Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጎረቤቶቿ የተስፋ ምድር

0 323

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጎረቤቶቿ የተስፋ ምድር

                                                        ታዬ ከበደ

ሰሞኑን ኢትዮጵያ በስምንት ወር ውስጥ ብቻ 72 ሺህ 890 ስደተኞችን ተቀብላ ማስተናገዷን የዜና አውታሮች ዘግበዋል። በእነዚህ ወራቶች ውስጥ ብቻ 44 ሺህ ከደቡብ ሱዳን፣ 17 ሺህ ከኤርትራ እንዲሁም 6 ሺህ 400 ስደተኞችን ከሶማሊያ ተቀብላለች። ይህም በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የስደተኞች ብዛት ወደ  852 ሺህ 721 ከፍ አድርጎታል። ይህ የአገራችን መንግስትና ህዝብ ህዝባዊ ወገንተኝነት ተግባርና እንግዳ ተቀባይነት ባህል ኢትዮጵያን የጎረቤቶቿ የተስፋ ምድር እንድትሆን ያደረጋት ነው።

ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿ የተስፋ ምድር መሆኗ ሚስጢሩ ግልፅ ነው። የምትከተለው የስደተኞች ፖሊሲ የአንበሳውን ቦታ ይወስዳል። ኢትዮጵያ የምትከተለው ለጎረቤቶቿ ማረፊያ የመሆን መርህ በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ያስቻለ ከመሆኑም ባሻገር ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የተወሰደ ርምጃ ነው፡፡ ተግባሩም ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ወዳድ ህዝቦች መልካምና ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡

የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር ተመርኩዞ የተዘጋጀውና በአሁኑ ወቀት ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅ ላይ ብሎም ሀገራዊ ህልውናችንን እያረጋገጠ ብሎም ለጎረቤቶቻቸን መድን የሆነው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፤ የውስጥ ችግሮቻችንን በመቅረፍ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በጋራ ጥቅም እና ሰላም ላይ እንዲመሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ሀገራችን ሰላማዊ ልትሆን ችላለች። ይህን ሰላማዊነት በመመርኮዝም የጎረቤት ሀገር ህዝቦች ኢትዮጵያንና ህዝቧን እንደ መጠለያቸው እየቆጠሩ ነው።

ህዝብና መንግስት ‘ስደተኞቹ ባይቸገሩ አገራቸውን ጥለው አይመጡም’ በሚል ሚዛናዊና ህዝብን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ያለውን ከማካፈል ባሻገር፤ ስደተኞቹ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲሳተፉ እያደረጉ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ህዝባዊነት ከውስጣዊ ባህሪ የሚመነጭ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች ለስደተኞች እያደረጉ ያሉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከመደነቅ ባሻገር፣ ተገቢው ትብብርም ሊደረግላቸው የሚገባ ይመስለኛል።

ያም ሆኖ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የጎረቤት ሀገራት ህዝቦችን ችግር የሚካፈሉት ድጋፍ እንዲደረግላቸው አይደለም—ለህዝቦች ካላቸው ፅኑ ፍቅርና የአገራቱ ዜጎች በየአገራቸው የተፈጠረው ችግር እስኪረጋጋ ድረስ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው በመቁጠር ቢኖሩ ቀጣናውን የማረጋጋት አካል ሊሆን ይችላል ብለው ስለሚያስቡ እንጂ። በመሆኑም ሀገራችን ለውስጧ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት የቀጣናውን ሀገራት ህዝቦች የሰላም እጦትን ለማገዝ የምታደርገው ጥረት ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ በቀጣናው ሀገራት መካከል ሰላም ሰፍኖ ልማታዊ ትስስር እንዲጎለብት ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ውጤትም እያገኘበት ነው።

በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በየብስ፣ በባቡርና በሌሎች የመሰረተ-ልማት አውታሮች ቀጣናውን ለማስተሳሰር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ተጠቃሽ ናቸው። እናም መንግስት የቀጣናው ህዝቦች መቸገር አገራችን እንዲኖር የምትሻው ቀጣናዊ የልማት ትስስር እንዳይኖር ያግዳል ብሎ ስለሚያምንም  ጭምር ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን የትስስር ሁኔታ ሲከውን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው ሁለት መሰረታዊ የውስጣዊ ሁኔታ ሁነቶችን ተከትሎ ነው። መንግስት ሀገራዊ ህልውናን የማስጠበቁ ጉዳይ ሊሳካ የሚችለው ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ላይ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል።  

በከፍተኛ ኋላ ቀርነትና የድህነት አዘቅት ተዘፍቃ ለቆየችው ሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ግንባታና ሰላምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ወደ ተግባር ተሸጋግሮ ላለፉት 26 ዓመታት ተጉዟል።

በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም የማስገን፣ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን እውን የማድረግ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ምቹ ምህዳርን የመፍጠር ተግባሮችን ከውኗል።

አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ መንግስት ለአገራችን ሰላምና ልማት እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ፅኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ነው ብሎ ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ የአገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

አገራችን በምትከተለው ይህ የትብብርና የህዝባዊነት ማዕቀፍ አብዛኛዎቹ አጎራባች አገራት ኢትዮጵያን እንደ ራሳቸው አገር እንዲቆጥሯት አድርጓል። በእርስ በርስ ጦርነትም ይሁን አገራቸው ውስጥ ባለው የግፍ አገዛዝ ምክንያት በቀዳሚነት የሚመርጧት አገር ሆናለች።

በዚህም ምክንያት ስደተኞቹ ኢትዮጵያን “ሁለተኛዋ አገራችን” ሲሏት ይደመጣሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር በገዛ አገራቸው ውስጥ የመኖር ያህልም ይቆጥራሉ። መጪ ተስፋቸውንም ከዚህችው ባለ ተስፋ ሀገር ጋር የሚያቆራኙ ጥቂት አይደለም።

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተላቸው ማናቸውም ፖሊሲዎች ህዝብን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ቅድሚያም ለህዝብ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የሚሰጡና የሚጨነቁ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ውስጥ አድጎ በህዝብ የሰላ ትችት እየተመራና ራሱን በራሱ እያረመ ዛሬ ላይ የደረሰ በመሆኑ ህዝባዊ ወገንተኛ ነው።

ይህ ህዝባዊ ባህሪውም የየትኛውንም ሀገር ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያከብርና በእኩል ዓይን የሚመለከት ነው። በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ የአብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች የተስፋ ምድር መሆን ችላለች።

ጎረቤቶቻችን በእርስ በርስ ጦርነትም ይሁን አገራቸው ውስጥ ባለው የግፍ አገዛዝ ምክንያት በቀዳሚነት የሚመርጧት አገር ሆናለች። በዚህም ሳቢያ ስደተኞቹ ኢትዮጵያን “ሁለተኛዋ አገራችን” ሲሏት ይደመጣሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር በገዛ አገራቸው ውስጥ የመኖር ያህልም ይቆጥራሉ። መጪ ተስፋቸውንም ከዚህችው ተስፋይቱ ምድር ጋር እየተቆራኘ ነው።

አሁን ባለው መረጃ መሰረት በእኛ አቅም 852 ሺህ 721 ስደተኞችን መያዝ ቀላል ባይሆንም፤ ከሁሉም በላይ የሰው ልጅ ክቡር ነውና የአገራችን መንግስትና ህዝቦች ለስደተኞች የሚያደርጉት ክብካቤ የትኛውንም ወገን የሚያስደስት ነው። እናም ነገም ቢሆን ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር ሆና የአገራባች ህዝቦችን ስቃይ እንደምትሸከም ግልፅ ይመስለኛል። ይህን ፖሊሲዋን አትቀይርምና።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy