።

ከሽግግር መንግስቱ ወዲህም ህብረ-ብሔራዊ ቅርፅ ይዞ የተቋቋመው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በላይቤሪያ፣ በዳርፉር፣ በአብዬና በሶማሊያ መስዋዕትነት እየከፈለም ጭምር ወደር የማይገኝላቸውን የሰላም ማስከበር ተግባሮችን በብቃት ተወጥቷል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በላይቤሪያ የተለያዩ አካባቢዎች ካለው ቀለብ በመቀነስ ለተቸገሩ የሀገሪቱ ዜጎች በመስጠት እንዲሁም በመንገድ ግንባታ፣ በድልድይ ስራ… ወዘተ. ተግባሮች ላይ በመሰማራት ከራሱ በፊት ለህዝብ የቆመ ኃይል መሆኑን ማስመስከር ከመቻሉም በላይ፤ በሚመራበት ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቡ እየታገዘም በዚያች ሀገር ምርጫ ተካሂዶ የዛሬዋ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የምትመራው ላይቤሪያ እውን መሆን የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።

ሁሌም መርሁ ሰላም የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን ውስጥ ለተከሰተው ችግር በመንግስታቱ ድርጅት በቅድሚያ መጠራት ችሏል። ይህን ተልዕኮ ተቀብሎ ወደ ዳርፉር ያቀናው የሀገራችን መከላከያ ሰራዊት ግዳጁን በወንድማማችና ህዝባዊ ፍቅር እስካሁን ድረስ በማከናወን ላይ ይገኛል። ይህም ሰራዊቱ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ ያለውን ተቀባይነት የሚያሳይ ነው።

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ዘይት በበለፀገችው የአብዬ ግዛት ሲጨቃጨቁም ሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በቅድሚያ በሰላም አስከባሪነት የጠሩት ይህንኑ ለህዝብ እንጂ ለማንም የማይወግን ሰራዊት ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በፀጥታው ምክር ቤት አሰራር ውስጥ የጎረቤት ሀገር ሰራዊት ለሰላም ማስከበር እንዳይገባ የሚያግደውን ድንጋጌ ያስቀረም ሰራዊት ነው።

ህዝባዊ አመኔታው፣ ልክ እንደሚመራው መንግስት በአንድ ሀገር ውስጥ የሚከናወኑ ጉዳዩችን በገለልተኝነት የሚይዘው ይህ ሰራዊት፤ በሰላም አስከባሪነት ወደ አብዬ በብቸኝነት ተሰማርቶ እስካሁን ድረስ ተግባሩን በወንድማማችነትና በህዝባዊ ወገንተኝነት በመምራት ላይ ይገኛል።

በሶማሊያም ውስጥ የአፍሪካ ህብረትና የመንግስታቱ ድርጅት አሸባሪውን አልሸባብ ለማዳከምና ለማጥፋት ባቀረቡት ጥሪ መሰረትም መከላከያ ሰራዊታችን በግንባር ቀደምነት እንዲሰለፍ ተደርጓል። ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሰራዊቶች ጋር በመሆን አሸባሪውን አልሸባብ በፀጥታው ምክር ቤት አንቀፅ ሰባት (Peace by enforcement) “ሰላምን በሃይል ጭምር ማረጋገጥ” መመሪያ መሰረት አሸባሪውን አልሸባብ እየተፋለመ ይገኛል።

ከዚህ በተጓዳኝም የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት እንዲቋቋምና የሀገሪቱን የፀጥታ ሃይሎች በማሰልጠን ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። ኢትዮጵያ በዚህ ጀግና፣ ከራሱ በፊት ለህዝብ የሚያስብና በዲሲፕሊን የታነፀ ሰራዊት አማካኝነት የሰላም ማስከበር ግዳጆችን በብቃት ተወጥታለች፤ እየተወጣችም ነው። ይህ ተግባሯም በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የሊቀመንበርነት ቦታ እንድታገኝ ያደረጋት እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካ ውስጥ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ሀገሪቱን ከማማከር ባለፈ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንድታደርግ የሚጠይቅበት ሁኔታን ፈጥሯል።   

ሀገራችንም በእነዚህ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ጠንክራ በመስራቷና ተወዳዳሪ መሆን መቻሏ እንዲሁም ባሰየቻቸው ተመስጋኝ ጥረቶች ተሳትፎዋ እየሰፋና ብስለት እያገኘ መጥቶ ዛሬ ስለ ሰላም ማስከበር አዲስ አጀንዳ እስከማስያዝና የውሳኔ ሃሳብ ሆኖ እንዲፀድቅ ማድረግ ችላለች።

ይህም ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም ያላትን የማይናወጥ አቋም ግልፅ ከማድረግ ባለፈ፣ በሰላም ዙሪያ ምን ያህል የመፍትሔ አካል መሆን እንደቻለች የሚያረጋግጥ ጭምር ነው። የመንግስታቱ ድርጅት ምን ያህል ዕውቅና የሰጣት መሆኑንም የሚያሳይ ይመስለኛል። ለዚህም ነው— ሀገራችን በተመድ ጉባኤ ላይ ያቀረበችውን የውሳኔ ሃሳብ ተመርኩዘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ “ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመድ ምስረታ ወቅት ጀምሮ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ላደረገችው አስተዋፅኦ ዕውቅና መስጠት አለብን” በማለት የተናገሩት።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy