Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዲፕሎማሲው ስኬት

0 316

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዲፕሎማሲው ስኬት

ዳዊት ምትኩ

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ማሳያ በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ነው። በዚህ ረገድ ከሚሊኒየሙ ወዲህ የተመዘገበውን እድገት ሊጠቀስ የሚችል ነው። በተለይም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የውጭ ግንኙነት መርህም የአገሪቱን ገጽታ ለውጧል። በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተሰሚነቷንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ ማጎልበት ችሏል።

መንግስት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና የአገራችንን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር መንግስት ሳይታክት በመስራት ላይ ይገኛል። በተለይም ዋናውን ትኩረት በጎረቤቶች ላይ አድርጎ መስራቱ ከሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ጋር ሀገራችን ያላት ግንኙነት ጠንካራና በጥሩ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አስችሏል።

በተለይም በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ሀገሪቱ ወደ መልሶ ግንባታ እንድትገባና ህዝቡ መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ አዲስ ከተመረጠው መንግሥት ጋር እጅግ ተቀራርቦ ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን የከፋ ድርቅ ለመቋቋም ሀገራችን ካላት ውስን ሃብት ወንድም ከሆነው ከዚያች አገር ህዝብ ጋር ተካፍለን እንድንጠቀም በማሰብ ህዝቡን ለመታደግ ኢትዮጵያ እየሰራች ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ደቡብ ሱዳን ውስጥ እየከፋ የመጣውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በቅርቡ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የታወጀው ‘ብሔራዊ ንግግር’ ሁሉንም አካላት ያካተተ እንዲሆን የማበረታታትና ከሰላምና ፀጥታው ባሻገር የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ እንዳይሄድ የማድረግ ስራዎችን ሀገራችን እያከናወነች ነው።

በንግድና ኢንቨስትመንት ለመተሳሰርም ከዚህ ቀደም በሀገራችን በኩል እስከ እስከ ደቡብ ሱዳን ድንበር ድረስ የሰራነው መንገድ ወደ ሁለት የክልል ከተሞቻቸው እንዲራዘም የማድረግ ስራን የኢፌዴሪ መንግስት እንዲያከናውን በጁባ አስተዳድር በተጠየቀው መሰረት፤ አገራችን መንገዱ ሁለቱ አገራት ካላቸው ወዳጅነት ማጠናከሪያ እንዲሆን በማሰብ የኢትዮ-ደቡብ ሱዳን የወዳጅነት መንገድ በሚል ይሁንታዋን ሰጥታ ስራውን ገቢራዊ እያደረገች ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ አልፋ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከሩዋንዳና ከኡጋንዳ፣ ከታንዛንያና ከቡሩንዲ ጋር ያላት ግንኙነትም ጠንካራ ነው። ይህን በጎ የሆነ የሀገራችንን የሁለትዩሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠልም እየሰራች ነው።

አገራችን በምትመራው በኢጋድ በኩል እንዲሁም የአህጉራችን ፓን አፍሪካዊ ድርጅት ከሆነው የአፍሪካ ህብረት ጋር የምታደርገውን ተሳትፎ ይበልጥ እያጎለበተች ትገኛለች። ከዚህ ባሻገርም በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ የናይል ኢንሺየቲቭ ማዕቀፍ እንዲጎለብት አገራችን የጀመረችው ስራ ሂደቱን በማነቃነቅ ዙሪያ ኢትዮጵያ መጫወት የሚገባትን ሚና እንድትወጣ እየሰራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከአህጉራችን አልፎ ከመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በጋልፍ ካውንስል አገሮች ጋር የተጀመረውን መልካምና ጠንካራ ግንኙነት ከሀገራችን ዘላቂ ጥቅም አኳያ እየተቃኘ ቀጥሏል።

እንዲሁም ከምስራቁም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም ጋር አገራችን ያላት ስትራቴጅካዊ ግንኙነት በተደጋጋሚ የጉብኝቶች በማጎልበት የልምድ ልውውጥ የተገኘበት ነው። ከዚህ አኳያ ከቻይና፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከሲንጋፖርና ከቬትናም ጋር እየተደረገ ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ይጠቀሳል። ከምዕራቡ አገራት ጋርም ያላት ቁርኝት ከፍተኛ ነው። እነርሱም የአገራችን ልማት ደጋፊ በመሆን ከጎናችን አልተለዩም።

እነዚህ የአገራችን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ከምንም የተገኙ አይደሉም። ኢትዮጵያ ከምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነው። እንዲህ ዓይነቱ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ኢንቨስትመንትን መሳቡ አይቀርም።

ከዚህ አኳያ የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በአገሪቱ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ የሚደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱና በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ፖሊሲው በርካታ ባለሃብቶችን በመሳቡ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲስፋፋ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ይህን በመመርኮዝም የኢትዮጵያ መንግስት የግሉ ሴክተር በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ፋይዳ በመረዳት የኢንቨስትመንት አዋጁን በተያ ጊዜያት በመከለስ የበለጠ ተወዳዳሪ፣ ሳቢና ግልጽ በማድረግ አሻሽሎታል።

ይህም የውጭ ኢንቨስትመንቱ ሳቢና ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ለማድረግ ያለመ ተግባር ነው። በዚህም መንግስት ያቀደውን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ አይታበይም፡፡    

እርግጥ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሠላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የአገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተተኪ የሌለው ሚና እየተጫወተ ነው።

እነዚህ የዲፕሎማሲ ስኬቶች ይበልጥ እንዲያብቡና በቀጣይነትም የተዋጣለት ውጤት እንዲያመጡ ሁሉም በየፊናው አገሩን ማሰብና መጥቀም ይኖርበታል። የአገሩ ገፅታ ግንባታ የእርሱ የወደፊት መለያው፣ ዕድገቷ መጠቀሚያው እንዲሁም በበጎ መነሳቷ ኩራቱ መመሆኑን በማወቅ እያንዳንዱ የማንነቱ መገለጫ ለሆነች አገሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy