Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢሬቻ— የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ወግ መገለጫ!

0 1,956

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ኢሬቻ— የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ወግ መገለጫ!

                                                          ቶሎሳ ኡርጌሳ

በያዝነው ወር የኢሬቻ በዓል በደመቀ ስነ ስርዓት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ወግ መገለጫ ነው። ከፖለቲካዊ ጉዳዩች ጋር የሚያያይዘው አንዳችም ነገር የለም። እናም በዕለቱ ይህን በዓል ለማክበር የሚወጣው የኦሮሞ ህዝብ እንዲሁም በበዓሉ ላይ የሚገኝ ታዳሚ ስለ ሰላም፣ መቻቻልና አንድነት ለፈጣሪው ምስጋና በማቅረብ ለሰላማዊ አከባበሩ መትጋት የሚኖርበት ይመስለኛል።

አንዳንድ ፅንፈኞችና ለሀገራችን ሰላም በጎ የማይመኙ ሃይሎች ባለፈው ዓመት በዓሉን ተገን በማድረግ እኩይ ዓላማቸውን ለማራመድ ሲሞክሩ ተስተውሏል። በወቅቱ በነበረው ትርምስም በሰላማዊ መንገድ በዓሉን ለማክበር የወጡ ወንድሞቻችን ህይወት አልፏል። አካልና ንብረትም ወድሟል።

ይህን የበዓሉን ፈጣሪ መለመኛነት በመተው የፖለቲካ ማራመጃ ለማድረግ የሞከሩት ፅንፈኞች በወቅቱ የፈጠሩት እንዲህ ዓይነቱን አጥፊ ተግባር እንጂ ለህዝቡ ምንም ዓይነት የፈየዱለት ነገር የለም። ወትሮም ፅንፈኞች ተግባራቸው የህዝብን ሰላምና መረጋጋት ማወክ በመሆኑ ከዚህ በላይ የሚፈፅሙት ነገር የለም።

ያም ሆኖ የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ወግ መገለጫ እንዲሁም ፈጣሪን መለማመኛ መሆኑን ማሳየት ስለሆነ ወደዚያው እዘልቃለሁ። እንደሚታወቀው የኦሮሞ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ከሚያከብረው በዓላት ውስጥ አንዱ ኢሬቻ ነው። ይህ የሰላም በዓል ማንኛውም የኦሮሞ ተወላጅ በላቀ ሁኔታ አምላኩን ያመሰግንበታል። አምላኩ ለስህተት፣ ለደባ፣ ለተንኮልና ለውሸት ትዕግስት የሌለው መሆኑን ያስባል።

ይህ አምላክ በሰማይና በምድር ያለውን ማናቸውንም ነገር ፈጥሮ የሰው ልጅ እንዲጠቀምበትና እንዲያዝበት ስልጣን ስለሰጠው፤ ለዚህ ሁሉ የማይነጥፍ አምላካዊ ስጦታውና ለተደረገለት ሁሉ የኦሮሞ ህዝብ ምስጋና የሚያቀርብበት ቀን ነው—የኢሬቻ በዓል። ስሙንም እየጠራ ‘እንኳን ከክረምት ወደ ፀደይ በሰላም አደረስከን’ እያለ ተዓምራቱን ከፍ የሚያደርግበትም ታላቅ ዕለት ነው።

በዓሉ በሁሉም የኦሮሞ ተወላጅ ልብ ውስጥ ሰፊ ስፍራ አለው። ከክረምት ወደ ፀደይ በሚደረገው ሽግግር፤ ክረምት በፀደይ ተተክቷልና ደስታ ይገለፃል።

የክረምቱ የጨለማ ጉም ተገፎ በብርሃን ተተክቷልና ደማቅ ብርሃን ይታያል። የፀደይ ፀሐይ ያለ ምንም ስስት በሙሉ አቅሟ ልግስናዋን ትቸራለችና ህይወት የደመቀች ትሆናለች።

የኦሮሞ አርሶ አደር የዘራው እህል ፍሬ ሊያፈራ በአበባ ደምቆ ሌላው ደግሞ እያሸተ ነውና በተስፋነት ይመሰላል። በክረምቱ ዝናብ ሳቢያ የጨቀየው መሬት በፀደዩ መግባት እየደረቀ ነውና ሁሉም ከየቀየው ብቅ ብሎ የሰላም ቄጤማን የሚያነጥፍበት ወቅት ይሆናል።

እናም ይህ ሰንሰለታዊ ክንውን በሁሉም የኦሮሞ ተወላጅና ባህሉን በሚያከብሩ የሀገራችን ወንድሞቹ ዘንድ በየዓመቱ ፀደይ ትውስታው ከታላቅነቱ ጋር አብሮ ውልብ ይላል— የኢሬቻ በዓል።

በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በከፍተኛ አክብሮትና ስነ ስርዓት በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ የሚከበረው “የፀደይ ኢሬቻ” እና መጪው በልግ ሲገባ የሚከበረው “የበልግ ኢሬቻ” በዓል የዘህ ኩሩና ጨዋ ህዝብ ወግና ባህል መገለጫ ብቻ ነው። እናም በፖለቲካ ጉዳዩች መጠለፍ የለበትም።

በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ መንግስት የራሱን በቂና አስተማማኝ ዝግጅት የሚያደርግ ቢሆንም፤ ህብረተሰቡም በዓሉ በአንዳንድ የህዝብን ሰላም በማይሹ ሃይሎች ድብቅ የተላላኪነት አጀንዳ እንዳይውል መከላከል ያለበት ይመስለኛል።

ይህን የምለው ከምንም ተነስቼ አይደለም። ባለፈው ዓመት በህዝባችን ላይ ፅንፈኞች የፈጠሩትን አሳዛኝ ተግባር ተመርኩዤ ነው። እንደምናስታውሰው አምና እነ ጃዋር መሐመድን የመሳሰሉ የውጭ ሃይል ተላላኪ ፅንፈኞች በበዓሉ ላይ ሁከት ፈጣሪዎችን በማደራጀት የበርካታ ንፁሃን ወገኖቻችን ህይወት እንዲጠፋና አካላቸውም እንዲጎድል አድርገዋል። ይህ በየትኛውም ዓይነት ተዋውሟዊ ስሌት ፖለቲካ ሊሆን አይችልም—ሆን ብሎ ህዝብን ለመጉዳት ማሴር እንጂ።

ፅንፈኞች በኦሮሞ ህዝብ ደስታ የማይደሰቱና ወግና ባህሉን የማያውቁ የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው። ህዝቡ በክረምት ውስጥ ሰጥሞ ፀደይን እንዳያይ የሚሹ፣ የፀደይ ፀሐይን ሳይጠግብ በዚያው እንዲያሸልብ የሚያደርግ አጀንዳን የሰነቁ፣ አርሶ አደሩ የዘራውን እሸት ማፍራቱን እንዳያይ የፈረዱበትና የነገ ተስፋው እንዲጨልምበት የሚያሴሩ ለህዝብ የማያስቡ ጠላቶቹ  ናቸው።

ታዲያ እነዚህ ለባዕዳን በተላላኪነት ተሰልፈው ከኦሮሞ ህዝብ ወግና ባህል ጋር የሚጋጩና የገዛ ወገናቸውን የሚያባሉ ግለሰቦችንና ቡድኖችን “ኦሮሞዎች ናቸው” ብዬ ለማሰብ ይከብዳል። “ለምን?” ከተባለ፤ ፅንፈኞቹ ከኦሮሞ ወግና ባህሎች እንዲሁም እምነቶች ጋር በገሃድ የሚጋጩ ከሆነ፤ የእነዚህ አካላት ኦሮሞነት በምንም ዓይነት ስሌት ቁጥር ውስጥ ሊገባ አይችልም—ኦሮሞ ሆኖ ራሱ ከሚያምንበት ወግና ባህል ጋር በመጋጨት የራሱን ትውፊት ሊቀለብሰው ይሞክራል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው።

ርግጥ የተላላኪ ፅንፈኞቹ ዓላማ ‘ገንዘብ እስካስገኘ ድረስ ማንኛውም የሁከት መንገድ ትክክል ነው’ የሚል በመሆኑም ባህላዊም ይሁን ሃይማኖታዊ ቀኖናዎችን ከመጋፋት ወደ ኋላ ይላሉ ተብሎ አይታሰብም።

ፅንፈኞቹ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እጅግ የሚከበሩትን አባገዳዎች እንኳን አያከብሩም። የዛሬ ዓመት ገደማ የተመለከትነው ይህንኑ ነው። አባገዳዎች ህዝቡ በግርግር እንዳይጨፈለቅ ንግግር ሲያደርጉ ተላላኪ ፅንፈኞቹ መነጋገሪያውን ከአባ ገዳዎች ላይ በገሃድ ሲነጥቁ ተስተውሏል። ይህም እነዚህ ሃይሎች ከራሳቸው ፖለቲካዊ ሴራ ውጭ የኦሮሞን ህዝብ ባህላዊ መሪዎችን አይቀበሉም። በእኔ እምነት እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ባህልንና ታሪክን ብሎም ታላላቅ አባቶችን አለመቀበል ነው።

እንደሚታወቀው ሀገራችን በዩኔስኮ ያስመዘገበችው የገዳ ስርዓት የዴሞክራሲ መሰረትና ሁነኛ ማሳያ ነው። ረጅም ታሪክ ያለው የኦሮሞ ህዝብ የስልጣን መሸጋገሪያ ስርዓትም ነው። የገዳ ስርዓት እንደ ማንኛውም ዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፤ የገዳ ስርዓትም ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈፃሚና ህግ ተርጓሚ አካላት አሉት።

በዚህ የስልጣን ክፍፍል መሰረትም ስርዓቱ ህዝቡን በባህላዊ መንገድ ያስተዳድራል። በስልጣን ክፍፍሉ ቦታ ውስጥ አባገዳዎች ቀዳሚውን ስፍራ ይወስዳሉ። የላይኛው የስልጣን እርከን የአባገዳው ነው። እናም በየስምንት ዓመቱ አንዴ የሚመረጠው አባገዳ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ መናቻውን ተግዳሮቶችን ይፈታል፤ የሚፈቱበትን መንገዶችንም ያመላክታል።

በስርዓቱ ውስጥ የቤተሰብ፣ የጎረቤት፣ የአካባቢ ወይም የደን ጥበቃ እንዲሁም የግጭት አፈታት ስርዓት እስከ አሁን የተረጋገጡና እየተሰራባቸው የመጡ ህግጋት ናቸው። የዚህ ስርዓት ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት አባገዳ በህብረተሰቡ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸውና ክብር የሚቸራቸው ናቸው።

ህብረተሰቡ እርሳቸው ያሉትን ነገር በባህሉና በደንቡ መሰረት ይፈፅማል። በአጭር አነጋገር አባገዳው የኦሮሞ ህዝብ ዘውግ ናቸው ማለት ይቻላል። ሁሉም የኦሮሞ ተወላጅ አክብሮትን በመቸር ለአባገዳው ውሳኔ ተገዥ ይሆናል። ፅንፈኛው ሃይል ግን ይህን ተፃርሮ በመቆም አባገዳዎችን የሚቀበል አለመሆኑን በገሃድ አሳይቷል።

ያም ሆኖ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ወግና ባህል መገለጫ እንዲሁም የፈጣሪ መለማመኛና ምስጋና ማቅረቢያ በመሆኑ፤ ህዝቡ እስካለ ድረስ በየዓመቱ ይከበራል። የትኛውም ሃይል የህዝቦችን ወግና ባህል ተፃርሮ እንዲቆም ህገ መንግስቱ አይፈቅድለትም። እናም የኦሮሞ ህዝብ ወግና ባህል ማሳያ የሆነው ኢሬቻ ባህለዊ ትውፊቱን ጠብቆ ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ መከበሩን ይቀጥላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy