Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላማችንና የመረጋጋታችን እሴቶች

0 335

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላማችንና የመረጋጋታችን እሴቶች

                                                         ዘአማን በላይ

የኢትዮጵያ ህዝብ በአብሮነት የዘመናት ታሪኩ የተጋራቸው በርካታ እሴቶች አሉት። መቻቻል፣ መፈቃቀድና መተሳሰብ ከእነዚህ እሴቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። እሴቶቹ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዲሁም ሰላምና መረጋጋቷን ጠብቃ እንድትቀጥል ያደረጓት ናቸው። በመሆኑም እነዚህ አሴቶች ሳይበረዙ እንዲቀጥሉ ማድረግ ያስፈልጋል።

በተለይም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ከወሰን ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ችግሮች አንዳንዶቹ መፈታታቸውን፣ ቀሪዎቹም እየተፈቱ ነው። ከዚህ አኳያ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፤ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች በመፍታት ረገድ አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል።

በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውና የሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት በህገ መንግስቱ መሰረት በክልሎቹና በፌዴራል መንግስቱ አማካኝነት እልባት እየተሰጠው ነው።

ምንም እንኳን ስርዓቱ ከተመሠረተ ወዲህ በተለያዩ ወቅቶች በተወሰኑ አካባቢዎች በጎሳዎች መካከልና በአንዳንድ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች መኖራቸው አይካድም። እነዚህ ግጭቶች ፌዴራል አወቃቀሩ የፈጠራቸው አልነበሩም። በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ግጭት መኖሩ ነባራዊ ሃቅ ነው።

ከእኛ ሀገር አንፃር የሚከሰቱት ግጭቶች ግን አንዳንዶቹ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ የጎሣ ግጭቶች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከልምድ ጉድለት፣ ከመልካም አስተዳደር እጦትና ይህንን ተንተርሰው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ጥቂት ግለሰቦች የሚያባብሷቸው ወይም የሚቀሰቅሷቸው ሁከቶች ናቸው።

ዛሬ ላይ እነዚህ ግጭቶች በሂደት እየቀነሱ መጥተዋል። ፌዴራል ሥርዓቱ ከተመሠረተ ጀምሮ ለተከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ መንስኤዎች ካለፉት ሥርዓቶች የተወረሱ ችግሮች በመሆናቸው፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ በየደረጃው እየተወሰዱ በመጡ መፍትሄዎች አማካኝነት ሳንካ የመሆናቸው ዕድል እየተመናመነ ነው ማለት ይቻላል።

ርግጥ የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት የግጭቶች ምክንያት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲጎለብትና እንዲያብብ ላለፉት 26 ዓመታት በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ ተግባራቶችን ሲያከናውን የነበረና በዚህም አበረታች ውጤት ያመጣ በመሆኑ ነው።

ያም ሆኖ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ እውን በመሆን ላይ የሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን የሚፃረሩ ተግባራትን ጠንክሮ ማስወገድ ይገባል። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሀገራችን ህዝቦች እሴት እየሆነ ነው ማለት ይቻላል። ይህ እሴት የሀገራችንን አንድነት በማጠንከር ኢትዩጵያዊነት እንዲያብብ እያደረገ መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ርግጥ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ማንነት ተደፍቆ ሊመጣ አይችልም። ተከብሮ እንጂ። ባለፉት 26 ዓመታትም ሁሉም ማህበረሰብ በራሱ ቋንቋ የመናገር መብቱ የተጠበቀለት በዚሁ ፅንሰ ሃሳብ መነሻነት ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል። ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ስለሆነ ነው።

እንደሚታወቀው በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ እውን እየሆነ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ከትምክህትና ከጠባብ ኃይሎች ጋር ለሚደረግ ትግል ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው። ይህ በአዲሲቷ ኢትዮ የራስን ማንነት እንደሚያከብር ሁሉ ሌሎችም በተመሳሳይ አሉ ብሎ የመቀበል ጉዳይ በመሆኑ መተሳሰብንና የጋራ ልማትን ያረጋግጣል።

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው። በመሆኑም ጽንሰ ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎች እና ክልሎች ምንም ዓይነት ግጭት አይከሰትም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው።

ታዲያ ይህን ይበልጥ ለማስቀጠል አልፎ አልፎ በተለያዩ ስፍራዎች የሚስተዋሉትን የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦች በጋራ መዋጋትና የውጭ ፅንፈኞችንም አደብ ማስገዛት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

እርግጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር ችሏል። በመሆኑም ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ እሴት ነው። ዛሬም የትምክትና የጠባብነት ፈተናዎች በሀገራችን ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው ግን አይቀርም። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይህ እሴት ይበልጥ እንዲያብብ ምቹ ሁኔታዎችን ስለፈጠረ ነው።

በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሴት ውስጥ የራስ ማንነትን ማወቅ፣ የሌሎችን ማንነት ማወቅ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና አካባቢን ማልማት ወሳኝ ጉዳዩች ናቸው። ማንነትን ከማወቅ አኳያ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን መለየት ያስፈልጋል። የጋራ የሆኑ ባህሪያትን መለየትንም እንዲሁ። የሌሎችን ማንነት በማወቅ ረገድም፣ ከሌሎች ጋር ያለውን የጋራ ፍላጎትና ጥቅም መለየት ያስፈልጋል።

እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀምን ያካትታል። አካባቢን ከማልማት አኳያም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ከባቢን በተገቢው መንገድ ለልማት የማዋል ሁኔታን የሚያካትት ነው።

ሀገሪቱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ለዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዕውን መሆንና ማበብ የታገለ ድርጅትና እንዲሁም እሳቤውን በመርህ በፅናት በማስፈፀም ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው። ምንም እንኳን በርካታ ህዝቦች ያሉት እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይገባልም።

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና ለማረጋገጥና ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር፣ የሌላውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ሲከብር በአንፃሩ ደግሞ  መከበርን ያተርፋል።

ርግጥ ያለፈው ታሪክ አንድን ህዝብ የራሱ ዘር ከሌላው ዘር በከፋ መልኩ በድሎት ሊሆን ይችላል። ይህ አስተሳሰብ ግን ገዥዎችን እንጂ ህዝብን የሚመለከት አይደለም። ሊሆንም አይችልም። አንድ ህዝብ ሌላውን የሚበድልበት ምንም ዓይነት መነሻ ሊኖረው ስለማይችል ነው።

እንደሚታወቀው የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ያለፉትን የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማንሳት አንድን ህዝብ ለመኮነን ይሞክራሉ። ሆን ብለውም አንዱን ከሌላው ጋር ለማጋጨት እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበታል። ይህ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ፍፁም ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ጋር የሚሄድ አይደለም።

እንዲህ ዓይነቶቹ ከህዝቦች ፍላጎት ጋር በተፃራሪነት የሚከናወኑ ተግባሮች በገነገኑ ቁጥር ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ያቀጭጫሉ። የሰላምና መረጋጋት እሴቶቻችንንም ሊሸረሽሯቸው ይችላሉ። እናም የሰላምና መረጋጋታችንን እሴቶች በመጠበቅ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ማጎልበት ይገባል እላለሁ።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy