Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግ ባተሌ ንብ እንጂ ራሱን የሚበላ ቁስላም ጅብ አይደለም

0 610

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግ ባተሌ ንብ እንጂ ራሱን የሚበላ ቁስላም ጅብ አይደለም

ኢብሳ ነመራ

የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛ ፕሮግራም ባለፈው ሳምንት ሰኞ ባስተላለፈው ማህደረ ዜና ፕሮግራሙ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ወሰንን ሰበብ አድርጎ የተቀሰቀሰው ግጭት ላይ ያተኩረ ዘገባ አቅርቦ ነበር።  በዚሀ ዘገባ ላይ ግጭቱን መነሻ በማደረግ በ1983 ዓ/ም በሽግግር መንግስት ውስጥ  ተሳትፎ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመነበር የነበሩትን አሁን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተሰኘ ስደተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አደራጅተው በሊቀመንበርነት የሚመሩትነ አቶ ሌንጮ ለታን አስተያያት አስደምጦናል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት መነሻ በማድረግ አቶ ሌንጮ ለታ ከሰጡት አስተያየት ውስጥ ምላሽ ይሻል ብዬ ያመንኩበትን ለመመልከት ወድጃሉ። ከዚያ በፊት ግን የፕሮግራሙ መሪ ጋዜጠኛ የመግቢያ አቀራረብ ላይ አስተያይት መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ሲገልጽ፤ በኢትዮጵያ በብሄር ወይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተው ፌደራላዊ ሥርአት ከጸናበት ጊዜ ጀምሮ ሃገሪቱ 26 ዓመታት የተጓዘችው የመጤና የነባሮች ግጭት፣ የአማራና የኦሮሞ ግጭት፣ የአፋርና የኢሳ (ሶማሌ) ግጭት፣ የጉጂና የቡርጂ ግጭት፣ የሶማሌና የኦሮሞ ግጭት፣ የኑዌርና የአኝዋ ግጭት፣ ወዘተ በግጭት ማግስት ግጭት እያስተናገደች ነው። በየግጭቶቹ የተገደሉ ሰዎች አስከሬኖች የተፈናቀሉ ዜጎቿን እያሰላች ነው ብሏል።

ይህ ግን የባለፉ 26 ዓመታት የኢትዮጵያ ዋና መገለጫ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኛው በጠቀሳቸው አካባቢዎች አለመግባባቶችና ግጭቶች የተቀሰቀሱ መሆናቸው ባይካድም፤ የግጭቶቹ ግዝፈት፣ የበሉት የዜጎች ህይወት፣ ያጋዩት የሃገር ሃብት ወዘተ ከ1983 ዓ/ም በፊት ከነበረው በመላ ሃገሪቱ በብሄራዊ የነጻነት ንቅናቄዎችና በወታደራዊው ደርግ መሃከል ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በአጠቃላይ ባለፉት ሃያስድስት ዓመታት በሃገሪቱ ግጭት አልነበረም ወይም የለም ሊባል የሚችልበት ሁኔታ ነው የነበረው።

የዛሬይቷ ኢትዮጵያ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከ50 በመቶ በላይ የነበረውን ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ወደ 22 በመቶ ዝቅ ማድረግ የቻለች ሃገር ነች። ለሁሉም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ማዳረስ የቻለች ሃገር ነች። ከ50 በመቶ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶቿ የ2ኛ ደረጃ የትምህርት እድል አመቻችታለች። 15 ብቻ የነበሩትን የሞያና የቴክኒክ ሞያ ማሰልጠኛ ተቋማት ቁጥር ወደ 1300 በማሳደግ እስከ 1 ሚሊየን ለሚደርሱ ወጣቶች የመካከለኛ ደረጃ የሞያ ስልጠና እየሰጠች የምትገኝ ሃገር ነች። ሁለት ብቻ የነበሩትን ዩኒቨርሲቲዎች ወደ 44 በማሳደግ ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑ ወጣቶቿን በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ የከፍተኛ ሞያ ትምህርት እየሰጠች ያለች ሃገር ነች።

የዛሬይቱ ትዮጵያ፣ በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎቿ የሥራ እድል መፍጠር የምትችልበት ደረጃ ላይ የደረሰች ሃገር ነች። በቀን ሶስቴ መመገብ አይችል የነበረውን፣ የተሟላ የቀንና የሌሊት ልብስ ያልነበረውን፣ ለእግሩ ጫማ ያልነበረውን አርሶ አደር መሰረታዊ ፍላጎቶቹን እንዲያሟላ ማድረግ ከመቻል ባሻገር በርካታ ባለጸጋ አርሶ አደሮችን ማፍራት የቻለች ሃገር ነች። አሁን የድርቅ አደጋ ካጋጠማቸው አካባቢዎች ውጭ ካሉና በሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ከታቀፉ ጥቂት አርሶ አደሮች በስተቀር የተቀረው አርሶ አደር በምግብ ራሱን ችሏል። ትርፍ አምርቶ ገቢውን ማሳደግ የቻለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በአንድ የአርሶ አደር መንደር አራት አምስት የጭነትና የህዝብ ማመላለሻ ካሚዮን፣ ለእግራቸው የቤት መኪና ያላቸው አርሶ አደሮች ተፈጥረዋል። በከተማ የሚከራዩ ቪላዎች ያስገነቡ አርሶ አደሮችም ቁጥር ቀላል አይደለም። ከአርሶ አደርነት ወደሃገር በቀል ኢንቨስተር ባለሃብትነት የተሸጋገሩም አሉ።

ኢትዮጵያ አሁነ ድርቅ ችጋር የማያስከትልባት፣ ለድርቅ ተጎጂዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በማቅረብ ረገድ የመሪነት ድርሻውን የተረከበች ሃገር ለመሆን በቅታለች። አሁን የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ያለባቸውን የምግብ እርዳታ ከረጢጦች እየተመለከትን ነው።

ኢትዮጵያ አሁን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአፍሪካ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሃገራት አንዷ ነች። የቀጠናውን ሰላም በማስጠበቅ፣ ከቀጠናውም አልፎ ለአፍሪካ ሰላም ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ የምትገኝ ሃገር ነች። በዓለም አቀፍ የአየር ንበረት ለውጥ አፍሪካን በመወከል በዓለም አቀፍ መድረክ ለመሟገት የተመረጠች ሃገር ነች። ሰሞኑን ከተባበሩት መንግስታት 72ኛ ጉባኤ በተጓዳኝ በተካሄደ በርካታ የዓለም መሪዎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ያቀረበችው የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ማሻሻያ ሀሳብ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። ኢትዮጵያ በታሪኳ የአሁኑን ያህል የዲፕሎማሲ ስኬት ከፍታ ላይ የደረሰችበት ጊዜ የለም።

በአጠቃላይ የአዲሲቱን ኢትዮጵያ ዋና መገለጫዎች በአጭር ጽሁፍ ዘርዝሮ መጨረስ ስለማይቻል ለማሳያነት ያህል ይህን ያህል ካነሳሁ ይበቃል።

ይህ ማለት ግን በሃገሪቱ ምንም አይነት ግጭት የለም ማለት አይደለም። ፌደራላዊ ስርአቱ ምንም የይገባኛል ጥያቄና ግጭት እንደማይነሳ ዋስትና የሚሰጥ አይደለም። ግጭቶችና አለመግባባቶች ሊነሱ ይችላሉ። የሁን እንጂ  በፌደራላዊ ስርአቱ የይገባኛል ጥያቄዎችና ግጭቶች ሲቀሰቀሱ ከ1983 ዓ/ም በፊት እንደነበረው አይነት ማባሪያ የሌለው አይነት ጦርነትና የመበታተን አደጋ ከማምራታቸው በፊት መፍታት የሚያስችል ህገመንግስታዊ ሥርአት አለ። የጀርመን ድምጽ የጠሰቀሳቸው ግጭቶች ከአንድ ሰሞን የአካባቢ ግጭትነት ሳይዘሉ እየተፈቱ፣ የሃገሪቱ ዋነኛ መገለጫ ሰላምና ልማት ሆኖ እንዲዘልቅ ማድረግ የተቻለው ለዚህ ነው። የአሁኗ ኢትዮጵያ ሁኔታ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ነው መታየት ያለበት።

አሁን የሰሞኑን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተነሳውን ግጭት መነሻ በማድረግ በአቶ ሌንጮ ለታ ወደተሰጡት አስተያየቶች ልመለስ። አቶ ሌንጮ ለታ በሰጡት አስተያየት፣ ግጭቱን የመራው ልዩ ፖሊስ የሚባል ሃይል ነው። ይህ ሃይል ሶማሌዎችን አይወክልም። በክልሉ መንግስት የሚታዘዝም አይደለም። በፌደራል መንግስት የሚታዘዝ ሃይል ነው።  እናም በኦሮሞዎች ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በቀጥታ በፌደራል መንግስት በኦሮሞዎች ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው። ይህ የተደረገው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትን (ኦሀዴድ) ለማፈራረስ ነው ብለዋል።

በቅድሚያ ኦህዴድን በከሃዲነት የሚፈድጁት አቶ ሌንጮ ለታ፣ በድንገት የኦህዴድ ተቆርቋሪ ሆነው መቅረባቸው ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ነው። እንግዲህ፣ የኦሮሞ ህዝብ የፌደራል መንግስቱን ከመሰረቱት ክልሎች አንዱ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋትም ቀዳሚው ነው። የፌደራል መንግስቱ ትልቁ የስልጣን አካል በሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በከፍተኛ ቁጥር የሚወከል ክልል ነው። ይህ የኦሮሞ ህዝብና ኦሮሚያ የፌደራል መንግስቱ ተለጣፊ አካል ሳይሆኑ አንድ ወሳኝ ብልት መሆናቸውን ያመለክታል። የፌደራል መንግስቱ ውሳኔዎች ውስጥ የክልሉ ህዝብ ተወካዮች አሉበት። ውሳኔውን በማስፈጸም ውስጥ በርካታ የኦሮሞ ልጆች አሉበት። እናም የፌደራል መንግስቱ የኦሮሞ ህዝብ ላይ ጥቃት አወጀ ማለት፣ ኦሮሞዎች አሮሞዎች ላይ ጥቃት አወጁ ከማለት የተለየ አይደለም። የአቶ ሌንጮን አስተያየት ከዚህ አንጻር ስንመዝነው ከጭፍን ተቃውሞ የመነጨ መሰረተ ቢስ ሆኖ እናገኘዋለን።

አቶ ሌንጮ የፌደራል መንግስቱ ኦሮሞዎች ላይ ጥቃት አወጀ ያሉበትን ምክንያት ሲገልጹ ኦህዴድን ማዳከም እንደሆነ ነግረውናል። ይህን ሃሳባቸውን አቃንተን ስንመለከተው፣ የፌደራል መንግስቱን የሚመራው ኢህአዴግ፣ ኦህዴድን የማፈራረስ ዓላማ አለው የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። እንግዲህ፤ ኦህዴድ የኢህአዴግ አንድ አካል ነው። ኦህዴድ የኢህአዴግ ግንጥል ጌጥ አይደለም፤ አንዱ አካሉ እንጂ። ኢህአዴግ ፓሊሲዎቹን ለማስፈጸም ያስቻለውን የስልጣን ውክልና ከህዝብ መረከብ የቻለው ኦህዴድንም ስለያዘ መሆኑን ያውቃል። ኦህዴድን ከውስጡ ቢያጠፋ ጎዶሎ ይሆናል። ኢህአዴግ ኦህዴድን አጥፍቶ ጎዶሎ ከሆነ የስልጣን ውክልና የማግኘት እድሉን እንደሚያመክን ያውቃል። ኢህአዴግ ኦህዴድን አጠፋ ማለት በእጁ እጁን ቆርጦ ጎዶሎ ሆነ ማለት ነው።

እስከምናውቀው ድረስ፤ ኢህአዴግ እንደቁስላም ጅብ ከራሱ ላይ እየገመጠ ሞቱን በእጁ የሚጠራ ቂል ድርጅት አይደለም። እናም አቶ ሌንጮ የሰጡት አስተያየት ከአንጋፋ ፖለቲከኛ በተለይ ኢህአዴግን ያውቃል ተብሎ ከሚገመት ፖለቲከኛ የሚጠበቅ አይደለም። እኔ በግሌ የአቶ ሌንጮ አስተያየት ክብራቸውን ዝቅ  የሚያደርግና አሳፋሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

አቶ ሌንጮ ይህን ተራ አስተያየት የሰጡት ከጭፍን ጥላቻ በመነሳት ነው። ኦህዴድንና የኦሮሞን ህዝብ ከኢህአዴግ በመነጠል ኢህአዴግን ለማዳከም ወይም ለማፍረስ በማሰብ ነው። ይሁን እንጂ ተራ ሃሳብ በዓመታት ፈታኝ ትግል እየተሳለ የመጣውን ኢህአዴግ የማፈራረስ አቅም እንደማይኖረው አስታውሰው የሚያዋርዳቸውን ሃሳብ ከመሰንዘር ቢታቀቡ መልካም ነበር። ለማንኛውም ኢህአዴግ እንደቁስላም ጅብ ራሱን ገምጦ ሞቱን የሚያቃርብ ደካማ ድርጅት ሳይሆን፣ በህዝቦች አንድነት ላይ የተመሰረተች የበለጸገች ኢትዮጵያን የመመስረት ግልጽ ግብ ያለው፣ ወደዚህ ግብ የሚያደርሰውን መንገድ የሚያውቅ፣ ከዚህ የሚያደናቅፈውን ነድፎ ማስወገድ የሚችል፣ ከህዝብ ጋር በመንጋ የሚተም ባተሌ ንብ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy