Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአስቆሮቱ ይሁዳ” መልክት ከአስመራ

0 774

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የአስቆሮቱ ይሁዳ” መልክት ከአስመራ

                                                      ዘሩባቤል ማትያስ

ከመሰንበቻው ራሱን “ግንቦት ሰባት” እያለ የሚጠራው የሽብር ቡድን መሪ ነኝ ባዩ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከወደ ለንደን አንድ ነጠላ ዜማ ለቀዋል፤ ‘ከምላላክበትና የጡት አባቴ  መዲና አስመራ ሆኜ ነው የምነግራችሁ’ በማለት። ሰውዬው ምናልባት ዲስኩራቸው እንደ መልዕክት ከተወሰደ ዋነኛ ማጠንጠኛቸው ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፤ ‘በሀገረ እንግሊዝ የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ መሰረት እዛው ለንደን ውስጥ ለጥፋት የተቀመረ ሰነዶችን በመያዝ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ክስ የተመሰረተባቸውን የድርጅታቸው ከፍተኛ አመራር የነበሩትን ዶክተር ታደሰ ብሩን ከተመሰረተባቸው ወንጀል እንታደጋቸው’ የሚል ነው።

ሰውዬው ይህን ለማድረግም “እኛ የምናካሂደው ትግል በሀገር ቤት ይሁን እንጂ አጠቃላይ የትግሉ አድማስ ውቅያኖስ ተሻግሮም ከምእራባዊያን ጋር ጭምር ነው”  የሚል አስቂኝ ዲስኩርም አሰምተዋል። እዚህች ላይ በአምባገነኑ የደርግ ስርዓት ወቅት ‘እገሌ የሚባለው አውራጃ ህዝብ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን አስጠነቀቀ’ የሚል አቅምን ያላገናዘበ ዜናን ያስታውሰኛል። የዶክተሩ አስቂኝ ዲስኩርም ከዚህ አኳያ የሚታይ ይመስለኛል።   

ያም ሆኖ የዚህ ፅሑፍ አንባቢያን ይህን የግለሰቡን ዲስኩር “ኢየሱስ ክርስቶስን በ30 ዲናር ተቀብሎ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ መልዕክት ለንደን ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከአፍሪካዊቷ ሰሜን ኮሪያ ኤርትራ” ብሎ ሊያነበው ይችላል። ርግጥ ውድ አንባቢያን በመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ የአስቆሮቶ ይሁዳ ለገንዘብ ሲል (ለዚያውም ለ30 ዲናር ብሎ) መጠጊያው የነበረውን ክርስቶስን አሳልፎ በመስጠቱንና በስተመጨረሻም ተፀፅቶ ራሱን ግራር ዛፍ ላይ ሰቅሎ መገኘቱን በማስታወስ የግለሰቡን ዲስኩር በዚህ መልኩ ቢተረጉሙት የሚገርም አይደለም። እኔ ግን እላችኋለሁ— ሰውዬው ገንዘብ እስካገኙ ድረስ ሀገርን ያህል ነገር ለፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችና ለሀገራችን ደመኞች በመላላክ አሳልፎ ለመስጠት እንኳንስ ዲስኩር ቀርቶ ያሻቸውን ከማውራት ወደ ኋላ የሚሉ ዓይነት አይደሉም።

አስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደካደው ሁሉ፤ የአስመራው “የአስቆሮቱ ይሁዳ” በሀገራቸው ላይ ከባዕዳን ጋር አብረው ሴራ መጎንጎናቸው ምንም ዓይነት “ሼም” የማይሰማቸው በመሆኑ በአስቆሮቱ ይሁዳ ሊመሰሉም ይችላሉ። እርሳቸውም ልክ እንደ መፅሐፍ ቅዱሱ “የአስቆሮቱ ይሁዳ” በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጀው በሀገራችን የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ መሰረት ሞት የተፈደረባቸው ናቸው። ያው የአስቆሮቱ ይሁዳም በስተመጨረሻው የተጎነጨው ሞትን መሆኑ ልብ ይሏል! እናም ተመሳስሏቸው የጎላ ነው። ልዩነታቸው የጊዜና የቦታ ካልሆነ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ሆኖ አላገኘሁትም። እናም በእኔ እምነት ሁለቱም “የአስቆሮቱ ይሁዳዎች” ምንም ልዩነት ስለሌላቸው፤ የሀገራችን ህዝብ “ስልቻም ቀልቀሎ፤ ቀልቀሎም ስልቻ ነው” እንደሚለው ዓይነት ነው።   

ያም ሆነ ይህ ግን እዚህ ላይ አሸባሪው ዶክተር ያነሱትን ሶስት መጠይቆችን በማንሳት ለአንባቢያን እውነታውን በግልፅ ለማሳየት እሞክራለሁ። የማምታታት አካሄዳቸውንም ጭምር። ታዲያ አውነታውን ለማጥራት የማጠይቃቸው ጉዳዩችም ‘እውን የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ታደሰ ብሩ ያለ ስማቸው ነው በእንግሊዝ መንግስት የአሸባሪነት ስም የተሰጣቸው?፣ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ በአሜሪካ ጉያ ውስጥ ተቀምጠው ምዕራባዊያንን እንዴት ነው የሚታገሉት? እና ይህ አባባላቸውስ እጅግ ከገነገነ ተስፋ መቁረጥ ውጭ ከቶ ሌላ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል?’ የሚሉ ናቸው።

“የአስቆሮቱ ይሁዳ” ምንም እንኳን የሽብር ድርጅታቸው ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶክተር ታደሰ ብሩ በእንግሊዝ መንግስት በአሸባሪነት ተከስሰው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስመልክተው ዓይናቸውን በጨው በመታጠብ “ምንም አላጠፋም” በማለት ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ የሌላቸውን የለንደን ዲያስፖራዎችን “ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ” በማለት ለማታለል ቢዳዳቸውም፤ ሃቁ ግን እ.ኤ.አ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እንግሊዝ ውስጥ በጥገኝነት መኖር የጀመሩት ዶክተር ታደሰ ብሩ ኬርሳሞ የሽብር ድርጅታቸውንና የእነ ኢሳይያስ አፈወርቂን የትርምስ ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእንግሊዝ ፖሊስ ተይዘው ለንደን ውስጥ እ.ኤ.አ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ፍርድ ቤት መቅረባቸው ነው።

ሰውዬው የተከሰሱበት ወንጀልም እንግሊዝ እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም ባፀደቀችው የፀረ- ሽብርተኝነት ህግ አንቀፅ 58 ስር በሰፈረው የሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ነው። አስገራሚው ነገር ይህ አንቀፅ ዓለምንና ምዕራባዊያንን እጅግ ያስመረረው “አይ ኤስ” የተሰኘው የሽብር ቡድን አባላትና አመራሮች ሲያዙ የሚከሰሱበት መሆኑ ነው።

ታዲያ እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ ይህ የእንግሊዝ መንግስት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጀው ግንቦት ሰባት አመራርም በእንግሊዝ ህግም አሸባሪ ተብሎ መፈረጁ ነው። እናም በእኔ እምነት ይህ የለንደን አስተዳደር ውሳኔ በ“ፍካሬያዊ” ትርጉሙ ስንረዳው፤ በሰው አራጁ “አይ ኤስ” እና ራሱን “ግንቦት ሰባት” እያለ በሚጠራው በእነ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ቦንገር የግብረ ሽብራ ቡድን አመራሮች መካከል ምንም ዓይነት ባህሪያዊና ምግባራዊ ልዩነት አለመኖሩን ያሳያል።

ከዚህ በተጨማሪ በእንግሊዝ መንግስት ዜግነት ያላቸው ናቸው በመባል ይታወቁ የነበሩት፣   ኋላ ላይም የየመን መንግስት ከሀገራችን ጋር ባለው ስምምነት ለኢትዮጵያ አሳልፎ የሰጣቸው፣ እነ “የአስቆሮቱ ይሁዳ” በተለያዩ ወቅቶች የለንደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርግ በቀቢፀ-ተስፋ ሲወጡና ሲወርዱ የነበሩበት እንዲሁም የአቶ ኢሳይያስ ቀኝ እጅ በመሆን በሽብር መጠሪያቸው “ወዲ ሓሪና” (ኤርትራ ውስጥ አሸባሪዎች በሚሰለጥኑባት ሓሪና የተባለች ቦታ ልጅ እንደማለት ነው) እየተባሉ የሚጠሩት ወንጀለኛው አንዳርጋቸው ፅጌም በወቅቱ በተጨባጭ ማስረጃ ባለመያዛቸው እንጂ፤ በእንግሊዞች እንደ ዶክተር ታደሰ ሁሉ እዚያው ለንደን ውስጥ በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው ይችሉ እንደነበር  የሚያመላክት ይመስለኛል።   

ያም ሆነ ይህ “የአስቆሮቶ ይሁዳ” በመልዕክታቸው እንዲህ ዓይነቱን በተጨባጭ ማስረጃ እጅ ከፍንጅ የተያዘን ግለሰብ ነው “ያለ ስሙ ስም ተሰጠው” በማለት በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ለማደናገር እየሞከሩ ያሉት። እንደ እውነቱ ከሆነ የእንግሊዝ መንግስት በተለያዩ ወቅቶች አሸባሪዎች ባደረሱት አደጋ ዜጎቹን ተነጥቋል። አሸባሪነት ቦታን፣ ዜግነትን፣ ዘርና ቀለምን እንደማይለይ ከደረሰበት የሽብር ጥቃት በሚገባ የተገነዘበ መንግስት ነው። እናም በየትኛውም ከሽብር ቡድን ጋር ንክኪ ያለው አካል በዚያች ሀገር ህግ መጠየቁ አይቀሬ ነው። ሽብርተኞች አደጋ ካደረሱ ራሳቸው ኢትዮጵያዊያንም ጭምር የአደጋው ሰለባ መሆናቸው አይቀርም።

ታዲያ እውነታው ይሀ ሆኖ ሳለ፤ “የአስቆሮቱ ይሁዳ” በመልዕክታቸው “የዶክተር ታደሰ ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው” በማለት የለንደንና አካባቢዋን ነዋሪዎች ለማደናገር እየጣሩ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ “የዶክተር ታደሰ ጉዳይ” (ያው ሽብርተኝነት መሆኑ ነው) የአሸባሪዎቹ የእነ ብርሃኑ ነጋና የአዝማቻቸው የኤርትራ መንገስት ጉዳይ እንጂ የማንም ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያዊያኑም በእንግሊዝ መንግስት በአሸባሪነት ለተጠረጠሩት ግለሰብ ድጋፍ መስጠት ማለት ሽብርተኝነትን ማበረታታት መሆኑን የሚገነዘቡት ይመስለኛል።

እናም የዶክተር ብርሃኑ ዲስኩር በምንም ዓይነት ልኬታ ቢታይ “ዓይን ሲመታ አፍንጫ ያለቅሳል” ከመሆን ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል አይደለም። ምክንያቱም በሽርብ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ዶክተር ታደሰ ጉዳይ በአሸባሪው “ግንቦት ሰባት” ትርጓሜ (ኧረ እንዲያውም በሌላ ሚዛናዊ ሰው እሳቤም ሊሆን ይችላል) አንደኛ፤ ከፍተኛው አመራር የያዙት ሰነድ የድርጅቱን በመሆኑ “የግንቦት ሰባትን” ማንነት ገሃድ የሚያወጣው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እነ ዶክተር ብርሃኑም የሰውዬው እጣ ፈንታ እኛንም መንካቱ አይቀሬ ነው በማለት “ነግ በእኔን” ፈርተው የሚያደርጉት ደመ ነፍሳዊ ጫጫታ ከመሆን የሚዘል አይደለም።

የዚህን ፅሑፍ አቅራቢ እጅግ ያስገረመኝ ጉዳይ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ (እኔ የምላችሁ እኚህኛውስ በምፅዋው ቤተ መንግስት የሁከት መጠሪያቸው ‘ወዲ ማን’ ነው የሚባሉት?…የሚያውቅ ሰው ካለ ሊነግረኝ ይችላል።) የሽብር ድርጅታቸውን በአስመራ የሁከት ማህፀን ውስጥ ፀንሰው፤ ሽሉን አሜሪካ ፔልሲቪኒያ ግዛት ውስጥ ተገላገለውት ሲያበቁ፤ እንዴት ነው “….የምንታገለው ምዕራባዊያንን ጭምር ነው” የሚሉት?…ርግጥ ሰውዬው በዜጎች ስም የልመና አኮፋዳቸውን ለመሙላት ሽብር በተባለ የንግድ ስራ ውስጥ ስለተሰማሩ “በማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ” የሚለውን ሀገራዊ ይትብሃል ስለዘነጉት እንጂ፤ ጉዳዩ ልጆች የሚጫወቱት የዕቃ-ዕቃ ዓይነት ጨዋታ መሆኑን ማንም ይገነዘበዋል። ምክንያቱም አሸባሪው ዶክተር እዛው አሜሪካ ውስጥ ተቀምጠው ቀይ ውስኪያቸውን እየጨለጡ በምዕራባዊያን ላይ “ቀይ መስመር” ሊያሰምሩ ስለማይችሉ ነው።  

ለነገሩ ‘ምዕራባዊያንን ጭምር እንታገላለን’ የሚለው ዲስኩራቸው ከቅዥት የመነጨ ሊሆንም ይችላል። እርሳቸው “ይህ አይደለም” የሚሉ ከሆነና ‘ምዕራባዊያንን እንታገላለን’ ያሉበት አግባብ ዶክተር ታደሰ በተያዙበት በሽብር ወንጀል ድርጊት ዓይነት ከሆነ ሊያስኬዳቸው ይችላል። “ለምን?” ቢሉ፤ ያኔ እርሳቸውም ይሁኑ ድርጅታቸው የኢትዮጵያን መንግስት ውሳኔ እዛው ለንደን ውስጥ ስለሚያገኙት ነው።

ርግጥም ያኔ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ሽብርተኝነትን አስመልክተው ምዕራባዊያን የሚያሳዩትን ቸልታ “የጥቁር ደም ቀይ ነው፤ የነጭም ደም ቀይ ነው” በማለት የተቹበትን እውነታ ለንደኖች ገቢራዊ ያደርጉታል። እናም አሜሪካ ቁጭ ብለው፣ አንዳንዴም በፈራ ተባ አስመራ እየተጓዙ ለንደን በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሽብርተኝነትን ለማንቆለጳጰስ የሚመኙት የሽብር ባለሟሉ ዶክተር ምላሹን ያገኙት ይሆናል።

ለንደን ያሉ ኢትዮጵያዊያን እርሳቸው እንደሚመኙት አሸባሪነትን በመደገፍ ምዕራባዊያንን የሚታገሉበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ላቡን አንጠፍጥፎ ያገኛትን ገንዘብ በእነ ብርሃኑ ነጋ ልመና የሚዘረፈው አንሶት፤ ሰርቶ የሚበላበትን ሀገር ለሽብርተኞች ሲል ሊታገል የሚችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖረው አይችልም። እኔ እስከሚገባኝና እስከማውቃቸው ድረስ በለንደንና አካባቢዋ የሚገኙ የሀገሬ ልጆች ስራቸውን ሰርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የመደገፍ ባህል ያላቸው እንጂ፤ የዕለት ጉርሳቸውን ትተው የአውሮፓዊያን ራስ ምታት የሆነውን ሽብርተኝነት በመደገፍ በአጋፋሪነት የመቆም ባህሪ የላቸውም። ከሀገራቸው የወጡት በኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሰርተው ለመለወጥ እንጂ የአሸባሪዎች መጠቀሚያ ለመሆን አይደለም።

እናም “…የምንታገለው ምዕራባዊያንን ጭምር ነው” የሚለው መልዕክት በምድረ በዳ ላይ እንደተዘራ ዘር የሚታይ ነው— በጭንጫ ላይ እንደተበተነ የማይበቅል ዘር። ከዚህ ይልቅ “ግንቦት ሰባት” በለመደው መንገድ ህዝቦችን ለማጋጨት በኤርትራ መንግስት እንዲሁም የኢትዮጵያን ዕድገት በማይመኙ አንዳንድ ሀገራት ድጋፍ ባቋቋመው “ኢሳት” በተሰኘ እሳት ማቀጣጠያ ጣቢያው የኤርትራ ወታደሮችን ቁምጣ አልብሶና ሸበጥ አስጫምቶ “የእኔ ናቸው” እያለ እንደሚያሳየው ሁሉ፤ እነዚህኑ ወታደሮች በውሰት ወስዶና የሲቪል ልብስ አልብሶ በለንደን አውራ ጎዳናዎች ላይ ሊያስለፍፍ ይችላል።

ይህ ካልተሳካም በአሜሪካ የሚገኙ መልካቸው ጭምር የሚታወቁ ኢምንት ጀሌዎቹን ሰብስቦ የተለመደውን የማያውቁትን የዴሞክራሲና የነፃነት መፈክሮችን አስይዞ ላንቃቸው እስኪተረተር ሊያስጮሃቸው ይችላል። ከእዚህ ተመራጭ ሳይሆን ምራጭ አማራጮች ውጭ ምንም ዓይነት ምርጫ የሚኖረው አይመስለኝም።

በአጠቃላይ ከእነዚህ “የአስቆሮቱ ይሁዳ” ዲስኩሮች የምንረዳው ትልቅ ጉዳይ ቢኖር፤ የሽብር ቡድኑ መሪ እታገላለሁ በሚሉት ነገር (ካለ ማለቴ ነው) የገነገነ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ መግባቱን ነው። አዎ! የሽብር ቡድኑ በሀገር ውስጥ ሊያደርጋቸው የሚከራቸው ጉዳዩች ሁሉ መቅኖ ቢስ ሆነውበታል። እነ ኤርትራ የላኩትን መልዕክት በአግባቡ ሳያደርስ በሰላም ወዳዱ ህዝባችንና በቀጥታ ኃይሎች ጥምረት እየተለቀሙ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ምዕራባዊያን በአሸባሪነት ላይ ምህረት የለሽ ርምጃ እየወሰዱ ነው። እነ እንግሊዝና አሜሪካ የኢፌዴሪ መንግስት ሀገሩንና ህዝቦቹን በተጨባጭ ልማት ስራው እየደፉ ነው። የህዝቦችን ደም ለማፍሰስ የሚሰራ የሽብር ቡድንን በመቃረን ፊታቸውን በልማት የዜጎቻቸውን ህይወት ወደሚለውጡ ሀገራት አዙረዋል። ለዚህም ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን አሜሪካም ሆነች እንግሊዝ ለሀገራችን የሰጡትን የልማት ድጋፎች በመመልከት ብቻ ሃቁን መገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል።

ርግጥ ማንም ቢሆን ልማትንና የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት የሚቀጥፈውን የግብረ-ሽበራ ተግባር በአንድ ዓይን ሊመለከት አይችልም። ሁለቱን ለንፅፅር ማቅረብ ህይወትና ሞትን በአንድ ሚዛን ላይ የማስቀመጥ ያህል ነውና። ታዲያ ይህ ሁኔታ በባንዳነት ተሰልፈው ሀገርን በመሸጥ ለሚተዳደሩት ለእነ “የአስቆሮቱ ይሁዳ” አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል። በዚህም ሳቢያ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ መሪ ነን ባዩች “እዚህ ቦታ ሆነን ነው የምንናገረው” እያሉ የተጠለሉበትን “ምዕራባዊያንን ጭምር እንታገላለን” እስከማለት መድረሳቸው የሚደንቅ አይደለም—ምንም እንኳን አባባሉ ማንነትን ካለማወቅና አቅምን ካለመገንዘብ በደመ ነፍስ የተነገረ ቢሆንም።

ርግጥ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንደሚባለው እነ “የአስቆሮቱ ይሁዳ” በስተመጨረሻቸው ምንም መፈናፈኛ ማጣታቸውን ‘መልዕክት ነው’ ባሉን ዲስኩር ነግረውናል። የእነ እንግሊዝ አቋም ነገ ወደ ሌሎቹ የሽብር ቡድኑ አመራሮች እንደሚዛመት በመፍራት የተነገረው ይህ ዲስኩር በርግጠኝነት የሚያስረዳን ነገር ቢኖር፤ እጅግ ከገነገነ ተስፋ ቆራጭነት ባሻገር የጀመሩትን የእርጥባን ማግኛ የሽብር “ፕሮጀክት” ላለማጣት ቀቢፀ-ተስፋዊ ሩጫ እያደረጉ መሆኑን ነው። ግና በአሁኑ ወቅት ምዕራባዊያን በሽብርተኝነት ላይ በያዙት ጠንካራ አቋም ይህ ሩጫቸው የመቶ ሜትር ርቀት እንኳን የሚያስኬዳቸው አይመስለኝም። አበቃሁ።         

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy