ethiopian news

Artcles

ለኢንዱስትሪው መር መደላድል…

By Admin

September 12, 2017

ለኢንዱስትሪው መር መደላድል…

 

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

በሕዝቦች ተሳትፎና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የተሰለፈች አገር ለመገንባት ራዕይ ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ለውጦችን እውን ለማድረግ እንቅስቃሴ ከተጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል። ኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት ባለሁለት አኃዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ማስመዝገቧን ተከትሎ ዕድገቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከ2002 – 2007 ዓ.ም የሚፈፀም እቅድ ነድፋ ሰርታለች።  

 

ይህ የመጀመሪያው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው ቀደም ሲል በአገሪቱ የተመዘገበውን የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንደ መነሻ በመውሰድ፣ ድህነትን ታሪክ በማድረግና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ዓላማ አንግቦ ነበር። በዚህ ዕቅድ የተቀመጠው የልማት አቅጣጫ እንደሚያሳየው ከ2002 – 2007 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት ዕድገት በእጥፍ በማሳደግ ግብርና መር የምጣኔ ሀብት መሠረትን ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር የሚያስችል ጽኑ መሠረት ለመጣል ነበር።

 

ዕቅዱም ተተግብሯል። የነበረው አፈጻጸፀም በሚጠበቀው መልኩ የተከናወነና ለቀጣይ የሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አስተማማኝ መሠረት የጣለ ሆኗል። ዕቅዱን በሚቀጥሉት ዓመታት በተጠናከረ መልክ በመፈፀም አገሪቱን በ2017 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ማሰለፍ እንደሚቻል መተማመን የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦችን በተሳካ መንገድ በማከናወን ግብርና መር ኢኮኖሚውን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያስችል አስተማማኝ መሠረት ይጣላል የሚል እምነት ይዟል። የኢንዱስትሪ ልማቱ ኤክስፖርት መር ሆኖ እንዲመራ በዕቅዱ ላይ በአቅጣጫ ተቀምጧል። የአገሪቱ ምርቶችና የፋብሪካ ውጤቶች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫም ተይዟል።

 

በሌላ መልኩ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርትንና ምርታማነትን በማሳደግ ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ አገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡትን ምርቶች መተካት ነው። ከዚህ አንጻር በሰፊው ሊሰራባቸው የሚገቡ ዘርፎች ተለይተው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አካል ሆነዋል። በሲሚንቶ፣ በስኳር፣ በኃይል ምንጭ፣ በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ የመሳሰሉ ዘርፎች የተያዙ ዕቅዶች ተቀናጅተው ይህንኑ ለማስፈፀም የሚያስችሉ እንደሆነም ይታመናል።

 

በዚህም መሠረት ወሣኝ ሚና ይኖረዋል በሚል በመጀመሪያው አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተያዙት ዐበይት የኢንዱስትሪ ግንባታዎች አንዱ የስኳር ልማት ፕሮጄክት ነው። ኢትዮጵያ ለስኳር ልማት ተስማሚ የአየር ጠባይ ካላቸው የዓለማችን አገራት በቀዳሚነት ትመደባለች። ለሸንኮራ አገዳ ምርት የሚውል እስካሁን ሥራ ላይ ያልዋልለ ሰፋፊ የእርሻ መሬትም ያላት አገር ነች። በዚህ ረገድ አገሪቱ ያላት እምቅ ሀብት በተገቢው መልክ ሥራ ላይ በማዋል ድህነትን ለመቅረፍ አጋዥ ሳይሆን ለዘመናት ቆይቷል። በአገሪቱ ቀደም ሲል የነበሩ ጥቂት ፋብሪካዎችም የማስፋፋት ሥራ አልተደረገላቸውም። የሚጠቀሙበት የቴክኖሎጂ ደረጃም የቆየ ከመሆኑ የተነሳ ምርታማነታቸውን ማረጋገጥ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ አልነበረም።

 

በዚህ ምክንያት የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም። ህዝቡ የሚፈልገውን ያህል አቅርቦት ባለማግኘቱ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን መንግሥት በከፍተኛ ወጪ ከተለያዩ አገራት ስኳርን ማስገባት የግድ ሆኖበታል። መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከተለያዩ አገራት እየገዛ በማምጣት ሲያከፋፍል ቆይቷል። ይህ ችግሩን ለማቃለል ጊዚያዊ መፍትሄ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን ስለማይችል ጉዳዩን በውል የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፋን ለማልማት ቆርጦ ወደ ሥራ ገብቷል።  

 

ቀደም ሲል በአገሪቱ የነበሩትን የስኳር ፋብሪካዎች በተገቢው መልክ በማስፋፋትና የያዙትን የምርት ቴክኖሎጂ በዘመናዊ መሣሪያዎች የመቀየር ተግባር በማከናወን ከእነዚህ ነባር ፋብሪካዎች የሚገኝ ምርትን ማሳደግ የሚቻልበት አቅጣጫ ተይዟል። የነባሮቹን ምርታማነት ከማሳደግ ጎን ለጎን ደግሞ አዳዲስ ፋብሪካዎችን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት የሕዝቡን የስኳር ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ይገኛል። ምንም እንኳን በታቀደው ጊዜ ግንባታዎቹ ባይጠናቀቁም።

 

በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቱ ያለው የስኳር ምርት ፍላጎት 0 ነጥብ 3 ሚሊዬን ቶን ነው፡፡ አገሪቱ እያመረተች ያለው ግን 0 ነጥብ 125 ሚሊዮን ቶን ብቻ ነው። በመሆኑ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን መገንዘብ ይቻላል። ይህንን ልዩነት ለማሟላትና ኅብረተሰቡ በስኳር እጥረት ምክንያት የእለት ኑሮው ላይ ጫና እንዳይደርስበት ለማድረግ መንግሥት ከውጭ ገበያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በመግዛት ሲያቀርብ ቆይቷል። ይህ መፍትሄ ጊዚያዊ መፍትሄ ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሄ ላይም ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።  

 

የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት በአስተማማኝ መንገድ ለማሟላትና አገሪቱ ለስኳር መግዣ የምታውለውን ምንዛሪ ለማስቀረት የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነ በመገንዘብ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የስኳር ልማት አንዱ መሠረታዊ የልማት ዘርፍ ሆኖ ተነድፏል።

በዚህ እቅድ መሠረት ነባሮቹን ፋብሪካዎች በተገቢው መንገድ በማስፋፋትና አዳዲሶቹን በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ በማጠናቀቅ የአገሪቱ የስኳር ምርት 2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ቶን ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡ እስካሁን የተከናወነው ተግባር በቀጣይ ዓመታት ከሚሰራው ጋር ተጣምሮ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

 

ከዚህ አንጻር አጠቃላይ የስኳር ምርቱን 2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ቶን በማድረስ የአገሪቱን ፍጆታ በማሟላት ቀሪውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዷል። በዚህ ረገድ በአገሪቱ ማምረት ሲቻል ከሌሎች አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገዙ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት አቅጣጫን ከማሳካት አንጻር አንድ ርምጃ ወደፊት መሄድ ይቻላል። ለስኳር መግዣ የሚውለውን ገንዘብ መቆጠብና ለሌላ ልማት ማዋልም ይቻላል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ኤክስፖርት መር የሆነውን የኢንዱስትሪ ልማት ዕድገት ለማገዝ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ አቅጣጫ ዘርፉ በአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ላይ የጎላ ድርሻ እንዲኖረው ለማድረግ ያስችላል።

 

የስኳር ልማት ፕሮጄክት የኢንዱስትሪና የግብርና ዘርፎች ከፍተኛ ተመጋጋቢነት እንዲኖራቸው በማገዝ ረገድ ቀላል የማይባል ድርሻ ይኖረዋል። ከስኳር ምርቱ ጎን ለጎን ለግብርናው ዘርፍ መጠናከር የሚያግዙ ተግባራት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ይደረጋል።

 

በተያያዥነት ሊሰሩ ከሚችሉት ተግባራት አንዱ የኢታኖል ምርት ነው። ኢታኖልን ከስኳር ፋብሪካዎቹ ተረፈ ምርት በሰፊው በማምረት አገሪቱ ለነዳጅ መግዣ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ያግዛል። የነዳጅ ሃብትን አፈላልጎ የማውጣት ተግባር በተገቢው መንገድ እያስኬዱ ከስኳር ምርቱ ጎን ለጎን ደግሞ የኢታኖል ምርትን በተገቢው መንገድ በመጠቀም የአገሪቱን ወጪ በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ያስችላል።

 

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የኢታኖል ምርቷን በማሳደግና ከቤንዚን ጋር በመቀላቀል ለነዳጅ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ያአስችሏታል። ሁለቱን የመቀላለቀልና ሥራ ላይ የማዋል ተግባር በአገሪቱ የተጀመረው በ2001 ዓ.ም ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ወደ ዚህ ሥራ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የአሜሪካን ዶላር ወጪ አድናለች።  

 

ይህ በአገር ውስጥ የሚመረተው ኢታኖል መጠን ባደገ ቁጥር አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የነዳጅ መጠን ለመቀነስ ስለሚያስችላት አሁን እየተስፋፋ ያለው የስኳር ልማት ፕሮጄክት ከዚህ አንጻር የሚሰጠው ጠቀሜታም የጎላ ይሆናል። ለኢንዱስትሪው መር መደላድልም መሆኑ እርግጥ ይሆናል…