Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኤችአይቪ/ኤድስ ዳግም ግርሻት

0 951

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኤችአይቪ/ኤድስ ዳግም ግርሻት

                                         ይነበብ ይግለጡ

ኢትዮጵያ ኤችአይቪ/ኤድስን በስፋት በመከላከልና ስርጭቱን በመግታት ረገድ  በታሪክ የተመዘገበ ትልቅ ውጤት ለማስመዝገብ በቅታ ነበር፡፡ ሀገርና ትውልድን ከሚያራቁተው ገዳይ በሽታ ለመከላከል ታላቅ ርብርብ አድርጋለች፡፡ የጤና ፖሊሲዋ ትውልዱን ለመታደግ ሰፊ አስተዋጽኦ አድርጎአል፡፡

በኤችአይቪ/ኤድስ ምክንያት ሀገራችን ምን ያህል ዜጎቿንን ስንትና ስንት ተስፋ የሚጣልባቸው የሀገር ሀብት የነበሩ ወጣቶቿን እንዳጣች፤ ሕጻናት ያለአባትና ያለእናት እንደቀሩ፤ የስንቶች ቤት እንደተዘጋ፤ አዛውንትና አሮጊቶች በመጦሪያቸው ዘመን እንደገና በስተእርጅና አባት እናት ያጡ የልጅ ልጆችን ለማሳደግ እንደተገደዱ ትላንትን ለሚያስታውስ ሁሉ ልብን የሚሰብርና አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡

ድፍን ሀገርና ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ ለስንት የሚበቁ ጎበዛዝትን አይኑ እያየ  በኤችኤቪ/ኤድስ ተነጥቆአል፡፡ በኤችኤቪ/ኤድስ ምክንያት በሀገራችን የወጣት እልቂት ወርዶአል፡፡ እድሮች በቀብር እስኪጨናነቁ ድረስ ከቀበሌ ቀበሌ ከመንደር መንደር ሕዝብ በእንባ ታጥቧል፡፡ይህን ችግር በሀገር ደረጃ ለመመከትና እንባን የሚያደርቅ ስራ የተሰራው መንግስት ታላቅ ርብርብ አድርጎ ኤችኤቪ ኤድስን ለመከላከል ሰፊ ብሔራዊ ዘመቻ በማድረጉ፤ ብሔራዊ ሚዲያውም ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ በመቻሉ ነው፡፡

በመንግስት ደረጃ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየድርጅቱ፣ በቀበሌና ገበሬ ማሕበራት ጭምር ሕብረተሰቡን ከማሳወቅ አኳያ ሰፊ ስራዎች መስራት በመቻላቸው ነው ትውልድን መታደግ የተቻለው፡፡ መድሀኒት የለውም የሚለው ስጋት ምድር አንቀጥቅጥና አስፈሪ በነበረበት ወቅት መንግስት የእድሜ ማራዘሚያ መድሀኒቱ አቅም በፈቀደ መሰረት ከውጭ በማስገባት ዜጎች እንዲያገኙ ለማድረግ ተችሎአል፡፡

በመላው ሀገሪቱ ባሉ ተቋማት ማለትም በትምሕርት ቤቶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል የሚያስችል ሰፊ የማስተማር ስራ ተሰርቶአል፡፡ በማስታወቂያ፣ በኪነጥበባት (በትያትርና በድራማ፣ በግጥም፣ በቢል ቦርድ)፣ በራሪ ጽሁፎችን በማዘጋጀት፣ የውይይት ክበባትን በማደራጀት እጅግ የላቁ ስራዎች በመሰራታቸው ነበር የኤችአይቪ ስርጭትን ትርጉም ባለውና ውጤታማ በሆነ መልኩ በሀገር ደረጃ መቆጣጠር ተችሎ የነበረው፡፡

እነዛን ድፍን ሀገር ሙሉ በእንባ የተራጨባቸውን፣ ማቅ የለበሰባቸውን መንደር ከመንደር፣ ሰፈር ከሰፈር በለቅሶና በዋይታ ሲጮህ ውሎ ሲጮህ ያድርባቸው የነበሩትን አመታት አንረሳም፡፡ በፍጹም የሚረሱም አይደሉም፡፡ ዳግም ልናየውም  አንፈቅድም፡፡

ኤችአይቪ/ኤድስ በተለይ የሚያጠቃው ወጣቱንና ሀገር ተረካቢ የሆነውን ክፍል ነው፡፡ ወጣቱ ደግሞ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ አምራች ወዛደር፣ ገበሬ፣ መምህር፣ መሀንዲስ፣ ወታደር፣ የቢሮ ሰራተኛ፣ የጤና ባለሙያ፣ ሾፌር፤ የቀበሌ፣ የክፍለ ከተማ፣ የክልል ወዘተ ሰራተኛ ሁኖ ሀገሪቱን እንደማገርና ምሰሶ፣ እንደወጋግራ ጭምር አቅፎ ያያዘ ትልቁ ግዙፍ ኃይል ነው፡፡ ዛሬም እንደቀድሞው ብሔራዊ ዘመቻ ከፍተን ካልተከላከልነው፤ ፈጥነን ካልተረባረብን ዳግም በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ያለ ሀገራዊ አደጋ ሁኖ ተጋርጦአል፡፡ ዳግም እንዲያገረሽ ያደረገውም መዘናጋታችን፣ ጥንቃቄ አለማድረጋችን ነው ፡፡

ዳግም ለመስፋፋቱ ዋነኛው ምክንያት በወጣቱ በአጠቃላይም በሕብረተሰቡ ውስጥ በሽታው የለም የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መደረስና ልቅ ወሲብ መፈጸም፤ ቀደም ሲል በስፋት ሲሰጥ በነበረው ትምህርት መሰረት የመከላከያ ኮንዶም አለመጠቀም፤ የአደገኛ እጾች ተጠቃሚ መሆን፤ በመላው ሀገሪቱ የጭፈራና የምሽት ቤቶች ገደብ በሌለው ሁኔታ መበራከት በዚህም የንግድ ወሲብ በአደገኛ ሁኔታ መስፋፋቱ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በከተማም ሆነ ከገጠር ወጣት ልጃገረዶች ከቤተሰብ እየፈለሱ በየቡና ቤቱ ለወሲብ ንግድ መሰማራታቸው ለዚህ ስራ የተሰማሩ ደላሎች በስፋት መኖርና ልክ እንደ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ወጣት ሴቶችን እያደፋፋሩ እየደለሉ ወደዚህ ስራ እንዲገቡ በማድረግ የገንዘብ ማግኛ አድርገው መጠቀሚያ ማድረጋቸውም ሌላው፣ ለዳግም ግርሻው ምክንያት ነው፡፡

መንግስት በተወሰነ ደረጃ ለመከላከል ጥረት ያደረገ ቢሆንም ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ የውጭ የወሲብ ፊልሞች በብዛት በከተሞቻችን መሰራጨታቸው፤ ወጣቱ በፍላሽ፣ በሲዲ እያደረገ ይሄንን ከባሕላችን ተጻራሪ በሆነና ትውልድን ከስነምግባር ውጭ የሚያደርግ የውጮቹን ርካሽ ባሕል የራሱ ለማድረግ የሚያደርገው ሩጫ ስልጣኔም እየመሰለው በሚደርገው ተግባር ጭምር የኤችአይቪን አደጋ እንዲከፋና ዳግም እንዲዛመት አድርጎታል፡፡

የዘመኑ ሶሾል ሚዲያና ኢንተርኔትም አደገኛ የዝሙት ባሕሎችን በማስፋፋት ረገድ ሰፊ አስተዋጽኦ አድርጎአል፡፡ በዚህ መልኩ በባእድ የባሕል ወረራ ውስጥም ወድቀናል፡፡ አፍ አውጥቶ ለመናገር የሚደፍር ቢታጣም ግብረ-ሰዶማዊነትም በአሳሳቢ ሁኔታ ስር እየሰደደ  ይገኛል፡፡ የሴቶች መደፈር ብቻ ሳይሆን የወጣት ወንዶች መደፈርም በተለያዩ ግዜዎች ሲሰማ ቆይቶአል፡፡ ይሄ ሁሉ በእኛ ውስጥ ያልነበረና የማናውቀው ነው፡፡

በውጭ የባሕል ወረራ ስር ወድቀናል ስንል ሁሉን ኃላፊነትና እዳ ውግዘት መንግስት ላይ ብቻ የሚጥሉ ወገኖች በእጅጉ ተሳስተዋል፡፡ በመሰረቱ ይህን መከላከል በዋናነት የሕብረተሰቡ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግስት እንደመንግስት መወጣት ያለበት የግዴታና ኃላፊነት አለ፡፡ የቴክኒዮሎጂው መስፋፋትና ማደግ መልካም ነገሮችን ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የማይበጁ አጥፊ ነገሮችንም ይዞ እንደሚመጣ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ የራስዋ የሆነ የተከበረ የየብሔር ብሔረሰቡ ባሕልና ስርአት ያላት ጥንታዊት ሀገር ነች፡፡ ከውጭ የሚገቡ የመጡ በሕብረተሰባችን ውስጥ ልቅ በሆነ ሁኔታ እየተስፋፉ በተለይ የወጣቶቻችንን ስነልቦናና ቀልብ እያሸፈቱ የራሳቸው የሆነውን ሁሉ እንዲረሱ የሚደረገውን ጉዞ ተረባርበን ልንገታው ካልቻልን ዛሬ ላይ ተመልሶ እያገረሸ ያለው ኤችአይቪ/ኤድስ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ተያያዥ ችግሮችም ሰለባ መሆናችን አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ችግር መንግስት የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ቻይና ከውጭ ሀገራት በገፍ የሚገቡት የወሲብ ሲዲዎችና ፊልሞች ዜጎችዋን በአደገኛ የባሕል ወረራና ብልሹነት ውስጥ እየከተተ ቢያስቸግራት ነው ከውጭ የገቡ የወሲብ ሲዲዎችንና ፊልሞችን በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ሰብስባ በአደባባይ በእሳት ያነደደችው፡፡ ይህንንም መላው አለም እንዲያየው አድርጋለች፡፡ በእርግጥ ይህ ግዜያዊ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው አስከፊነቱን በሀገር ደረጃ ማስተማርና ማሳወቅ ነው፡፡

ተተኪውን ትውልድ ለመበከል በውጭ ኃይሎች የሚሰራው ስውር የአጥፊነት ስራ ሀገርንም ትውልድንም ቀስ በቀስ እንደሚገል መረዳቱ ተገቢ ነው፡፡ ትውልዱ የራሱን ባሕል እንዲከተል በራሱ እንዲኮራ የማድረግ ሰፊ ስራ መስራት ከሕዝብም ከመንግስትም ይጠበቃል፡፡ ትላንት መንግስት ሰፊ ርብርብ አድርጎ በማስተማርና በማሳወቅ የስርጭት አድማሱ እንዲገታ ያደረገው እስከስሙም ብዙ የማይነሳ የነበረው ኤችአይቪ/ኤድስ ዳግም በሀገራችን ላይ የአደጋ ጥላውን አጥልቷል፡፡ እንደ ሰደድ እሳትም እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ከቀድሞው ልምድ በመቀመር በብሔራዊ ደረጃ ልንዘምትበት ትውልዱንም ልንታደግ ግድ ይላል፡፡

በቅርብ ግዜያት ጋምቤላ ከተማ በኤችአይቪ ስርጭትና መስፋፋት ቀይ የአደጋ ቀጠና ውስጥ የነበረች ሲሆን ዛሬ ደግሞ አዲስ አበባ የመሪነቱን ቦታ ይዛለች፡፡ ሌሎች ታዳጊ ከተሞቻችንም በዚሁ መስመር ውስጥ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገራችን ትልቅ ፈተናና አደጋ ነው፡፡ ትውልዱን ከመፍጀቱ በፊት መንግስትም ሕዝብም በመረባረብ ስርጭቱን ለመግታት እንደገና ብሔራዊ ዘመቻ መክፈትና ታላቅ ርብርብ ማድረግ የወቅቱ ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ቀድሞ በሀገሪቱ ፕሬዚደንት ይመራ የነበረውንና ድምጹ የጠፋውን የብሔራዊ ኤችአይቪ/ኤድስ ሴክሬታሪያት ዳግም ንቁ ሁኖ ስራውን እንዲጀምር ማድረግ ወሳኝም አስፈላጊም ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy