Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግጭቱ የህዝቦች አይደለም

0 330

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግጭቱ የህዝቦች አይደለም

ብ. ነጋሽ

ሰሞኑን በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ አጎራባች አካባቢዎች መልካም ወሬ አይሰማም። በሁለቱ ክለሎች አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች ለንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋትና ከመኖሪያ አካባቢ መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግጭቶች አጋጥመዋል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ባሉት ዓመታት አሁን በምንሰማው ልክ ደም ያፋሰሰ ግጭት አጋጥሞ አያውቅም። በመሆኑም ሁኔታው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አስደንግጧል፤ አሳዝኗልም።

በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ አወሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት መንስኤ የድንበር ጉዳይ መሆኑ ይነገራል። ኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከምስራቅ እስከ ደቡብ ምስራቅ የሃገሪቱ አካባቢ የሚዘልቅ በሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚለካ ድንበር ይጋራሉ። በእነዚህ አዋሳኝ አካባቢዎች በማንኛውም ሁለት የተለያየ ማንነት ያላቸው ህዝቦች በሚዋሰኑበት አካባቢ እንደሚሆነው የቋንቋና የባህል መወራራስ አለ። ሁለቱ ብሄረሰቦች በመሃከላቸው ችግር ሲፈጠር የሚፈቱበት የጋራ ሸንጎ የሚመሰርቱበት ሁኔታ ሁሉ መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ በቦረና አካባቢ ለዘመናት የሚሰራበት የሁለቱ ብሄሮች የሃገር ሽማግሌዎች የሚወከሉበት ነጋ ቦረና የተሰኘው የግልግልና እርቅ ሸንጎ ለዚህ አስረጂነት ይጠቀሳል።

የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ አዋሳኝ አካቢዎች ነዋሪዎች በአመዛኙ በሁለቱም ወገን አርብቶ አደሮች ናቸው። የአርብቶ አደር አኗኗር ለከብቶች የግጦሽ ሳርና ውሃ ፍለጋ በመንቀሳቀስ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ የሁለቱ ብሄር አወሳኝ አካባቢ ነዋሪዎች ተንቀሳቃሽ መሆን ለዘመናት የግጭት መንስኤ ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለጸው ግጭቶች ሲፈጠሩ ሰላማዊ መፍትሄ የሚያገኙባቸው ባህላዊ ስርአቶች አሏቸው። በዚህ ምክንያት በሁለቱ ብሄሮች መሃከል ግዚያዊ ግጭቶች የሚነሱበት ሁኔታ የተለመደ ቢሆንም፣ በአብሮነታቸው ውስጥ ከግጭት ይልቅ አንድነታቸው ጎልቶ ይታያል።

በአዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች ያሉ የሁለቱም ብሄር አባላት አንዱ የሌላውን ቋንቋ ለመግባቢያነት ይጠቀማል። እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሁለቱም በሄሮች አባላት በጋብቻ ተሳስረዋል። በዚህ መሃከል የተወለዱም አሉ። የሁለቱ ብሄሮች ትስስር ይህን ያህል ነው። ከግጭታቸው የበለጠ አንድነታቸው ጎልቶ ለዘመናት አብረው እንዲኖሩ ማድረግ ያስቻለውም ይህ ነው።

የኢትዮጵያ ሶማሌም ሆነ የኦሮሞ ብሄሮች የሚጋሩት ታሪክ አለ። ይህም ባለፉት ስርአቶች ተጭኗቸው የኖረ ብሄራዊ ጭቆና ነው። ከዚህ ብሄራዊ ጭቆና ለመላቀቅ እንደወቅቱ ሁኔታ በተለያያ አነሳሽ ምክንያቶች በአንድ ግንባር ተሰልፈው የተዋጉባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። ሁለቱም ብሄሮች የኢፌዴሪ ህገመንግስት አጽድቀው በስልጣን ውክልና በቋቋሙት ፌደራላዊ ስርአት ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመቻቻልና በመከባበር ለመኖር ከተስማሙት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሃከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። ይህ የአደሲቱ ኢትዮጵያ መስራችና ባለቤቶች መሆናቸውን ያመለክታል።

እንግዲህ አሁን በመሃከላቸው የተፈጠረው ግጭት ወሰንን መነሻ ያደረገ መሆኑ ነው የሚነገረው። በሁለቱ ክለሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የወሰን ጉዳይ ከአስራ ሦስት ዓመታት በፊት የግጭት ምክንያት ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ ምክንያት የትኛው አካባቢ ወደየትኛው ክልላዊ መንግስት መካለል እንዳለበት ለመወሰን በ1997 ዓ/ም በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተመራ ህዝበ ውሳኔ ተካሂዷል። በዚህ ህዝበ ውሳኔ የትኛው ቀበሌ ወደየትኛው ክልል መሆን እንዳለበት ህዝቡ ራሱ ወስኗል። እርግጥ ይህ በህዝብ ተረጋገጠ ወሰን መሬት ላይ ሳይካለል ቆይቷል። አሁን ለግጭት መንስኤ እንደሆነ የሚነገረው ይህ ያልተካለለ የወሰን ጉዳይ ነው።

ሁኔታውን ለዘመናት ከቆየው የሁለቱ ህዝቦች ችግሮቻቻውን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ዝንባሌና ወሰኖቻቸውን በህዝበ ውሳኔ ከማረጋገጣቸው አኳያ ሲታይ፣ ለዘመናት አብረው የኖሩት ወዲያ ማዶና ወዲህ ማዶ የሚኖሩ ህዝቦች ድንብራቸው መሬት ላይ ባለመካለሉ ብቻ በወሰን ይገባኛል ጥያቄ ጠመንጃ ተማዘው ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ገብተዋል የሚለው ጉዳይ ስህተትነቱ ያይላል። ሁለቱ ህዝቦች ግዛታቸውን ለማስፋፋት አንዱ የሌላውን ድንበር ጥሰው በመዝለቅ በወሰዱት ጥቃት የተቀሰቀሰ ግጭት መሆኑን የሚያመለክት ተጨባጭ አስረጂ የለም። የአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች ከሰጡት ምስክርነት እንደሰማነው፣ መሳሪያ ታጥቀው ጥቃት የሚሰነዝሩት ሰዎች አርብቶ አደር ወይም አርሶ አደሮች አይደሉም። የታጠቁት መሳሪያም በአካባቢው የተለመደ የነብስ ወከፍ መሳሪያ አይደለም። ስለዚህ ግጭቱ በደንበር አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄሮች መሃከል የተቀሰቀሰ ግጭት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። የግጭቱ መንስኤ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ተደርጎ ሊወሰድም አይችልም።

በድንበር አካባቢ በሚፈጠመው ግጭት ህይወታቸው የሚያልፈው ሰላማዊ የአካባቢው ነዋሪዎች ቢሆኑም የሰው ህይወት የሚያጠፋውን የሃይል ጥቃት የሚወስዱት ግን በአመዛኙ የአካባቢው ነዋሪዎች አይደሉም። ከሌላ አካባቢ የሚመጡ የአካባቢው አርሶ አደር ከብቶቹን ለመጠበቅ ከሚታጠቀው የነብስ ወከፍ መሳሪያ የተለየ ከበድ ያለ የጦር መሳሪያ የታጠቀ፣ በአግባቡ የሰለጠነና የተደራጀ ሃይል ነው። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የአካባቢው አርብቶ አደሮች በሰጡት ምስክርነት የሚተኮሰውን መሳሪያ ድምጹን ከዚህ ቀደም ሰምተን አናውቅም ሲሉ ገልጸዋል። በግጭቱ ውስጥ የተተኮሱ መሳሪያዎች ከባድ መትረየስና በተደራጀ ተዋጊ ሃይል እጅ ብቻ የሚገኝ ድሽቃ የተባለ የጦር መሳሪያ መሆኑን የአካባቢው የፖሊስ ሃይል ማረጋገጫ ሰጥቷል።

እናም ግጭቱ በአሰዋሳኝ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች መሃከል የተቀሰቀሰ ሳይሆን፣ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ድንበርን መነሻ ያደረገ ግጭት በመፍጠር አካባቢውን ማተራመስ በሚፈልግ ሌላ ስተኛ ሃይል የተቀናጀና የሚመራ ነው። ይህ ሶስተኛ ሃይል ማን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቢቻልም ይፋዊ ማረጋገጫ እስኪሰጥበት ማቆየቱን መርጫለሁ። የሰዎች ህይወት እየጠፋ የሚገኘው በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ከድንበር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች መሆኑም ግጭቱ በወሰን ይገባኛል ምክንያት ብቻ የተቀሰቀሰ አለመሆኑን ያመለክታል። እርግጥ በታጣቂ ሰርጎ ገቦች በየእለቱ የሚጠፋው የሰው ህይወት እየጨመረ ሲሄድና ድርጊቱ ሲደጋጋም በጥቂት ቀበሌዎች ውስጥ የእርስ በርስ ግጭት የተቀሰቀሰበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም።

እንግዲህ ከላይ በመጠኑ የተመለከትናቸው እውነታዎች በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሱት ግጭቶች በሁለቱ ህዝቦች መሃከል የተፈጠሩ አለመሆኑን ያመለክታሉ። ዋነኛ መንስኤውም የመሬት ይገባኛል ጥያቄ አይደለም። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሰሞኑን የሁለቱ ክልላዊ መንግስታት አንዳንድ አመራሮች ግጭቱን ከማብረድ ይልቅ ሊያባብስ የሚችል ስሜታዊ የቃላት ልውውጠች ውስጥ መግባታቸውን ታዝበናል። በክልለዋ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ስም በተከፈተ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ግጭት የሚቀሰቀሱና የሚያባብሱ ሃሰተኛ ማስረጃዎችና ፎቶ ግራፎች ተለጥፈው ተመልክተናል። ይህ ሃላፊነት የጎደለውና ጸያፍ ድርጊት ነው። የሁለቱም ክልሎች አመራሮች ግጭቱ የህዝቦች ግጭት አለመሆኑን ለአፍታም ሳይዘነጉ፣ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል አስከፊ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ መላ ሃገሪቱን ለማተራመስ አየተንቀሳቀሰ ያለው ሶስተኛ ወገን ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነው።

የሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ ሃገሪቱን ለማተራመስ የሚፈልጉ ቡድኖች ሲጓጉለት የኖሩት የእርስ በርስ ግጭት አቀጣጣይ ላለመሆን ከማንም በላይ የመጠንቀቅ የህግም የሞራልም ሀላፊነት አለባቸው። በሁለቱ ህዝቦች መሃከል መሬቴ ተወስዷል የሚል ግምትና ስጋት የለም። የግጭቱ መንስኤና ዓላማ ከዚህ የተለየ ነው። ይህን በመረዳት በህዝቦች መሃከል ለዘመናት የኖረውን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ እንቁም።  

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy