Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ካስማ መሆኗን ትቀጥላለች

0 478

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ካስማ መሆኗን ትቀጥላለች

 

አሜን ተፈሪ

 

የራሷን ሰላም ከጎረቤቶችዋ መለየት እንደማይቻል በውል የተገነዘበችው ኢትዮጵያ፤ ስምንት ሐገሮች አባል በሆኑበት ኢጋድ የተሰኘ ክፍለ አህጉራዊ ድርጅት አማካይነት፤ ክፍለ አህጉሩ ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች፡፡ አካባቢውን የማረጋጋት ሚና እየተጫወተች የቆየችው ኢትዮጵያ ከራሷ ግዛት አልፎ ለጎረቤቶቹ ሰላም ዋስትና መሆን የቻለ የመከላከያ ሠራዊት ያላት ናት፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተለያዩ የሶማሊያ ጎሳዎችን ለማስማማት በኢጋድ በኩል ጥረት ስታደርግና የአሸባሪ ኃይሎችን ትንኮሳ ለመቋቋም ስትሞክር የቆየችው ኢትዮጵያ፤ በመጨረሻ በአሸባሪ ቡድን ጅሃድ ሲታወጅባት ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ በማስገባት አደጋውን ለመቀልበስ ሰርታለች፡፡ በዚህም የአሸባሪ ቡድኖችን አከርካሪ በመስበር ሶማሊያ የሐገር ግንባታ ጉዞ እንድትጀምር ለማድረግ ችላለች፡፡  

 

በርግጥ ክፍለ አህጉሩን ለማመስ ከሚሰራው የኤርትራ መንግስት በስተቀር፤ የኢጋድ ሐገራት በጋራ በመንቀሳቀስ ለመስራት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም አሁን የኢጋድ ሐገራት ሲንቀሳቀሱ የቆዩበት አውድ ምልኩን እየቀየረ ይታያል፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት ወደ ሰሜን አፍሪካ ተሻግሮ የስደተኞችን ቁጥር አበራክቶታል፡፡ የአሸባሪ ቡድኖች እንቅስቃሴም ከሳህል አካባቢ ወደ ሶማሊያ የተዘረጋበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

 

በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ እየተሳቡ የሚመጡት የተለያዩ ወገኖች እንቅስቃሴ፤ ወትሮም እንደ እንቁላል በቀላሉ ተሰባሪ የሆነ ጂኦፖለቲካዊ ባህርይ ባለው በዚህ የአህጉሪቱ ክፍል ሊያሳድሩ የሚችሉት ተጽዕኖ አሳሳቢ ሆኖ ይታያል፡፡ ለምሳሌ፤ የባህረ ሰላጤው ሐገራት ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የተጠናከረ ትስስር ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸው አካባቢው አዲስ መልክ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ ታዲያ በመካከላቸው በተፈጠረ ቁርሾ እየታመሱ ወደ አፍሪካ ቀንድ እየገቡ ያሉት ሐገራት፤ ፊና ለይተው በአፍሪካ ቀንድ የየራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር መራኮት ጀምረዋል፡፡ በክፍለ አህጉሩ የተጽዕኖ ቀጣና ለመፍጠር መሻኮት ይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ ለውጦች ውስጥ ጠንካራ አቋም ይዛ የአካባቢው ሰላም ሳይደፈርስ እንዲዘልቅ በማድረግ ጥሩ ሥራ ሰርታለች፡፡

 

‹‹የባህረ ሰላጤው ሐገራት ሁኔታ ያሳስበኛል›› የሚለው የምዕራቡ ዓለም፣ እንዲሁም የሌሎች ሐገራት የደህንነት ፍላጎቶች በአንድ ለማደር የሚያስችል ተስማሚ ባህርይ የለውም፡፡ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በወጉ በመያዝ የአፍሪካ ቀንድ ጨርሶ ሳይናጋ አንጻራዊ መረጋጋት ይዞ እንዲዘልቅ ለማድረግ ስትሞክር በቆየችው ሐገራችን አሁንም የሰላም ካስማ ሆና ቆማለች፡፡

 

አዎ፤ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካስማ እና ማዕከል ሆና የምትታየው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች፣ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ኤምፓየር አጽንታ ዘመናትን የተሻገረች፤ የበርካታ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝብ ሐገር በመሆኗ፤ ለብሔር – ብሔረሰቦችዋ ዕውቅና የሰጠ ፌደራላዊ ስርዓት የተከለች ሐገር ናት፡፡ ነገር ግን አሁን የጸናው ስርዓት ይዟት የሚቆመው፤ የሚታየው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና የሐብት ክፍፍሉ የወጣት ልጆችዋን ፍላጎት የሚያረካ ሆኖ መዝለቅ እስከቻለ ድረስ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የራሷንም ሆነ የክፍለ አህጉሩን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በኢኮኖሚው፣ በመልካም አስተተዳድር እና በዴሞክራሲው ዘርፍ ጠንክራ መስራት ይኖርባታል፡፡  

 

ሆኖም የኢትዮጵያ ሰላም በጎረቤት ሐገራት ካለው ሁኔታ ጋር ተለይቶ ሊታይ አይችልም፡፡ የሶማሊያ ጉዳይ የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ፈተና ሆኖ የሚታየው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ በእያንዳንዱ የአፍሪካ ቀንድ ሐገራት ዘላቂ መሠረት ያለው እና ብሔራዊ መግባባትን የፈጠረ መንግስታዊ ስርዓት ማቆም እስካልተቻለ ድረስ፤ ሐገራት በውስጣዊ ግጭት ውስጥ መዘፈቃቸው እና ውሎ ሳያድር ችግራቸው ወደ ጎረቤት ሐገራት መዛመቱ የማይቀር ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሚያሳየን ይህን ነው፡፡

 

ባለፉት አርባ ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ጎልተው የታዩ አምስት የሚሆኑ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ በየሐገራቱ የታዩ ጦርነቶች የጎረቤት ሐገራትን የጎተቱ ነበሩ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኝ አንድ ሐገር የራሱን ውስጣዊ ጉዳይ ማስተካከል ሲሳነው፤ ወዲያው የአካባቢውን ሐገራት ሰማይ የሚያደፈርስ ጥይት ይሆናል፡፡ ከአምስቱ ጦርነቶች አንደኛው የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ነበር፡፡ ይህ ጦርነት የየመንግስታቱን ሐብት በማውደም በመጨረሻ ወደ ውድቀት እንዲያመሩ ያደረጋቸው ነበር፡፡ ሶማሊያ ለሁለት አሥርት ዓመታት የዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በመዘፈቅ የተበታተነች ሐገር ለመሆን በቅታለች፡፡ አልሸባብን ለመሰለ አሸባሪ ኃይል መፈልፈያ ምቹ ማህጸን ለመሆን ትችላች፡፡ ይህም የጎረቤት ሐገራትን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ አስገብቷቸው፤ በአፍሪካ ህብረት ስም በሶማሊያ ጉዳይ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል፡፡

 

የአፍሪካ ቀንድ ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ቀጣና ነው፡፡ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደም አፋሳሽ ጦርነት ካደረጉ በኋላ ‹‹ሰላም ወይ ጦርነት›› ለማለት በሚቸግር ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ 20 ዓመታትን ገፍተዋል፡፡ ሱዳን ከራሷ ጋር ጦርነት ውስጥ ነች -ኮርዶፋን እና ዳርፉር፡፡ ደቡብ ሱዳን የነጻነት አዋጇን ባወጀች ማግስት ዘግናኝ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ዜጎችዋን ለአስከፊ እልቂት እና ለከፋ ሰብአዊ ቀውስ የዳረገ፤ አሳሳቢነቱ እየጨመረ የመጣ ግጭት የምታስተናግድ ሐገር ሆናለች፡፡ ታዲያ እንዲህ ዓይነት በቀላሉ ተሰባሪ የሆነ ውስጣዊ እና አካባቢያዊ አንድነት ያለውን የአፍሪካ ቀንድን ከቀውስ የማውጣት ተግባርን ቀዳሚ ግብ ሆኖ እየሰራች የምትገኘ ኢትዮጵያ ናት፡፡

 

የአፍሪካ ቀንድ ዥንጉርጉር ገጽታ እና ዘወትር በቋፍ ሆኖ የሚያስጨንቅ የደህንነት ሁኔታ ያለው ክፍለ አህጉር ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ መልከ – ብዙ ከመሆኑ የተነሳ፤ ማንኛውም ሰው የፈለገውን አንዱን መልክ በማንሳት፤ ‹‹የክፍለ አህጉሩ መገለጫ ይኸ ነው›› እያለ በተለያየ መልክ ሊገልጸው የሚችለው አካባቢ ነው፡፡  አንዳንዶች፤ የአፍሪካ ቀንድ ሐገራትን እና በየሐገራቱ የሚኖሩ ህዝቦችን ለግጭት ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደረጋቸው፤ ይኸው የመልክዐ ምድር፣ የታሪክ፣ የሥነ ህዝብ፣ የፖለቲካ እና የባህል ልዩነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህም ልዩነት ከቀጣናው ውጪ ያሉ ኃይሎች ‹‹የውክልና ፖለቲካ›› ተዋናዮችን በቀላሉ ለማግኘት አስችሏቸዋል ይላሉ፡፡ ‹‹ልዩነት ለግጭት ይዳርጋል›› የሚለው ሐሳብ ችግር ያለበት ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታን እና ታሪክን በመጥቀስ መከራከርም ይቻላል፡፡ ሆኖም ክርክር ሊነሳበት የማይችለው ጥሬ ሐቅ፤ የአፍሪካ ቀንድ ለዘመናት የግጭት – የጦርነት አውድማ ሆኖ መቆየቱ እና ወሳኝ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያለው ክፍለ አህጉር የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡

 

አንዳንዶች የአፍሪካ ቀንድን ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ለመግለጽ፤ ‹‹በቀጣናው ነገር ቸልተኛ የሚሆኑ ወገኖች ሁሉ፤ ለቸልተኝነታቸው አንድ ቀን ከባድ ዋጋ መክፈላቸው እንደማይቀር ሁሉ፤ አካባቢውን ለጥቅማቸው የተመቸ ለማድረግ የሚሰሩ ወገኖችም ጣታቸውን በእሣት መቃጠላቸው አይቀርም›› ይላሉ፡፡ እናም በታሪክ መስቀለኛ መንገድ ቆሞ የሚታየው የአፍሪካ ቀንድ፤ ዘመን አይሽሬ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ዳግም ለማረጋገጥ፤ ዛሬም የታላላቅ ሐገራትን ትኩረት በኃይል ሲጎትት ይታያል፡፡ በዚሁ መጠን በክፍለ አህጉሩ የምትገኘውን ሐገራችንን ያሳስባታል፡፡

 

በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠረው የሽብርተኛ ቡድኖች እንቅስቃሴ፤ የዓለም ህብረተሰብ ቀልብ ከአካባቢው እንዳይነሳ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢስላማዊ ሐገራት መካከል የተፈጠረው የጥቅም ግጭት እና መፋጠጥ፤ በአካባቢው የሚታየው የስትራቴጂያዊ አጋርነት አሰላፍ፤ ያልተገመተ ቅርጽ እንዲይዝ ወይም ለመረዳት የሚያስቸግር የለውጥ ሂደት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ እንዲሁም በየመን የሚካሄደው ጦርነት የምሥራቅ እና የምዕራብ የዓለም ክፍሎች መገናኛ የሆነውንና በመካከላቸው ለሚካሄደው የንግድ እንቅስቃሴ ዋና የደም ሥር ተደርጎ የሚታሰበውን የቀይ ባህር የጉዞ መስመር ደህንነትን ከመቸውም ጊዜ የከፋ አደጋ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ በአካባቢው በፍጥነት ሲስፋፋ የሚታየው የሐይማኖት አክራሪነትም፤ በአፍሪካ ቀንድ በሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በሰላም አብሮ የመኖር ዕድል ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡

 

በሌላ በኩል፤ ዓለም አቀፍ ገጽታ ባለው የስደት እንቅስቃሴ እና በሽብርተኝነት ጉዳይ ሲጨነቅ ቆየው የምዕራቡ ዓለም፤ ለአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት ለመስጠት ተገድዷል፡፡ ከክፍለ አህጉሩ ጋር ያለውን የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ዘርፍ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመያዝ ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያም የቀጣናውን ችግሮች በተናጠል እና በጋራ መድረኮች ለመፍታት ወይም ለማስታገስ ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች፡፡

 

የአፍሪካ ቀንድ ሐገራት፤ ከዚህ የመርገም አዙሪት (vicious cycle) ወጥተው፤ በጸጋ አዙሪት (virtuous cycle) ለመሽከርከር ከፊታቸው የተጋረጡ እንቅፋቶችን ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ትኩረታቸውን አሳታፊ መንግስት በመመስረት እና ክፍለ አህጉራዊ ገበያ በመፍጠር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ለመገንባት ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ቀድሞ ለመጣ ገዢ ፍላጎታቸውን በችርቻሮ ለመሸጥ የሚጣጣሩ ሳይሆን፤ እንደ አፍሪካ ቀንድ አንድ አካል አድርጎ የሚያሰልፍ የጋራ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ ከውጪው ዓለም ጋር ለመደራደር የሚያስችል ቁመና መገንባት ይኖርባቸዋል፡፡

 

ይህ ሥራ የሚያግባባ ስርዓት መፍጠር ተስኖት ለቆየው፤ እንዲሁም የመነጣጠል እና የመዘነጣጠል መጥፎ የታሪክ ጓዝ ተሸክሞ እዚህ ለደረሰው የአፍሪካ ቀንድ፤ ከባድ ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ ሌላው ቀርቶ የአካባቢው ሐገራት ተመሳሳይ ወይም የጋራ የሆነ የቅኝ ግዛት ታሪክ እንኳን የላቸውም፡፡ አንዱ በጣሊያን፣ አንዱ በፈረንሳይ፣ አንዱ በእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ስርዓት ውስጥ የቆዩ ሐገራት የሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ ሐገራት ውስጥ ሦስቱ (ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ) ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም መፍትሔ ሊገኝለት ያልቻለ ከባድ የእርስ በእርስ ጦርነት አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙ ናቸው፡፡ አንድ አቅጣጫ የሌለው የተበታተነ ጎዳና ይዘው የሚጓዙ ሐገራት ያሉበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ፤ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተግባራዊ የተደረገበት ብቸኛው (ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን) የአፍሪካ ክፍል ነው፡፡ በተመድ ወይም በአፍሪካ ህብረት ሥር የሚንቀሳቀስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰላም አስከባሪ (በኃይል አስጠባቂ) ኃይል የተሰማራበት የዓለም ክፍል ነው፡፡ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ከሚያመርቱ (ደግሞም ከሚያስጠልሉ) ጥቂት የዓለማችን ክፍሎች የሚመደብ አካባቢ ነው፡፡

 

እንዲህ ባለ ቀጣና ውስጥ የምትገኘው ሐገራችን የአፍሪካ ቀንድ ሰላም የመሻሻል ጉዞ እንዲይ ለማድረግ ችላለች፡፡ ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሁንም ትኩረት ሰጥታ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ በተካሄደው የተመድ 72ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ኢትዮጵያ ያቀረበችው እና ሙሉ ተቀባይነት ያገኘው ረቂቅ ሐሳብ በሰላም ማስከበር ጉዳይ ያተኮረ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟን ከጎረቤት ሐገራት ሰላም ጋር አስተሳስራ ማየቷ ለራሷ እና ለጎረቤቶችዋ ትልቅ ፋይዳ አስገኝቷል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ካስማ መሆኗን ትቀጥላለች፡፡

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy