Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

        ለትምህርት ዘመኑ ስኬት!!

0 363

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

        ለትምህርት ዘመኑ ስኬት!!

                                   ታከለ አለሙ

አዲሱን አመት አሀዱ ብለን ጀመርን፡፡በሀገር ደረጃ ቀጣይ ሰፊ ስራዎችን ለመስራት ታጥቀን የምንነሳበት፤ለተለያዩት ችግሮቻችን በሰላምና በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ የምናበጅላቸው፤በተለይም በትምሕርቱ መስክ ተተኪና ጠንካራ ትውልድን የማነጽና የመገንባቱ በእውቀት የበለጸገ የታነጸ ዜጋ የመፍጠሩ ስራ በአዲሱ አመት በስፋት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በአዲሱ አመት ተማሪዎች በአዲስ መንፈስ በትጋት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲገቡ ለማድረግ በመንግስት በኩል ሰፊ ዝግጅቶች ተደርገዋል፡፡ቀጣዩን ትውልድ በእውቀት በስነምግባር አንጾና ኮትኩቶ የማዘጋጀቱ አደራና ኃላፊነት የተጣለው በመምህራኑና በመንግሰት ብቻ ላይ አይደለም፡፡ይህን ሀገራዊ አደራ በመወጣት ረገድ ቤተሰብና ሕብረተሰቡም ታላቅ ኃላፊነትና ግዴታም አለባቸው፡፡

ተማሪው በትምህርቱ ውጤታማና ስኬታማ ሁኖ ሊዘልቅ የሚችለው በእውቀትና በስነምግባር የታነጹ ለሀገር የሚበጁ አዝመራዎችን ለማፍራት የሚችለው መምህሩ በእውቀቱ የደረጀና ብቁ ሁኖ ሲገኝ ነው፡፡መምህራን የቀለምና የሙያ ትምሕርት ብቻ ሳይሆን በአርአያነት የሚጠቀስ ስነምግባርም ለተማሪዎቻቸው የማስተማር የማሳወቅ የማስተላለፍ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

በስነስርአትና በዲስፕሊን በስነምግባር የታነጸና የተኮተከተ ወጣት ነው ከፍተኛ ኃላፊነትን ተሸክሞ መስራት የሚችለው፡፡በአዲሱ አመት ተማሪዎች ለሚጠብቃቸው ትምሕርት ራሳቸውን በሁሉም መስክ አዘጋጅተው አእምሮዋቸውን አስልተው የበለጠ ውጤታማ ተማሪ ሁነው ለመገኘት መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ትምህርት ነው ሀገራትንም አለምንም የለወጠው፡፡እድገትና ልማትን የሚያመጣው፡፡ከድሕነት ለመውጣት ትልቁ መሳሪያ ትምሕርትና የእውቀት ባለቤት መሆን ብቻ ነው፡፡

በሳይንስና በቴክኒዮሎጂው መስክ ሀገራት የላቀና የመጠቀ ደረጃ ላይ የደረሱትና የሚደርሱት በትምህርትና በትምህርት ብቻ ነው፡፡ከዚህ ውጭ ያለ አቋራጭ መንገድ የለም፡፡ሊኖርም አይችልም፡፡ለእውቀት የሚያጠናና የሚሰራ የሚመራመር ተማሪ የቤተሰቡ የሀገርና የሕዝብ ተስፋ ነው፡፡

ተማሪው ለፍቶ ተግቶ በመስራትና በማጥናት ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ያልሰራበትን ያልደከመበትን ውጤት በኩረጃ የሚያገኝና የሚጠብቅ ከሆነ የመጨረሻው ለሀገር ተስፋ መሆኑ ቀርቶ ተሸሎክሉኮ ቢያልፍ እንኳን በስራ ላይ ሲሰማራ ውድቀቱ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሀገርና ለሕዝብም ይተርፋል፡፡

በሀሰተኛ የትምሕርት ማስረጃ በሙስናና በማጭበርበር  በተገኘ ወረቀት ዲፕሎማ ዲግሪ ተቀጥረው የነበሩ ሰራተኞች በብሔራዊ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ራሳቸውን በየመንግሰት መስሪያ ቤቱ ሲያጋልጡ በስፋት እየታየ ነው፡፡ይህ ሀገራዊ ውድቀትን የሚያመጣ ትልቅ ችግር በመሆኑ ነው ልንጸየፈውና ልንከላከለው የሚገባው፡፡ መንግስትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግሩ ለዘለቄታው የሚወገድበትን መንገድ መቀየስ ይጠበቅበታል፡፡

ይህ አይነቱ አስነዋሪ ምግባር በሂደት የሚጎዳው ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ዛሬ ለሀገራችን ፈተና ሁኖ የቀረበው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ባልሰሩበት ባለፉበት የመንግስትና የሕዘብን ሀብትና ንብረት ዘርፎ በአቋራጭ የመክበር በሽታና አባዜ ሲሆን ተማሪው እንዲህ አይነቱን ዝንባሌ ከትምህርት ቤቱ ጀምሮ ሊዋጋው ይገባል፡፡ይህም ራሱን የቻለ በትምህርት መስክ የሚፈጸም ሙስና ነውና፡፡

በኩረጃ በጎበዝ ተማሪው ልፋት ለማለፍ መሞከር ሌላኛው በእውቀት ላይ የሚፈጸም ሙስና ነው፡፡ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር የሚሰራው ስራ መጀመር ያለበት ከትምህርት ቤቶች ነው፡፡ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ሀገርና ትውልድ ገዳይ በሽታ ነው፡፡እድገትን ልማትን የነገ ታላቅ ሀገራዊ ተስፋን ሁሉ ይገዳደራል፡፡ መንግስታዊና ሕዝባዊ አስተዳደርን ያዛባል፡፡የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግሮች በዋነኛነት የሚፈጠሩት የሚቀፈቀፉት ከሙስናና ከኪራይ ሰብሳቢው ጋር በተቆራኘ ሁኔታ ነው፡፡

አገራችን በያዘችው ትልምና እቅድ መሰረት በአለማችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ያስቀመጠችውን ራእይ ውጤታማ ለማድረግ የጀመረችውን   ሕዳሴ ለማሳካት በጀመረችው ሰፊ ጉዞ ውስጥ የተማረው የሰው ኃይል የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተማሪው በአግባቡ ሊገነዘበው ይገባል፡፡  

ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ከሁሉም ነገር ቅድሚያ ሰጥተው በማተኮር፤ የትምህርት የውይይት ክበባትን በተለያዩ የሙያ መስኮች በመፍጠር፤አንብበውና ተዘጋጅተው በመቅረብ በየግዜው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውይይት በማድረግ አዳዲስ ሀሳብን በማፍለቅ በማጎልበት እውቀትና የክህሎት ደረጃቸውን ማሳደግ ከማንም በላይ የሚጠቅመው ለራሳቸው መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡የቀድሞ ተማሪዎችም ልምድ የሚያሳየው ይሄንኑ ነው፡፡

ማንበብ ማንበብ ማንበብ በትንሽ እውቀት ሳይወሰኑ ሰፊ እውቀት መያዝ ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር፡፡በእውቀት መላቅና መብቃት የሚገኘው የሚመጣውም በዚህ መልኩ ነው፡፡ ሀገራችን ከወጣት ተማሪ ልጆችዋ ብዙ ትጠብቃለች፡፡በጣም ብዙ፡፡ለዛ ደረጃ ለመብቃት ጠንክሮ መማር ማጥናት የእውቀት አዝመራን በለጋ እድሜያቸው መሰብሰብ ከተማሪዎቻችን በስፋት ይጠበቃል፡፡

አንዱ በቀጣይነት ተጠናክሮ የሚሰራው ስራ የትምህርትን ጥራት የማስጠበቁ ጉዳይ ነው፡፡ጥራትና ብቃት የሌለው የትምሕርት አሰጣጥ አሁንም ተመልሶ የሚጎዳው ሀገርንና ሕዝብን ነው፡፡በሀገራችን በርካታ የትምህርት ተቋማት በብዛት ከመስፋፋታቸው ጋር ተያይዞ የትምሕርት ጥራት ጉዳይ አነጋጋሪ ሁኖ ቆይቶአል፡፡

የትምሕርት አመራሮች፤መምሕራን፤ወላጆችና መላው የትምሕርት ባለድርሻ አካላት በአጠቃላይም ሕብረተሰቡ የትምሕርትን ጥራትና ብቃት ተደራሽነት በተመለከተ በትኩረት መስራትና መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡የተናጠል ስራ ከመንግስት ብቻ የሚጠበቅ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡

ኢትዮጵያ በፈጣን የልማትና የኢኮኖሚ እድገት ላይ የምትገኝ ሀገር ለመሆንዋ ተደጋግሞ የተነገረ እውነት ነው፡፡ይሄንን ሀገራዊ እድገት ሊያስቀጥል የሚችለው የሀገሪቱ ተማሪ በትምህርትና በእውቀት ተግቶና በቅቶ መገኘት ሲችል ብቻ ነው፡፡ የተከበረና የተረጋገጠ ሀገራዊ ሰላሙን ከየትኛውም አቅጣጫ ከሚሰነዘር ጥቃት መጠበቅና መከላከል ሲችል ነው፡፡ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ነው የተገኙትን የኢኮኖሚ እድገቶች ልማቶች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚቻለው፡፡

ጽንፈኛና አክራሪ  በጥላቻ የተዋጡ ፖለቲከኞች ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም የሚጠቅም አጀንዳ የሌላቸው መሆኑን ተማሪው ጠንቅቆ ሊያውቀው ይገባል፡፡የሀሰት ቅስቀሳና የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ በመርጨትና ተማሪውን በማነሳሳት ከትምህርት ገበታውም እንዲያቋርጥ ለማድረግ የሚክለፈለፉት ኃይሎች ለተማሪውም ለሕብረተሰቡም የማይጠቅሙ ይልቁንም ወርቃማ በሆነው ግዜው የፖለቲካ ቁማራቸውን ለመጫወት የሚሮጡ መሆናቸውን ተማሪው በውል ሊረዳው ይገባል፡፡ ሊከላከላቸው ሊያጋልጣቸውም ይገባል፡፡በሀገር የምትለማው በትምህርት ነው፡፡በመማር ነው፡፡ በየትኛውም ጎራ ያሉና የሚገኙ ጽንፈኞች ለሀገር ለሕዝብም አይጠቅሙም፡፡ ተማሪው ይሄንን እውነት አውቆና ተረድቶ ሁሉም በሰላም ለጋራ ሀገሩ ቆሞ የሚሰራበት ሁኔታዎች እንዲጎለብቱ ለሰላም ያለውን ፍቅር በማሳየት የበኩሉን ሀገራዊ ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

መደማመጥ መከባበር የሰፈነበት መቻቻል የነገሰበት ሀገራዊ ችግሮች በሰላምና በሰላም ብቻ የሚፈቱበትን ሁኔታ ተማሪው እያጎለበተው መሄድ ይገባዋል፡፡ የጽንፈኞችና የአክራሪዎችን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ማጋለጥና መዋጋት ከተማሪው በሰፊው ይጠበቃል፡፡ምክንያቱም ትምህርቱ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ልማትና እድገቱ ሳይሰተጓጎል መቀጠል ሰላሙ መከበር ስላለበትም ጭምር ነው፡፡

ዛሬም በሕዝብ ቁስል ብሶት ችግር ላይ እንደገና ቤንዚን እያርከፈከፉ ሀገርን ለማጥፋት ሕዝብንም የመረረ ዋጋ ለማስከፈል ዘረኛ ግጭት ቆስቋሽ መርዛቸውን በመርጨት ላይ የሚገኙት ኃይሎች ለማንም አይበጁም፡፡ተማሪው በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ እኩይ ሴራቸውን ሊያጋልጠው ይገባል፡፡፡

የትኛውም የውስጥ ችግር የሚፈታበት ሕግና ስርአት አለው፡፡በሰላማዊ ሁኔታ በመደማመጥ በውይይት በመነጋጋር ነው የሚፈታው፡፡ሁከት ትርምስና አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚሰሩ ወገኖች ተማሪውን ኢላማ ሊያደርጉ በተደጋጋሚ ሞክረው አልተሳካላቸውም፡፡ተማሪው ሀገራዊ ሰላሙን ነቅቶ መጠበቅ ትምሕርቱንም በትጋትና በትኩረት መከታተል ይጠበቅበታል፡፡የነገው የሀገሪቱ ልማትና እድገት ታላቅ ተስፋ በእውቀት ላይ የተገነባው የተማረው ወጣት የሕብረተሰብ ክፍል ነውና፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy