Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶች በጊዜያዊ ችግር አይደናቀፉም!

0 427

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶች በጊዜያዊ ችግር አይደናቀፉም!

                                                               ደስታ ኃይሉ

በአንዳንድ የኢትዮጵያ ሶማሊና የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በቅርቡ የተከሰተው ግጭት ሁለቱን ህዝቦች የሚመለከት አይደለም፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ተመሳሳይ ባህልና ወግ ያላቸው ሲሆኑ፤ ለዘመናት የገነቡት የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶታቸው በጊዜያዊ ችግር ሊደናቀፉባቸው አይችሉም፡፡ በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ህዝቦች ተጋብተውና ተዋልደው እንዲሁም በደም ተሳስረው የሚኖሩ በመሆናቸው ይህን ትስስራቸውን ጊዜያዊ ችግር ሊፈታው አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ የምትመራበት ህገ መንግስትም ተፈቃቅዶ በአንድነት ለመኖር እንጂ ለመለያየት በር የሚከፍት አይደለም።

ሕገ መንግስቱ እንደማናቸውም የፌዴራል መንግስት ስርዓት እንዳላቸው ሀገሮች ሁሉ፤ የመንግስትን ስልጣን በሕግ አውጪ፣ በሕግ አስፈፃሚውና በዳኝነት አካላት መካከል ብቻ ሳይሆን ብዛት ባላቸው የስልጣን ማዕከላት ማለትም በፌዴራልና በክልል መስተዳድሮች መካከል ያከፋፍላል። ባለፉት ድርዓቶች ገቢራዊ ሆኖ የነበረው አሃዳዊ ስርአት በኢትዮጵያ የህዝቦች መካከል ቅራኔንና መካረርን እንዲሁም የመበታተን አደጋን ፈጥሮ ነበር።

በተለይም ላለፉት 10 ዓመታት ፌዴራላዊ ስርአቱ በመፈቃቀድ፣ በየደረጃው ገቢራዊ በሚሆን እኩል ተጠቃሚነትና በሰፊ የክልሎች ስልጣን በመመስረቱ ለልማትና ለዴሞክሲያዊ አንድነት እንዲሁም ለሰላም ዋስትናን ፈጥሯል።

በእነዚህ ዓመታት ብሔራዊ ጭቆናንና የአሃዳዊ ስርአት አስተሳሰብንና ተቋማዊ አደረጃጀትን ስር ነቀል በሆነ መንገድ በማስወገድ በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ የፖለቲካ ማዕቀፍ መፍጠር መቻሉ የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርአት መገለጫዎች ናቸው ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ህዝቦች በህገ-መንግስታቸው መግቢያ ላይ “….እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች…” በማለት የእምነታቸው ማሰሪያ እንዲሆናቸው ቃል ኪዳን መግባታቸውን ያረጋገጡት። እነርሱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የማይገሰስ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን በህገ መንግስቱ ላይ አውጀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን ለማድረግ በነፃ ፍላጎታቸው በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ አላቸው። መጪው የጋራ ዕድላቸው መመስረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆን እንዳለበት የተቀበሉ መሆናቸውን በተደጋጋፊነት በፍትሐዊና ፈጣን ልማት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ በህገ መንግስቱ ገልፀዋል።

በሕገ መንግስቱ ለዚህ ዓላማቸው መሳካት የግለሰብና የቡድን መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ሃይማኖቶችና ባህሎች ያለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ አድርገዋል። ኢትዮጵያ የየራሳቸው አኩሪ ባህል ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገር መሆኗን፣ የየራሳቸው መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበራቸውና ያላቸውን በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረው አብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት ሀገር በመሆኗ ያፈሩት የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለው የሚያምኑ መሆናቸውንም በህገ መንግስታቸው ላይ በማያሻማ ሁኔታ ደንግገዋል።

በህገ መንግስቱ የስልጣን ምንጭ ማዕከላዊ መንግስት ሳይሆን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸው ተገልጿል። ለራሳቸው በቂ ስልጣን አስቀርተው ለጋራ ጉዳይ የሚያስፈልግ ስልጣንን ለማዕከላዊ መንግስት ቆርሰው ሰጥተዋል።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ልዩ ባህሪያት አሉት። ሕገ መንግስቱ የብሔሮች የብሔረሰቦችና የህዝቦች እንደ መሆኑ መጠን፤ የህገ-መንግስት የበላይነትን ለማረጋገጥ ህገ-መንግስቱ በማናቸውም የመንግስት አካላት ብቸኛ ውሳኔ ሊሻሻል እንደማይችል በማስቀመጥ አንዱ የሌላው የበታች እንዳይሆን ይከላከላል።

የክልሎች ሃሳብ በፌዴራል ምክር ቤቶች እንዲወከሉ በማድረግም በፌዴራል የጋራ ጉዳዮች ውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል። ህግ- መንግስትን የመተርጎም ስልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በመሰጠት፤ በህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽን የውሳኔ ሃሳብ አቅራቢነት የሚወሰንበትን ስርአት ህገ መንግስቱ ዘርግቷል።

በአገራችን ውስጥ የራስን መብት በራስ የመወሰን ተረጋግጦ እያለ ዜጎች የቆየ አብሮነታቸውን በጊዜያዊ ግጭት ሊያፈርሱት አይችሉም። እንደሚታወቀው ሁሉ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በሕገ መንግስታችን ሶስት ዋና ዋና የሆኑና የተቆራኙ መብቶችን ያቀፈ ፅንስ ሐሳብ ነው፡፡ አንደኛ ማናቸውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ በቋንቋው የመናገር የመፃፍና የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ እንዲሁም የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡

ሁለተኛ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው፡፡ በዚህም መሰረት እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማት የማቋቋም መብት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት አለው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፌዴራልም ሆነ በክልል መስተዳድሮች የስልጣን እርከኖች ውስጥ በመንግስት አስተዳደር ስራ ውስጥ መሳተፍ እንዲችሉ ህገ መንግስታዊ ዋስትና የሚሰጣቸው መብት ነው፡፡

ይህ መብት በአንድ በኩል በየሰፈሩበት መልክዓ ምድር ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራስ አስተዳደርን ለማቋቋም የሚያስችላቸው መሆኑን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራል እና በክልል መስተዳድሮች ሚዛናዊ ውክልና እንደሚኖራቸው በመደንገግ የራስ አስተዳደርን እና የጋራ አስተዳደርን ስርዓቶች በማጣመር ስራ ላይ የሚውሉበትን ህገ መንግስታዊ መሰረት ይጥላል።

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ የተካተተው ሶስተኛው ጉዳይ የመገንጠል መብት ነው። የዚህ መብት ህገ መንግስታዊ ዕውቅና ያስፈለገበትን ምክንያት ለመረዳት በህገ መንግስቱን መግቢያ ላይ በደንብ የሰፈረ ይመስለኛል።

ይኸውም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመመስረት በህገ መንግስቱ የወሰኑት በራሳቸው ነፃ ፍላጎት እንደሆነና የሚገነቡትም አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ይገልፃል። የሚገነባው ማህበረሰብም በእያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ፈቃድና ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም የመገንጠል መብት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መሰረት የህዝቦች ፈቃድና ፍላጎት መሆኑን የሚያበስርና ዋስትና የሚሰጥ መብት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ይሁንና ይህ “የመገንጠል መብት” አንቀፅ በአንዳንድ ወገኖች በበጎ መልኩ አይታይም። እነዚህ ወገኖች ይህን መብት “ሀገርን የሚገነጣጥል ነው” ሲሉም ይቃወሙታል። ነገር ግን አንቀፁ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በአንድነት መኖር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ዕድልንም አብሮ የሚሰጥ ነው። እርግጥ ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመፍጠር ህዝቦች የእኩልነት መብታቸው መከበር ይኖርበታል። ይህ በመሆኑም ለመገንጠል ፍላጎት የሚኖረው ህዝብ አይኖርም።

ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘመናት አብሮነት ቆይታው ተቻችለው የኖሩ ህዝቦች በምንም ዓይነት ሁኔታ አብሮነታቸው ሊፈታ አይችልም። የዛሬን ሳይሆን የትናንትንና የነገን ህይወታቸውን ይመለከታሉ። እናም ጊዜያዊ ችግር አብሮነትን የማያበላሽ በመሆኑ ለዘላቂ ህይወት በጋራ ተሳስቦ መኖር አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy