Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አዲስ ዓመትን በአዲስ የስራ መንፈስ

0 350

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አዲስ ዓመትን በአዲስ የስራ መንፈስ

                                 ዳዊት ምትኩ

አዲስ ዓመት ሊመጣ ጥቂት ቀናቶች ይቀሩታል። 2010 ዓ.ም ብሩህ ተስፋን ሰንቆ ይመጣል፤ በተለይም የአገራችን ህዝብ 70 በመቶ ያህል ለሚሆነው ወጣት። ታዲያ አዲስ ዓመትን ስናስብ ወጣቱ በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ፊት ለፊቱ የሚጠብቀው መሆኑን እንገነዘባለን። በሌላ በኩልም ወጣቱ በአዲስ ዓመት በአቋራጭ እከብራለሁ የሚል የጥገኝነት ስሜት እንዳይኖረው፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ሊገነዘብ፣  የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እንዲያውቅ እና በየትኛውም ዘርፍ ችግሮች መኖራቸውን ሊረዳ የሚገባ ይመስለኛል።

ወጣቱ ችግሮችን ‘ታግዬ አሸንፋለሁ፣ ነገ እለወጣለሁ’ በሚል መንፈስ መወጣት እንዳለበት እንዲሁም በስሜታዊነት ሳይሆን በ“ምክንያታዊ” አስተሳሰብ መመራት ይኖርበታል። እናም በአዲሱ ዓመት በአዲስ የስራ መነሳሳት መንፈስ ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ያለበት ይመስለኛል።

መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ለወጣቱ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ ገልጿል። ወጣቱ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሱ ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሉት በመሆኑ ጥያቄዎቹን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠው አስታውቋል። በዚህም መሰረት ተንቀሳቃሽ ፈንድ ከመመደብና ወጣቱም ተጠቃሚ እንዲሆን ከክልሎች ጋር በመስራት ላይ ይገኛል።

ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራችን ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርበታል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

መንግሥት የግሉና የመንግሥት የዘርፎች ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች እየተከተለ መሆኑን ወጣቱ ሊገነዘብ ይገባል።

ይህም መንግስት ታዲያ እዚህ ላይ የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል የሚካሄድ መሆኑን ማወቅ አለበት።

መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ የሚገኝ በመሆኑ ወጣቱ ይህን ሁኔታ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሊያውለው ይገባል። ይህን ካደረገ የነገ ስራው ብሩህ ይሆናል። አዲሱ ዓመትም ይፈካለታል። በተጨባጭ ተስፋዎች ላይ ተመርኮዞም ራዕዩን እውን ሊያደርግ ይችላል።

የመጪው አዲስ ዓመት የወጣቱ ራዕይ ተጨባጭ መሆን አለበት።  “አዲስ ዓመት ጠባ…” ብለን 2010 ዓ.ምን ስንቀበል፤ በግለሰብ ደረጃ የምናቅደው አዲሱ ውጥናችን የሚደረስበትና ሰላማዊ መሆን እንዳለበት መዘንጋት አይኖርብንም። የትላንት የሁከትና የብጥብጥ ችግሮቻችንን የምንክስበት ዓመት ሊሆን ይገባል። የሰላምን ፀዳል የምንላበስበት መሆኑም እንዲሁ። እናም ወጣቱ ትውልድ ከምንም በላይ ለሰላማዊነት ትልቅ ቦታን በመስጠት ዓመቱን ሊጀምረው ይገባል።

ወጣቱ በተጠናቀቀው ዓመት ከነበረበት ቦታ ይበልጥ ወደ ላይ ከፍ ማለት ይኖርበታል። በትናንቱ ቦታ ፈፅሞ መገኘት አይኖርበትም። ከትናንቱ ጠንካራ ጎኖችን በመውሰድ ነገ ይበልጥ ሊያጎለብታቸው ይገባል። አመለካከቱ በአዲሱ ዓመት በአዲስ ሰላማዊና የተጠቃሚነት መንፈስ መቀየር አለበት። ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበሩትና ወጣቱ በማወቅም ይሀን ባለማወቅ ተሳታፊ የሆነባቸው የሁከትና የትርምስ ጉዳይ አስፈፃሚዎችን አሉባልታ ባለመስማት አዲሱን ዓመት በአዲስ የስራ መንፈስ መጀመር አለበት።

ወጣቱ በ2010 ዓ.ም መተግበር ያለበት በአሮጌው ዓመት የነበሩብንን ችግሮች የሚያቃልል፣ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል እንዲሁም በሰላማዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ እውነታን እንጂ በአቋራጭ መበልፀግን መሆን የለበትም።

በአቋራጭ ለመበልፀግ መሞከር ሀገርንና ህዝብን ከመጉዳቱም በላይ በራስና በቤተሰብ ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን ከላይ የጠቀስኩት አብነት ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል።

በመሆኑም በሚጠባው መስከረም ያልተገባ ጥቅምን ወይም ኪራይ ሰብሳቢነትን በማውገዝና ሰላማዊ ሆነን ሀገርንና ህዝብን በማይጎዳ ተግባር ላይ በመዋል አዲስ ተስፋን መሰነቅ አለበት። በአቋራጭ ለመበልፀግ መሞከር መዘዙ ከባድ ነው።

በራስ፣ በቤተሰብና በአጠቃላይ አገራዊ እድገት ላይ ችግር ይፈጥራል። ይህን እውነታ ወጣቱ በመረዳት ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን መጠየፍ፣ ተፈፅሞም ሲያገኝ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት ይጠበቅበታል። እንዲያውም ይህን ጉዳይ በቁልፍ ተግባርነቱ ቢወስደው በዚህ ረገድ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በከፈተኛ ደረጃ ያግዛል።

በሌላ በኩልም ወጣቱ የፅንፈኞችን አሉባልታ ሊያወግዝ ይገባል። የፅንፈኞቹ ዓላማ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ እያገኘ ያለውንና ወደፊትም ይበልጥ ሊያገኝ የሚችለውን ተጠቃሚነት የሚያስቀር ነው።

ምንም እንኳን የሁከት ኃይሎቹ በተቀናጀ ሁኔታ የህዝቡን ብሶቶችና የራሳቸውን አሉባልታዎች በማያያዝ ለማራገብ እንዲሁም ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑና የሚምታቱ ፀረ-ልማት ሃሳቦችን እያቀረቡ ለማሳሳት ቢሞክሩም ወጣቱ ጆሮውን ሊሰጣቸው አይገባም። ይህ በአዲሱ ዓመት ፈፅሞ መቀየር ያለበት ገዳይ ነው።

የማናቸውም ችግሮች መፍትሔ የሚመነጨው በሀገሪቱ መንግስት እንጂ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ብሎም የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ምንደኛ በመሆን በህዝቦች ስቃይ ትርፍ ለማጋበስ በሚፈልጉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ባለመሆኑ ሃቁን መገንዘብ ይኖርበታል። መንግስት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቱ ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን በመረዳት በአዲስ የስራ መንፈስ 2010 ዓ.ምን ሊቀበለው ይገባል። እኔም መልካም አዲስ ዓመትን ለሁሉም የአገራችን ወጣቶች እመኛለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy