Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአዲሱ ዓመት ተስፋ

0 360

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአዲሱ ዓመት ተስፋ

                                                                                              ይነበብ ይግለጡ

2009ን አሰናብተን መጪውን 2010 አመተ ምሕረት ለመቀበል ጥቂት ቀናት ቀሩን፡፡ አሮጌውን አመት ላይመለስ ስንሸኘው በግለሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ የተከወነውን መልካምና በጎ ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል፤ ከደካማ ጎኖችም በመማር የተሻለና የጎለበተ ስራ ለመስራት በመዘጋጀት ጭምር ነው፡፡

እያገባደድነው ባለው አመት የሀገራችንን ልማትና እድገት የሚያፋጥኑ ከድሕነት ጋር የሚደረገውን ትግል በድል አድራጊነት ለመወጣት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በሀገር ደረጃ ጥልቁ ተሀድሶ በሕዝባዊ ንቅናቄ ተደግፎ ተግባራዊ የሆነበት ለሕዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም መልስ ለመስጠት የተቻለበት በሙሰኞች ላይ ከፍተኛ እርምጃ መውሰድ የተጀመረበት አመት ሁኖ ቀጣዩን የቤት ስራ ለአዲሱ አመት አስተላልፎአል፡፡

በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተጀመረው ትግል በዋነኛነት በሀገር ደረጃ  የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ሰፊ ትግል ማድረግ እንደሚገባ በተግባር ያሳየ ነው፡፡ ግለሰቦችን በማሰርና በመፍታት ብቻ የሚቋጭ ትግል ሳይሆን እንደ ሀገርና ሕዝብ ይህን የመሰለውን አደጋና ሊያስከትል የሚችለው ችግር በተተኪው ትውልድ ውስጥ ስር ሰዶ እንዳይተላለፍ የማስተማርና የማሳወቅ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር ተግቶ መሰራት እንዳለበት ማስጠንቀቂያ የሰጠ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በሸኘነው አመት በመላው ሀገሪቱ ሰፊ ሕዝባዊ የክርክር መድረኮች ተካሂደዋል፡፡ ሕዝቡ በነቃ ተሳትፎ በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ ረገድ ያጋጠሙትን በደሎች ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ግልጽነትና ቀጥተኛነት በተመላበት መልኩ ለመንግስት አቅርቦአል፡፡ መንግስት የሕዝቡን ቅሬታና በደል ብሶት በማዳመጥ ችግሩን ለመፍታት በስፋት ተንቀሳቅሷል፡፡

በዚሁ እየሸኘነው ባለው አሮጌው አመት ጥልቅ ተሀድሶውን በመመርኮዝ መንግስት የአዳዲስ ሚኒስትሮች ሹመት አካሂዶአል፤ አመራሮችን ለውጦአል፡፡ ከ50ሺህ በላይ በሆኑ በሙስና፣ ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ወዘተ ችግር ውስጥ ተዘፍቀው የተገኙ የኢሕአዴግ አባላትን ከድርጅቱ አሰናብቶአል፤ ከስህተታቸው ሊማሩ የሚችሉትን እንዲታረሙ እድል ሰጥቶአል፤ ጉዳያቸው በሕግ የሚያስጠይቀውንም በሕግ እንዲታይ አድርጎአል፡፡

ተሀድሶው እያጠሩ መሄድ እያራገፉ መጓዝ ጭምር በመሆኑ ከሕዝብና ከድርጅቱ አላማና መስመር ውጭ ቆመው በተገኙትም ሆነ በሚገኙት ላይ የሚወስደውን  ጠንካራ እርምጃ በአዲሱም አመት በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል፡፡ ለግለሰቦች ሲባል የሀገርና የሕዝብን ደህንነት በምንም መልኩ አደጋ ላይ መጣል አይቻልም፡፡ ከምንም በላይ የሀገርና የሕዝብ ሰላም ይበልጣል፡፡ ማንም ሆነ ማን ባለስልጣንም ሆነ አልሆነ በተጨባጭ ማስረጃ ሙስና ውስጥ ተነክሮ  እስከተገኘ ድረስ በሕግ ይጠየቃል፡፡

በዚህ ረገድ ጥርጣሬ ውስጥ የሚገቡ የተለያየ ትርጉም የሚሰጡ ግለሰቦች ቡድኖች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከሙስናው ውስብስብ ባሕርይ በመነሳት ችግሩን ከስሩ መንቀል የሚቻለው ሰፊና ጠንካራ ሕዝባዊ ተሳትፎን በማሳደግ በመሆኑ ከሀገር፣ ከሕዝብ እና ከሕግ በላይ ማንም የለም የሚለው የኢሕአዴግ እምነት በተግባር የሚገለጽበት ወቅት አሁን ነው፡፡

መጪው አዲስ አመት ከቀደሙት አመታት የበለጠና ያደገ የጎለበተ ልማትና ሀገራዊ የእድገት ስራ በአዲሱ አመት እንደሚሰራ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የተጀመሩት ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ፍጻሜ አግኝተው ወደ ተግባር የሚገቡበት፣ ለብዙ ሺህ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል የሚፈጠርበት፣ ወጣቱ በሀገራዊ ፍቅር ታንጾ ያደገችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት  ከምን ግዜውም የበለጠ ተግቶ የሚንቀሳቀስበት፣ ከመንግስት የተሰጠውን ድጋፍና እገዛ መነሻ አድርጎ የላቁ ውጤታማ ስራዎችን የሚሰራበት አዲስ አመት ነው የሚሆነው፡፡

አዲሱ አመት ከአሮጌው አመት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ፈትሸን በአዲስ ሀገራዊ የስራ የልማትና የእድገት መንፈስ በብሔራዊ ደረጃ የምንነሳበት፣ ለአላማችን ጸንተን የምንቆምበትም ግዜ ነው የሚሆነው፡፡ ሀገራችን በአለፉት አስር አመታት አለምን ያስደመሙ ምስክርነትም ያሰጡ እጅግ የላቁና የገዘፉ የልማትና የእድገት ስራዎችን አከናውናለች፡፡ ማንም አይቶ የሚመሰክረው ብቻ ሳይሆን ማንም የማይክደው ስራም ነው የተሰራው፡፡

በየዘርፉ ማለትም በመንገድ፡ የግብርና ምርትን በማሳደግ (በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መቻሉ፡ የመሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ማደግ፤ የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ከማሳካት አኳያ ከአንደኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት በአዲስ አበባም በክልሎችም ቀድሞ ከነበረው በላይ በብዙ እጥፍ ማደጉ፡ የጤና አገልግሎትና ተቋማት መስፋፋትና  መሻሻል፤ በባቡር ግንባታ ረገድ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት የመጀመሪያውን የከተማ የባቡር መስመር የዘረጋች፣ ረዥሙን የባቡር መስመር ከጅቡቲ ወደብ እስከ አዲስ አበባ ከቀድሞው በዘመነና በተሻለ ሁኔታ የገነባች ሀገር ለመሆን በቅታለች ኢትዮጵያ፡፡

ሀገራችን ቀድሞም ታዋቂና ገናና የነበረውን የኢትዮጵያ አየርመንገድ በዘመኑ ቴክኒዮሎጂ የታገዘ እንዲሆን ከማድረግዋም በላይ የበርካታ ዘመናዊ ጀቶች፣ ድሪም ላይነሮች፣ ኤየር ባሶች ባለቤት በመሆን ለአለም አቀፍ ደንበኞች በምትሰጠውም ጥራትና ብቃት ያለው አገልግሎት በዚህም በተደጋጋሚ በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች፡፡

እንደቀደሙት አመታት ሁሉ ሀገራዊ የግብርና አሰራርን ለማዘመን እያለቀ በአለውም አመት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ኋላቀር የነበረውን ግብርና ዘመኑ በሚጠይቀው እውቀትና ክሂሎት በመመራት የበለጠ ውጤታማና አምራች እንዲሆን አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በየደረጃው የማስተማርና የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ምርቱንም በእውቀት ተደግፎ እንዲያሳድግ ተደርጎአል፡፡

በአለም ደረጃ የተከሰተውን ድርቅ ለመመከት በራስ አቅም አይችሉትም የተባለውን ድርቁ የከፋ አደጋ እንዳያስከትል ከመገደብ አንስቶ ለዜጎች በተጠናከረ መልኩ በመድረስ አስፈሪ የሆነውን የድርቅ አደጋ ለመመከት ተችሎአል፡፡ ለዚህም መሰረታዊ የኢትዮጵያ መንግሰት እርምጃ ለጋሾች ጭምር አድናቆታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሁንም ችግሩ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መንግስት የተቻለውን እገዛና እርዳታ ፈጥኖ ለዜጎቹ የማድረስ ስራና ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

የተፈጥሮ አደጋ የትም ሀገር ላይ በማንኛውም ግዜ ሊከሰት የሚችል ችግር ነው፡፡ ለዚህም ከሰሞኑ በአሜሪካ የተከሰተውን የሁራካን ሀርቤ አውሎ ንፋስና የውሀ መጥለቅለቅ መመልከት ይበቃል፡፡ መንግስት ወይንም ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ የሚያመጣው ችግር አይደለም፡፡ ትልቁ ነጥብ ለተፈጠረው ችግር መንግስት ፈጥኖ ለተጋረጠው አደጋ የሰጠውና የሚሰጠው ምላሽ ሕዝቡን ከአደጋ ለመከላከልና ለመጠበቅ የወሰደው እርምጃ ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፈጥኖ በመድረስም ሆነ ሕዝቡን ከአደጋ ከመታደግ አኳያ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት፣ በቀደሙት አመታት በሀገራችን በብዙ ዘርፍ ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግ ተችሎአል፡፡ የጤናና የትምህርት አገልግሎት ቀድሞ ባልነበረ መልኩ በመላው ሀገሪቱ ተስፋፍቶአል፡፡ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች  በተመራጭዋ ሀገራችን ሰፊ የኢንቨስትመንት እድል አግኝተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆኑ የተለያዩ አለምአቀፍ መገናኛ ብዙሐን አጉልተው በመዘገብ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ በታላቅ ሀገራዊ ተስፋ የልማትና የእድገት ጉዞዋን በመቀጠል ላይ ያለች ሀገር ነች በሚለው የእለት ተእለት ዘገባቸው የአፍሪካን ብሎም የአለምን ቀልብ ስበዋል፡፡ ከዚህ ታላቅ ተስፋን ከሰነቀ ሀገራዊ ጉዞዋ የሚያናጥባትም ሆነ ከጀመረችው ጉዞ የሚገታት ሀይል የለም፡፡ ለኢትዮጵያ ነገ ብሩህና ተስፋን የሰነቀ ታላቅ ቀን ነው፡፡

ለዚህም ዜጎችዋ ሁሉ ልዩነትን በልዩነት በመያዝ ሀገርን በመጠበቅና በማሳደግ ረገድ ታላቅ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰፊው የሀገራችን ሕዝብ ወጣቱ፤ ሴቶች፣ አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች፣ የመንግስት ሰራተኛው በተገኘው ልማትና ሀገራዊ እድገት በአብዛኛው ተጠቃሚ ሁነዋል፡፡

የዜጎቻችን የበለጠ ሀገራዊና ሕዝባዊ ተጠቃሚነት የሚገኘው በርትቶና ጠንክሮ በመስራት መሆኑን ካለፉት በርካታ አመታት ተምረዋል፡፡ አሁንም ዜጎች በየተሰማሩበት መስክ ሀገራቸውን የበለጠ ለማልማትና ከከፋው ድህነት ለመላቀቅ በቁርጠኝነት ተሰልፈው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

አዲሱ ዘመን ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቅበት፣ የበለጠ ሀገራዊ ልማትና እድገት የሚገኝበት፣ ልዩነቶች በመቻቻል፣ በመደማመጥና በመነጋገር የሚፈቱበት፣ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት በአንድነት፣ በሕብረት የምናስጠብቅበት ይሆናል፡፡ ለዚህ እውን መሆንም ከሁሉም ዜጋ በጽናት መቆም ይጠበቃል፡፡ መልካም አዲስ አመት!!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy