Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ እንዳይደናቀፍ…

0 337

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ እንዳይደናቀፍ…

                                                   ዘአማን በላይ

ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ፌዴራሊዝምን አስመልክተው በአንድ ወቅት፤ ሀገር ማለት ተራራና ወንዝ ሳይሆን ህዝብ ነው በማለት የተናገሩት ንግግር ከማንም ህሊና ውስጥ የሚጠፋ አይደለም። ይህ አባባላቸው በጥልቀት ሲታይ እንደ የድንበር ማካለል ዓይነት ጉዳዩች ከአንድ ሀገራዊና ህዝባዊ መንፈስ መነሳት እንደሚኖርበት የሚገልፅ ይመስለኛል።

ርግጥ ርሳቸው እንዳሉት አንድ ተራራ ከሌላው በተለየ ሁኔታ ፍቅር የሚያሲዝበት ምክንያት የለም። አንድ ህዝብ ግን ከሌላው ህዝብ የተለየ ፍቅር ያሲዛል። ዋናው ጉዳይ በድንበር መለያየቱ ሳይሆን፤ ሁለት ህዝቦች በድንበር ሲካለሉ ዋናው ነገር የድንበር መካለሉ ጉዳይ የህዝቦቹን አንድነት የማያናጋ፣ ተቀላቅሎ የመኖር ዘይቤን የማይሸረሽርና መከባበርን በማያሳጣ መልኩ መሆን ይኖርበታል።

ሀገራችን አንድ የጋራ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ማህበረሰብ እንደምትገነባ በህገ መንግስቷ ላይ በግልዕ ደንግጋ ስታበቃ፤ የሀገራችን መሬትም ሆነ ሌላው የተፈጥሮ ሃብት ለጋራ ልማት የምንጠቀምበት እንጂ ልክ እንደ አፓርታይድ ስርዓት ደንብ ‘ከዚህ አካባቢ ባሻገር የእገሌ ብሔር ተወላጅ ዝር ማለት የለበትም’ ብለን የምናጥርበት መሆን አይገባውም። የሀገራችንን ፌዴራላዊ ስርዓት እውን ካደረገው ህገ መንግስታችን መርህ ጋር የሚጣረስ ነው።   

ከዚህ አኳያ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውና የሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት ከፌዴራሊዝም ፅንሰ-ሃሳብ ጋር የማይሄድ ከመሆኑም በላይ፤ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ጥላሸት የሚቀባው በመሆኑ በፍጥነት መታረም ያለበት ይመስለኛል።

ርግጥ ፌዴራል መንግስትና ሁለቱ ክልሎች ግጭቱ እንዳይስፋፋ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በግጭቱ ተዋናይ የነበሩ ግለሰቦችን ህግ ፊት ለማቅረብ እያደረጉት ያለው ጥረት አድናቆት የሚቸረው ቢሆንም፤ እንዲህ ዓይነቱ ሁለቱን ህዝቦች የማይወክል ተግባር የህዳሴ ጉዟችን እንዳይደናቀፍ ሲባልም ችግሩን ከመሰረቱ መቅረፍ ያስፈልጋል። ለዚህም ከሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ተጠቃሚ በመሆን ላይ የሚገኘው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ይህን መሰሉ ብቅ ጥልም እያለ የሚከሰት ችግርን በተገቢው ሁኔታ መፍታት ይገባል።

የዚህ ሀገር ህዳሴያዊ ዕድገት ማንም ተመኝቶት የሚያገኘው አይደለም። ዛሬ ምስጋና ለልማታዊው መንግስት ይግባውና በሁሉም ዘርፎች መጠነ ሰፊ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው። ዛሬ ሀገራችን የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተገቢው ሁኔታ አጠናቃ፤ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ለማምጣት የተለመችበትን ሁለተኛውን የዕድገት ትልም ከተያያዘች ወደ ሶስተኛው ዓመት ተሸጋግራለች።

ታዲያ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አያሌ ለውጦች ተመዝግበዋል። ምንም እንኳን የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት በኢኮኖሚው መስክ ሊፈጥረው የሚችለው እጅግ አነስተኛ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል የሚካድ ባይሆንም፤ ችግሩ ግን ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የፈጠረ አይደለም።

በተለይም ከምርት አኳያ የተፈጠረ ችግር ባለመኖሩ በያዝነው ዓመትም ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል። ታዲያ ይህ የሚሆነው ሁሉም የህበረተሰብ ክፍል እድገትን ሊቀለብስ የሚችል ተግባሮችን መኮነን ሲችል ነው። ለአንድ የጋራ ሀገራዊ ዓላማ ያለ ንትርክ መደሰለፍ ሲችልም ጭምር።

ባለፉት 26 ዓመታት በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት የሀገራችንን ኢኮኖሚ ስር ከሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ እንዲሁም የህዝቡን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማህበራዊ የልማት ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ተቀርፀው ስራ ላይ ውለዋል።

ውጤታቸው ስኬታማ እንደነበርም ከእነዚህ ዓመታት በፊት የነበረችውንና የዛሬዋን ኢትዮጵያ በማየት መመስከር የሚቻል ይመስለኛል—“ማየት ማመን ነው” እንዲል ብሂሉ። የትናንቷ ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ጋር የጎላ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ልዩነት አላት። ደርግ ከእነ ዕዝ ኢኮኖሚዋ ባለ ባዶ ካዝና አድርጓት ጥሏት የሄደው የትናንትዋ ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ላይ በበሊዮን የሚቆጠር በጀት መዳቢ ሆናለች። ይህም እዚህ ሀገር ውስጥ ህዝቦቿ በድንበር ምክንያት ሳይጋጩ በሰላማዊነታቸው ያገኙት ውጤት መሆኑ አይካድም።

ላለፉት ሰባት ዓመታት በላይ በሁለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥ ያለፈችውና በማለፍ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፤ የትናንት ቁስሏን ከመመልከት ይልቅ ህዘቦቿን በአንድነት እያሳተፈች በልማት ጎዳና በመገስገስ ላይ ትገኛለች። በዚህም ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ የምትሻለዋን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ደፋ ቀና እየለች ነው።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን እያስመዘገበች በሂደት የምስራቅ አፍሪካን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት ለመምራት የምትችልበትን አቅም መገንባት የምትችል መሆኗን በተግባር እያስመሰከረች ትገኛለች።

እናም በመጪው ጊዜያት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የቀጣናው መሪ መሆኗ አይቀርም። ለዚህ ደግሞ ሀገራችን በትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራች ያከናወነቻቸው ስራዎች ዛሬ ለምንገኝበት እመርታ ምቹ ምህዳርን መፍጠር መሆናቸው ዋስትናችን ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ እንዲሆንም አሁንም ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በአንድ ሀገራዊ መንፈስ መስራት ይኖርባቸዋል።  

ባለፉት 10 የፈጣንና ተከታታይ ምጣኔ ሃብታዊ እመርታዎች ውስጥ ሀገራችን ባለፉት ሰባት ዓመታት ዕውን እንዲሆኑ ያደረገቻቸው የልማት ዕቅዶች የነበረንን የዕድገት ፍጥነት ይበልጥ ያጎኑት ናቸው። በተለይም የመጀመሪያው የልማት ዕቅድ እጅግ በጣም የተለጠጠና ሊደረስበት የማይችል መስሎ ቢቀርብም፤ ሀገራችን አብዛኛዎቹንየዕቅዱን ውጤቶች ማሳካት ችላለች።

ከመጀመሪያው ዕቅድ ለሁለተኛው ተሞክሮ በመውሰድ የልማት ትልሟን እያፋጠነችም ትገኛለች። በተለይም በሁለተኛው የልማት ዕቅድ መጨረሻ ላይ መዋቅራዊ የምጣኔ ሃብት ለውጥ ለማምጣት ተግታ እየሰራች ናት። በዚህም ህዳሴዋን ቅርብ ለማድረግ እየሰራች ነው። ህዳሴያችን ፈፅሞ መስተጓጎል የለበትም።

ታዲያ ይህን ጠንካራ የልማት ግስጋሴ ለማስቀጠል እዚህም ሆነ እዚያ በድንበር ሰበብ የሚካሄዱ ተግባሮች መቆም አለባቸው። ድንበር በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭት ምክንያት ሊሆን አይችልም። አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብን ለመገንባት ቃል የተግባባ ህዝብ በጥቃቅን ጉዳዩች መነታረክ የለበትም። የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ፀረ ሰላም ሃይሎችም ሰለባ መሆን የለበትም። የሚያነሳቸው ተገቢ ጥያቄዎችም በፀረ ሰላም ሃይሎች እንዳይጠለፉና ለርካሽ ፖለቲካቸው መጠቀሚያ እንዳያደርጓቸው መጠንቀቅ ይኖርበታል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የሀገራችን ህዝብ ያለው በከፍታው ዘመን ላይ ነው። በዚህ የከፍታ ወቅት ህዳሴውን የሚያፋጥኑ ሁለንተናዊ ጉዳዩችን ማከናወን አለበት። የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ለጥቃቅን ጉዳዩች ቦታ ባለመስጠት አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ከመገንባት አኳያ የልማት ትልሞቹን ማሳለጥ ይኖርበታል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy