Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብአዴን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተጠናቀቀ

0 403

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተጠናቋል።

“እየሠራን እንታደሣለን፤ እየታደሥን እንሠራለን” በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 15 እስከ 18/2010 ዓ.ም የጥልቅ ተሃድሶ የአንድ ዓመት አፈፃፀምን የገመገመው ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ በባህር ዳር ሲካሄድ ቆይቷል።

በኮንፈረንሱ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል እና የህዝብ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ የታዩ ውጤቶች መገምገማቸውን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረው የርዕየተ-ዓለማዊና ፖለቲካዊ መዳከም፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እንዲሁም በስልጣን ላይ ያለ የአመለካከት መዛባት ያስከተላቸው ችግሮች የህዝቡን ቅሬታ ማባባሳቸው በግምገማው ታይቷል።

በአንዳንድ የሀገሪቱና የክልሉ አካባቢዎች ግጭት በመከሰቱ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አስከትሎ ማለፉ ነው በኮንፈረንሱ የተመለከተው።

በመሆኑም ብአዴን ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና የገጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከነሐሴ 2ዐዐ8 ዓ.ም ጀምሮ በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረክ ውስጥ እንደሚገኝ በመድረኩ ተነስቷል።

የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴው ባለፈው አንድ ዓመት ስርዓቱን ለአደጋ የጣሉትን መሰረታዊ ችግሮች በመለየት የመፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድ እና አፋጣኝ ለውጦች እንዲመዘገቡ ማድረጉ ተነግሯል።

ኮንፈረንሱ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው የሚገኝበትን ደረጃ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ተወያይቶ መግባባት መፍጠርን ዓላማው በማድረግ ተካሂዷል ነው የተባለው።

ብዝሃነትን በማስተናገድና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመገንባት በተደረገው ርብርብ ሁሉም ማንነቶች ዕውቅና ያገኙበት እና አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ርብርብ መደረጉ ተገምግሟል።

ሆኖም የፌደራል ሥርዓቱን እና የህዝቦችን አንድነት እንዲሁም ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር አሴትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች አሁንም መኖራቸው ተረጋግጧል ነው የተባለው።

ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማረጋገጥ አኳያ የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ሰብል ራስን በመቻል፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመዋቅራዊ ሽግግር መሠረቶች መጣላቸው እንደተገመገመ ተነስቷል።

የፀረ-ኪራይ ሠብሳቢነት ትግል በመጀመር እርምጃም እየተወሰዱ መሆኑን ያነሳው መግለጫው፥ የአመራር ሽግሽግ እና ሥምሪት መካሄዱን፣ ከፀረ-ዴሞክራሲና መርህ-አልባ ግንኙነት አኳያም የድርጅቱን ድክመቶች ማረም መጀመሩ ነው የተነሳው።

የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄን ምላሽ ለመስጠት ህብረተሰቡን ባሳተፈ፣ ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ አግባብ ህዝበ-ውሣኔ ውይይት ተደርጎበታል።

በአማራ ጠገዴና በትግራይ ፀግዴ ወረዳዎች መካከል የነበረውን የወሰን ጥያቄ ህዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ እልባት መሰጠቱን በጥንካሬ ገምግሟል።

በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ የማስገባት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተነገረ ሲሆን፥ ተሳታፊዎች ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ኮንፍረንሱን አጠናቀዋል።

 

 

የመግለጫውን ሙሉ ቃል ያንብቡ

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የአቋም መግለጫ

እኛ የብአዴን/ኢህአዴግ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች “እየሠራን እንታደሣለን፤ እየታደሥን እንሠራለን” በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 15-18/2ዐ1ዐ ዓ.ም በክልላችን ርዕሰ መዲና በባህር ዳር ከተማ የጥልቅ ተሃድሷችን የአንድ ዓመት አፈፃፀምን የገመገመ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ አካሂደናል፡፡

የጥልቅ ተሃድሶው አካል የሆነው ድርጅታዊ ኮንፈረንሳችን ቀደም ብሎ የተካሄዱትን የኢህአዴግ ምክር ቤትና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የጥልቅ ተሃድሶ የአንድ ዓመት አፈፃፀም ግምገማና መሠረታዊ አቅጣጫዎች መነሻ በማድረግ የተካሄደ ነው፡፡

ድርጅታችን ብአዴን/ኢህአዴግ የዛሬ 16 ዓመት ባካሄደው ተሃድሶ ያጠራውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መሥመራችንን ይዘን በልማት፣ በዴሞክራሲና እና በመልካም አስተዳደር ተግባሮቻችን ላይ የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ በድርጅታችን ውስጥ የለኮስነው ትግል የምልዓተ ህዝቡን ንቅናቄ ፈጥሮ በአገራችን በሁሉም መስክ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በሂደቱም በየደረጃው የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ድህነትን ለማሸነፍ በተደረገው ጠንካራ ርብርብ በሁሉም መስኮች ለህዳሴው ጉዞ መሠረት የሚሆኑ አንፀባራቂ ድሎችን አስመዝግበናል፡፡

የተመዘገቡት ስኬቶችም አገራችንን ከድህነት የማውጣትና የበለፀገ ህብረተሰብ የመፍጠር ህልማችን እውን እንደሚሆን እና መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን በተግባር አረጋግጠናል፡፡

የተመዘገቡት ድሎችም እጅግ አንፀባራቂ በመሆናቸው በማንኛውም ሃይልና በየትኛውም ድክመት ሊደፈቁ እንደማይችሉ ተገንዝበናል፡፡

ሆኖም ግን በመጀመሪያው ተሃድሷችን ባስቀመጥናቸው አቅጣጫዎችና በተግባባንበት ልክ የድርጅትንና የመንግስትን የመፈፀም አቅም በቀጣይነት በማጠናከር አዳጊ የህብረተሰብ ፍላጐትን የሚያረካ ለውጥን በማስቀጠል፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን በሚፈለገው ደረጃ በማስፈን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ያለምህረት በመታገል እና የልማታዊነት የበላይነትን በማረጋገጥ፣ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄዎችን ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት እና በአጠቃላይ የህዝባችንን እርካታ በማረጋገጥ በኩል በነበሩብን ድክመቶች ምክንያት ህዝባችንን ወደ ቅሬታ ያስገቡ ሁኔታዎች ተፈጥረው እንደነበረ ይታወሳል፡፡

ውሎ አድሮም በድርጅታችን ውስጥ የተፈጠረው የርዕየተ-ዓለማዊና ፖለቲካዊ መዳከም፤ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እንዲሁም በስልጣን ላይ ያለን አመለካከት መዛባት ያስከተላቸው ችግሮች እየተደማመሩ በመምጣታቸው የህዝቡ ቅሬታ ጎልብቶ በአንዳንድ የአገራችንና የክልላችን አካባቢዎች ወደ ግጭት በማምራቱ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አስከትሎ አልፏል፡፡

የውስጥ ችግሮቻችንን እና ድክመቶቻችንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የለውጥ አደናቃፊ ሃይሎች የህዝቡን ቅሬታ ወደ አልሆነ አቅጣጫ በመምራትና ሁኔታውን በማባባስ የክልላችንና የአገራችን ሠላማዊ ሁኔታ እንዲታወክ በማድረጋቸው ያለፈውን ዓመት አብዛኛውን ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ለማለፍ ተገደናል፡፡

በመሆኑም አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና የገጠሙንን ችግሮች ለመቅረፍ ከነሐሴ 2ዐዐ8 ዓ.ም ጀምሮ በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረክ ውስጥ እንገኛለን፡፡

የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሰያችን ባለፈው አንድ ዓመት ስርዓታችንን ለአደጋ የጣሉትን መሰረታዊ ችግሮች በመለ የት የመፍትሄ እርምጃ እንድንወስድና አፋጣኝ ለውጦች እንድናስመዘግብ ዕድል ሰጥቶናል፡፡ ይህ ኮንፈረንስም ባለፉት ተከታታይ 3 ቀናት በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄያችን የሚገኝበትን ደረጃ እና ቀጣይ አቅጣጫዎቻችንን በተመለከተ በሰከነ መንፈስና በብስለት መወያየትና መግባባት መፍጠርን ዓላማው በማድረግ ተካሂዷል፡፡

በዚህ መነሻነት ለ4 ቀናት ባካሄድነው ኮንፈረንስ ባለፋት 26 የለውጥ ዓመታት በተለይም ባለፉት 16 ዓመታት የአገራችንን ህዳሴ እውን ሊያደርጉ የሚችሉ ጅምር ስኬቶች መመዝገባቸውን ገምግመናል፡፡

ታዳጊው ፌደራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ብዝሃነትን በማስተናገድና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመገንባት በተደረገው ርብርብ ሁሉም ማንነቶች ዕውቅና ያገኙበት እና የአገራችን ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በየደረጃው ባሉ የህዝብ ምክር ቤቶች የሚወከሉበትና የሚደመጡበት፣ የህዝቦች ሉዓላዊነት መገለጫ የሆነው ምርጫ በመድለ ፓርቲ ሥርዓት ማዕቀፍ እንዲፈፀም የተደረገበት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር እና አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ርብርብ የተደረገበት መሆኑን ገምግመናል፡፡

ሆኖም የፌደራል ሥርዓቱን እና የህዝቦችን አንድነት እንዲሁም ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር አሴትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ቀላል በማይባል ደረጃ አሁንም ያሉ መሆኑን በግምገማችን አረጋግጠናል፡፡

ድርጅታችን ብአዴን/ኢህአዴግ አንግቦት ከተነሳው ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማረጋገጥ አኳያ የኢኮኖሚያችን ዋልታ የሆነውን የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ሰብል ራሳችንን በመቻል፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመዋቅራዊ ሽግግር መነሻ የሚሆኑ መሠረቶች መጣላቸውን፣ ከተሞቻችን ወደ ተነቃቃ ዕድገት መግባት መጀመራቸውን፣ በመሠረተ ልማት ዘርፍም በመንገድ፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትና የባቡር ትራንስፖርት ዕድገት መመዝገቡን ገምግመናል፡፡

ይሁን እንጂ በመሠረተ ልማት ተደራሽነት እና ጥራት በኩል ህብረተሰቡን ያረካ አገልግሎት ማቅረብ ያልቻልን ከመሆኑም በላይ በተለይም የመብራት አገልግሎት ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ መሆኑን በጥልቀት ገምግመናል፡፡

ከማህበራዊ አገልግሎት አኳያ በትምህርትና በጤና ዘርፎች ፍትሃዊ ተደራሽነት በማረጋገጥ በኩል ሊደነቅ የሚችል ውጤት ያስመዘገብን መሆኑን የገመገምን ሲሆን አሁንም በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ ትኩረት ማድረግ የሚገባን መሆኑን በግምገማችን ተግባብተናል፡፡

በክልላችን የተመዘገቡት ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ምንጭ ደግሞ ድርጅታችን ብአዴን አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ ባህሪውን ጠብቆ ላለፋት 16 ዓመታት ልማታዊና ዴሞክሲያዊ መስመራችንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ብቃት ለመገንባት በመቻሉ፣ ጠንካራ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመፍጠር በመረባረቡ መሆኑን ገምግመናል፡፡

ይሁን እንጂ ድርጅታችን በሂደት በገጠሙት ጥንካሬውን የሚፈታተኑ የአስተሳሰብና የተግባር ችግሮች ምክንያት ወደ ጥልቅ ተሃድሶ መገባቱን በማስታወስ የአንድ ዓመት የጥልቅ ተሃድሶ ጉዟችንን በጥልቀት ገምግሟል፡፡

በግምገማውም ርዕዮተ- ዓላማዊና ፖለቲካዊ ግልፅነትን ከማሳደግ አኳያ በግምገማ የተለዩትን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ዝርዝር ግምገማዎችና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች በመካሄዳቸው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ልዕልናን የሚያሳድጉ የአመለካከትና የተግባር አንድነትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው፤ የኪራይ ሠብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን ከመዋጋት አኳያ መላ አባሉንና ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የፀረ-ኪራይ ሠብሳቢነት ትግል መጀመሩንና እርምጃም እየተወሠደ መሆኑን፤ ይህንንም መነሻ በማድረግ የአመራር ሽግሽግ እና ሥምሪት መካሄዱን፣ ከፀረ-ዴሞክራሲና መርህ-አልባ ግንኙነት አኳያም የድርጅታችን ድክመቶች በውስጠ-ድርጅት ትግል ማረም መጀመሩን በዚህም በአባላትና በህዝቡ ውስጥ ሊኖረን የሚገባው ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን፣ ህዝብን ያማረሩ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ተግባራት በዝርዝር እየተገመገሙበየደረጃው እርምጃ እየተወሠደ መሆኑን፣ የህዝቦችን አንድነት እና አብሮነት የሚያሻክሩ የትምክህተኝነት፣ ጠባብነት እና የኃይማኖት አክራሪነት አመለካከቶችና ተግባራት ሰፊ ትግል የተደረገባቸው እና በሚያስከትሉት አደጋ ላይም መግባባት የተደረሠ መሆኑን፣ የህዝብን አንገብጋቢ ችግሮች ለይቶ ከመፍታት አኳያ መዘናጋት ባለበት ጊዜ ሁሉ ህዝባዊ ቁጣና ጥፋት እንደሚያስከትል በመገንዘብ ጉዳዩን በዝርዝር ገምግሞ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ፣ የመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በመንግስት፣ በግልና በውጪ ባለሃብቶች ተሳትፎ ወደ ሥራ እንዲገቡ የማግባባት ሥራ የተሠራ መሆኑን፣ የሥራ አጥነትን ችግር ከመቅረፍ አኳያ ልዩ ርብርብ በመደረጉ በርካታ ሠራ አጥ ወገኖች ወደ ሥራ መሠማራታቸውን፣ የመንግስትን አስተዳደራዊ አወቃቀር ለህዝብ ተደራሽ ማድረግን ታሳቢ ባደረገ አኳኋን በአንዳንድ አካባቢዎች ሰፊ ሥራ የተሠራ መሆኑን፣ የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄን ምላሽ ለመስጠት ህብረተሰቡን ባሳተፈ፣ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ አግባብ ህዝበ-ውሣኔ የተካሄደ መሆኑን፣ በአማራ ጠገዴና በትግራይ ፀግዴ ወረዳዎች መካከል የነበረውን የወሰን ጥያቄ ህዝቡን ባሳተፈና በሠከነ ሁኔታ እልባት መሰጠቱን በጥንካሬ ገምግመናል፡፡

ይሁን እንጅ ከፖለቲካዊና ርዕዮተ-ዓላማዊ ሥራዎቻችን አኳያ በአመለካከት በተግባባንበት ልክ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በኩል ውሥንነት መኖሩን፣ የኪራይ-ሠብሳቢነት ትግል ከጅምር የዘለለ አለመሆኑን፣ ፀረ-ዴሞክራሲና መርህ አልባ ግንኙነትን ከሥረ-መሠረቱ የመቅረፍ ሥራም ተከታታይና የማያቋርጥ ትግል የሚጠይቅ መሆኑን፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያላሉ የትምክህት፣ የጠባብነት እና የኃይማኖት አክራሪነት አመለካከቶች ጠንካራ ትግል የሚጠይቁ መሆኑን፣ የህዝቡን አንገብጋቢ ችግሮች ከመፍታት አኳያ በአንድ በኩል የቆዩ እና የተከማመሩ ችግሮችን መፍታት፣ በሌላ በኩል አዳዲስ ፍላጐቶችን ማርካት እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናና ጥራት አኳያ አሁንም ህዝቡን የሚያማርሩ ችግሮች መኖራቸውን እና እነዚህን ችግሮች መፍታት ለነገ የማይባል መሆኑን በመገምገም በያዝነው ዓመት ጥልቅ የተሃድሶ እንቅስቃሴውን አጠናክረን በመቀጠል የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን ህልውናና የህዳሴ ጉዟችንን ስኬት ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1ኛ. እኛ የብአዴን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተሃድሶ መነሻችን ላይ እንደተቀመጠው ንቅናቄው የአንድ ወቅት ተግባር ሳይሆን ያለማቋረጥ የሚካሄድ ህብረተሰባዊ እንቅስቃሴ በመሆኑ የጀመርነውን የህዳሴ ጉዞ በማያቋርጥ ሁኔታ ለማስቀጠልና ለማጠናከር የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሷችንን አጠናክሮ ማስቀጠል የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ባለፈው አንድ ዓመት ያስገኘናቸውን ውጤቶች በማስጠበቅ ተሃድሶው ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ መላ የክልላችንን ህዝቦች በማሳተፍ እንረባረባለን፡፡
2ኛ. የጥልቅ ተሃድሶው መሪ የሆነው ድርጅታችን ብአዴን በውስጡ የለኮሰውን ንቅናቄና የውስጠ-ድርጅት ትግል በማጠናከር በሂደቱ የታዩ የአስተሳሰብ እና የተግባር ዝንፈቶችን ለማረምና ወቅቱ የሚጠይቀውን የአመራር ብቃት በመጎናፀፍ የህዳሴ ጉዟችንን በስኬት ለማስቀጠል ድርጅታዊ መርሆዎቻችንና እሴቶቻችን ከፍ አድርገን በማንገብ ትግላችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን፡፡

3ኛ. የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችንን የህዝብ አገልጋይነት ባህል በማሳደግና የመፈፀም አቅምን በማሻሻል ህዝባችንን ያማረሩ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን በቀጣይነት በመታገል ሁሉን አቀፍ እምርታዊ ለውጥ በማምጣት የህዝቡን እርካታ ለማረጋገጥ ቃል እንገባለን፡፡

4ኛ. የአማራ ክልል ህዝቦች ተጠቃሚነት ቀጣይነት የሚኖረው እና ወደ ላቀ ደረጃ የሚሸጋገረው የፌዴራል ሥርዓቱ ሲጠናከርና ዴሞክራሲያዊ እንድነታችንን የሚፈታተኑ ችግሮች ሲቀረፉ መሆኑን በማመን ከመላው የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም አጋርና እህት ድርጅቶቻችን ጋር በመተባበር ለህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ መጠናከር በተለመደው የድርጅታችን በህዝባዊ ወገነተኝነትና የዓላማ ፅናት መንፈስ እንሠራለን፡፡

5ኛ. የተጀመውን የ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቦች በሁሉም ዘርፍ ለማሳካት በመረባረብ ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዕውን በማድረግ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማፋጠን ያመለጡንን ዕድሎች በሚያካክስ ሁኔታ እንረባረባለን፡፡

6ኛ. በህዝብ አንገብጋቢ ችግርነት የለየናቸውን የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ችግሮች ለማቃለል፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የመሣሠሉትን ልዩ ትኩረት በመስጠት በመፍታት የህዝባችንን እርካታ ለማረጋገጥ ተግተን እንሠራለን፡፡

7ኛ. በ2ዐዐ8 ዓ.ም በክልላችንና በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ገጥሞን የነበረው የሰላም እጦት በሁሉም መስክ ጐድቶን ያለፈ ቢሆንም ሠላም ወዳዱ ህዝባችን፣ መንግስትና ድርጅታችን ባደረጉት ያለሰለሰ ጥረት ክልላችን ወደ ነበረበት ሠላማዊ ሁኔታ ተመልሷል፡፡ በመሆኑም ይህንኑ ሠላማዊ ሁኔታ አጠናክሮ በማስቀጠል የክልላችን ህዝቦች ያለምንም ሥጋት የሚኖሩበት፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተጠናክሮ የሚቀጥልበት እና በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን ያስቀመጥናቸው ግቦች ሙሉ በሙሉ የሚሳኩበት ይሆን ዘንድ ክልላዊ ሰላማችን ለማጠናከር እንረባረባለን፡፡
በመጨረሻም ያጋጠሙንን ፈተናዎች እንድንወጣና የጀመርነውን የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ ከጎናችን ሁናችሁ ለተረባረባችሁ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ የክልላችን አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ወጣቶች፣ ተማሪዎችና ምሁራን፣ የፀጥታ አካላት በአጠቃላይ ለመላው የክልላችን ብሎም የአገራችን ህዝቦች ያለንን ከፍተኛ አክብሮት እየገለፅን ጥልቅ ተሃድሷችን ባለፈው አንድ ዓመት ያስመዘገባቸው ውጤቶች ገና ጅምር እና ሰፊ ትግል የሚጠይቁ በመሆናቸው ትግላችን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በምናደረግው ርብርብ ከጐናችን በመሰለፍ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንደታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋላን፡፡

“እየሠራን እንታደሣለን፤ እየታደሥን እንሠራለን”
ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት!
መስከረም 18/2ዐ1ዐ ዓ.ም
ባህር ዳር

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy