Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

               አማን ሰላም !!

0 278

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

               አማን ሰላም !!

                                                                 ታከለ አለሙ

የአንድ ሀገር የሕልውና መሰረት ሳይናጋ መቀጠል የሚችለው በጸና መሰረት ላይ የቆመ የተረጋጋና የተረጋገጠ ሰላም መኖር ሲችል ብቻ ነው፡፡የሀገር መሰረቷ ዋነኛው ምሰሶ ሕዝቦችዋ ናቸው፡፡የሀገር በሰላም ውሎ ማደር ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ከሀገር ሰላም በላይ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ሀገር አማን ነው? ሰላም ነው? የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሰላም በአለማችን በምንም ዋጋ ሊተመን የማይችል የመጨረሻው ወድ ነገር ነው፡፡አማን ሰላም እንዲሉ፡፡

የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባሉባት ሀገራችን ትልቁን ጠብቀን ልናሳድገው የሚገባን ተከባብረው እንዲኖሩ፤መቻቻልን እንዲያሳድጉ፤ችግሮችን በመግባባት በመደማመጥ በመነጋገር እንዲፈቱ፤ለዘመናት የኖረውን አብሮነታቸውን ጠብቀው በመካከላቸው ፍቅርን እንዲያሳድጉ ነው መሆን ያለበት፡፡በታሪክ እንደተመዘገበው በሕዝቦች መካከል ምንም አይነት ችግር የለም፡፡ኖሮም አያውቅም፡፡

ሁልግዜም የችግሮች መነሻ ፖለቲከኞች የስልጣን ጥምና ፍቅር አእምሮአቸውን ያናወዛቸው ግለሰቦች ሕዝብን ከሕዝብ ለማባላት የሚያደርጉት ስውር ሴራ ነው ጥፋት የሚያስከትለው፡፡ የሕዝቦች አንድነት አብሮነትና የተሳሰረ ቀጣይ ሕይወት በምንም መልኩ የሚበጠስ ወይንም የሚቋረጥ አይደለም፡፡በጥላቻ የሰከሩና የእብደት ፖለቲካ የሚያራምዱ ግለሰቦች በተለያየ ሁኔታ በሚቀሰቅሱትና በሚያነሳሱት ግጭት በአለማችን ለሚሊዮኖች እልቂት ምክንያት መሆናቸው በታሪክ ተመዝግቦአል፡፡

አሳዛኙ ነገር ከውድመቱም ከእልቂቱም በኃላ እነዛው ሀገራት እንደገና ሀ ብለው ሕይወትን ከውድመትና ከአቧራ በመነሳት መጀመራቸው ነው፡፡ከተሞቻችው ወድመው ሕዝቦቻቸው አልቀው ቀባሪም ጠፍቶ የሰው ልጅ አስከሬን በየቦታው በየጥሻው በየአውድማው  በየሸለቆው ወድቆ ወንዞችና ባሕሮች ጭምር በሰው ልጅ አስከሬን የተሞሉበት እጅግ ሰቅጣጭ ልብ የሚያደማ ታሪክ አለማችን አይታለች፡፡አስተዋይነት የጎደላቸው አርቆ ማሰብ የተሳናቸው በጥላቻና በዘረኝነት ልክፍት የተዋጡ አረመኔዎች የቆሰቆሱት እሳት እነሱንም ይዞአቸው ጠፍቶአል፡፡አንደኛው ወገን ጠፍቶ ሌላኛው አልተረፈም፡፡ ለዚህ ነው አይበጅም የምንለው፡፡ ሰላም ይበልጣል፡፡

በግራም በቀኝም ወገን የተጋደሉት ወንድማማቾች ያጠፉትና  ያወደሙትም የጋራ ሀገራቸውን ነው፡፡ዘርና ትውልድ ረግፏል፡፡ጠፍቶአል፡፡የእርስ በእርስ ጥላቻና መናቆሩ የመጨረሻው ውጤት ይሀው ነው፡፡ከዚህ ሁሉ አሰቃቂ ውድመት በኃላ ሀገር መኖርና መቀጠልም ስላለባት እንደገና ሀ ብለው የተረጋጋ ሰላም ፈጥረው መኖር ጀመሩ፡፡ ቀጠሉ፡፡የሩዋንዳው ዘግናኝና አሰቃቂ እልቂት ለዚህ አለምን ጉድ ላሰኘ የጥላቻ ፖለቲካ  በእማኝነት ተጠቃሽ ነው፡፡በሕዝቦች መካከል ጥንትም ዛሬም ግጭት የለም እይኖርምም፡፡ ሊያበርዱት ሊያባብሱት የሚችሉት ፖለቲከኞቹ ናቸው፡፡

የዚህ ተዋናዮች በዘረኝነት በጎጠኝነት ያበዱና የተለከፋ አርቀው ለማሰብ ያልቻሉ የሕዝቦችን ሰላም አብሮነት መቻቻልና መከባበር የሚደፈጥጡ ለእነሱ ፖለቲካዊ ቁማር ሲባል ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ የሚያባሉ የፖለቲካ መሪዎችና በጠባብነት በእብሪትና በትምክሕት የተበከሉ የፈለገው ደም ለምን እንደ ዥረት አይፈስም የሚሉ ደንቆሮዎች ሲሆኑ በፍጹም ለሀገርና ለሕዝብ አይበጁም፡፡ይህንን አይነቱን አስተሳሰብ የግድ መዋጋትና ማስወገድ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም ቀዳሚ ስራ መሆን ይገባዋል፡፡ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ፡፡ጥፋት ከተፈጸመ በኃላ ሙሾ ማውረዱ አይጠቅምም፡፡

በሀገራችን ውስጥ የሚነሱና የሚከሰቱ ማንኛቸውም አይነት ችግሮች መፈታት ያለባቸው በቆየውና ዘመናትን በተሻገረው ባሕላችን መሰረት በመደማመጥና በመከባበር ብቻ ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ኢትዮጵያ ታላቅ ተስፋን የሰነቀች በልማትና በእድገት ጎዳና ላይ የምትገኝ ሀገር የመሆንዋ እውነት የግድ ሰላምና መረጋጋትዋን እንድንጠብቅ አብሮነቱንና አንድነታችንን በጸና መሰረት እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነትም ግዴታም አለብን፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ድንበር አካባቢ ቀደም ካሉ ግዜያት ጀምሮ የተከሰተው አለመግባባት ዛሬ እጅግ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ከሁለቱም ወገን ያሉ ዜጎቻችንን በሞት እንድንነጠቅ አድርጎናል፡፡ ችግሩ ገፍቶ ወደዚህ ጫፍ ከመሄዱ በፊት መንግስት የሁለቱንም ክልሎች መሪዎች በማነጋገር መግባባት እንዲፈጠርና የተከሰተው ችግር እንዲፈታ ለማድረግ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ሁኔታም ነበር፡፡

እየዋለ እያደር መልኩን እየቀየረ ደም መፋሰስን ባልተጠበቀ ሁኔታ አስከተለ፡፡መሆን የነበረበት ማብረድና መረጋጋትን መፍጠር ሰላም እንዲፈጠር መስራት ነበር፡፡የዚህ ሁሉ ዜጋ ሞት በእጅጉ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡የአንድም ንጹሕ ዜጋ ሕይወት መጥፋት አልነበረበትም፡፡

በአንድ ፌደራል መንግስት በሕግና በስርአት ስር የሚኖሩ መሆናቸውን እስከ መዘንጋት የደረሱ ግለሰቦችንም አስተውለናል፡፡ ይሄ ሁሉ እንደ ሀገር አይጠቅመንም፡፡ላይ ሶሻል ሚዲያው ጉዳዩን የማብረድ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ የማቀጣጠል ስራ ሲሰራ ነው የከረመው፡፡በዚህም አለ በዚያ ተጎጂው ሀገርና ሕዝብ ነው፡፡ማንም አትራፊና ተጠቃሚ የለም፡፡

በሁለቱም ወገን የወደቁት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ሀዘኑም የሀገርና የሕዝብ ነው፡፡ ከሶማሊያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሲሰጥ የነበረው እጅግ ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ነገሩን ወደባሰ ጫፍ ከመውሰዱም በላይ ግለሰቦችን በመኮነንና በመወንጀል ላይ ያነጣጠረ ሁኖ መገኘቱ በእጅጉ ኃላፊነት የጎደለው የማይጠበቅ ድርጊትና ተግባርም ነበር፡፡ከዚህ ሁሉ የእርስ በእርስ መወነጃጀል ይልቅ ለሀገርና ለሕዝብ ይበጅ የነበረው በረጋ መንፈስ መወያየቱ መነጋገሩ መደማመቱ ነበር፡፡ጉዳዩ እዚህ የከረረ ጫፍ ላይ መድረስም አልነበረበትም፡፡

አንድ ሕዝብ መርጦኛ ድርጅቱ ወክሎ በኃላፊነት በክልል አመራር ያስቀመጣቸውን ሰዎች የሌላ ክልል ሹም ተነስቶ ከስልጣን ይውረዱ ይነሱ ለማለት በምንም መልኩ አቅምም ስልጣንም የለውም፡፡ አሁን ያለው ስርአት ከነችግሮቹ በዲሞክራሲዊ መርህ በአብላጫ ድምጽና በሕዝብ ውሳኔ የሚመራ እንጂ አምባገነናዊ ስርአት አይደለም፡፡ከሕግ አግባብ ውጪ ግለሰቦችን መሾምም መሻርም አይችልም፡፡ካልተነሱልኝም ሞቼ እገኛለሁ አመራሮቹ ይነሱ ማለት ሕግና ስርአትን የረገጠ በሌላም መልኩ በሀገሪቱ ሕግና ስርአት ሕገ መንግስቱም እንደሌለ አድርጎ የመቁጠር ስሜትም የሚያንጸባርቅ አምባገነናዊና አደገኛ አካሄድም ጭምር ነው፡፡

አሁንም መንግስት ለችግሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ካልፈታውና ካልተከታተለው በስተቀር እንደነዚህ አይነት ግለሰቦች ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ያመጣሉ ብሎ ማሰብ በእጅጉ ይከብዳል፡፡ በሕዝብ መካከል ቅሬታና አለመግባባት እንዲሰፍን ግጭቶች በቀላሉ መፍትሄ እንዳያገኙ የመፈለጉ ዝንባሌ ለማንም አይጠቅምም፡፡የሚጠቅምን የጋራ ሰላም ነው፡፡ችግሮችን በሰላም በጨዋነት መፍታት ነው፡፡

ችግሮችን በማራገብና በማባባስ ስራ የተጠመዱ ግለሰቦችን ሶሻል ሚዲያዎችን በስፋት እያየን ያለንበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡በሕዝብ ልጆች ደም መፍሰስ ቢዝነስ ለመስራት ለመነገድ የሚጥሩ ዋልጌዎችም አይጠፉም፡፡የሀገርና የሕዝብ ሰላም ይበልጣል፡፡በጎሳና በዘር ጥላቻ የተጠመዱ ዘረኝነትን በእዚህም ሆነ በዛኛው ጎራ የሚያራግቡ ከንቱዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይበጁትም፡፡

የእነሱ ፍላጎት ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲተላለቅ፤በከፋ የደም ጥማት ፍላጎት ተሰንገው  ሀገሪቱን ወደ አልፈተፈለገ አቅጣጫ ለመምራት በመቅበዝበዝ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ የመጨረሻው መጨረሻ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት እልቂትና ውድመት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ኢትዮጵያ እንደነዚህ አይነት የአእምሮ ሕሙማንን መሸከም አትችልም፡፡ የተረጋጋ ሰላምን ሊያሰፍን የሚችል ሕዝብን ከሕዝብ የሚነጥል ሳይሆን መቻቻል መከባበርን የሚያሰፍን አመራር ነው ለማየት የምትፈልገው፡፡ተስፋዋን የሚያለመልሙ እንጂ የሚያመክኑ ሰዎችን ቡድኖችን ወዘተ ማየት መስማት አትሻም፡፡

መታረምና መዳን ከቻሉ ወደልቦናቸው ተመልሰው ሕዝቡ በፍቅር በመቻቻል እንዲኖር ችግሮች ቢከሰቱም በሰላምና በውይይት እንዲፈቱ ሕዝብ እንዳይጎዳ ሰውም እንዳይሞት ንብረትም እንዳይወድም ማድረግ ነው የሚገባቸው፡፡ዘመን ግዜ ስልጣንም ያልፋል፡፡ በስልጣን ላይ እስከ ወዲያኛው ለመኖር የፈቀደ የሚፈቅድም ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ ሕግ የለም፡፡እንደ ሰው ባለን የተወሰነ የእድሜ ዘመን ውስጥ ለሕዝብም ለሀገርም የሚበጅ ስራ ሰርቶ ሕዝብን አጣልቶና አናክሶ ሳይሆን በፍቅር ተከባብረው ተስማምተው እንዲኖሩ አደርጎ ማለፉ ነው የሚበጀው፡፡

አሁን ያለው አዝማሚያ በአጭሩ ካልተገታ በቀር እንደ ሕዝብም እንደ ሀገርም በእጅጉ ያሳስባል፡፡ዋጋም ሊያስከፍለን ይችላል፡፡ኢሕአዴግን በመደገፍ ስም የሚንቀሳቀሱ ሶሻል ሚዲያዎችም ልክ እንደ ጽንፈኛው ሚዲያ ሁሉ በከፋና በከረፋ የዘርና ጎሳ ፖለቲካ ውስጥ   ተጥደው  ሲርመጠመጡ ሕግና መንግስትስ የለም ወይ እስኪባል ድረስ  የማረጋጋት ስራ ሳይሆን የማባላትና ሕዝብን ከሕዝብ የማናከስ እኩይ ስራና ሴራ እየሰሩ መሆናቸውም በእጅጉ ያሳስባል፡፡በጽንፈኛውና አክራሪ ፖለቲከኛው ላይ የምንቃወመውን ይህን አይነቱን ልቅ የጥላቻ መንፈስ ማንም አይጠይቀንም በሚል የጥላቻ ነጋሪት ሲጎስሙ ውለው በማደር የሕዝቡን ስሜት በከፋ ሁኔታ እያሻከሩት መሆኑን የተረዱም አይመስሉም፡፡ጽንፈኛነት አክራሪነት ዘረኝነት በየትኛውም ወገን ቢሆን ለሕዝብ አብሮነት አይጠቅምም፡፡

መቸም ሀገርን በሰላምና በመረጋጋት በመምራት የደረሰችበትን ከቀድሞ የተሻለ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት አስጠብቆ መዝለቅ የሚፈልገው ኢሕአዴግ እሱን በመደገፍ ስም ከሕግና ከስርአት ውጭ መረን የወጡትን የማባላት ስራ የሚሰሩ ዋልጌዎችን ደግ አደረጋችሁ እንደማይላቸው እርግጠኛ ነው፡፡የዘረኝነት ፖለቲካ የመጨረሻው ውጤት ለሀገር ጥፋትና ለሕዝብ እልቂት ከማምጣት ውጪ የሚበጅ አንድም ምንም ነገር የለውም፡፡ሳይረፍድ በግዜ ማረሙ ተገቢ ነው፡፡ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ዘረኝነትን እየሰበኩ አንዱ በሌላው ላይ የማጥላላት ዘመቻ እያደረገ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ በእጅጉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ውሎ አድሮ መፍጠራቸው ጥርጥር የለውም፡፡

ሚዛናዊነት ትክክለኛ መረጃን ማድረስ ከወገናዊነት መራቅ ለእውነትና ለእውነት ጸንቶ መቆም ለሕዝብም ለመንግስትም ይጠቅማል፡፡ችግሮችን በሰላም ለመፍታትም ይረዳል፡፡ ለሀገር ሰላምና መረጋጋትም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡አስተዋይና በሳል ብሎገሮች የመኖራቸውን ያህል በማሕበራዊ ሚዲያ ስም የሚንጫጩ ትንሽ መስመር በመጻፍ ሕዝብን በጥላቻ የሚያነሳሱ ሲያቀረሹ የሚውሉ ጨዋነት የጎደላቸው ትናንሽ ጭንቅላቶች  አሉ፡፡በኢህአዴግ ደጋፊነት ስም የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ጠባብና አክራሪ ኃይል እንዲሁም አክራሪው የዲያስፖራ ጽንፈኛም ሁለቱም ለኢትዮጵያ*ና ለሕዝብዋ አይጠቅሙም፡፡ የሚያስከትሉት መዘዝ መመለሻ የለውም፡፡ከወዲሁ መረምና ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡

ለሀገር ሰላምና መረጋጋት መስራት ሲገባቸው ትልቅ ትርምስና ሁከት እንዲፈጠር የሕዝቡን ስሜት በመመረዝና የጥላቻ ፖለቲካ እንዲነግስ በማድረግ ላይ የተሰማሩ ለታላቅዋ ሀገርና ሕዝብ ልቀትና አስተሳሰብ የማይመጥኑ በመሆናቸው እየተንጠራሩ ሊያገዝፉት የሚጥሩት ስብእናቸው እጅግ የወረደ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል፡፡ጨዋ ሕዝቦችን የወለደች እንደየባሕላቸውም በስነምግባር አርቃ ያሳደገች ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ከሁሉም በላይ የሀገርና የሕዝብ ሰላም ይበልጣል፡፡ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም፡፡ስለዚህም በሁሉም አቅጣጫ ትኩረት ማድረግ የሕዝብን አብሮነት መቻቻል ተከባብሮ መኖርን ማጎልበት ማሳደግ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማድረግ በዋነኛነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy