Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ያለ ግልፅ ጨረታ በ140 ሚሊዮን ብር የሚገነባው መንገድና ውዝግቡ

0 883

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጥገና የተደረገለት መንገድ ተገቢ አገልግሎት ሳይሰጥ ለብልሽት ተዳርጓል፤ 

የጋምቤላ ክልል በ2008 .ም ያዘጋጀው 10ኛው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ስኬታማ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ ለአብነትም የመሰብሰቢያ አደራሾች፣ ስታዲየም እና የእንግዳ ማረፊያዎች ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አዳዲስ የአስፋልት መንገዶች ሥራ እና ጥገና ተከናውኗል፡፡

በከተማዋ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ከተጀመሩት መንገዶች መካከል ያለ ግልጽ ጨረታ በ140 ሚሊዮን ብር የተገነባው መንገድ ግን የውዝግብ ምንጭ ሆኗል፡፡ በወቅቱ የመንገድ ግንባታ ሥራው በህጋዊ ጨረታ የወጣ ሳይሆን ከአምስት የማይበልጡ ተቋራጮችን በማናገር የተሻለ አፈፃፀም ያለውን በመምረጥ ነበር ለተቋራጩ የተሰጠው፡፡

የክልሉ መስተዳድር፣ አስቴር መንግሥቱ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭና ውሃ ነክ ሥራዎች ድርጅት እንዲሁም ኢቲጂ የተባለው አማካሪ ድርጅት የጉዳዩ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ተቋራጩ እና አማካሪው ክፍያ በአግባቡ አልተፈፀመልንም ሲሉ፤ ክልሉ ደግሞ የጥራት ችግር ስላለበት ለመክፈል እቸገራለሁ በማለት በመወዛገብ ላይ ይገኛሉ።

የጋምቤላ ክልል ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኦኬሎ ኦማን እንደሚሉት፤ ተቋራጩ መንገዱን ሲሠራ የተጠቀመውን ጠጠር በአግባቡ ባለመጠቅጠቁ መንገዱ ለብልሽት ተዳርጓል። ግንባታውም የተከናወነው በክረምት ወቅት በመሆኑ አስፋልቱ እንዳይጎዳ የውሃ ማስቀየስ ሥራው በውሉ ላይ ቢካተትም በአግባቡ አልተሰራም፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ሥራዎቹ በአግባቡ ከተከናወኑ ክልሉ ክፍያ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ይገልፃሉ።

የጋምቤላ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ አቶ ላክዴር ላክባክ በበኩላቸው፤ ተቋራጩ እና አማካሪው ድርጅት ከክፍያ ጋር የሚያነሱት ጥያቄ ተገቢነት የጎደለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሥራው የጥራት ጉድለት ስለነበረው ሙሉ ክፍያ አልተፈፀመም፡፡ በተጨማሪ ህዝቡ የተሠራው አስፋልት ወደ ጭቃ መቀየሩን አይቶ እያማረረ ነው፡፡

ይህንን እያየን ክፍያ መፈፀም የመልካም አስተዳደር ችግር መፍጠር ነው፡፡ሥራው መልሶ መሠራት እንዳለበት ከተቋራጩ ጋር መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ ግንባታው በአግባቡ ሲከናወን ክፍያው እንደሚፈፀም ይናገራሉ፡፡

አቶ ሙሉነህ አደሬ የኢቲጂ አማካሪ ድርጅቱ ተጠሪ መሐንዲስ ናቸው፡፡ ክልሉ ሥራውን በፍጥነት እንዲከናወንለት በመፈለጉ የመንገድ ሥራው በዝናብ ወቅትና በከፍተኛ ሩጫ የተሰራ ነው፡፡ የጥራት ጉዳይ በሚገባ የታሰበበት አይመስለኝም ይላሉ፡፡ የውሃ ማስቀየስ ዲዛይን ሥራም ከመጀመሪያው ዲዛይን እንዲቀየር በመደረጉ ለተቋራጩ በወቅቱ አልተሰጠም፡፡ አማካሪ ድርጅቱ ክልሉን ከአንድ ዓመት በፊት የተጠየቀው ክፍያ ባለመፈፀሙ ሥራውን አቋርጧል፡፡ 800ሺ የሚጠጋ ብር አልተከፈለውም፡፡ አሁንም ቢሆን የክፍያው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

አቶ አብርሃም ጌታሁን በአስቴር መንግስቱ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭና ውሃ ነክ ሥራዎች ድርጅት የሳይት መሐንዲስ ሲሆኑ፤ የጥራት ጉዳይ ለማስተባበል ካልሆነ በቀር ችግር የለበትም ይላሉ፡፡ «ሁሉም ግብዓት በላቦራቶሪ ተፈትሾ ያለፈ ነው፡፡ ሐምሌ 2007 .ም ነበር ሥራው የተጀመረው፡፡ በዚህ ወቅት መሰራቱ መንገዱን ሊጎዳው እንደሚችል በተደጋጋሚ በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡መሬቱ ከስር ረግረጋማ በመሆኑ መንገዱ ሊበላሽ ችሏል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚሄደው እና ከፍተኛ ብልሽት የደረሰበት ከመንገድ ዲዛይን እና ከመሸከም አቅም በላይ በርካታ ተሸከርካሪዎች በመንገዱ ተመላልሰውበታል፡፡ ይህም ብልሽቱ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ስለሆነም ተቋራጩ ሊወቀስ አይገባም» ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

አቶ እዮብ ታፈሰ የአስቴር መንግስቱ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭና ውሃ ነክ ሥራዎች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡16 ኪሎ ሜትር ቀድሞ የነበረ አስፋልት ጥገና እና አራት ኪሎ ሜትር አዲስ የመንገድ ሥራ ለማከናውን ውል ገብተናል፡፡ በተጨማሪም የክልሉን አምስት ብሄር፣ ብሄረሰቦችን ሊገልፅ የሚችል የአደባባይ እና ሐውልት ለመገንባት ተዋውለው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

«የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ሊከበር በመቃረቡ ሥራው በአስቸኳይ መከናወን እንዳለበት ከክልሉ መንግሥት ጋር ውል ገብተናል፡፡ ድርጅቱም እንደሚችል ተማምኖ ሥራውን ጀመረ፡፡ ምንም እንኳን ባለሙያዎች በክረምት ወቅት አስፋልት መንገድ መስራቱን ባይመክሩም፤ በፍጥነት መጠናቀቅ አለበት በሚለው የክልሉ ካቢኔ ውሳኔ 24 ሰዓት በመስራት በአምስት ወር ውስጥ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል፡፡በችኮላ በመሰራቱ ብልሽት ገጥሞታል» በማለት መንገዱ ለብልሽት የተዳረገበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

አቶ እዮብ እንደሚሉት፤ ከአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ውስጥ አንዱ ከመሃል ከተማ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያቀናው መንገድ ነው፡፡ ከዚህ መንገድ 200 ሜትር የሚሆነው አስፋልት ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በአስፋልቱ አካፋይ ለኤሌክትሪክ ምሰሶ መትከያ የሚሆኑ ጉድጓዶች ተቆፍረው ስለነበር ውሃው ውስጥ ለውስጥ በመሄድ አስፋልቱን ስለጎዳው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ግንባታ እያካሄደ በመሆኑ ከመንገዱ መሸከም አቅም በላይ የሆኑ ከባድ ጭነት የያዙ ተሽከርካሪዎች በመመላለሳቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡ ይሁን እንጂ ከጥራት ጋር በተያያዘ የሚነሳው ችግር ግን ከእውነት የራቀ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ቀድሞ የተሰጣቸው ዲዛይን በግለሰቦች ሆቴል ውስጥ ስለሚያልፍ ወደ ተግባር መግባት አልተቻለም፡፡ የውሃ ማስቀያሻ ሥራዎች በሚከናወኑበት ሥፍራዎችም ክልሉ እና አማካሪ ድርጅት በፍጥነት ዲዛይን ሰርተው ሊያስረክቧቸው ባለመቻላቸው አማካሪውና ክልሉ መናበብ አልቻሉም፡፡ ይህም ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሠሩ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ የውሃ ማስቀየስ የዲዛይን ሥራውም የተሰጣቸው በ2009 .ም ከሦስት ወር በፊት ነው፡፡ አንዳንድ ጥገና የሚያስፈልገው የመንገዱ አካልም በክረምት ጥገና መደረጉ ጉዳት እንደሚያመጣ ለክልሉ በደብዳቤ ቢያሳውቁም ሰሚ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡

«መሰራት ያለባቸው ሥራዎች ተከናውነውም ምንም ብልሽት ሳይከሰት ክልሉ 42 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ ተቋራጩ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ገብቷል፡፡ ማሽን ያከራዩ ባለንብረቶችና ሠራተኞች በድርጅታችን ላይ ክስ መስርተዋል፡፡ ለእስርም ተዳርገናል» በማለት ያስከተለባቸውን ኪሳራ ያስረዳሉ።

ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር ያላቸውን ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዳያከናውኑም ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ። በዚህ ፕሮጀክት በተፈጠረው ጫናም ድርጅቱ 47 ክሶችን ለማስተናገድ መገደዱን ጠቁመዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅትም ከ42 ሚሊዮን ብር ውስጥ ክልሉ ቀሪ 26 ሚሊዮን ብር ክፍያ ሊፈጽም አልቻለም፡፡ ሆኖም ድርጅቱ በራሱ ወጪ ማሽኖችን አስገብቶ የጥገና ሥራ ጀምሯል፡፡ ከክልሉ ጋር ርክክብ እስኪፈፀም ድረስ የተበላሸውን አስፋልት ለመስራትና ለመጠገን ግብዓቶችና ማሽኖች ተገዝተው ገብተዋል፡፡ በክረምት ሥራው ከተሠራ ችግር ስለሚፈጠር ከመስከረም በኋላ ለመስራት መዘጋጀ ታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት አሁን ወደ ውዝግብ ይግባ እንጂ በወቅቱ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባዔ እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሏክ ቱት የመልካም ሥራ አፈፃፀም የምስጋና ምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸውም ያስታውሳሉ፡፡ በመሆኑም ክልሉ ተገቢውን ክፍያ እንዲፈፅምላቸው ይማጸናሉ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy