Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የጉልቻ መለዋወጥ…” እንዳይሆን

0 299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የጉልቻ መለዋወጥ…” እንዳይሆን

                                                        ታዬ ከበደ

አገራችን ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የፀረ ሙስና ትግል ግለሰቦች ለሰሩት ጥፋት ተጠያቂ ማድረግ በቀጣይም የሚከናወን ተግባር መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ሙስናን ከምንጩ ማድረቅ የሚቻለው አሰራር በመዘርጋት እንጂ ግለሰቦችን በመከታተል አይደለም። መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል ቁርጠኛ አቋም ያለው ለመሆኑ በርካታ ታላላቅ የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች ሳይቀሩ ለፈጸሙት ጥፋት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እያደረገ ከመሆኑም በላይ፤ ይህን ተግባሩን ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።  

ታዲያ የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነትና የፀረ ሙስና ትግሉ ግለሰቦችን በማሳደድ ብቻ ተፈላጊውን ለውጥ ያመጣል ማለት የዋህነት ይመስለኛል።  ሰዎችን በማሰር የሚመጣ አጥጋቢ ለውጥ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። የግለሰቦች እንጂ የአስተሳሰብ ለውጥን አያረጋግጥም።  እንደ  ዘላቂ መፍትሄም የሚቆጠር አይሆንም። አንዱን በሌላኛው መቀየር ብቻ ነው የሚሆነው። ልክ “የጉልቻ መለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” እንደሚባለው ዓይነት። እናም የመልካም አስተዳደር ችግር የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ተግባር ለማክሰም የአሰራር ስርዓትን መዘርጋት የሚመረጥ አማራጭ ነው።

እንደሚታወቀው በአገራችን የተጀመረውን የሰላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማደፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና ማለታቸው አይቀርም።

የሃገር ውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችና የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና የማይሹ የውጭ ኃይሎች ዓላማ ህገ መንግሥቱንና ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በመናድ ሀገራችን የጀመረችውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማደናቀፍ እንዲሁም የማያባራ ሁከትና ግጭትን በማቀጣጠል ሥርዓት አልበኝነትን ማስፈን መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህን ተልዕኳቸውንም ለማሳካት እንደ ምቹ ሁኔታ የሚወስዱት የራሳቸውን አቅምና ጥንካሬ ሳይሆን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የሚፈጥሩ ኃይሎችንና በችግሩ የሚማራሩ ወገኖችን በመሣሪያነት በመጠቀም ነው። ስለሆነም የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩትን ጥረቶች ማጠናከር ወሳኝ ነው።

በየትኛውም መስክ ለጥፋት የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ይገባል። የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በፅናት መታገል ያስፈልጋል።

ታዲያ ትግሉን በህዝብ ድጋፍ በማጀብ ማሳካትም ይቻላል። ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች እነማን እንደሆኑና በዕለት ተዕለት ህይወቱ የሚያጋጠመውን የመልካም አስተዳደር ችግርም ጠንቅቆ ያውቃል።

ስለሆነም ህዝቡን ማዕከል ያደረግ ትግል ይበልጥ ማካሄድ ተገቢ ነው። ህዝቡ በትግሉ ውስጥ እንዲሳተፍ ለማስቻል በአስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ህዝብን የሚያሳትፍ አሰራር መዘርጋት ይገባል። የአሰራር ስርዓት ከተዘረጋ እያንዳንዱ አስፈፃሚ ተግባሩን በስርዓቱ መሰረት እንዲፈፅም ያስችላል።

ኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ህዝቡ የአንበሳውን ድርሻ እንዲወስድ ማድረግ ያስፈልጋል። ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ቁርጠኛ አቋም እንዲይዝና የዘመቻው አካል ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም። እርግጥ መንግስትና ገዥው ፖርቲ መልካም አስተዳደር ጊዜ ስለሚወስድ ተግባሩን ላለማከናወን እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠዋል እያልኩ አይደለም።

እንዲያውም ላለፉት 26 ዓመታት መልካም አስተዳደር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ውስጥ ስር እንዲሰድ ዘርፈ ብዙ ጥረት አድርገዋል። አርኪ የሚባል ባይሆንም መልክ የማስያዝ ተግባራትን መከወናቸውን መካድ አይቻልም።

ዛሬ ላይም ቢሆን ከህዝቡ ጋር የተጀመረው የፊት ለፊት ውይይትን መሰረት በማደረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሲፈጥሩ በነበሩት አመራሮችና ፈፃሚዎች ላይ ርምጃ ወስደዋል፤ በመውሰድ ላይም ይገኛሉ። በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች…የተወሰዱት አስተማሪ ርምጃዎች ሁነኛ ማሳያዎች ይመስሉኛል። ይህ አሰራር በጎ ጅምር ነው። ይሁንና የአሰራር ስርዓትን መዘርጋት ይገባል።

በአሰራር ስርዓት የሚመራ ማንኛውም አስፈፃሚ በተቀመጠለት ህግና ስርዓት ብቻ ተግባሩን ይፈፅማል። በዚህ መንገድ ህዝባዊ አገልጋይነቱን የሚያረጋግጥ ማንኛውም አመራር ይሁን አስፈፃሚ ችግር የሚፈጥርባቸውን ቀዳዳዎችን ሊያገኝ አይችልም። ምናልባትም ቀዳዳዎች ካሉ መስሪያ ቤቱ በተገልጋዩ መገምገሙ ስለማይቀር የሚኖረው ክፍተት ይሸፈናል። ከህዝብ ዓይን የሚሰወር ነገር ስለማይኖር በየደረጃው የሚገኝ አስፈፃሚ ህዝብን አክብሮ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱ አይቀሬ ይሆናል። ያኔም የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቀረፋቸው አይቀርም።

እናም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ሰዎችን ከመቀያየር ባሻገር ያለውን ቁልፍ ተግባር መገንዘብ ይገባል፤ የአሰራር ስርዓትን የመዘርጋት ተግባር። የአሰራር ስርዓት በሌለበት ቦታ አስፈፃሚው አካል በዘፈቀደና እርሱ በሚመቸው መልኩ ብቻ ተግባሩን ሊከውን ይችላል። ይህ ደግሞ ሙስናን ለመሳሰሉ ብልሹ አሰራሮች በር የሚከፍት ነው።

የአሰራር ስርዓት እስካልተበጀ ድረስ ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል የሚቻል አይመስለኝም። አመራሩም ይሁን ፈፃሚው አካል በተቀመጠለት ስታንዳርድ መሰረት ተግባሩን ካልከወነ ህዝባዊ አደራን መወጣት አይቻልም።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ሰዎችን በመቀያየር ብቻ መልካም አስተዳደርን ማምጣት እንደማይቻል ግንዛቤ መያዝ ያለበት ይመስለኛል። ዋናው ጉዳይ ህዝቡን ማዕል ያደረገ የአሰራር ስርዓትን ፈጥሮ በህግና በስርዓት መመራት አግባብነቱ አጠያያቂ አይደለም።

እንደሚታወቀው ሁሉ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት እርምጃ ለመውሰድ ተንቀሳቅሰዋል።

በፌዴራልና በክልሎች በተካሄዱ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ በተገኘው ግብዓት መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ ያለ ምህረት እርምጃ ተወስዷል። በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ውስጥ ተዘፍቀው የህዝቡን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉ የነበሩት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም በቁጥጥር ስር ውለዋል። ተጠያቂም እየሆኑ ህግ ፊት ቀርበው ክስ እየተመሰረተባቸው ነው።

ሆኖም ግለሰቦችን ከኃላፊነት ቦታቸው በማንሳትና በማገድ ወይም እያሳደዱ በመክሰስ የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ የሚችል  አይመስለኝም። ምክንያቱም ጉዳዩ “የጉልቻ መለዋወጥ…” የሚባለው ዓይነት ባዶ ለውጥ ስለሆነ ነው። እናም የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻው ግለሰቦችን እያሳደዱ በማሰር ብቻ ተጠምዶ “የጉልቻ መለዋወጥ…” እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy