Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመልካም አስተዳደር ችግሮቻችን እልባት እንዲያገኙ…

0 264

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመልካም አስተዳደር ችግሮቻችን እልባት እንዲያገኙ…

ዳዊት ምትኩ

መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተለይም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብንና ተግባርን በዘላቂነት ማስወገድ የሚቻለው አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የግልፀኝነትና የተጠያቂነት አሰራሮችን በማጎልበት መሆኑን ያምናል። ከፍተኛ አመራሮቹን ሳይቀር በማስረጃና በመረጃ ላይ ተደግፎ በፈጸሙት ጥፋት ልክ የተጠያቂነት አሰራርን እያሰፈነም ነው።

ይህ የመንግስት የቆየ አሰራር ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ተጠናክሮ የቀጠለና ወደፊትም ይበልጥ በተጠናከረ ሁኔታ የሚቀጥል ነው። ይሁን እንጂ፤ ግለሰቦችን በማሳደድና በማሰር ብቻ የታሰበውን ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የሚፀየፍና እንደ ነውር የሚያይ ህብረተሰብ የመፍጠር አስፈላጊነት አጠያያቂ አይሆንም።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመጣመር በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህግ መንግሥት የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ መከበር እንዳለባቸው ይደነግጋል።

መንግሥትም ይህንን ድንጋጌ ተግባራዊ ለማድረግ ሠርቷል። በሃገሪቱም በርካታ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያጎለብቱና የሚያፋጥኑ ተግባራትም ተከናውነዋል።

በዚህም ህዝቡ በየደረጃው የልማት ተጠቃሚ ቢሆንም አሁንም ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ያልተፈቱና ህዝቡን እያማረሩ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ይጠበቅበታል፤ ይህንንም እየተገበረ ነው።

የህዝቡን የማይተካ ሚና ስለሚገነዘብም የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት ዕርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው። ባለስልጣናትንና ግለሰቦችን በጥፋታቸው ልክ ተጠያቂ እያደረገ ነው።

እርግጥ ግለሰቦችን ከኃላፊነት ቦታቸው በማንሳትና በማገድ ብቻ ችግሩን ማስወገድ አይቻልም። ይልቁንም ችግሩ እንዳይከሰት የአሰራር ስርዓትን ማበጀት ቁልፍ ተግባር ነው። ይህ አሰራር በጥልቀትና በስፋት በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መሥራት ያስችላል።

እንደሚታወቀው የተጀመረውን የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና ማለታቸው አይቀርም።

የሃገር ውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችና የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና የማይሹ የውጭ ኃይሎች ዓላማ ህገ መንግሥቱንና ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በመናድ ሀገራችን የጀመረችውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማደናቀፍ እንዲሁም የማያባራ ሁከትና ግጭትን በማቀጣጠል ሥርዓት አልበኝነትን ማስፈን መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህን ተልዕኳቸውንም ለማሳካት እንደ ምቹ ሁኔታ የሚወስዱት የራሳቸውን አቅምና ጥንካሬ ሳይሆን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ ኃይሎችንና በችግሩ የሚማራሩ ወገኖችን በመሣሪያነት በመጠቀም ነው። ስለሆነም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩትን ጥረቶች ማጠናከር ወሳኝ ነው።

በየትኛውም መስክ ለጥፋት የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ይገባል። የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ አንዳንድ ድብቅ የጥፋት ኃይሎችን ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በፅናት መታገል ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።

ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች እነማን እንደሆኑና በዕለት ተዕለት ህይወቱ የሚያጋጠመውን የመልካም አስተዳደር ችግርም ጠንቅቆ ያውቃል። ስለሆነም ህዝቡን ማዕከል ያደረግ ትግል ይበልጥ ማካሄድ ተገቢ ነው።

ህዝቡ በትግሉ ውስጥ ይበልጥ እንዲሳተፍ ለማስቻል በአስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ህዝብን የሚያሳትፍ አሰራር በግልፀኝነት መዘርጋት ይገባል። የአሰራር ስርዓት ከተዘረጋ እያንዳንዱ አስፈፃሚ ተግባሩን በስርዓቱ መሰረት እንዲፈፅም ያስችላል።

እርግጥ ተደጋግሞ እንደሚነገረው መልካም አስተዳደር በሂደት የሚገነባ እንጂ በአንድ ጀምበር የሚመጣ አይደለም። ምዕራባውያንም ቢሆኑ ዛሬ ለደረሱበት የመልካም አስተዳደር ተግባር ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል።

በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ያለ ጀማሪ የዴሞራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ አራማጅ ሀገር ተግባሩን በአጭር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ታመጣለች ብሎ ማሰብ አይቻልም። ለዚህም አንድ ቁልፍ ምክንያትን በተግዳሮትነት መጥቀስ ይቻላል። እርሱም ካለፉት ስርዓቶች በቀጥታ የወረስነውና ተንከባሎ ዛሬ ላይ የደረሰው በጉዳዩ ዙሪያ የሚታየው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው። “ብላና አብላኝ” የሚለው ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብ አንድ ቦታ ላይ መገታት አለበት።

በአሰራር ስርዓት የሚመራ ማንኛውም አስፈፃሚ በተቀመጠለት ህግና ስርዓት ብቻ ተግባሩን ይፈፅማል። በዚህ መንገድ ህዝባዊ አገልጋይነቱን የሚያረጋግጥ ማንኛውም አመራር ይሁን አስፈፃሚ ችግር የሚፈጥርባቸውን ቀዳዳዎችን ሊያገኝ አይችልም።

ምናልባትም ቀዳዳዎች ካሉ መስሪያ ቤቱ በተገልጋዩ መገምገሙ ስለማይቀር የሚኖረው ክፍተት ይሸፈናል። ከህዝብ ዓይን የሚሰወር ነገር ስለማይኖር በየደረጃው የሚገኝ አስፈፃሚ ህዝብን አክብሮ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱ አይቀሬ ይሆናል። ያኔም የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቀረፋቸው አይቀርም።

እናም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ሰዎችን ከመቀያየር ባሻገር ያለውን ቁልፍ ተግባር መገንዘብ ይገባል፤ የአሰራር ስርዓትን የመዘርጋት ተግባር። የአሰራር ስርዓት በሌለበት ቦታ አስፈፃሚው አካል በዘፈቀደና እርሱ በሚመቸው መልኩ ብቻ ተግባሩን ሊከውን ይችላል። ይህ ደግሞ ሙስናን ለመሳሰሉ ብልሹ አሰራሮች በር የሚከፍት ነው።

ከሁሉም በላይ ግን ተግባሩን የሚያወግዝ ህብረተሰብ መፈጠር ይኖርበታል። “ልስጥህና ፈፅምልኝ” የሚል ህብረተሰብ ካለ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ውጤት ሊመጣ አይችልም። እናም በህብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።

ህብረተሰቡም በተገልጋይነቱ ብቻ ሳይሆን የመንገስት ሹመኛ ወንበር ላይ የተቀመጠው እርሱን ለማገልገል መሆኑን ተገንዝቦ መብትና ግዴታውን ማስፈፀም ይኖርበታል። ይህን መሰሉ አሰራር የመልካም አስተዳደር ችግሮች እልባት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy