Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላማችንና የብልጽግናችን ዋስትና

0 317

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላማችንና የብልጽግናችን ዋስትና

ዳዊት ምትኩ

አገራችን በመከተል ላይ የምትገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት የሰላማችንና የብልጽግናችን አስተማማኝ ዋስትና ነው። በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ በሰላም፣ በልማትና በብልጽግና ረገድ የተጓዘችበትን ርቀት የሥርዓቱን ጥንካሬ የሚያመላክት መሆኑ አታበይም። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሥርዓቱ በፈጠረው አመቺ ሁኔታ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ተጠቃሚ ሆነዋል። ያለፉት 10 ዓመታት ውጤቶች መጪው ጊዜ የአገራችን ከፍታ እውን እንዲሆን መሠረት የጣሉ ናቸው።

በአገራችን እየተገነባ ያለው ይህ ሥርዓት አስተማማኝ ሰላም ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ እንዲሁም ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በነፃነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ ችሏል። ይህም የዚህ ፅሑፍ ማጠንጠኛ የሆነውን ሰላም በመመለስ ለትግላቸው እውቅና በመስጠት ጥያዌዎቻቸውን መመለስ ችለዋል።

በአገራችን ዕውን እየሆነ ያለው ስርዓት ሰላምን ማረጋገጥ በመቻሉ፤ በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል።

ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ፌዴራሊዝም የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም እንዲችሉ አድርጓቸዋል።  

እናም ስርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት ችሏል። ይህ ሲሆን ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ችግሮች መፈራቸው ነባራዊ ነው። ይሁን እንጂ ሥርዓቱ የተፈጠሩ ችግሮችን በወቅቱ እልባት ሰጥቷቸዋል።

ያም ሆኖ ህዝቡ በሰላሙ ላይ ስለማይደራደር ለግጭት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳር እንዳይኖር አድርጓል። ምንም እንኳን በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው የሚነቀሳቀሱ ሆነዋል።

በዚህም በመልካም አስተዳደርና በሙስና ህዝቡን ሲያማርሩት እንደነበር የሚታወቅ ነው። እነዚህ ሃይሎች የፈጠሩት ምሬት ከትምክህትና ከጥበት አራማጆች አጀንዳ ጋር ተዳምሮ የሀገራችንን ሰላም ማወኩ የቅርብ ጊዜ ትውሰታችን ነው።

እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ። የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሔር ብቻ ልዕለ ኃያል ነው ብሎ ያምናል። እንዲሁም ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየነው ብሎ ከማሰብ በተጨማሪ ‘ሁሌም ለመግዛት የተፈጠርኩ ነኝ’ በማለት የሚያምን ነው።

በአንፃሩም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራ እና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ፣ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ የመቁጠር አባዜ የተጠናወተው ነው። የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም የመቀበል ተፈጥሮ የለውም። እናም በተቻለው መጠን ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን ቀዳዳዎችን በሙሉ ሲጠቀምባቸው ተመልክተነዋል።

የትምክህት ሃይሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ ከህዝቦች አንድነት ይልቅ የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው።

የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰው ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖርን የእሬት ያህል ቆጥሮ የሚጎመዝዘው ነው። ኋላ ቀርነት መገለጫ ነው ሊባልም ይችላል። እነዚህ ሃይሎች ቢኖሩም አገራችን የምትከተለው ሥርዓት በየጊዜው የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የቻለ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የበለጸጉት  ሀገሮች  ለመልማት  ባደረጉት  እንቅስቃሴ  በዓለማችን  ሥነ ምህዳር  ላይ በፈጠሩት  ቀውስ  ሳቢያ  በሚፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት የተለያዩ አህጉሮች  በድርቅ  አደጋ ይጠቃሉ፡፡  ከእነዚህም ውስጥ  እንደ አፍሪካ  ያሉ ያላደጉ አህጉሮች ባልፈጠሩት ችግር ግንባር ቀደም ሰለባ ይሆናሉ፡፡  በተለይም  የምስራቅ አፍሪካ  ሀገሮች  የችግሩ  ተጠቂዎች  ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በዚህ የበለጸጉት ሀገሮች  በፈጠሩት የአየር መዛባት  ምክንያት  በድርቅ  የምትጠቃው  ሀገራችን፤ ከድህነት ገና ሙሉ ለሙሉ ያልተላቀቀች  በመሆና የአየር ንብረቱ  የተለየ ክስተት  ሲያሳይ  በአንዳንዱ ዝናብ  አጠር  አካባቢዎች የምግብ  እጥረት  መከሰቱ የግድ ነው፡፡

ምንም  እንኳን  ድርቅና  ረሃብ  በአመዛኙ  በተፈጥሮ  የአየር  መዛባት  ምክንያት  የሚፈጠሩ  ቢሆኑም፤ ድርቅ በዝናብ  እጥረት   ሳቢያ  የሚፈጠርና  ጊዜያዊ  የምርትና  ምርታማነት  መስተጓጎልን  ሊያስከትል  የሚችል  ችግር ነው፡፡  ረሃብ ግን በተከታታይ  በሚፈጠር ድርቅ ሳቢያ በሚከሰት  የምግብ  እጥረት  ህብረተሰቡ  የሚላስና  የሚቀመስ  ሳይኖረው  በመቅረቱ  ለሞት  የሚያበቃ  ችግር  መሆኑ  ይታወቃል፡፡

ከሀገራችን ተጨባጭ  ሁኔታ  አኳያ  ድርቅ  እንጂ፤  ረሃብ  አለመኖሩ  ከዚህ አንፃር ከሚያቀነቅኑ ወገኖች የተሰወረ ጉዳይ  አይመስለኝም፡፡ ይሁንና ጉዳዩን የፖለቲካ ማራገቢያ  ለማድረግ  ሲሉ ድርቁን ሆን ብለው ወደ “ረሃብነት” ሲቀይሩት ተስተውሏል፡፡

ሐቁ ይህ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚከሰተው ድርቅ የተፈጠረው ድርቅ እንጂ ረሃብ አይደለም፡፡ በሀገሪቱ በረሃብ ሳቢያ የሞተም ሆነ የሚሞት አንድም ሰው የለም፡፡ ምክንያቱም መንግስት ረሃብ እንዳይከሰት ከፍተኛ ስራዎችን በማከናወኑ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት  የመንግስት ትኩረት ምንም ዓይነት የአየር ንብረት መዛባትና ድርቅ ቢያጋጥምም፤ ህዝባችን የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ ቆይቷል፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን ድርቅ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረግ  እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ  በሆነ አኳሃን  ጥቅም ላይ  እንዲውል አድርጓል፡፡ እያረረገም ነው፡፡

በተደረገው ድህነትን የመቅረፍ ጥረት በዚህም ምክንያት ድርቁ ወደ ረሃብነት እንዳይሸጋገር የሚያደርጉ ተግባራትን  አከናውኗል፡፡ ይህም  አንድም  ሰው እንዳይሞት ያበረከተው አስተዋጽኦ  ከፍተኛ  ከመሆኑም  በላይ፤  መንግስት  ለዜጎቹ  ያለውን ከፍተኛ  የኃላፊነት ስሜት  የሚያመላክት ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው ሥርዓት ባለፉት 10 ዓመታት ወደ ልማት ያመራን ሲሆን የብልጽግናችንም ዋስትና እየሆነ ነው፡፡ በመጪው ጊዜያትም በዚህ ሥርዓት እስከተመራን ድረስ በቀጣዩቹ ዓመታት አገራችን ከፍታው ላይ የማትወጣበት ምንም ዓይነት ምክንያት የሚኖር አይስለኝም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy