Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመንግስትና የህዝብን ገንዘብ በማሳጣት በተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

0 741

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመንግስትና የህዘብ ገንዝብን በማሳጣት ወንጀል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሰልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልን ጨምሮ 14 የተያዙና ያልተያዙ ግለሰቦች ላይ በሁለት መዝገብ ክስ ተመስርቷል።

በሌላ በኩል የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ 10 የስራ ሃላፊዎችና አንድ ስራ ተቋራጭ ላይ ከፍተኛ የብር ብክነት በማድረስ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት ነው ክሱ የቀረበው።

በቀዳሚነት በሶስት ክስ የተከሰሱት የኢትዮጵያ የመንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል የምህድስና እና ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳሪክተር አብዶ መሃመድ ጨምሮ የተያዙና ያልተያዙ 11 ግለሰቦች ናቸው።

በዚህ መዝገብ በአንደኛው ክስ በ1ኛ 2ኛ ከ4ኛ እስከ 10ኛ ባሉ ተከሳሾች ላይ ብቻ ክስ ቀርቧል።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው 1ኛ የባልስልጣኑ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል፣ 2ኛ የምህድስና እና ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዶ መሃመድ፣ 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት የባለስልጣኑ የሰው ሃይል እና የፋይናንስ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገላሶ ቦሬ ከሌሎች ካልተያዙ ግለሶቦች ጋር ተመሳጥረዋል።

ከባለስልጣኑ የግንባታ ውል አፈጻጸም ዲቭዢን ሃላፊዎች ከነበሩት 9ኛና 10ኛ ተከሳሾች፣ የሃረር ጂጂጋ የመንገድ ፕሮጀክት አማከሪ ከነበረው ከ”ራውተን ኢንተርናሽናል አማካሪ ድርጅት” ሰራተኛ ከነበረው 6ኛ ተከሳሽ፣ “የፓን አፍሪካ አማካሪ ድርጅት” ሰራተኛ ከሆኑት 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች እንዲሁም 5ኛ ተከሳሽ ከሆኑት “የሁናን ሁንዳ የመንገድ ድልድይ ስራ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ” በግል ማናጀር ሆነው ሲሰሩ ከነበሩት ሚስተር ያንግ ሬንኋ ጋር በጥቅም መመሳጠራቸው በክሱ ተመላከቷል።

በ5ኛ ተከሳሽ ድርጅት እና በባለስልጣኑ መካከል ለሃርር-ጂጂጋ የመንገድ ግንባታ ስራ 20 ሚሊየን 192 ሺህ 409 ብር የተመደበለት ነበር።

ሆኖም በተደረገ የለውጥ ክለሳ ስራ ወደ 26 ሚሊየን 013 ሺህ 534 ብር የተጨመረ ሆኖ እያለ በፈረጆቹ ከ2008 እስከ 2012 ባሉት ጊዜያት በተደረጉ ተከታታይ ክፍያዎች ከተለወጠው የውል ዋጋ በላይ 32 ሚሊየን 111 ሺህ ብር በላይ ያለአግባብ በመጨመር ባጠቃላይ 58 ሚሊየን ብር በላይ መከፈሉ በክሱ ተጠቅሷል።

አቃቤ ህግ በዚህ ክስ ላይ በዋናነት በተከናወነ የኦዲተር የክዋኔ ሪፖርት ገንዘቡ ከውል ውጪ ያለአግባብ መከፈሉ እየታወቀ ያለአግባብ የተከፈለው ተጨማሪ ገንዘብ መመለስ ሲገባው፥ ባለመመለሱ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አብራርቷል።

በዚህም በሁሉም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በ2ኛ ክስ ደግሞ 1ኛ 2ኛ 5ኛ እና 11ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ ክስ ቀርቧል።

በዚህም ክስ ላይ በፈረንጆቹ ታህሳስ 16 ቀን በ2005 ከሃረር-ጂጂጋ የመንገድ ግንባታ ስራ ሲሰራ የአካባቢ የሃይድሮሎጂና የዲዛይን ጥናት ሳይደረግ ከጂጂጋ ከተማ ማስተር ፕላን ጋር የማጣጣም፣ ድልድዮችን የማከታት፣ የብረት መካላከያ የማከታተት ስራዎች ሳይሰሩ ከ5ኛ ተከሳሽ ከሁናን ሁንዳ የመንገድ ድልድይ ስራ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ቻይናዊው ሚስተር ያንግ ሬንኋ በብር 346 ሚሊየን 262 ሺህ 115 ብር ውል እንዲዋዋል መደረጉ ተገልጿል።

ከዚያ በኋላ 2ኛ ተከሳሽ የለውጥ ውል ትዛዝ በመስጠት ከ206 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ እንዲከፈልና ባጠቃላይ ለስራው ማጠናቀቂያ 720 ሚሊየን 292 ሺህ ብር በላይ ያለአግባብ በመክፈል፥ በለውጥ ስራ ምክንያት በጊዜ መራዘም ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የመንግስት እና የህዝብ ገንዘብ የሚጎዳ ተግባር መፈጸማቸው ነው በክሱ የተጠቀሰው።

በ3ኛ ክስ ደግሞ 3ኛ እና 11ኛ የባለስልጣኑ የስራ ሃላፊ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን፥ አቃቤ ህግ በፈረንጆቹ በ2007 ከጎሬ-ጋምቤላ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት 3ኛ ተከሳሽ በቀለ ኑጉሴ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት አጢነው መስራት እና ባለስልጣኑ የገንዘብ ብክነት መካለከል እንዳልቻሉ ገልጿል።

ይኸውም የመንገዱ ግንባታ ሲከናወን ለካምፕና ለኳሪ ሶርስ ቦታ ለተቃራጩ ከ16 ወር በላይ አሳልፈው በማስረከባቸው ባለስልጣኑ ከ64 ሚሊየን 492 ሺህ ብር በላይ ካሳ ኮንሶ ሎዴትድ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ያለአግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸው ተብሯርቷል።

በሁለተኛ ክስ ደግሞ የባለስልጣኑ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ዛይድ ወልደ ወልደገብርኤል እና በባለስልጣኑ ሰራተኞች በአቶ ገብረአናንያ ጻዲቅ፣ በአቶ አሰፋ ባራኪ እና በአቶ ዘላለም አድማሱ ላይ ነው ክስ የቀረበው።

የአቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ ለ”ኖክ ኢትዮጵያ” ለመንገድ ጥገና የሚውል አስፓልት በውል ስምምነት ከተዋዋለ በኋላ በፈረንጆቹ ታህሳስ 24 ቀን 2004 “mc 3000” የተባለ የአስፓልት አይነት ከተቀመጠው ስታንዳርድ ውጪ መሆኑን በላብራቶሪ መረጋገጡን እያወቁ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዳቸው ተብሯርቷል።

በዚህም በተሰራው ደረጃውን ያልጠበቀ ስራ ከ1997 እስከ 1999 አስፓልቱ ስራ እንዲውል በተደረገባቸው መልካሳ፣ ሶደሬ፣ በደሌ፣ መቱ፣ ሻሸመኔ፣ አላባ፣ ሃዋሳ ሃገረማርያም፣ ደጀን፣ ደብረማርቆስ፣ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት ላይ የመሰንጠቅ፣ ወጣ ገባ የመሆን፣ ጉድጓድ የመፍጠር ባለጠቃላይ ደረጃውን የጠበቀ አለመሆኑንነሰ ብልሽት የታየበት መሆኑን እየታወቀ 62 ሚሊየን 382 ሺህ ብር በላይ ጉዳት መድረሱ በክሱ ተማላክቷል።

በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት በስልጣን አለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ባጠቃላይ ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል ዋስትና የማያሰጥ መሆኑን የገለፀው ችሎቱ፥ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ እና በቅጣት በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ለማቅረብ ለጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።

በሌላ በኩል ችሎቱ በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በሁለት መዝገብ የፋብሪካው የቀድሞ ዋና ስራ አስኪያጅ በነበሩት አቶ ፈለቀ ታደሰ እና የፋብሪካው የእርሻ ኦፕሬሸን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በጋሻውን ጨምሮ በአምስት የፋብሪካው የተለያዩ ዘርፍ የስራ ሃላፊዎች ላይ ላይ ክስ ቀርቧል።

የአቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉ ተከሳሾች ከ2005 እስከ 2006 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ለ”ባቱ ኮንስትራክሽን አክሲዮን ማህበር” ከ300 እስከ 400 ሄክታር የሚሆን መሬት ድልዳሎ ስራ በሚፈለገው ጥራት ሳይሰራ ርክክብ እንዲፈጸም እና በፋብሪካው ማሽነሪዎች እና ሰራተኞች በድጋሚ እንዲሰራ ትዛዝ መስጠታቸው ተጠቅሷል።

በ2ኛ ክስ በ5ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ተከሳሹ የቀድሞ የፋብሪካው ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ ተስፋዬ በነሃሴ እና በየካቲት 2004 ዓ.ም ለድልዳሎ ስራ በሚል ያለ አግባብ በሁለት ክፍያ ከ28 ሚለየን ብር በላይ እንዲከፈል ማድረጋቸው በክሱ ተመላክቷል።

በሶስተኛ ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ በቀረበ ክስ ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ለባቱ ኮንስትራክሽን የመሬት ድልዳሎ ስራ ተጨማሪ ወጪ በፋብሪካው ማሽነሪ እንዲሰራ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በ4ኛ ክስም በ3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ ለባቱ ኮንስትራክሽን ላልተሰራ የመሬት ድልዳሎ ስራ 225 ሺህ 832 ሄክታር እንደተሰራ በማስመሰል ባጠቃላይ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ እንዲከፈል ማድረጋቸውን አቃቤ ህግ አብራርቷል።

በሁለተኛ በመዝገብ ደግሞ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የቀድሞ ስራ አስኪያጅ አበበ ተስፋዬን ጨምሮ 4 የፋብሪካው የስራ ሃላፊዎች ላይ እና በ”የማነ ግርማይ የስራ ተቋራጭዕ ላይ ነው ክስ የቀረበው።

በዚህም ክስ ላይ አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ ከ2003 እስከ 2005 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት 31 ሚሊየን 856 ሺህ ብር ግዥ የተፈፀመበት የፋብሪካው ሲሚንቶ ርክክብ ሳይደረግና ፋብሪካው ከልማት ባንክ ብድር ያገኘና ወለድ የሚከፍልበት መሆኑን እያወቁ ከ31 ሚሊን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአርማታ ብረት ግዥ በመፈፀም ለ”ኦአይኤ” ስራ ተቋራጭ እና ለ5ኛ ተከሳሽ የማነ ግርማይ በመስጠት ፋበሪካው ከ4 ሚሊየን 265 ሺህ ብር በላይ ወለድ ለባንኩ እንዲከፍል ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።

ባጠቃላይ በልዩ ወንጀል ተካፋይ የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን፥ የዋስትና ይፈቀድልን ጥያቄያቸውን ውድቅ ያደረገው ችሎቱ ሶስተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ተስፋይ ድምፁ ተላን በ10 ሺህ ብር ዋስ ፈቅዷል።

በሌላ በኩል ዛሬ ማምሻውን ችሎቱ በስድስት በሙስና ንብረታቸው የታገዱ የግል ኩባንያዎችን የንብረት ማስተዳደርና የሰራተኛ ደሞዝን በሚመለከት በፌዴራል ፖሊስና በባለንብረቶች ጠበቆች በኩል የቃል ክርክር ጀምሯል።

ችሎቱ የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን እና የኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ላይ ክርክር ያደረገ ሲሆን፥ በየማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን የቃል ክርክር ላይ በማቆም ለመስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy