Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ“ይቻላል” መንፈስን የፈጠረ ታላቅ ፕሮጀክት!

0 417

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ“ይቻላል” መንፈስን የፈጠረ ታላቅ ፕሮጀክት!

ኢትዮጵያ እያስመዘገበቻቸው ካሉ  በርካታ ድሎች መካከል ቢሊዮን ዶላርን ወጪን የሚጠይቀውና  ግንባታው በራስ አቅም እየተካሄደ ያለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አንዱና ዋንኛው  ነው። ይህ ፕሮጀክት ከሌሎች የልማት ስራዎቻችን በበርካታ መልኩ የተለየ ነው።  የመጀመሪያው  ጉዳይ  የሁሉንም  ኢትዮጵያዊ  ቀልብ  የገዛና መሆኑና  የሁሉም አሻራ ያረፈበት  መሆኑ እንዲሁም ወጪው እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም  ሙሉ ለሙሉ  በውስጥ አቅም ብቻ የሚገነባ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው መስራት በመቻላቸው  ይህን በታዳጊ አገር አቅም  መገንባት አይታሰብም  የተባለውን  ግዙፍ ፕሮጀክት አሁን ላይ ከ60 በመቶ በላይ  ማድረስ  ችለዋል። እየተደረገ ያለው ህዝባዊ  ድጋፍ የሚያመላክተው የፕሮጀክቱ  ግንባታ  በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ በእርግጠኝነት መናገር የሚያስችል ነው።  

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከሃይል ማመንጫነቱ ባሻገር የአንድነታቸውና የትብብራቸው ማሳያ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ፕሮጀክት ነው። እንደኔ እንደኔ  ይህ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያዊያን  መለያ (ብራንድ)  ነው። ምክንያቱም የእያንዳንዱ ዜጋ  አሻራ ያረፈበት  ፕሮጀክት በመሆኑ  ነው።  ይህ  ታላቅ ፕሮጀክት  በመጋቢት  24 ቀን 2003 ዓ ም  ዕቅዱ  ይፋ ሲደረግ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ከጫፍ እስከ ጫፍ  ግልብጥ ብላው በመውጣት  ድጋፋቸውን  አሳይተዋል። ይህንንም በተግባር አረጋግጠው አይቻልም የተባለውን ፕሮጀክት ወደማጠናቀቁ  እያንደረደሩት ይገኛሉ።   

ይሁንና ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና አንዳንድ ወዳጅ  አገራት ሳይቀሩ  ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር  እንዲህ ያለ የባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪንና  ልምድ የሚጠይቅን  ፕሮጀክትን እንደኢትዮጵያ ያለች ደሃና ታዳጊ አገር ልትሰራው አትችልም የሚል ግንዛቤ አድሮባቸው ነበር። በእርግጥ እነዚህ አገራት እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ቢፈጠርባቸው  የሚገርም አልነበረም። ምክንያቱም  ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ በዓለም ህዝቦች ዘንድ ትታወቅ የነበረው በጦርነት፣ ረሃብና ድርቅ እንጂ በመልካም ጎኗ አልነበረም። ይህ ሁኔታ በዚህ ትውልድ በመቀየር ላይ ነው።  

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአገራችን ዴሞክራሲያዊ  መንግስት መገንባት  በመቻሉ መንግስትና ህዝብ  ትኩረታቸውን  ድህነትን መዋጋት ላይ ማድረግ በመቻላቸው የአገራችን ገጽታ እጅጉን ተቀይሯል። ከፍተኛ  የሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎችን  ለአብነት ከፍተኛና  ተከታታይነት  ያለውን ድርቅ  በራስ አቅም መቋቋም   ተችሏል።  በአገራችን  ዘላቂ  ሰላም ማስፈን  በመቻሉና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት  መገንባት  በመቻሉ አገራችን  በአፍሪካ ግንባር ቀደም የኢንቨስትመንት ማዕከል ለመሆን  በቅታለች።  የወቅቱ የአገራችን   ሁኔታ  የሚያረጋግጠው  መንግስትና ህዝብ  ተቀራርበው መስራት  ከቻሉ የማይቻል ነገር እንደሌለ ነው። ለዚህ  ጥሩ ማሳያ  የሚሆነው   ታላቁ  የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት እውን እየሆነ ያለው መንግስት ህዝቡን ማሳመን መቻሉና ህብረተሰቡን  በፍላጎቱ ከጎኑ ማሰለፍ በመቻሉ ነው። ህዝብ ያመነበት ፕሮጀክት ሁሌም ህዝባዊ ድጋፍ እንደሚኖረው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጥሩ ማሳያ ነው።   

ታላቁ መሪ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የዚህን ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በጣሉበት ወቅት ህብረተሰቡን ከመንግስት ጎን ሊያሰልፍ የሚችል ታላቅ ንግግር አድርገው ነበር። ይህ ንግግር ለእኔ ታላቅና መሳጭ ነበር።  “ያሉን ሁለት አማራጮች ናቸው፤ አንድም ይህን ግድብ በራሳችን አቅም መገንባት አሊያም ግድቡን ያለመስራት፤ ይሁንና የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ግድብ በራሳችን አቅም እንገነባለን እንደሚል ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም” ሲሉ ተናግረዋል ነበር። አዎ ታላቁ መሪ የህዝባቸውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ጠንቅቀው የሚያውቁና በህዝባቸው የሚተማመኑ  መሪ በመሆናቸው  የህብረተሰቡን ትክክልኛ ምላሽ ስለሚያውቁ ነበር።  

በአባይ ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት የኢትዮጵያዊያኖች የዘመናት ቁጭት  ነው። ምክንያቱም የተለያዩ የግብጽ መንግስታት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ልማት እንዳታካሂድ  የተለያዩ ነገሮችን ሲያደርጉ  መቆየታቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው።  ግብጽ አባይን ለውስጥ የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያነት ሲገለገሉበት እንደነበር እንዲሁም የግብጽ ህዝብ የኢትዮጵን መንግስትና ህዝብ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱት ያላደረጉት ጥረት አልነበረም።  ግብጻዊያን የአባይ ውሃ ለብቻቸው እንደተሰጣቸው አድርገው በመቁጠር    የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የአባይን ውሃ እንዳይጠይቁ ወይም እንዳያለሙ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም።  በግብጽ ስውር እጆች ሳቢያ  ኢትዮጵያ አባይን ለማልማት ብድርም ሆነ እርዳታ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንደማታገኝ የአደባባይ ሚስጢር ነው።  ይህን የተረዳው የኢትዮጵያ መንግስት  ግንቦት ሃያ 20ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት ታላቁ መሪ በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰበው  ህዝብ እንዲህ  ብለው ነበር።  “ግንበኞቹም እኛው፣  መሃንዲሶቹም እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮቹም እኛው” ሲሉ ይህ ፕሮጀክት የኛው በኛው  የሆነ ፕሮጀክት መሆኑን  አሳይተዋል።  

ኢትዮጵያ ይህን ፕሮጀክት ዕቅድ ካስተዋወቀች ጊዜ ጀምሮ የምታራምደው አቋም  ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል የሚል መርህን ነው። የአገራችን  የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በአገራት መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መርህን የተከተለ በመሆኑ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብንም በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም  የሁሉንም የተፋሰስ አገራት ህዝቦች መካከል “ፍተሃዊ የወሃ ክፍፍል” እንዲነግስ  የሚያስችል  ነው። ይህ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሚሰጠው ጥቅም ባልተናነሰ ለታችኞቹ የተፋሰስ  አገራት በተለይ ለሱዳንና ግብጽ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ ነው። ይሁንና የዚህ ፕሮጀክት ወጪ ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ነው።  እስካሁን የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ  ምንም የውጭ ብድርም ሆነ እርዳታ ባልተገኘበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእውቀታቸው፣ በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸው፣ በቁሳቁስ አቅርቦት ብቻ ሁሉም በሚችለው ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፉቸውን በመቸራቸው ግንባታውን ከ60 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል።

ኢትዮጵያ የተከተለችው “ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ” መርህ የትኛውንም የተፋሰስ አገራት ላይ እዚህ ግባ የሚባል ጉዳት ሳያደርስ  የውሃው ምንጭ የሆነችውን አገር መጥቀም የሚያስችል ነው። ይህ የአገራችን  ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል መርህ በአብዛኛዎቹ የተፋሰሱ አገራት ሳይቀር አድናቆትን የተቸረው መርህ  ነው። ይህ ግድብ ለእኛ ኢትዮጵያዊያኖች “የአይቻልም መንፈስን የሰበረ” የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የትብብር ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

አገራችን ከድህነት በፍጥነት ልትመጣ የምትችለው እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ስትችል ብቻ ነው።  ይህን ታላቅ አገራዊ ፕሮጀክት ከዳር ለማድረስ ህብረተሰቡ እስካሁን  እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ህዝብና መንግስት መተባበር ከቻሉ የማይፈፅመው ነገር እንደሌለ  ይህ ፕሮጀክት ጥሩ  ማሳያ ነው። አሁን ላይ የአገራችን የሃይል አቅርቦት ከ4300 ሜጋ ዋት በላይ ቢያድግም አሁንም በሃይል ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ከፍትኛ ክፍተት ይታያል። የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል በየዓመቱ 25 በመቶ የሃይል አቅርቦት ዕድገት ማሳየት ይኖርበታል።

ታላቁ  የህዳሴ  ግድብ ፕሮጀክት በሙሉ አቅሙ  ሃይል ማመንጨት ሲጀምር የአገራችንን የሃይል አቅርቦት ችግር ትርጉም ባለው ሁኔታ ይቀርፈዋል።  ከዚህም ባሻገር ቀሪውን ለጎረቤት ሀገራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ  ጭምር ይሆናል። ይህ ፕሮጀክት  ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ከምጣኔያዊ ጠቀሜታው በላይ  ፖለቲካዊ  እንድምታው  የጎላ ነው።  ይህ ፕሮጀክት የህዝቦች  የትብብራቸው ማረጋገጫ፣ የአብሮነታቸው ማሳያም ጭምር ነው። ታላቁ  የህዳሴ  ፕሮጀክት ለገጽታችን መለወጥ ጥሩ ማሳያ ከመሆኑም  ባሻገር  በሁሉም  ረገድ የአገራችንን የመደራደርና የመደመጥ  አቅምንም ያሳድገዋል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy