Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የአራምባና ቆቦ” መንገድ

0 439

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የአራምባና ቆቦ” መንገድ

ዳዊት ምትኩ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትብብርና የአንድነት ማሳያ ነው። ከስድስት ዓመት በላይ በግድቡ ግንባታ ላይ በሁለንተናዊ መስኩ የሚሳተፈው የአገራችን ህዝብ በፕሮጀክቱ ላይ ተመሳሳይ አቋም ያለው መሆኑንም ያስመሰከረበት ነው ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታም የጥበትና የትምክህት ሃይሉ ከህዝብ የሚነጥላቸው ዋነኛው ጉዳይ ይመስለኛል።

እርግጥም የህዳሴው ግድብ የትምክህትና የጥበት ሃይሎችን አጀንዳ ባዶ ያስቀረ ነው። የህዝቡ አስተሳሰብ በጋራ ሆኖ አገርን የማልማት ሲሆን የእነዚህ ሃይሎች ፍላጎት ግን ፀረ-ልማትነት መሆኑን ያረጋገጠ ነው። “አራምባና ቆቦ” እንደሚባለው ዓይነት።

እንደሚታወቀው ሁሉ የግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ለዘመናት በውሃው የመጠቀም መብቱ ተነፍጎ የቆየው መላው የሀገራችን ህዝብ በገንዘቡም ይሁን በጉልበቱ እንዲሁም ቦንድ በመግዛት የግድቡ ስራን ከዳር ለማድረስ ቃል የገባው በማንም ጎትጓችነት አይደለም።

የአገራችን ህዝብ በራሱ ፍላጎት የአገሩን ልማት አሳድጎ እርሱም ተጠቃሚ እንደሚሆን አሳምሮ ያውቃል። ይህን እውነታ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት ይበልጥ በማጣጣም አረጋግጧል። እናም ግድቡ አሁን ከሚገኝበት ከ58 በመቶ በላይ ግንባታ ላይ እንዲደርሰና ፍፃሜውም ዕውን እንዲሆን ከ10ሺህ በላይ ወጣቶች በስራ ላይ ይገኛሉ። ይህን ስራቸውን ለ24 ሰዓት እያከናወኑ ነው። ለግንባታውም ህዝቡ የማይነጥፍ ድጋፉን እየሰጠ ነው።

ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ግን ለባዕዳን ተላላኪ በመሆን ይህን የህዝብ የልማት ፍላጎት ለማጨናገፍ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። እርግጥ ገና ከጅምሩም ቢሆን ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ በትምክህትና በጥበት ሃይሎች በርካታ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ቢሰነዘሩም፤ ግድቡ በአገራችን ህዝቦች ባለቤትነት የሚካሄድ በመሆኑ ምንም ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። ከህዝብ የልማት ፍላጎት ጋር መላተም ራስን ከማጋለጥ ውጭ ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደሌለውም ያሳየ ነው። እርግጥም የህዝቡ ፍላጎት ሌላ ሆኖ ሲያበቃ፤ የእነርሱ ፍላጎት የህዝብን ልማት ማኮስመን መሆኑን ስራ ወዳዱ የአገራችን ህዝብ በሚገባ ተገንዝቧል።

እንደምናስታውሰው የግድቡ ግንባታን መበሰር ተከትሎ በመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተፈጠረው ስሜት የትናንት ትዝታችን ነው። ዕድሜ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ዘርና ቀለም ሳይለይ ድጋፉን ለመግለጽ ወደ አደባባይ ሲተም የማንንም ግፊት ሳይጠብቅ እንደነበርም ከእኛ በላይ ምስክር የሚሻው ጉዳይ አይደለም። መላው ዜጋ ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ቃል የገባበትን ሂደትንም የሚዘነጋ ኢትዮጵያዊ አለ ማለት አይቻልም።

ታዲያ ከልጅ እስከ አዋቂው የግድቡ ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥበት የቦንድ ግዥ በመፈጸም ቃል መግባት ሲጀምር ጉዳዩ ከመላው ዜጋ ጋር መጋጨት መሆኑን የተገነዘቡት እነዚህ ኃይሎች የግድቡን ግንባታ የሚደግፉ መስለው ለመቅረብ ሞክረዋል።

የመንግስትነት ስልጣን ከአንዱ ወደ ሌላው የሚሸጋገር ሂደት መሆኑና የግድቡ ግንባታ ግን የትውልድ ሀብት ስለሆነ ግንባታውን እንደማይቃወሙ አስተያየቶቻቸውን ሲሰነዝሩ ተስተውለዋል። ሆኖም በስተመጨረሻ ማንነታቸው እርቃኑን ወጥቷል።

ወትሮም ቢሆን ቀናነትን የማያውቁት እነዚህ የትምክህትና የጥበት ሃይሎች “የታጥቦ ጭቃ” በትራቸውን ለመሰንዘር አልዘገዩምና አፍራሽ አስተያየተቸውን ይፋ አደረጉ፡፡ ከግድቡ ግንባታ ስራ በፊት ብሔራዊ መግባባት መቅደም ስለነበረበት የግንባታው አካሄድ የተሳሳተ እንደሆነም ደስኮሩ፡፡ በዚህም “የህዳሴው ግድብ ባለቤት ኢህአዴግ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም” የሚል አቋማቸውን አንጸባርቀዋል። ህዝቡ ግን ባለቤቱ እኔ ነኝ ብሎ እነሆ ከስድስት ዓመታት በላይ በግድቡ ግንባታ ላይ ደፋ ቀና እያለ ነው።

ታዲያ የእነዚህ ኃይሎች ከንቱ ጩኸት በዚህ አላበቃም። የመረጡት የማደናገሪያ ስልት ባለመስመሩ ሳቢያ ሌላ ዘዴን መጠቀም መረጡ። እናም የ‘እንደግፋለን ግን … አንደግፍም’ አቋማቸውን ዳግም ሰንቀውም ብቅ አሉ፡፡ “ኢህአዴግ የግድቡ ግንባታን ለፖለቲካ መጠቀሚያነት እያዋለ ነው” የሚል አቤቱታቸውን ማስተጋባትም ስራዬ ብለው ተያያዙት። በዚህም ከህዝቡ ለመነጠል በቁ።

እንደሚታወቀው ሁሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት የሚያካሂደው ጥረት እየተጠናከረ ከመሄድ ያገደው አንዳችም ኃይል አልተገኘም። የህዝብና መንግስትን ልማታዊ ቁርጠኝነትም በእነዚህ ኃይሎች ባዶ ጩኸት  ስላልተሸረሸረ ጅምሩ ተጠናክሮ ቀጠለ።

ለዚህ እውነታ ምክንያቶችን መደርደር አያስፈልግም። ዋነኛው ጉዳይ አገራችን ውስጥ የህዝብን ፍላጎት ተገንዝቦ ምላሽ የሚሰጥ መንግስት ህዝብን ከጎኑ ማሰለፍ የመቻል ብቃት ስላለው ነው። እርግጥ እነዚህ የጥበትና የትምክህት ሃይሎች የህዝብን ቀልብ መሳብ የሚቻለው በየአደባባዩ በሚካሄድ ውስጠ ባዶ ንግግሮች አማካኝነት መስሏቸው ከሆነ “ሁለተኛው ጥፋት ቆሞ ማንቀላፋት” እንዲሉ ከዚህ ግዙፍ ስህተታቸው የተማሩ አይመስልም። በአንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጉያ ስር ተወሽቀው “የህዳሴውን ገድብ አንደግፍም” ሲሉም ተደምጠዋል።

እነርሱ በዚህ ሀክዝብ ተቃራኒ በሆነ ጎራ ውስጥ ሲሰለፉ፤ በሌላ በኩል በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ያልተለየው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጠቀሜታው በአገሪቱ ሳይወሰን ለጎረቤት አገሮችም ጭምር እንደሆነ እማኝነታቸውን የሚሰጡ ወገኖች እየተበራከቱ መጥተዋል። ይህ ለትምክህትና ለጥበት ሃይሎቹ የሞት ሞት ይመስለኛል።

ከሁሉም የበለጠው አስገራሚው ጉዳይ ግን የአገራችን የባዕዳን ተላላኪ ትምክህተኞችና የጥበት ሃይሎች እንዲህ ዓይነቱን ፀረ-ህዝብ ተግባር ሲፈፅሙ፤ የተፋሰሱ አባል አገራት ግን የኢትዮጵያ መንግስትን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍትሃዊነት በመደገፍ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ማረጋገጥ ቻሉ። ይህ ተግባራቸውም እነዚህ ሃይሎች የዚህ አገር ዜጎች አይደሉም እንዴ? የሚል ጥያቄን አጭሯል።

ሃቁን እንደ ዜጋም ይሁን ትብብርንና አብሮ ማደግን በመፈልግ የተፋሰሱ አገር ስንመለከተው፤ በአባይ ወንዝ ሀብታችን የመጠቀምና የመበልጸግ ጉዳይ መንግስትን ለሚደግፍም ሆነ ለሚቃወም ድርሻውም ሆነ ፍላጎቱ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የአባይ ያለ ምንም ፋይዳ የዘመናት ጉዞ የሁላችን ቁጭት በመሆኑ ነው። እነርሱ ግን ይህን ሃቅ ለመገንዘብ የሚፈልጉ አይደሉም።

እርግጥ የእነዚህ ወገኖች ድርጊት ከዚህም በላይ አልተራመደም ማለት አይቻልም። ከአፍራሽ የፕሮፓጋንዳ ተግባር ወደ አፍራሽ የሽብርተኝነት ተግባርም ተሸጋግሯል። ለዚህ የህዳሴው ግድብ ግንባታን በአደባባይ እስከመቃወም የደረሰው የአሸባሪው ኦነግ አሳፋሪ ተግባር እንዲሁም ራሱን “የቤኒሻንጉል ነፃ አውጭ” ነኝ የሚለው የኤርትራ መንግስት ቅጥረኛ የሽብር ቡድን ግድቡን ለማሰናከል ያደረገውን ርባና ቢስ ሙከራውን ማውሳት ይቻላል። ይህም የፅንፈኞችንና የህዝቡን አራምባና ቆቦ መንገድ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy