Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ታላቅ ተስፋን የሰነቀ የከፍታ ጉዞ

0 292

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ታላቅ ተስፋን የሰነቀ የከፍታ ጉዞ

                                                        ይነበብ ይግለጡ

ሀገራችን ነገን ብሩህ ለማድረግ ተግታ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ የእስከአሁኑ ሀገራዊ የልማትና የእድገት ጉዞአችን በተለይ በኢኮኖሚው መስክ የታላላቅ ድሎች ባለቤት አድርጎናል፡፡ በበርካታ ዘርፎችም ስኬታማ ሁነን ተጉዘናል፡፡ የተገኙትን ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትና ልማቶች የሚገዳደሩ ችግሮች ጎልተው የተከሰቱ ቢሆንም እነዚህን ለመፍታትና እልባት ለማበጀት በጥልቅ ተሀድሶው መሰረት ከፍተኛ ስራዎች ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ይገኛሉ፡፡

 

ልማትና እድገትን ሊያደናቅፉ የሚችሉ በሙስና፣ በኪራይ ሰብሳቢነትና በመልካም አስተዳደር፤ እንዲሁም በፍትሕ ችግሮች ዙሪያ የተከሰቱና ጎልተው የወጡ በሕዝቡ ውስጥ መመረርና መከፋትን ያስከተሉ ችግሮችን ለመፍታት ቀን ከለሊት በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህን ችግሮች ከስሩ መፍታት፤ የሕዝቡን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ቀጣዩን ጉዞ  የበለጠ ስኬታማ የሚያደርገው ከመሆኑ አንፃር የመንግስት ተግባር ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡

 

ባጠናቀቅነው አመት ማክተሚያ አካባቢ በመንግስትና በሕዝብ ሀብት ላይ ዘረፋ ሲፈጽሙ በቆዩ በተለያየ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ላይ በነበሩ ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቤ ሕግ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጎ የምርመራ ስራ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህም ወደ 63 የሚጠጉ በተለያዩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች በኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

 

በየትኛውም ደረጃ የነበረና ያለ የመንግስት ባለስልጣን ከሙስና ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች በበቂ ማስረጃ ከተገኘ፤ የማይነካ የሚባል ነገር የለምና፡ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይችልም። መንግስትና ሕዝብ የሰጣቸውን ታላቅ አደራና ኃላፈነት በመርገጥ፤ የግል ጥቅም በማሳደድና በዘረፋ ላይ ተሰማርተው በተገኙት ላይ የሚወሰደው የሕግን የበላይነት የማስከበር እርምጃ በተጀመረበት መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ወደኋላ የሚባልበት አንድም፤ ምንም አይነት ምክንያት የለም፡፡

 

በዘረፋ የተወሰደው የሕዝብና የመንግስት ሀብት በሕግም ውሳኔ የሚያገኝበት፤ ወደ ባለቤቱ ካዝናም የሚመለስበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

 

በሌብነት ሰርቆና ዘርፎ ሳይሆን በላቡ ሰርቶ፣ ለፍቶና ደክሞ የሚከብር ዜጋና ትውልድ ለማፍራት ነው ትግል እየተደረገ ያለው፡፡ ለሀገር ኩራት አሳቢና ተቆርቋሪ የሚሆነውም በዚህ መልኩ እያደገ የሚሄድ ዜጋ ለመፍጠር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የመንግስትም የሕዝብም መሰረታዊ ፍላጎት ይሄው ነው፡፡

 

በሕገወጥ መንገድና በወንጀል የመንግስትና የሕዝብን ሀብት በመዝረፍ መክበር ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ወንጀል ነው፡፡ ከድሕነት ለመውጣት ታላቅ ትግል እያደረገችና በርካታ አበረታች እርምጃዎችን እየተራመደች ካለች ሀገር ካዝና በሰበብ አስባቡ መዝረፍና መስረቅ ሀገርንና ሕዝብን ከመግደል የሚተናነስ ድርጊት አይደለም፡፡ በርካታ ትምሕርት ቤቶች፤ የጤና ተቋማትና ክሊኒኮች፤ መንገዶች፤ ድልድዮች፤ ግድቦች፤ ኮሌጆች፤ የአረጋውያን መጦሪያ፤ የሕጻናት መዋያ፤ የገጠር ጥርጊያ መንገዶች ሌላም ብዙ ብዙ ተግባራት ሊሰራበት የሚችል የመንግስትና የሕዝብ ሀብትና ገንዘብ ነው የተዘረፈው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ሙሰኞች ብቻ ሳይሆኑ ጸረ ሕዝብ፤ ጸረ ሀገርም ናቸው ሀይ ሊባሉ የግድ ነው፡፡

 

ባገባደድነው አመት ትልቁ የኢሕአዴግ ድል ሆኖ የተመዘገበው በሙሰኞች ላይ በቀጥታ መውሰድ የጀመረው እርምጃ ሲሆን፤ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍና ተቀባይነትንም አስገኝቶለታል፡፡ በሕዝቡ የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄ መሰረት በተካሄዱት ሰፊና ጥልቅ የተሀድሶ ንቅናቄዎች መሰረት ነው በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ የተጀመረው፡፡

 

ሀገራችን ታላቅ ተስፋን በሰነቀ ጉዞ ላይ የምትገኝ ከራስዋም አልፎ ለሌሎች ሀገራት በተምሳሌነት የምትጠቀስ ሀገር ለመሆን የበቃች፤ በአፍሪካና በአለም በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ካሉት ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ውስጥ የምትገኝ ናት፡፡ የቱንም ያህል ችግሮች ይከሰቱ በልማትና በኢኮኖሚ እድገት ረገድ የተሰሩትና እየተሰሩ ያሉት ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች በሁሉም ዘንድ አክብሮትና አድናቆት የተቸራቸው ናቸው፡፡ እነዚህን ታላላቅ ውጤቶች ይዘን ሰላማችንን ጠብቀን መጓዝ የበለጠ ድልና ውጤት ለማስመዝገብም መትጋት ይጠበቅብናል፡፡

 

አዲሱ አመት የበለጡና የላቁ ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶችና ድሎች የሚመዘገቡበት ይሆን ዘንድ የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ የዘንድሮውን አዲስ ዓመት ስንጀምር ሰፊ ሀገራዊ የቤት ስራዎች ይጠብቁናል፡፡ ባለፈው አመት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ወደዘንድሮው አመት የተዛወሩ ሀገራዊ ስራዎች በውጤት የሚጠናቀቁበት፤ በሙሰኞቸና በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ የተጀመረው ትግል በስፋት ቀጥሎ የተዘረፉ የመንግስትና የሕዝብ ሀብቶች ወደ መንግስት የሚመለሱበት፤ ለዚህም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ከፍተኛ ድርሻ የሚወጣበት፤  በአቅምና በቁጠባ የመኖር ባሕል የበለጠ የሚገነባበት ነው አመት እንደሚሆን የሁሉም ሰው እምነት ነው፡፡

 

በሀገር ደረጃ ሰላማችንን፤ እንዲሁም የተገኙ የልማትና የኢኮኖሚ ድሎቻችንን የበለጠ አስጠብቀን ወደላቀው ምእራፍ የምንሸጋገርበት ዘመን እንዲሆን ያለማሰለስ መትጋት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡ ሀገራዊ አንድነትን፣ መከባበርን፣ መደማመጥን፣ መቻቻልን በበለጠ መሰረት ላይ የምንገነባበት አመትም እንዲሆን ጠንክሮ መስራት ለነገ የማይባል ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ጥንትም ዛሬም ነገም የሀገሩ ባለቤትና ጠባቂ ከማንም በላይ ሕዝቡ ነው፤ የመንግስት ሚና እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

 

በመንግስታት የመፈራረቅ ሂደት ውስጥ በየትኛው ዘመን የትኛው መንግስት ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ ምን ስራ ሰርቶ አለፈ የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሀገርን ለመለወጥና ለማሳደግ ኢሕአዴግ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን ሰርቶአል፡፡ ግዙፍ በሆነ ደረጃ የመሰረተ ልማትን አስፋፍቶአል፡፡ በሀገሪቱ ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ ሶስትና አራት ዩኒቨርሲቲዎችን በማስፋፋት ከ35 በላይ እንዲደርሱ አድርጎአል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ትምሕርት በስፋት እንዲስፋፋ እድሜያቸው የደረሱ ታዳጊዎች በአቅራቢያቸው ወደ በሚገኝ ትምሕርት ቤት ገብተው እንዲማሩ የማድረግ ስራ ተሰርቶአል፡፡ ከአርሶ አደሩ ሌላ በመዘዋወር የሚኖረው አርብቶ አደር በሰፈራ እንዲሰባሰብ በማድረግ የትምሕርት፣ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውሀ አገልግሎት ወዘተ እንዲያገኝ ለማድረግ ከተሰራው ስራ በተጨማሪ ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶችም ተከፍተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡ ቀድሞ በሀገራችን ባልነበረና ባልታየ መልኩ ሰፋፊ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በብዙ ዘርፎች ለዜጎቻችን ሰፊ የስራ እድል ተከፍቶ በርካታ ዜጎች በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

 

ባለፉት ዘስር አመታት በርካታ ቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪዎች ተገንብተው በስራ ላይ ውለዋል፡፡ ከተሞችን የማሳደግና የማስፋፋት ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል፡፡ የእናቶችንና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ በጤናው መስክ በተሰራው ስራ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቦአል፡፡ ዜጎችን በስፋት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ባለቤትና ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሎአል፡፡ በቅርቡ ስራቸውን የጀመሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማእከል እንደሚያደርጓት ከወዲሁ ከፍተኛ ምስክርነት እየተሰጠባቸው ይገኛሉ፡፡ ግብርናውን በማዘመን በኩልም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ድርቅና ረሀብን ለመከላከል በራስ አቅም ውጤታማ ስራ ተሰርቶአል፡፡ የተከሰተው ድርቅ ኢትዮጵያ ባለፉት ሀምሳ አመታት ካየቻቸውና ከገጠሟት ሁሉ የከፋው መሆኑ ቢታወቅም ይህንን ድርቅ ለመመከትና ዜጎችን ለመታደግ ታላቅ ስራ ተሰርቶአል፡፡ አለም አቀፍ የለጋሾች እርዳታ ከመድረሱ በፊት በድርቁ ሰለባ የሆኑት ወገኖች የከፋ ችግር ውስጥ እንዳይወድቁ ሕይወታቸውን የመታደግ ስራ የተሰራው በራስ ሀገራዊ አቅም ብዙዎችን ያስገረመ ቢሆንም ግን ተችሏል፡፡ ለዚሀም አለም አቀፍ ለጋሾች አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ተሰርተው በስራ ላይ ውለዋል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በራስ ብሔራዊ አቅም የተጀመረና የሚገነባ በመሆኑ ሕዝብና መንግስት በጋራ ባደረጉት ታላቅ ርብርብ ግድቡን ቀን ከለሊት የመስራቱ ስራ በከፍተኛ ደረጃ እየቀጠለ ሲሆን ትርጉም ያለው ውጤታማ ደረጃ ላይ ደርሶአል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ተከትሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ፣ ስፋት ያለቸው አዳዲስ የስራ መስኮች ለዜጎች ይፈጥረዋል፡፡

 

ይሄ ሁሉ ሀገራዊ ተግባርና ስኬት ሲታይ ታላቅ እርምጃ ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ላቀው ማማ የመውጣታችን ማሳያም ነው፡፡ የሀገራችንን ሰላም፣ ልማትና እድገት ጸንተን መጠበቅ የሚገባንም በነዚዙ መሰረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡ የሀገራችንን መልማትና ማደግ የማይፈልጉ ከድሕነት ለመውጣት የምታደርገውን ትግል ለማኮላሸት እንቅልፍ ተኝተው የማያድሩ፣ የቅርብና የሩቅ ጠላቶች ድሮም ነበሩዋት፤ ዛሬም አሉዋት፡፡ ይህን ለመከላከልና ለመመከት የሚቻለው የጸና አንድነትን ጠብቆ ሀገራዊ ልማትና እድገታችንን ለማስቀጠል ሲቻል ብቻ ነው፡፡

 

ባለፉት አስር ዓመታት መንግስትና ሕዝብ  በበለጠ ተቀራርበውና ተናበው መስራት በመቻላቸው በአገራችን  ከገጠር እስከ ከተማ  በየዘርፉ በርካታ  ስኬቶችን ማስመዝገብ አዲስ ታሪክም ለመጻፍ ተችሎአል፡፡ የኢትዮጵያን የጥንት ታላቅነት መልሶ ለማረጋገጥ የተጀመረው የሕዳሴ ጉዞ በሂደት በጠንካራ ሀገራዊ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ ለስኬት የሚበቃ ለመሆኑ ማረጋገጫው  በፈርጀ ብዙ ዘርፎችና መስኮች የተመዘገቡት ተጨባጭ ውጤቶች ናቸው፡፡

 

ባጠቃላይ፣ ከሀገራዊ ልማትና ግንባታው ጎን ለጎን ብሔራዊ መግባባትን፣ መቻቻልን፣ ልዩነትን በልዩነት ይዞ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ መቆምና መስራትን ከመቸውም ግዜ በላይ ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ ከሕዝቡ የተነሱትን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በተገቢው መልኩ አጠናክሮ መመለስ፣ ሙሰኞችን ማጽዳት፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሕን በተገቢው መንገድ ማስፈን የአዲሱ አመት ቀዳሚ የመንግስት ስራ ሊሆን ይገባል፡፡ በየትኛውም ደረጃ በሀገራችን የተከሰቱትን የሙስናና የመልካም አስተዳደር የፍትሕ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ሰፊ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ በመሆኑ ሕዝቡ ቀጣይ  ተሳትፎውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡

 

መጪውን ዘመን የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ የመላውን ሕዝብ ከፍተኛ ንቅናቄና ተሳትፎ ማጎልበት ይጠበቃል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy