Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያን ከፍታ በሰላም መነፅር

0 359

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያን ከፍታ በሰላም መነፅር

 

ስሜነህ

 

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚሊኒየሙን ግብ በማሳካት ሃገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ለማሰለፍ የሚያስችላቸውን የሚሊኒየሙን ቃል ኪዳን ካሰሩ እነሆ በ10ኛው አመት ዋዜማ ላይ ይገኛሉ። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከነሃሴ 26 2009 እስከ ጷግሜ 5 2009 ለተከታታይ 10 ቀናት የሚቆይ እና “መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” በሚል መሪ ቃል የሚመራ ኩነት ይፋ ሆኗል። ኩነቱን በበላይነት የሚመራው እና ሃገራዊ የማስተባበር ሃላፊነት የተሰጠው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እንዳለው ከአዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በኋላ በተቆጠሩት አስር አመታት የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም፤ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋፋትና ድክመቶችን በማረም ብሄራዊ መግባባትን ይበልጥ ለማጎልበት እና የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ለማድረግ ሁነቶቹ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል። ስለሆነም ከነሃሴ 26 ጀምሮ ላሉት 10 ተከታታይ ቀናት ከላይ ስለተመለከተው ድርሻ ስም ተሰይሞላቸው እንደሚከበሩ ታውቋል። ይህ ተረክም የነሃሴ 29ን የሰላም ቀን ያወሳል።

 

የኢትዮጵያ ከፍታን እውን ለማድረግ መሰረቱ ሰላም ነው። ስለሆነም የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት መልካሙን ለማስፋፋትና ድክመትን ለማረም ሲባል ሁነቶቹ ተዘጋጅተዋል ባለው አግባብ ባሳለፍናቸው 10 አመታት ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን እንዲጠናከሩ ደካሞቹ ደግሞ ይታረሙ ዘንዳ ማውሳት ተገቢ ነው።

 

በመሰረቱ ያለፉትን 10 አመታት የሰላም ግምገማ ለማድረግም ጭምር እንድንበቃ ያደረገን ህገ-መንግስት አስቀድሞ ለዘመናት ያልተመሰሉ የዜጎችን የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖትና ራስን በራስ የማስተዳደር በአገሩ የመጠቀምና የማደግ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ያስቻለ ከመሆኑም በላይ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ዜጎች የጋራ ቃል ኪዳናቸውን ያስቀመጡበት ሰነድ በመሆኑ መሰረታዊ የሰላም ዋስትናችን ነው ብሎ ማስቀመጥ ተገቢ ይሆናል፤ ህገ-መንግስቱ አዲስቷን ኢትዮጵያ የፈጠረና እየገነባ የሚገኝ ሰነድ መሆኑም በተመሳሳይ። ህገ-መንግስቱ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ድንጋጌዎችን ከአገራችን ተጨባጨ ሁኔታ ጋር አገናዝቦ ያስቀመጠና የተቀበለ ከመሆኑም በላይ ከሰው ልጆች ተፈጥሮዋዊ ድንጋጌዎች የሚመነጩ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ያካተተ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ያስከበረ፤ ዜጎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በዕድሜ፣ በፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ አድልዎና ልዩነት ሣይኖራቸው በህግ ፊት እኩል የሚሆኑበት ድንጋጌዎችንም ያካተተና በተግባርም የቀየረ በመሆኑ የአገራችን ህዝቦች የሰላምና ደህንነት ጥያቄዎች በመሠረታዊ መልኩ እንዲፈታ አስችሏል፡፡

 

ህገ-መንግስቱ ባጐናፀፈው ድልና ስኬት የአገራችን የመንግስት አደረጃጀቱም ፌዴራላዊ የመንግስት ቅርፅ እንዲይዝ በመደረጉ ይህም በዋናነት የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ማንነታቸውንና አሰፋፈራቸውን ማዕከል ያደረገ አስተዳደራዊ አደረጃጀት ተፈጥሮላቸው አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበትና የሚያለሙበት፤ ከልማቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት የተፈጠረ ከመሆኑም በላይ በፌዴራልና በየደረጃ ባሉ የፖለቲካ መድረኮችና የህዝብ ምክር ቤቶች በመርህ ላይ የተመሠረተ ውክልና እንዲኖራቸው በማደረጉና ይህም በተግባር ውጤት ያመጣ በመሆኑ የአገራችን ህዝቦች የሰላምና ደህንነት ጥያቄያቸው እንዲፈታ አስችሏል። ያለፉትን 10 አመታት የሰላም ሁኔታ ለማወደስም ሆነ ለመንቀፍ መነሻና መሰረቱ ሊሆን የሚገባው ይኸው ህገ መንግስት ነው መባሉ ከላይ ስለተመለከቱት መሰረታዊ አጀንዳዎቹ ነው።

 

በዚህ አግባብ ያለፉትን 10 አመታት ስናወሳ ከውስጥ ያሉ አክራሪ የጥበትና የትምክህት ሃይሎች በውጭ ከሚገኙ አሸባሪ ቡድኖች ጋር በተናጠልና አንዳንዴ በጋራ የሽብር አደጋ በተደጋጋሚ ለመፈፀም የሞከሩ ቢሆንም በወሳኝ መልኩ የፀጥታ መዋቅሮች በጋራና በቅንጅት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሠሩት ጠንካራ ሥራ የአገራችን ህዝቦች የሠላምና ደህንነት ሁኔታ አስተማማኝ እንዲሆን ማድረግ የተቻለባቸው አመታት ነበሩ ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይህ ሙከራ በተለይ 2008  ላይ ሰፋ ባለ መልኩ የተጠናከረ የነበረ ቢሆንም በተመሳሳይ ህዝቡና መንግስት ባደረጉት የተጠናከረ ዘመቻ ሊከሽፍ ችሏል። ያም ሆኖ ግን ሰላማችንን ለማወክ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉት ሃይሎች መነሻና አጀንዳ ኪራይ ሰብሳቢ የሆኑ የመንግስት አስፈጻሚዎች የፈጠሯቸው ቀዳዳዎች የነበሩ መሆኑ በድክመትነት ሊነሳ የሚገባው  መሰረታዊ ነጥብ ነው። አሁንም እነዚህን ከመልካም አስተዳደር እና ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር ተያያዥ የሆኑ ቀዳዳዎችን መድፈን ካልተቻለ ለማይተኙት አክራሪ፣ ትምክህተኛ እና የጥበት ሃይሎች እድሉ የሚሰፋ እና ሰላማችን አደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የእርምት እርምጃ ስለሰላም ቀን ሊወሰድ ይገባል።

 

የውጭና የደህንነት ፖሊሲው ላይ በግልፅ እንደተጠቀመው መነሻው ውስጣዊ ሁኔታ ሲሆን ይህም የትኛውም ጉዳይ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማሸነፍ የሚደረግ ሥራና እንቅስቃሴ መሆን እንዳለበት የተቀመጠው አቅጣጫ ለሰላማችንም ዓይነተኛ ዋስትና ነበር ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ድህነትና ኋላ ቀርነት ሥር በሰደደበት ህብረተሰብ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር አይችልምና፡፡

 

ሌላው ትኩረቱ ከየትኛውም አገር የሚኖረን ግንኙነትና ትስስር በሰላም አብሮ በመኖርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ እንደሆን እንዲሁም አንዱ በሌላኛው የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር የሚያስረግጥ በመሆኑ ከጐሮቤቶቻችንም ሆነ ከሌሎች የዓለም አገሮች የውጭ ግንኙነታችን ሰላማዊ እንዲሆን ያስቻለና በዚህም ያለፉት 10 አመታት በተለየ ሰላማችን በማይናወጽ መሰረት ላይ የቆመ መሆኑን ያረጋገጥንበት  አመታት ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ ጀግናው መከላከያ ሃይላችን የአገራችንን ሠላም ከማረጋገጥ በተጨማሪ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ከመሆኑም በላይ የአገራችንንና የህዝባችን ገፅታ በበጎ እንዲገነባ በማድረግ ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

 

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የክፍለ-አህጉሩ ክፍል የአፍሪካ ቀንድ በመሆኑና ይህ አካባቢ ደግሞ በተለያየ ምክንያት የሰላምና መረጋጋት እጦት እየተጋረጠበት የሚገኝ አካባቢ ሲሆን ይህንን ጀግናው መከላከያ ሃይላችን ኃላፊነቱን ተረክቦ ግዳጁን በብቃት ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል፡፡  

 

ሌላው በአገራችን ከባለፉት 10 አመታትም አስቀድሞ የነበሩትና ባሳለፍናቸውም 10 ዓመታት ለሰላማችን እጅግ ጠንቅ ሆኖ የቆዩት አገር በቀል አሸባሪ ድርጅቶች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ኦነግ፣ ግንቦት 7፣ አርበኞች ግንባር፣ አብነግ እና ሌሎች ተመሳሳይ የሆኑና የሻዓቢያ መንግስት ተላላኪዎች ሲሆኑ ዋንኛ ተልዕኮዋቸውም የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች የተቀዳጁትን ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት ማፍረስ ነው፡፡ ይህንን የተረዳው መንግስታችን የሽብርና የጠላት ተልዕኮን ለመከላከል የሚያስችል ፖለቲካዊና ህጋዊ ሥርዓቶች በመዘርጋት ትክክለኛ የትግል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በተለይም በአገራችን ተግባራዊ የሆነው ፀረ-ሽብር አዋጁ የእነዚህን አሸባሪ ድርጅቶችንና ተላላኪዎችን ቅስም የሰበረ ከመሆኑም በላይ የፀጥታ ሃይሎችና ህዝቡ የተባበረ ትግል እንዲያደርግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተበት ስለሰላም ቀን ሊጠናከር የሚገባው አቅጣጫ ነው።

 

የአገራችንና የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እነዚህ አሸባሪና ፀረ-ሰላም ድርጀቶችና ቡድኖች የህዝቡን ህይወት የሚቀጥፉ የሽብር እርምጃዎች ለመውሰድ በርካታ ጊዜ ሞክረዋል፤ በአንዳንዶቹ እርምጃዎች ንፁሃን ዜጎች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፤ ቀላል የማይባል ንብረትም የወደመበትን ክስተት ስለሰላም ቀን ማስታወስ ተገቢ ነው። ስለሆነም የህዝቡን የሰላምና ደህንነት ጥያቄ በበቂ መጠን ምላሽ ለመስጠት የጥቃቱ ተጋላጭ የሚሆነው እና መሆኑም በተደጋጋሚ የተረጋገጠው ወጣቱ ትውልድ ለሰላምና ፀጥታ መስፈን የተከፈለውን ዋጋ እንዲያውቅ ማድረግ ወሳኝና እሱም ይህንን ሰላም ተረክቦ ወደፊት ማስቀጠል ይጠበቅበታል።

 

በጥቅሉ ያለፉት 10 ዓመታትን በሰላም ቀን መነጽር ስንመለከተው የአገራችን ህዝቦችና የፀጥታ ሃይሎች በሰጡት ትኩረትና በከፈሉት መስዋዕትነት ሃገራችን የተረጋጋ የሰላም ባለቤት ለመሆን ችላለች። በዚህም የአገራችን ህዝቦች ሙሉ ቀልብ ወደዋንኛው ጠላታችን ድህነት ላይ ሆኗል። ስለዚህም ነው ባለፉት ተከታታይ 10 ዓመታት  ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ ሃገራት ተርታ በመሰለፍ የአለምን ቀልብ ለመግዛት የቻልነው። አገራችን የምትገኝበት ቀጠና በአብዛኛው ሠላም የታጣበት ሆኖ እያለ ብቸኛዋ የቀጠናው ሰላም ምንጭ በመሆን የራሷን ሰለም ከማረጋገጥ አልፋ ለቀጠናው የሰላም ተስፋ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ይህ የሰላም አቅጣጫ  ለኢትዮጵያ ከፍታ በተከፈለ መስዋእትነትም የተረጋገጠ ነውና የአገራችን ህዝቦች አደራ በመሆኑ በፀጥታ ሃይሎቻችንና በህዝቡ የተጠናከረ ተሳትፎ ሊቀጥል፤ ስለሰላም ቀን ሲባልም ሊዘከር የሚገባው ያሳለፍናቸው 10 ዓመታት ምርጥ ተሞክሮ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy