Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህዝበ-ውሳኔን ማክበር መሰልጠን ነው!

0 556

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህዝበ-ውሳኔን ማክበር መሰልጠን ነው!

                                                       ዘአማን በላይ

መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. የቅማንትና የአማራ ህዝቦች ተቀላቅለው ከሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ውስጥ በስምንቱ ቀበሌዎች በተከናወነው የድምፅ አሰጣጥ ከ90 በመቶ በላይ መራጩ ህዝብ ድምፅ መስጠቱ ይታወቃል። ይሁንና ጉዳዩን ባስፈፀመው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በኩል ምንም ዓይነት መግለጫ ሳይሰጥ የህዝቦችን አንድነት የማይፈልገው ፅንፈኛው ሃይል ከወዲሁ የራሱን ግምት በማስቀመጥ ለብጥብጥ ጉዳዩን ሊጠቀምበት እየሞከረ ነው።

ዳሩ ግን ፅንፈኛው አካል ያሻውን የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ ቢያራምድም የሀገራችን ሀዝብ የየትኛውንም ቀበሌ ህዝበ- ውሳኔን ማከበር የስልጣኔ ምልክት መሆኑን የሚገነዘብ ነው። እንዲሁም የየትኛውም አካባቢ ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ውሳኔ ማክበር ለጠንካራ የህዝቦች አንድነትና አብሮነት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በሚገባ ያውቃል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ ስምንት ላይ እንደተመለከተው፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውንና ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ-መንግስቱ መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት እንደሚሆን ደንግጓል።

ይህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በግልፅ እንደሚያሳየው ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነው ህዝብ ይሁንታ ብቻ መሆኑን ነው። ህዝቡ ሲፈልግ ይሾማል፤ ሳይፈልግ ደግሞ ይሽራል። ይህን መብት ለህዝቦች የሰጡት ራሳቸው ህዝቦች ናቸው። ሌላ የትኛውም ወገን አይደለም። እናም አማራና ቅማንት ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው ስምንት ቀበሌዎች ውስጥ የተካሄደው ህዝበ-ውሳኔ ከዚህ አኳያ የሚመዘን ነው።

ርግጥ በህገ መንግስቱ የተለያዩ አንቀፆች ውስጥ የተቀመጡት ሁሉም መብቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በትግላቸው የተጎናፀፏቸው ትሩፋቶች ናቸው። እነዚህን ህገ መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን መብቶች ተጠቅመውም የበርካታ ትሩፋቶች ባለቤቶች መሆን ችለዋል። የአማራና የቅማንት ህዝቦችም እነዚህን ትሩፋቶች እያጣጣሙ ናቸው። በህገ መንግስቱ ላይ ለራሳቸው የሰጡትን መብት እየተጠቀሙበት ነው። ሌላ ምንም ዓይነት ተልዕኮ ያለው አይደለም።

ታዲያ እዚህ ላይ መብትንና ብሔራዊ መግባባትን ማጣረስ አይገባም። የአማራና የቅማንት ህዝቦች ጉዳይ ህገ መንግስታዊ ነው። አሁንም ‘ብሔራዊ መግባባት አልተፈጠረም’ የሚያስብል አይደለም። ርግጥ እዚህ ሀገር ውስጥ ህዝቡ የሚግባባቸው በርካታ የብሔራዊ መግባባት ጉዳዩች አሉ። የህዳሴው ግድብ ከእነዚህ ጉዳዩች ውስጥ የሚጠቀስ ነው።

ለነገሩ በዓለም ላይ ያለ ማንኛውም ህዝብ በሁሉም ጉዳዩች ላይ ሊግባባ አይችልም። እንኳንስ ህዝብን የሚያክል ትልቅ የማህበረሰብ ስብስብ ቀርቶ፤ በቤተሰብ ውስጥም ቢሆን ባልና ሚስት፣ ወንድምና እህትም ቢሆኑ በሁሉም ጉዳዩች ሊግባቡ አይችሉም።

በማህበረሰብም ይሁን በቤተሰብ ውስጥ ልዩነት ያለና የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ነው። እናም ብሔራዊ መግባባት ማለት አብዛኛው ህዝብ በአብዛኛው ጉዳይ የጋራ አተያይን እንዲያዳብር ማድረግ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። በዚህም ከሀገር ሉዓላዊነትና ዕድገት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን ማከናወን የተቻለ ይመስለኛል።

እናም አንድ ህዝብ ህዝበ ውሳኔ አካሂዳለው በማለት ህገ መንገስታዊ መብቱን ሲጠቀም ከመሬት ተነስቶ ጉዳዩን ከበሔራዊ መግባባት ጋር ለማጣመር መሞከር ስህተት ይመስለኛል። ህዝበ ውሳኔን ማካሄድም ይሁን ውጤቱን በፀጋ መቀበል የመሰልጠን ምልክት ነው።

ሀገራችን ውስጥ የየትኛውም ህዝብ ህጋዊ መብት ተከብሯል። ለአማራና ለቅማንት ህዝቦች ተለይቶ የሚከለከል አይደለም። ህገ መንግስታዊ መብታቸው ነው። ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፣ ለዴሞክራሲያው አንድነት መሰረት የተጣለበት፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነት፣ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት መሆናቸውም የተረጋገጠበት፣ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ግንባታ ጉዞ የተጀመረበት መሰረቱ ይኸው  ህገ መንግስትና ለህገ መንግስቱ ዘብ የቆመ ጠንካራ አመራርና ህዝብ ነው። በእኔ እምነት የአማራና የቅማንት ህዝቦች ጉዳይ የዚህ እውነታ ነፀብራቅ ነው።  

የህገ መንግስቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፣ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፣ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው፣ የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል። በእኔ እምነት የአማራና የቅማንት ህዝቦች ጉዳይ የዚህ እውነታ ነፀብራቅ ነው። እናም መብቶቻቸው በፅንፈኞች ዋይ…ዋይታ የሚጣጣል አይደለም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የእኩልነት መብት ማረጋገጫ የሆኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች…ወዘተ ተከብረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲካዊ አስተዳደር በኩል እኩል የመሳተፍ መብት ያገኙ ሲሆን፤ በልማት ስራው ላይም እኩል ዕድል እዲያገኙና በውጤታቸው መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡

በመሆኑም አንዳንድ ወገኖች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ላይ ያላቸው የስጋት ምንጭ ቀዳሚዎቹን አሃዳዊ ስርዓቶች ከመናፈቅ የመጣ አሊያም ህገ መንግስቱን ቀድዶ ለመጣል ከመፈለግ የመነጨ ከመሆኑ በስተቀር እስካሁን ድረስ ያለው ተጨባጭ እውነታ የመበታተን ስጋትን የሚያመላክት አይደለም።

ምንም እንኳን የመገንጠል ጥያቄ ሊኖር የሚችለው በፌዴራል ስርዓቱ ውስጥ ነው ተብሎ ቢታሰብም እስካሁን ድረስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያመላክተው አብዛኛዎቹ አሃዳዊ መንግስታት መበታተናቸውን ነው። እግርጥም “አራምባና ቆቦ” ስጋት ይሏል እንዲህ ነው።

ያም ሆነ ይህ፤ በፌዴራሊዝም ስርዓታችን ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኘው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የአንድነታችን ዋስትና እንጂ የመለያየታችን ስጋት ሊሆን አይችልም። በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙና ይህ አንቀጽ የሌላቸው ሀገራት በብጥብጥና በሁከት እየታመሱ ያሉትም በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን ማምጣት ባለመቻላቸው መሆኑን ካሉበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ መመልከት ተገቢ ነው።

የአማራንና የቅማንትን ሀዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትም የህዝቦችን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን የሚያረጋግጥ እንጂ ለመበታተን ምክንያት የሚሆን አይደለም። የህዝቦችን መብት ማክበርና ፍላጎታቸውን ማረጋገጥ የስልጣኔ ምልክት እንጂ በሌላ መንገድ የሚተረጎም አይደለም። እናም የህዝበ ውሳኔው ውጤት ተዋረዱን ጠብቆ በሚገለፅበት ወቅት ውጤቱን በፀጋ መቀበል ያስፈልጋል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy