ለግጭት በር የሚከፍቱ መንስኤዎችን እናርቅ!
ታዬ ከበደ
ሰላም በዓለማችን የሚገኝ ውድ ነገር ነው። ያለ ሰላም ምንም ማድረግ አይቻልም። ሰላምን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጠም ለመጋጨት መንስኤ የሆኑ ጉዳዩችን ማራቅ ይገባል። በግጭት ምክንያት የሚፈጠሩ የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ እጦቶች መልሶ የሚጎዳው ህብረተሰቡን ስለሆነ መንስኤዎቹን አስቀድሞ መከላከል ያስፈልጋል።
እንደሚታወቀው ሁሉ ሰላምን ከሁከት ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። በሰላም ውስጥም ሁከት ሊታሰብ አይችልም። ስለ ሰላም ስናስብ ሁከትን በተቃራኒ ገፅታው እየተመለከትነው ነው። ሁከት በህዝብና በሀገር ውስጥ ሊፈጥረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖንም እየኮነንነው ነው። የድርጊቱ ዕውን መሆን የእኛነታችንን በመሻሻል ላይ የሚገኝ ገፅታን ጥላሸት ከመቀባት ባሻገር፣ የእኛ ሰላም መሆንና መታደስ እንዲሁም የሀገራችን ዕድገትና ብልፅግና ለሚያንገበግባቸው የውጭም ይሀን የውስጥ ኃይሎች ሰፊ በር ይከፍታል። ይህም የብጥብር በርን በርግዶ በመክፈት የትርምስ ምህዳርን ይፈጥራል። ትናንት ወደ ነበርንበት የጦርነት፣ የድህነትና የኋላ ቀርነት ታሪክ ይመልሰናል።
የሁከት በር አፉ ሰፊ ነው። በተሳሳተ አቅጣጫ የሚጓዝን ዜጋ ሁሉ ያስገባል። ሚዛናዊነትን አይፈጥርም። ስሜታዊነትን ያነግሳል። በዚህ በር ውስጥ ለማስገባት የሚፈልጉ ኃይሎችም የበሩን ግራና ቀኝ እጀታ ይዘው በስሜትና በአሉባልታሌገንን ሊያስጋልቡት ይከጅላሉ። የጥፋት አውድንም ይፈጥራሉ። ጥፋቱ ግን የህዝቡን ክቡርና የማይተካ ህይወት ከመንጠቅ ባሻገር ሃብቶቹንና መጠቀሚያዎቹን ሁሉ ያወድማል። ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲያጤኑት ግን ቁጭትን ይፈጥራል።
የሁከት ኃይሎቹ ያላቸውን የቅጥፈትና የአሉባልታ አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው በመጠቀም ህዝቡ ላለፉት ዓመታት ከሰላም ያገኛቸውን ትሩፋቶች ይነጥቁታል። እነርሱ በዚህም ይሁን በዚያ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ጥቅም እስካሳካላቸው ድረስ እዚህ ሀገር ውስጥ የፈለገው ቢሞትና ንብረቱ ቢወድም ጉዳያቸው አይደለም። ባህር ማዶ ሆነው የሚለኩሱት እሳት ወላፈኑ በእነርሱና በልጆቻቸው ላይ እንደማይደርስ ስለሚያውቁ፤ እሳቱ ሀገር ውስጥ ማንንም ቢያቃጥል ከምንም አይቆጥሩትም።
የእነዚህ ሃይሎች ዓላማ ሁለት ይመስለኛል። አንደኛው፤ ሃይሎቹ ከዚህ ቀደም ሀገር ውስጥ በነበሩበት ወቅት በከሰረ ፖለቲከኝነታቸውና በፀረ-ህገ መንግስታዊነታቸው በህዝብ የተተፉ በመሆናቸው ሳቢያ በህዝቡ እምቢተኝነት ያጡትን ስልጣን በሁከትና በብጥብጥ ለመያዝ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፤ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና የልማት ጎዳና ማየት የማይሹ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች እያዘዟቸውና ገንዘብ በገፍ እያሸከሟቸው ሰላማችንን እንዲያደፈርሱ ታዘው በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች ሁከትን መቀመር ነው።
እነዚህ ጥቂት ሃይሎች ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ እዚህ ሀገር ውስጥ በስውር ያደራጇቸው የጥፋት ቀማሪዎች የሉም ማለት አይቻልም። ይሁንና በመንግስት በኩልም መልካም አስተዳደርንና ሌሎች የህዝቡን እርካታ የማያረጋግጡ ምክንያቶች በወቅቱ ተገቢ ምላሽ አለመሰጠቱ የሁከት ኃይሎቹን ፍላጎት በማገዝ ረገድ የበኩሉን ሚና መጫወቱ አይካድም።
በመንግስት በኩል የውስጥ ተጋላጭነት መንስኤን በመቀነስና የህዝቡን እርካታ በማረጋገጥ ረገድ መከናወን የሚገባቸው ብዙ የቤት ስራዎች እንዳሉ የሚያሳይ ነው። እርግጥ መንግስትና ገዥው ፓርቲ በያዝነው የበጀት ዓመት ከመልካም አስተዳደርና የመንግስት ስልጣንን የግል ኑሮ መደጎሚያ ከማድረግ አኳያ የሚታዩ ጉድለቶችን እንዲሁም ህዝቡን ለምሬት የሚዳርጉ አሰራሮችንና ተግባሮችን በቁርጠኝነት እያስተካከሉ ነው። አጥፊዎችም በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው።
እርግጥ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ውስጥ ያለው ሥርዓት ለግጭት ቦታ አይሰጥም። ለዘመናት በአንድነት የኖረ፣ በባህልና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች አገራዊ ትውፊቶች የተሳሰረን ህዝብ የራሳቸው የጥበትም ይሁን የትምክህት አጀንዳ ያላቸው ታጣቂዎችና የታችኛው እርከን አመራሮች ሳቢያ በአንድ ጀንበር የሚፈጠር መለያየት ሊኖር ስለማይችል ነው።
ወሰን ተጋሪ የሆኑት የኦሮሚያም ይሁን የኢትዮጵያ ሶማሊ ህዝቦችን ጨምሮ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በደማቸው ዋጅተው እውን እንዲሆን ያደረጉት የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትና እርሱን ተከትሎ እውን የሆነው የሀገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት ለግጭት የሚሆን ቦታን የላቸውም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ለግጭት የሚሆን ምህዳር የሌለ መሆኑ በሕገ መንግስቱ መግቢያ በተገቢው ሁኔታ ተብራርቷል።
የሕገ መንግስቱን መግቢያ በከፊል ስንመለከተው፤ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነጻ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤…ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፤ መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤ ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነጻነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤…” የሚል የህዝቦችን ፍላጎትን ይዞ እናገኛዋለን።
ይህም የአገራችን ህዝቦች የሚሹት ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፣ ማህበረ-ኢኮኖሚ እድገታቸውን እንዲፋጠን አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዲገነባ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የሚያመላክት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ጥቅምና አመለካከት ያላቸው፣ ይህን ጥቅማቸውን እየተደጋገፉ በጋራ በማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ፍላጎት አላቸው።
ይህም “የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ” በሚለው በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 1 ላይ የተቀመጠውና “ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል” በሚል የተገለፀው መንግሥታዊ ሥርዓት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን የሚያብራራ ነው።
ይህ በአገራችን ህዝቦች ሙሉ ፈቃድ እውን የሆነው ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፤ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እምነታቸውም ይሁን መፃዒ ዕድላቸው በሚመሰርቱት አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘውግ ያለው ሥርዓት ላይ እንጂ፤ ያለፉት ሥርዓቶች ጥለውት የሄዱትን የተበላሸ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰቦችን መልሶ መላልሶ በማመንዠግ ቁርሾ መያዝና ይህንንም ለግጭት ብሎም ለንፁሃን ህይወት መጥፊያነት በማለም አይደለም።
አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ህዝቦች ይሻሉ ሲባል፤ በራሳቸው እምነትና ፈቃድ እንዲፈጠር የፈለጉት ፌዴራላዊ ሥርዓት የተዛቡ ቀደምት ግንኙነታችንን ያስተካክልልናል፣ አንዳችን የሌላችንን ሃይማኖት፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ባህል በማክበር በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን እናድጋለን፣ የጋራ ተጠቃሚነታችንንም እናሳድጋለን ማለት ነው።
በዚህ የህዝቦች እምነት መሰረት፤ አንዱ ብሔር ከሌላኛው ጋር ተስማምቶና የጋራ ሃብቱን በጋራ ለማልማት እንዲሁም ጥቅሙን በፍትሐዊነትና እኩልነት ለማጣጣም ፍላጎት መኖሩን ያሳያል። ይህም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አንድ የጋራ ማህበረሰብን የመፍጠር ዓላማን ያነገበ እንጂ፤ ‘አንተ ከወዲያ ማዶ ነህ…እኔ ደግሞ ከወዲህ ማዶነኝ’ በሚል ህዝቦችን በቦታ የመከፋፈል መንፈስ ላይ የተመሰረተ አይደለም።
እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እንኳንስ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በምትከተለው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርቶ፤ በገዛ ሀገራቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያ መብታቸው ተገፍፎ ‘ከዚህ ቦታ እንዳታልፉ’ ተብለው ከነጮች ጋር ምንም ዓይነት የጋራ መስተጋብር እንዳይኖራቸው በቦታ ተገድበው ይኖሩ በነበሩት የደቡብ አፍሪካ ዜጎች እንኳን ዛሬ ላይ የሚያስታውሱት አይመስለኝም። እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከዘመነ-አፓርታይድ ጋር አብሮ ከስሟል። ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ህዝቦችን ለግጭት የሚዳርጉ መንስኤዎችን እግር በእግር እየተከታተሉ መቅጨት ያስፈልጋል።