Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌደራላዊ ሥርአቱ በልክ የተሰራ መዋቅር ነው

0 346

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌደራላዊ ሥርአቱ በልክ የተሰራ መዋቅር ነው

ኢብሳ ነመራ

ሰሞኑን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ህዝቦች መሃከል ግጭት ለመቀስቀስ የተደረገው ሙከራ የአሃዳዊ ስርአት ተስፈኞችን በሙሉ ከተኙበት ቀስቅሷቸዋል። በውጭ ሃገራት የኢፌዴሪን ህገመንግስታዊ ሥርአት ዋጋ ለማሳጣትና ህዝብን ለተቃውሞ ለማነሳሳት ያገኙትን ጉዳይ በሙሉ የሚወረውሩ ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች እንዲሁም፣ ፌደራላዊ ሥርአቱን በይፋ የሚቃወሙ ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት እንደማይሰራ ተረጋገጠ ሲሉ ተደምጠዋል።

በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት የተዋቀረውን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት መቃወም በራሱ (ተቃውሞው ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ) እንደጥፋት አይታይም። የፌደራል ሥርአቱን በአሃዳዊ ሥርአት የመተካት አቋም ይዞ ወይም በአመዛኙ በብሄራዊ ማንነት ላይ የተዋቀረውን ፌደራላዊ ስርአት በማፍረስ በወንዝና በተራራ የተሸነሸነ ፌደራላዊ ሥርአት እመሰርታለሁ የሚል አቋም የማራመድ መብት በህገመንግስት ተረጋግጧል። ዜጎች አቋማቸውን በሰላማዊ መንገድ እስካራመዱ ድረስ ያመኑበተን አመለካካት የመያዝ ህገመንግስታዊ መብት አላቸውና።

በዚህ ጽሁፍ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት የተረጋገጠበት ፌደራላዊ ሥርአት ለኢትዮጵያ በልክ የተዘጋጀ መዋቅር ነው ወይንስ የማይመጥንና አደጋ የሚያስከትል ነው የሚለውን ጉዳይ ልመለከት ወድጃለሁ። እንግዲህ ሰሞኑን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሃከል ሊቀሰቀስ የተሞከረውን አጠቃላይ የእርስ በርስ ግጭት ጨምሮ በክልሎች ወይም በአንድ ክልል ውስጥ በዞን ወይም በወረዳ መዋቅር ራሳቸውን በሚያስተዳድሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሃከል በማንኛውም ጉዳይ የይገባኛል ጥያቄ በተነሳ ቁጥር፣ ፌደራላዊ ስርአቱ ሃገሪቱን ሊያፈርስ ነው የሚል ጩኸት ስንሰማ ቆይተናል።

እነዚህ ወገኖች፤ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመከባበርና በእኩልነት መኖር የሚያስችላቸው ፌደራላዊ ሥርአት ሃገሪቱን የሚያፈርስ ሆኖ ነው የሚታያቸው። እርግጥ የአንዳንዶቹ ስጋት ከክፋት ሳይሆን ከየዋህነት የመነጨ ነው፤ በሃገሪቱ የነበረውንና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ካለመረዳት የመነጨ። በተለይ በውጭ ሃገራት የሚኖሩት ጽንፈኛ ተቃዋሚዎች አቋም ግን ከትምክህት አመለካካት የመነጨ ነው።

እነዚህ ወገኖች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የሚኖሩበትን ፌደራላዊ ሥርአት ኢህአዴግ ያመጣው አድርገው ነው የሚወስዱት። አንዳንዶቹ እንደውም በተለይ በትምክህት አመለካካት የሰከሩት፣ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተረጋገጠበትን ፌደራላዊ ስርአት በህወሃት የተሰጠ አድርገው ሲያቀርቡ ይሰማሉ። ኢህአዴግ/ህወሃት የኢትዮጵያን ብሄሮችና ብሄረሰቦች የፈጠረ መለኮታዊ ሃይል ያለው አድርገው የሚወስዱ የዋሆችም አሉ። የሁሉም መደረሻ ኢህአዴግ ሃገሪቱን ከፋፈለ፤ አንድነቷን ለአደጋ አጋለጠ የሚል አቋም ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ህዝቦች መሃከል የተሞከረውን የእርስ በርስ ግጭትም የዚህ ማሳያ በማድረግ ነው ፌደራላዊ ስርአቱ እንደማይሰራ ተረጋገጠ የሚል ፕሮፓጋንዳ መንዛት የጀመሩት።

በመሰረቱ፤ ኢትዮጵያ የምትባለው ምድር አንድ ብሄራዊ ማንነት ያለው ህዝብ መኖሪያ ሃገር አይደለችም። ይሄ ወዴትም ሊመነዘርና ሊለወጥ የማይችል ተጨባጭ እውነት (axiom) ነው። ኢትዮጵያ የምትባለው ምድር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የሚያውቅ ሰው ይህን እውነት ሊክድ አይችልም። ኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ልማድ፣ ታሪክ፣ ስነልቦናዊ ሁኔታ ያላቸው በየራሳቸው መልክዓምድራዊ ወሰን ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ነች። ይህም የማይመዘር ተጨባጭ እውነት ነው። እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ ራሱን የቻለ አንድ አካል (entity) ነው።

እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ በቋንቋው የመጠቀም – የመገበያየት፣ አገልግሎት የማግኘት፣ ሃሳቡን የመግለጽና ሃሳብ የመቀበል፣ የመማር ወዘተ የማይገሰስ መብት አለው። ከዚህ በተጨማሪ በባህልና በወጉ መሰረት የመኖር፣ ባህሉንና ቋንቋውን የማጎልበት፣ ትክክለኛ ታሪኩን የማወቅና የመንከባከብ፣ መሬትን ጨምሮ በሚኖርበት አካባቢ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም ከህልውናው ጋር የተቆራኘ የማይገሰስ መብት አለው።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ መብቶች የሚሰጡ ሳይሆኑ ከማህበረሰቡ ጋር አብረው የተፈጠሩና የማይነጠሉ መብቶች ናቸው። ያልተሰጡና ከማህበረሰቡ ጋር አብረው የተፈጠሩ መብቶች በመሆናቸው በማንም ሊገሰሱ አይገባም። እነዚህን መብቶች በሃይል ወይም በማንኛውም አስገዳጅ ስልት መንፈግ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ለእነዚህ መብቶች ህጋዊ እውቅና የመስጠት ጉዳይ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን፣ ሰብአዊ መብትን የማክበር ወይም የመጣስ ጉዳይ ነው።

እነዚህ ከብሄራዊ ማንነት ጋር የተቆራኙ መብቶች መከበር የሚችሉት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበት ሥርአት ሲኖራቸው ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ያለው ፌደራላዊ መንግስት ገንብተው ለመኖር የተስማሙት በዚህ ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት፣ በክፉም ይሁን በደግ ለመቶ ዓመታት ያህል በተጋሩት ታሪክ ያጎለበቱት መልካም የጋራ እሴት ላይ ተመስርተው፣ በብሄራዊ መብታቸው ያላቸውን የማይገሰስ መብት እያጣጣሙ በእኩልነት የሚኖሩበት ሥርአት ነው። ይህን ሥርአት አለመቀበል የሰብአዊ መብት ጥሰት በመሆኑ በመርህ ደረጃ ስሀተት ነው። ይህን ሥርአት በማፍረስ ህዝቦችን በአንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ለመጨፍለቅ ወይም ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የማይችሉበትን ሁኔታ መፍጠር በመርህ ደረጃ ጥፋት ነው።

ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት ጋር በተገናኘ ያለው ሌላው እስኪሰለቸን ላለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ሲነገር የቆየ አመለካካት፣ ፌደራላዊ ስርአቱን ኢህአዴግ በተለይ ህዋሃት እንዳመጣው አድርጎ የማቅረብ ጉዳይ ነው።

በመሰረቱ፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ የምትባለው ምድር የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር መሆኗ ተጨባጭ እውነታ ነው። እነዚህ የተለያየ ብሄራዊ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል ከህልውናቸው ጋር የማይነጠል ቁርኝት ያለው ብሄራዊ መብታቸውና ነጻነታቸውን በህግ ተነፍገው፣ በአንድ አሃዳዊ ሥርአት ስር እንዲተዳደሩ ተደርገዋል። አንድ ማንነት፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ . . . ያለው ህዝብ ለመፍጠር በአንድ ማንነት ስር እንዲጨፈለቁ ለማድረግ ተሞክሯል። የትኛውም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ በቋንቋው የመንግስት አገልግሎት የማግኘት፣ ቋንቋውን ለትምህርት አገልግሎት መስጫነት የመጠቀም፣ በወኪሎቹ አማካኝነት የመተዳዳር፣ በሚኖርበት አካባቢ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም ወዘተ መብት አልነበረውም። ይህ በህግ ነው የተከለከለው። ብሄራዊ ማንነቶች እንዲደበዝዙና እንዲጠፉ ታሪካቸው ተዛብቶ ተጽፏል፣ በማንነታቸው እንዲሸማቀቁ ተደርጓል። በቋንቋቸው የመጠቀምና ባህላቸውን የማሳደግ ተነሳሽነት እንዳይኖራቸው አንድ ብሄር ወይም ብሄረሰብ ሁለት፣ ሶስትና ከዚያ በላይ በሆነ አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲሸነሸን ተደርጓል። ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑት በአንድ አስተዳደር መዋቅር ውስጥ እንዲታጨቁ ተደርጓል።

በዚህ አኳኋን በኢትዮጵያ የነበሩት አሃዳዊ ሥርአቶች በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ ብሄራዊ ጭቆና ጥለዋል። ይህ ጭቆና በብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦች እና በአሃዳዊው ሥርአት መሃከል ቅራኔ ፈጥሯል፤ ብሄራዊ ጭቆና የወለደው ቅራኔ።

አሃዳዊ ሥርአቶቹ ይህን ብሄራዊ ቅራኔ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ህገመንግስታዊ ሥርአት አልነበራቸውም። በዚህ ምክንያት ቅራኔው እየከረረ ሄደ። የቅራኔው መክረር፤ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብትና ነጻነታቸውን በሃይል ለማስከበር ወደትጥቅ ትግል እንዲገቡ አደረጋቸው። የመጨረሻውን አሃዳዊ የወታደራዊ ደርግ ሥርአት ለማስወገድ የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ሃያ ገደማ የሚሆኑ በብሄር የተደራጁ የነጻነት ንቅናቄዎች የዚህ የተካረረ ቅራኔ ወጤት ናቸው። አሃዳዊ ስርአቱን ለማስወገድ ያበቃው ይህ የከረረ ብሄራዊ ቅራኔ የወለደው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የነጻነት ትግል ነው።

ኢህአዴግ ወይም ህወሃት በሃያ ከሚቆጠሩት ብሄራዊ የነጻነት ግንባሮች እንደአንዱ በሃገሪቱ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ – ብሄራዊ ቅራኔ የወለደው ነው። የብሄራዊ ነጻነት ትግሉን የግድ ያለው ቅራኔ በኢትዮጵያ ህዝዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ በሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ ወዘተ አልተፈጠረም። ቅራኔው ነው ብሄራዊ የነጻነት ንቅናቄዎቹ እንዲፈጠሩ ያደረጋቸው።

ኢሀአዴግና ሌሎች መሰል የነጻነት ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ንቅናቄዎች በሃገሪቱ ያለውን መሰረታዊ የብሄር ቅራኔ ምንጭ እንዲሁም ሃገሪቱ ህብረብሄራዊ አንድነት ያላት ሆና እንድትቀጥል ምን መደረግ እንዳለበት በሚገባ ተንትነው መረዳት ችለዋል። ይህም የሃገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመከባበርና በእኩልነት ላይ በተመሰረተ በፍቃዳቸው በገቡበት አንድነት የሚኖሩበት ፌደራላዊ ሥርአት ነው። ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ ተበታትኖ የተለያየ ሃገር ሆኖ መቀጠል ብቻ ነበር። አሁን በሃገሪቱ ያለው ፌደራላዊ ሥርአት በዚህ ነባራዊ ሁኔታ አስገዳጅነት የመጣ የሃገሪቱን አንድነት ማስጠበቅ ያስቻለ ብቸኛ አመራጭ እንጂ በኢህአዴግ ወይም በሌላ አካል የተጫነ አይደለም።

በኢፌዴሪ ህገመንግስት የተረጋገጠው ፌደራላዊ ሥርአት በክልሎች መሃከል ወይም በሌላ ደረጃ በሚገኙ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው በሚያስተዳድሩባቸው መዋቅሮች መሃከል ሊነሳ የሚችል የይገባኛል ጥያቄና አለመግባባት የሚያስቀር አይደለም። በፌደራላዊ ሥርአት ውስጥ በሚገኙ ግዛቶች መሃከል ከውሃና ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እንዲሁም ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ፣ በወሰን ወዘተ አንዱ ሌላው ላይ የይገባኛል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል። በግዛቶች መሃከል አለመግባባት ሊፈጠር ይችላል። ፌደራላዊ ስርአት ማለት የይገባኛል ጥያቄዎችንና አለመግባባቶችን በማያዳግም ሁኔታ የሚያስቀር ሳይሆን፣ ጥያቄዎቹ ሲነሱ፣ አለመግባበቶች ሲፈጠሩ ወደየከፋ ግጭት ሳይሸጋገሩ መፍታት የሚያስችል ህጋዊ አግባብ ያለው ሥርአት ማለት ነው። ከ200 ዓመታት በላይ እድሜ ባስቆጠረው የአሜሪካ ፌደራላዊ ሥርአት፣ በግዛቶች መሃከል ከወሰን፣ ከውሃ አጠቃቀም ወዘተ የመነጩ የይገባኛል ጥያቄዎችና አለመግባባቶች ሲነሱ ነው የቆዩት፣ አሁንም እየተነሱ ነው። ጥያቄዎቹ መነሳታቸው ፌደራላዊ ስርአት ለአሜሪካ አያስፈልግም ወደሚል ድምዳሜ አልወሰደም። የአሜሪካ አንድነት መቀጠል የሚችለው በፌደራላዊ ሥርአት ብቻ መሆኑን ያውቃሉና። ሌላው አማራጭ መለያየት ብቻ ነው።

የኢትዮጵያም ሁኔታ ከዚህ አንጻር ነው መታየት ያለበት። በሁለት ክልሎች መሃከል የወሰን ጥያቄ በተነሳ ቁጥር በብሄራዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ ፌደራላዊ ሥርአት ለኢትዮጵያ አይሰራም የሚለው ወሬ ከአሃዳዊ ሥርአት ተስፈኞች የመነጨ እንጂ ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ያስገባ አይደለም። ከልቡ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቅ ወገን፣ ፌደራላዊ ሥርአቱ እንዲጸና የሚታገል መሆን ይኖርበታል። አሁን እንደምንመለከተው ለኢትዮጵያ አንድነት እየሰሩ ያሉት በባዶ ሜዳ የኢትዮጵያ አንድነት እያሉ የፊውዳል ነገስታትን  እያወደሱ የሚጮሁት ሳይሆኑ፣ ስለብሄር ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚሞገቱትና የኢፌዴሪ ህገመንግስትን የሚደገፉት ናቸው።

እርግጥ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከክለላዊ መንግስታት ህገመንግስት እንዲሁም ከኢፌዴሪ ህገመንግስት ድንጋጌዎች አፈጻጸም ችግር የመነጩ የተንዛዙ አለመግባባቶችና ግጭት ቀመስ ቅሬታዎች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል። በአማራና በትግራይ ክልሎች መሃከል፣ እንዲሁም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሃከል የተነሳው የወሰን ጥያቄ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። የክልሎቹ ህገመንግስቶች እንዲሁም የፌደራሉ ህገመንግስት በክልሎች መሃከል የሚነሳ የወሰን ጥያቄ የሚፈታባቸውን ድንጋጌዎች ይዘዋል። ይሁን እንጂ ጥያቄዎቹ ሲነሱ የህገመንግስቶቹ ድንጋጌዎች ወሰን እስከማካለል ድረስ ተፈፃሚ ስላልተደረጉ አለመግባባትና ግጭት መቀስቀስ የሚያስችል አመቺ ሁኔታን ፈጥረዋል። ይህ ማለት ግን ግጭት ቀስቃሽ ሁኔታዎቹ በፌደራላዊ ሥርአቱ የተፈጠሩ ናቸው ማለት አይደለም።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት ሃገሪቱ በህዝቦች እኩልነት ላይ የተገነባ አንድነት ኖሯት እንድትቀጥል የሚያደርግ፣ ከሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የመነጨ በልኳ የተሰራ መዋቅር ነው። ኢትዮጵያ አሁን ካለው ፌደራላዊ ሥርአት የተለየ አንድነቷን ሊያስጠብቅ የሚያስችል በልኳ የተሰራ አወቃቀር ልታገኝ አትችልም። ትንሽ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ፌደራላዊ ሥርአቱ የፈጠረው አስመስለው የሚንጫጩት፣ የሃገሪቱን ነባራዊ እውነታ ያልተረዱ፣ አለያም ህዝቡ ውስጥ ውዥንብር በመንዛት ትርምስ መቀስቀስ የሚፈልጉ በምኞት የሚነዱ የአሃዳዊ ሥርአት ተስፈኞችና የሥርአቱ ጠላቶች ናቸው።    

   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy