Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአንድ አካባቢ ኮሽታ አገርን አይወክልም!

0 613

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአንድ አካባቢ ኮሽታ አገርን አይወክልም!

                                                            ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። በቀዳ ስፋትም ይሁን በህዝብ ብዛት ከፍ ያለ ቦታ ላይ የምትገኝ አገር ነች። በአንድ ለሌት ውስጥ የት ቦታ ምን እንደተፈፀመ ማወቅ አይቻልም፡፡ የአንድ አካባቢ ችግር የሌላው ሊሆን አይችልም፡፡ እናም በዚህች ታላቅ አገር ውስጥ በአንድ አካባቢ ኮሽ ያለ ጉዳይ እንደ አጠቃላይ የአገሪቱ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የቀዬ ወይም የመንደር አሊያም የአካባቢ መገለጫ ብቻ አይደለችም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያን እንደ አገር ሊያስቆጥራት የሚችለው የሁሉም ቀዬዎች፣ መንደሮችና አካባቢዎች ድምር ውጤት ናት፡፡ በመሆኑም በአንድ ቦታ የሆነ ነገር ተከሰተ ማለት ችግሩ መላው አካባቢውን የማያካልል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ችግሩ በተከሰተበት አካባቢ የተለያዩ የመንገስት መዋቅሮች አሉ፡፡ ህዝብም አለ፡፡ መዋቅሮቹና ህዝብ በአንድ ላይ እልባት የሚሰጡት ይሆናል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ ችግር ለምን ኖረ ብሎ መጠየቅ አይቻልም። ምክንያቱም በየትኛውም ማህበረሰብ መስተጋብራዊ ግንኙነት ውስጥ  ግጭት መፈጠሩ ስለማይቀር ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ እንዴት አድርገን ልናረጋጋቸው እንችላለን የሚለው ነው፡፡ ግጭቶች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም፡፡ መጥፎ የሚያደርጋቸው አስተሳሰባችን ነው፡፡

ለውጥን መሰረት ባደረገ አስተሳሰብ ከተቃኘ፣ ግጭት የለውጥ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ፌዴራሊዝም የግጭት መነሻ ነው የሚባለው አመለካከት መሰረት የሌለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት መቻቻልን ያመጣና በሂደትም በመጎልበት ላይ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ አወቃቀር ብዝሃነትን እንደ ውበት አድርጎ የሚነሳ በመሆኑ ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን በማጠናከር የመቻቻል መንፈስ እንዲዳብር ተደርጎ በህዝቦች ስለተዋቀረ ነው፡፡

ያም ሆኖ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች መነሻውን ድንበር በማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት አሉ። እነዚህ ተግባራት መነሻቸው ህዝብ አይደለም። ህዝብ ለሰላም እንጂ ለግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለግጭት የሚሆን ምህዳርን በተቻለ መጠን ማጥበብ ይገባል።

እንደሚታወቀው የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት ዕርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው። በክልሎች በተካሄዱ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ በተገኘው ግብዓት መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ ዕርምጃ መወሰድም ተጀምሯል፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

እርምጃውን በጥልቀትና በስፋት በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መሥራት የግድ ነው። የህልውና ጉዳይም ነው። ምክንያቱም ችግሩ በቅርቡ በተወሰኑ የሃገራችን አካባቢዎች ለሰላም እና መረጋጋት መጥፋት መንስኤ ሆኖ ተስተውሏልና። ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

እርግጥ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸው የግድ ነው። እነዚህ የተጀመረውን የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና ማለታቸው በቅርቡ በኦሮሚያና በጋምቤላ የተከሰቱት ድርጊቶች ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው።  

ያም ሆኖ ምክንያቶችን መድፈን ይገባል። ቀዳዳዎችን ያለ አንዳች ሽንቁር መድፈን የግድ ይላል። ለግጭት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ወሳኝ ነው። ይህን ለመከወን የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በቁርጠኝነት መታገል ይገባል።

በተለይም ግጭትን ቦታ ለማሳጣት የትምክህትንና የጥበት አራማጆችን መታገል የግድ ይላል። እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ፡፡ የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሄር ብቻ ልዕለ ኃያል የሆነ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየ፣ ሁሌም ለመግዛት የተፈጠ ርኩ ነኝ ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ ጐን ለጐንም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም አይቀበልም። ስለሆነም ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳ ሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ይህ ካልሆነ ሀገር ትጥፋ ህዝብም ይለቅ የሚል ህሳቤም የተጠናወተው ነው። ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው። የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰ ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖር የእሬት ያህል የሚጎመዝዘው ኋላ ቀር አሳቢ ነው። በጠባብነት ድንበር የታጠረ እንደመሆኑ መጠንም ከሱ ብሔር ውጪ ያለ ህዝብ በአካባቢው እንዳይኖር ሌላ ቋንቋ እንዳይነገር ይሰብካል፡፡ ያስባል፡፡ ያልማል፡፡

ይህ የጥበት ሃይል በመስበክ ብቻ ራሱን አያቅብም፡፡ የብሔሩ አባል ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲመለከተው ዕድሉ ሲመቻችለትም እንዲያጠቃና እንዲያጠፋው ተግቶ ይሠራል፡፡ በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አይቀበልም። የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፀር በመሆንም ሌላውን ዜጋ ለመጨፍለቅ ይሞክራል—ቢሳካለትም ባይሳካለትም፡፡

ታዲያ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፅኑ ጠላት የሆኑትና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት ባለባቸው ሃገሮች ፈጽሞ ሊሠሩ የማይችሉት እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች፤ በአሁኑ ወቅት በሰላማችንና በልማታችን ላይ የተደቀኑ እንቅፋትና ጋሬጣዎች መሆናችው ፍንትው ብሎ እየታየ ነው፡፡

አንድ ምሳሌ ላንሳ፡፡ ጃዋር መሐመድ የተሰኘ ግለሰብን፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ጃዋር መሃመድ የተሰኘው ጠባብና የእነ ግብፅ መንግስት ተቋማት ተላላኪ ነው፡፡ የጃዋር የጥበት መጠን ‘አንገቱን በሜጫ’ እስከሚል አስገራሚ ዲስኩር የሚዘልቅ ነው፡፡ ይህ ግለሰብ በፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ዳረጎት ሰጪነት ያቋቋመውን የቴሌቨዥን ጣቢያ በማቋቋም አገራችን ውስጥ ብጥብጥ ለመፍጠር እየተሯሯጠ ነው፡፡ ይይን ተግባሩን ሀዝቡ ሁሉ ሊኮንነው ይገባል፡፡ የተለያዩ ፅንፈኛ ሃይሎች እንደሚያስወሩት በእነ ጃዋር የተሳሳተ አሉባልታ የሚቀሰቀሰው ችግር ሁሉንም አካባቢ የሚመለከት አይደለም፡፡

እንኳንስ ሁሉንም የአገራችንን ክፍል ሊመለከት ቀርቶ በኦሮሚያ ውስጥም በአብዛኛው ቦታ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ህዝቡ የፅንፈኞችን ዓላማ በውል እየተገነዘበ በመምጣቱ በአካባቢ ቀርቶ በቀየም ውስጥ ሁከት አምላኪዎች ቦታ እያጡ ነው፡፡ ይህም ህዝቡ በየጊዜው ተግባራቸውን ከመገንዘቡ ጋር የተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል፡፡

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy